ሰዎች ይመስሉኛል። በጎችም ይመስሉኛል። ሰዎች ብዬ ስጠራቸው አቤት ይላሉ። በጎች ብዬ ስጠራቸውም አቤት ይላሉ። ሰዎች ናቸው በጎች?
በቡድን ነው የሚኖሩት። በቡድንን ይንቀሳቀሳሉ።እንደማንነታቸው ሁሉ አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት ከባድ ነው።
ጠጋ ብዬ እረኛቸውን ጠየኩት።
“አልገባኝም በጎች ናቸው ሰዎች? ”
ፈገግ ብሎ መለሰልኝ፣
“በግ ለመሆን የተስማሙ ሰዎች ናቸው ”
እንዲያብራራልኝ ጠየኩት።
“አየህ የሰው ልጅ ሰው የመሆንንም፣ በግ የመሆንንም አቅም በውስጡ ይዟል። የሰው ልጅ ከምክንያት ወዲያ ወይም ወዲህ በመሻገር ይህ እጣውን ይወስናል። ጆርጅ ሳንታያነ የተባለ የማድሪድ ተወላጅ የሆነ አሜሪካዊ ፈላስፋ ምን ይላል መሰለህ፣ ” Reason is ‘man’s imitation of divinity” ይላል። ከምክንያት ውጪ መሆን ደግሞ የሰው ልጅ ከበግ መምሰያ መንገዱ ነው።
እኚህ ያየሃቸው ሰጎች ምክንያትን የጣሉ ናቸው። ያኔ ገና ንፁህ ሰው መሆን ሊያቆሙ ሲሉ እኔ እረኛቸው እንድሆን መርጠውኛል። አሁን ግን ወደ “ሰግ ” ነት ስለተለወጡ፣ የተመረጠላቸውን እንጂ የመረጡትን አይኖሩም። ሰው መሆኑን በፍቃዱ የጣለ ሁሌም እንደዚህ ነው።”
“አንተ የነሱ እረኛ በመሆን ምን ትጠቀማለህ? ”
“የፈለኩትን አገኛለህ። አንደኛ ሰዋዊ የሆነ የበላይነት ስሜቴን አረካለሁ። ከዛ ባለፈ፣ ሰጎቹ ሰው ሳሉ የነሱ የነበረ ሁላ የእኔ ይሆናል ”
“ከሰጎቹ መሃል ይህንን አውቆ የሚያምፅ የለም?”
“ይሄ የሚጠበቅ ነው። እዛህ ጋር መሳሪያ የታጠቁት ሰጎች ይታዩሃል? … እነሱ ያልከው አይነት አመፅ እንዳይነሳ በትጋት ይጠብቃሉ። ለስራቸው ጥሩ የሰው ምግብና የበግ ሳራ ይሰጣቸዋል። እሱን ለማግኘት ያልካቸውን ይሰራሉ…”
“ወዲያ ‘ቲሊቃ’ ተብሎ የተፃፈበት አጥር ውስጥ የተዘጋባቸውስ?”
” እነሱ ሰው መሆን የጀመሩ ናቸው። ሰግ ላደርጋቸው ብሞክርም አልቻልኩም። ሌላውን እንዳይበርዙ በጠባቂ ሰጎቼ ይከለልባቸዋል።”
“ካልታሰሩት ውስጥ ያሉት በብዛት የሰው ደረጃ ላይ ደርሰው ቢያምፁስ? ”
“እሱ እንኳን ለጊዜው አያሰጋኝም። ሰጎች ሰው እንዳይሆኑ ወይም እንዳይጣሉህ ከፈለክ ዋናው ነገር እርስ በእርስ እንዲጣሉ ማድረግ… ”
ማዶ ላይ እርስ በእርስ የሚዋጉ ሰጎችን አሳየኝ።
” ይህንን በተለያዩ መንገዶች አሳካለሁ። ብዙዎቹን በቀለም አጣላቸዋለሁ። እገሌ የተባለው ሰግ ያሾፍብሃል ይንቅሃልም እላቸዋለሁ። በሰው ቋንቋ እየሰሙኝ በበግ አዕምሮ ይረዱኛል። እነሱ ደጅ ብጥብጥ፣ እኔ ሰፈር ሰላም ይወለዳል።
ሌሎቹን ደግሞ በውል በማያውቁት ታሪክ አጣላቸዋለሁ። ‘ ድሮ ያንተን ዘመዶች ወግቶብሃል’ እለዋለሁ። በነገርህ ላይ መዋጋት የሰው ልጅ ሳይሆን የበግ ነው። የሰው ልጅ ግን “መዋጋት ” የሚለውን ቃል ለጦርነት ሲያውለው ታያለህ። ይህ እንግዲህ ልቡሰ ጥላው፣ በግ መሆኑን ስታውቅሰውን ለመግለፅ ከበጎች ድርጊት የወሰደችው ቃል ነው። ”
ቀጥሎ የምጠይቀው አልነበረኝም። ወዶ ሰውነቱን የሰዋ፣ ሰው ልሁን ማለቱ ወንጀል ተደርጎ እንደሚወሰድ ገባኝ። ሰውነታቸውን ያልሰዉ በቀደሞቻቸው ፍቃድ ልክ ባለመራመዳቸው እንደ ቲሊቃ ባሉ ማጎሪያዎች ይታጎራሉ። ሌሊች በእረኛቸው ፍላጎት ልክ የተንበረከኩ ድኩማን ይሆናሉ። መንገዴን ቀጠልኩ። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። የሰግነት ባህሪ ሊጋባብኝ ነው መሰል።ከሰጎች ባህሪ አንዱ ወዴት እንደሚሄዱ አለማወቅ ነው። ወዴት እንደምሄድ ለመወሰን ቆም አልኩ…