ህእ….ልወደው ነው እንዴ?
አዬ..በምን እድሌ? አይደለም። እስካሁን ያወራሁላችሁ ሁሉ ስለ ኤፍሬም አይኔ ያየውን፣ አንጎሌ የመዘገበውን እንጂ አብላልቼ፣ ሳላስበው ለልቤ የነገርኩት፣ ልቤም ከእኔ የተቀበለውን የውደጂው ጥሪ ተቀብሎ ንዝንዙን የጀመረበት…ልክ ኬቢን የወደድኩበት መንገድ የሚመስል አይደለም። (አያችሁ….አይንና አንጎል ገለልተኞች ናቸው። ሊስት ይዘው ሰው የሚመዝኑ…ይሄ አሪፍ ነው ይሄ ይደብራል የሚሉ……ልብ ግን …ልብ ግን አንዴ ከወደደ ወገንተኛ ነው….ዝርዝር ሳያወጣ…ምክንያት ሳይደረድር በቃ ወደድኩት ብሎ ግግም የሚል…ግድፈት የሚያይ አይን የሌለው…የሚያመዛዝን አንጎል የሌለው ደደብ ነገር ነው ልብ። …)
አዎ ልጁ ድንቅ ነው።
መልከ-መልካም ነው (በሰፊው እንዳየሁት…በሰፊው እንዳወራሁት)
ጨዋ ነው (ለሳምንታት እንደቃረምኩት)
ደስ ብዬዋለሁ ( በአስተማማኝ መረጃዎች ላይ ተመሰርቼ እንደገመትኩት)
ግን ምን ያደርጋል…. ሺህ ጊዜ ቢያምር፣ የት አባቱን ያህል ቢያማልል፣ ለአመታት ቢያነሆልል አንድ ነገር ግን ይጎድለዋል። ኬቢ አይደለም።
——————–
ይሄ በሆነ በወር ከምናምኑ በኬቢ ‹‹ሞክሪው›› ግፊት ተነድቼ፣ በኤፍሬም አሪፍነት እና ‹‹ወደድኩሽ›› ጉትጎታ ይሉኝታ ተይዤ፣ ኬቢን በልቤ ዙፋን አደላድዬ እንዳስቀመጥኩ፤ ከኤፍሬም ጋር ፍቅር የሚመስል ነገር ጀመርን።
እዚህና እዚያ ቡና እና ማኪያቶ። ክትፎና ሽሮ….እዚህ እና እዚያ ሶቶ ተያይዞ መሄድ….እንደ ፍቅረኛ ፊልም ገብቶ ፊልምና ፖፕ ኮርኑን ትቶ ከንፈርን መቃመስ። የከረረ ግንኙነት አልነበረም። ፍቅር አልሞካከረኝም። ከመሳሳም ያለፈ ነገር አላደረግንም፣ ያቺ አመፀኛ ልቤ መች ፈቅዳ። ከኤፍሬም ጋር ውለን ስንለያይ ቤት ስገባ አይናፍቀኝም። አጠገቤ ከሌለ ትዝ አይለኝም። ሳገኘው ግን አይከፋኝም።
ለጥቂት ሳምንታት ይሄ ስሜት ምን እንደሆነ ውሉ ጠፋኝና ቤቴ ስገባ መስታወት ፊት ቆሜ ራሴን ‹‹ምናባሽ እያደረግሽ ነው?›› ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ። እስከዛሬም ደፍሬ መጠየቅ አልፈለግኩም እንጂ መልሱ ሩቅ አልነበረም።
ኬቢ ለኤፍሬም አንፀባራቂ ትሪ ላይ አድርጎ፣ አሳልፎ ከሰጠኝ በኋላ፣ በእሱ ፈንታ ከኤፍሬም ጋር ስውል…ጊዜዬን በሙሉ ስቀማው እስከዛሬ በዝቼ በመገኘቴ ምክንያት ታይቶት የማያውቀው ታላቅ ክፍተት ይፈጠራል ብዬ በማሰብ ነው። ከእጁ ስወጣ ከመዳብነት ወደ ወርቅነት እቀየራለሁ ብዬ ተስፋ በማድረግ ነው። እስከዛሬ አስተውሎት በማያውቅ ሁኔታ ይወደኝ እንደነበር…ይፈልገኝ እንደነበር የሚረዳበትን መልካም የቅናት አጋጣሚ እፈጥራለሁ ብዬ ነው።
አላሳዝንም?
አላሳዝንም፤ ምክንያቱም ከሳምንታት ቸልተኝነት እና ‹‹እንዴት ነው ተመቻቻሁ አይደል?›› የሚሉ ልብ ማቁሰሎች በኋላ ፤ እሰቲ ዞር ስል ዋጋዬ ከታየው ብዬ….ከቀኖቼ የሚበዙትን ለኤፍሬም ፍጆታ ማዋል ስጀምር፣ ከኤፍሬም ጋር ብቻ ወጣ ገባ ማለት ስጀምር፤ ኬቢ በጣም መደወል ጀመረ።
‹‹ ጠፋሽ…ላወራሽ ምፈልገው ጉዳይ አለ›› ብሎ እንደመለማመጥ ሁሉ ሰራው። በርትቼ ትንሽ ባንገላታው እወድ ነበር…ግን ያቺ ገለልተኝነት የማታውቅ…ላፈቀረችው ሰው የቀናት ጭካኔን የማትፈቅድ ስቱፒድ ልቤ እምቢ አለችኝ።
‹‹ሲሪየስ ትመስላለህ…ሰላም አይደለህም እንዴ ኪቢዬ?›› አልኩት አንዱን ቀን ካልተገናኘን ብሎ ሲወጥረኝ።
‹‹እኔ ደህና ነኝ…ዛሬ እንገናኝ….›› አለ ጥድፍ ብሎ።
‹‹ዛሬ?››
‹‹አዎ…ምነው….›
‹‹አይ ኤፊ ጋር ነኝ….››
‹‹ማለት ከእሱ በፊት ወይ በኋላ አግኚኛ!››
(ልጁ ብሶበታል….አርባራቱ ታቦቶች ፀሎቴን ሰምተው በእጄ ሊያስገቡት ይሆን…?)
‹‹አይ…ኬቢዬ ከስራ እንደወጣሁ አርሊ ሄጄ እዛው ላድር ነበር…››
የኤፍሬም ‹‹ ከከንፈር እንውረድ›› ጉትጎታ ቢበረታም፣ ‹‹እሺ በቃ ዝም ብለሽ ነይና እደሪ…አይ ስዌር አልነካሽም›› ልምምጥ የዘወትር ስንቄ ቢሆንም፤ ለኤፍሬም ከንፈሬን እንጂ ሌላ ነገር አልሰጠሁትም። አድሬ አላውቅም። የማደር አጭር እቅድም የለኝም።
ኬቢን ለምን ‹‹ላድር ነው››› እንዳልኩት ጥንቅቄ አውቃለሁ። ያበጠው እንዲፈነዳ ነው። ኬቢ በሆዱ ያለውን ፍቅር (እሱ ባያውቀውም) ቶሎ እንዲወልደው ‹‹ከኤፍሪም ጋር እየተኛሁ ነው›› የሚል የምጥ መርፌ መውጋቴ ነው።
‹‹ላድር?›› ከልክ በላይ ጮኸ።
(ሰምሯል ሃሳቤ ሰምሯል….ሆኗል ምኞቴ ሆኗል…..)
‹‹ምን ያስጮህሃል…?››
‹‹ማደር ጀምራችኋል እንዴ….?››
(ለምንድነው እንደዚህ የሚጮኸው? ቀና…….? ተቃጠለ? እርር ድብን ብሎ አስረክቤ መጣሁ አስረክቤ ወርቅ አምባሬን ከእጄን እያለቀሰ መዝፈን ጀመረ….?)
‹‹ቦይፍሬንዴ መስሎኝ….›› አልኩ ትንሽ ወጠር ብዬ።
‹‹ቢሆንስ…ቢሆንስ…ገና በወር ከምናምን…ገና ምንም ሳታውቂው….››
‹‹ምንም ሳታውቂው? አንተ አይደለህ እንዴ ላንቺ ከእሱ በላይ ሰው የለም ብለህ ስትገፋኝ የነበርከው….?ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?›› (አሁን እኔም መጮህ ጀመርኩ። የከረመች ‹‹እንዴት ለጓደኛው አሳልፎ ይሰጠኛል›› ብስጭቴ እድል አግኝታ ወጣች።)
ቀጥሎ ምን እንደሚል ለመገመት ስሞክር፣
‹‹ይሄ በስልክ አይሆንም…ያለሽበት መጥቼ መነጋገር አለብን….ቀልዴን አይደለም…የት ነሽ?›› አለኝ።
የት ነሽ ነው ያለኝ?
(ፈንጠዚያ አለም ላይ ነኝ የኔ ኦክስጅን።። ከደመና በላይ እየተንሳፈፍኩ በምንም በማንም የማልረበሽበት ውብ የፈንጠዚያ አለም ላይ ነኝ ኬብዬ ማለት አማረኝ።)
በአካል አግኝቼው ሁሉ ነገር ሲፍረጠረጥ…እወድሻለሁ ሲለኝ…ለአመታት የጎመጀሁትን ከንፈሩን ሲሰጠኝ ፣ ለአመታት ያለምኩትን ፍቅር ሲያሳየኝ ታየኝና ሳላቅማማ ተስማምቼ አንዱ ካፌ ተገናኘን።
ተረጋግቶ፣ በአመለጠችኝ….ከሌለ ተኛች ፀፀተ አለንጋ ተገርፎ፣ ….አንገቱን ደፍቶ እና ያፈቀረ ወንድን የልብ ስብራት ይዞ ይጠብቀኛል ብዬ ነበር። ግን ቱግ እንዳለ ነበር። ቀይ ፊቱ ደፍርሷል። አይኖቹ ይባስ ጠበዋል።
የአሸናፊነት ስሜት ውስጥ እየዋኘሁ፣ እንደዋዛ ጉንጩን ሳም አደረግኩትና ተቀመጥኩ። (ከደቂቃዎች በኋላ እንደ ፍቅረኛ ከንፈሮቹን እንደምስም እያሰብኩ…ያውም ለመጀመሪያ ጊዜ…)
መግቢያም ያልነበረው ወሬያቸን ከስልክ ጥሪው ቀጥታ ቀጠለ።
‹‹ለምንድነው አብራችሁ የምታድሩት?›› ብሎ ጀመረ።
ሳቅኩ። በልቤ እያዘንኩለት..ግን ደግሞ….በዚያች የእሱ ባሪያ በሆነች ልቤ እየራራሁለት ሳቅኩ።
(ተነካ እንዴ ይሄ ልጅ?)
‹‹እንዴ ምን ማለትህ ነው?›››
‹‹ምን ታደርጋላችሁ አብራችሁ ስታድሩ…..?››
‹‹ኬቢዬ..ትላንት ነው እንዴ የተወለድከው?›› ብየ እንደገና ሳቅኩ።
‹‹ምእራፍ አትቀልጂ…ጥያቄዬን መልሺልኝ…››
‹‹ያው አልጋው ላይ ካርታ እንጫወታለና…ሌላ ምን እናደርጋለን?!›› በማሾፍ መለስኩለት።
ፊቱን እጆቹ ውስጥ ቀበረና ቀና ብሎ አየኝ። ተለዋጭ እና የተሻለ መልስ የሚጠብቅ ይመስላል።
የጀመርኩትን መጨረስ አለብኝ። ያደፈረስኩትን ማጥራት አለብኝ። መቅናቱን እንዲናዘዝ፣ ማፍቀሩን ይፋ እንዲያወጣ መገፍተር አለብኝ።
‹ምን ይመስልሃል…? ዊ ፋክ….በቃ….!›› አልኩት።
እንዲህ ስድ መሆኔን፣ ኬቢ ላይ እንዲህ መባለግ መቻሌን ማመን አቃተኝ። ግን ይሄ ግልብ መልስ ከልክ በላይ አንድዶት፣ ይሄንን ድብብቆሽ ቶሎ የሚያፈርስና ‹‹እወድሻለሁ›› የሚያስብለኝ፣ ለአመታት የጠበቅኩትን ልጅ በደቂቃዎች የሚሸልመኝ ስለመሰለኝ እንደዚያ አልኩ።
ልቡ በተሰበረ ሰው አኳሃን አየኝ።
እመኑኝ፤ አግኝቼዋለሁ።