Tidarfelagi.com

ሴት እና ትዳር- ‹‹እርቃን››- (ክፍል ሁለት)

ፀሃፊ፡ ቢኮዙሉ ‹‹The Emperor’s Naked”
ትርጉም፡ ሕይወት እምሻው

ትዳራችን ይነፍስበት የጀመረው እዚህ ግባ በማይባሉ ጥቃቅን ነገሮች መነሻነት ነበር።

አለ አይደል…ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ እንዴት አደርሽ ማለት ሲተው…(ባሎች፣ እባካችሁ..ሁሌም ሚስቶቻችሁን እንዴት አደርሽ ብላችሁ ጠይቁ….በክር ከተሰራች አሻንጉሊት ጋር አይደለም እኮ ተኝታችሁ ያደራችሁት! አንድ ቀን እንዴት አደርሽ ብላችሁ መጠየቅ ስትረሱ ነገም አታስታውሱም…ከዚያ ይለምድባችሁና ልክ አዳሪ ትምህርት ቤት እንደሚኖር ተማሪ ብድግ ብላችሁ ካልጋ መውጣት ትጀምራላችሁ። )

እና እንዳልኳችሁ ጠዋት መነሳትና ሰላም ሳይለኝ ወደ ሽንት ቤት መሄድ ጀመረ።
ሁልጊዜ እንዴት አደርህ የምለው እኔ ሆንኩ። ከዚያ እኔ ብቻ እንዴት አደርህ ማለቱ ታከተኝ። እየቆየ ሲሄድ ጠዋት ጠዋት እኔን ማየት እንኳን እንዳቆመ ማስተዋል ጀመርኩ።

ልብስ እየለባበስን ስናወራ እንኳን ጭራሽ አያየኝም። ለማየት የማስቀይም አይደለሁም፤ ሁሌም ራሴን በመስታወት ስለምመለከት ይሄንን አውቃለሁ። እና ታዲያ ምን ሆኖ ነው የማያየኝ? እኔ ደግሞ ሰው ካላየኝ ኖርኩ አልኖርኩ ግድ እንደሌለው ነው የሚሰማኝ። ካላየኸኝ የለሁም ማለት ነው…ድምጽ ብቻ ያላት መንፈስ ሆንኩ ማለት ነው…(.ወንዶች፣ እባካችሁ ሚስቶቻቸሁን እዩ። )

ጠዋት ጠዋት ሰላም ማደሬን ባይጠይቀኝም፣ ባያየኝም ግን ትዳራችን ጥሩ የሚባል ነበር። ቤቱን ማስተዳደር ላይ አልሰነፈም። ለልጆቹ መጫወቻ እና ልብስ ይገዛል። አንዳንዴም አብሯቸው ይጫወታል።

ከዚያ ሕይወት በማይታሰብ ፍጥነት መክነፍ ጀመረች። ልጆቻችን ትምህርት ቤት ሲገቡ የትምህርት ቤት ክፍያ ራስ ምታት እና ለነገ ጥሪት የመቋጠር ጭንቀት ይወጥረን ጀመር። ባለቤቴ ትልልቆቹን ወጪዎች ሲችል እኔ ደግሞ ጥቃቅን የቤት ቀዳዳዎችን እየደፈንሁ ኑሮ ቀጠለ።

ከዚያ ሳይታወቀን ሁለታችንም በየራሳችን ዛቢያ የምንሽከረከር፣ በማይገናኙ መንገዶቻችን አለእረፍት የምንሮጥ እና የምንባዝን ሰዎች ሆንን።
እሱ ቤት ከሚኖርበት ጊዜ ስራ ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ እየበዛ፣ ቤት ሲመጣም በድካም ብትንትን ብሎ እና ልጆቹን እንኳን ማናገር እንዳይችል ሆኖ፣ ለመኝታ ብቻ ሆነ።

እሁድ እሁድ ቤት ይሆናል ግን ከቅዳሜ የዞረ የመጠጥ ድምሩን ስለሚያወራራድ እንዳለ አይቆጠርም። ሁሌም በስራ ደክሞ ስለሚገባ ልጆቼን ብስክሌት መንዳት እንኳን ያስተማርኳቸው እኔ ነኝ። ለነገሩ ጭራሽም ለማድረግ አልሞከረ።

እያደር እሱ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ስራዎችን ፣ ሊወጣቸው የሚገቡ ሃላፊነቶችን እኔ ማድረግና መወጣት ጀመርኩ። የቧንቧ ሰራተኛ ፈልጎ ማግኘት…የልጆቹን ትምህርት ቤት መምረጥ።

ልጆቻችን እያደጉ ሲሄዱ አብሯቸው ማሳለፍ ያለበትን ጊዜ ሳያሳልፍ እድሜያቸው እንዳያልፍና እንዳይቆጨው ብዬ ጊዜ እንዲሰጣቸው የምችለውን ሁሉ ጣርኩ። እስቲ መናፈሻ ወይ መጫወቻ ቦታ ውሰዳቸው…ብስክሌት አብረሃቸው ጋልብ….አዋራቸው፣ ወንዶቹን ደግሞ እንዴት አይነት ወንድ…እንዴት አይነት አባት መሆን እንዳለባቸው አሳያቸው ስል ወተወትኩት።

እሱ ግን ሁሌም ጊዜውን የሚሻማ ነገር አያጣም። ሁሌም ከዚህ የሚበልጥበት ነገር አይጠፋም።
ከዚያ የቤተሰቡ ራስ እኔ ሆንኩ፣ ውሳኔ አሳላፊዋ ሆኜ አረፍኩ። ከጊዜ በኋላ የትምህርት ቤት ክፍያ በጊዜ መክፈል አቆመ። ጭራሽ ትምህርት ቤቱ ደውሎ ክፍያ ይጠይቀኝ ጀመር። ያን ጊዜ የዚያኛውን ሴሚስተር ራሴ እከፍልና የሚቀጥለውን እንዲከፍል ባየው ባየው እሱ እቴ!

አባቴ ለእናቴ ምን አይነት ባል እንደነበር አላውቀም፡- ምናልባት እንደ ባል ያጎደለባት ነገር ይኖር ይሆን አላውቅም።፡ ለእኔ ግን ምን አይነት አባት እንደነበር ጠንቅቄ አውቃለሁ። ሃላፊነቱን የሚያውቅና በአግባቡ የሚወጣ አባት ነበር። በዚያ ላይ ኩሩ ነበር- የእኔ አባት።

አንዴ አስታውሳለሁ- አስር ወይ አስራ አንድ አመቴ እያለ- ቅዳሜ ቀን ነው…. ጠዋት ቁርስ እየበላን በልጅነት አእምሮዬ ያኔ- ምክንያቱ አልገባኝም ግን የሆኑ የባንክ ሰራተኞች ወደ ቤታችን መጡ። አባዬ እኔና እማዬን ካለንበት ትቶን ሊያናግራቸው ይሄዳል።
በሳሎኑ መጋረጃ ውስጥ ውጭ ቆሞ ሲያዋራቸው አያለሁ። ከአጥራችን ውጪ የቆመው የጭነት መኪና የቤት እቃችንን በሙሉ ለቃቅሞ ለመሄድ የጓጓ ይመስላል። እማዬ ከተቀመጠችበት ሳትነሳ፣ አንዴ እንኳን ሳትንቀሳቀስ፣ ተነስታ ወደ አባዬ ሳትሄድ እዛው ቁጭ ብላለች።
የእሷ ተረጋግቶ መቀመጥ እኔንም ሲያረጋጋኝ አስታውሳለሁ። እሷ እንደዛ ረጋ ብላ ቁጭ ካለች ውጪ እየሆነ ያለው (መጥፎ ነገር ይመስላል) ምንም ነገር ቢሆን አባዬ መላ እንደማያጣለት እና ወደ ቁርሱ እንደሚመለስ ነገረኝ።

እናም ልክ እንዳሰብኩት ሆነ። አባዬ ያንን ቀን ልክ ሌሎች ቀኖችን እንደሚያሳልፈን በብልሃት አሳለፈን።
ከዚያ በኋላ ስለ ወንድነት ያለኝ ግምት አባቴን ተደግፎ የተሳለ ሆነ። ወንድ ልጅ፣አባወራ ሲሆን ቤተሰቡ የሚገጥመውን ችግርን ወጥቶ እንደ ወንድ መጋፈጥ እንዳለበት፣ ከዚያም በኩራትና በልበ ሙሉነት መቆም እንዳለበት ከአባዬ ተማርኩ።
.
እናትና ሚስት ሆኜ ቤቴን ማስተዳደር ምኞቴ ነበር። ባሏን የምትከተል፣ ታታሪና ጨዋ ሚስት መሆን ነበር ፍላጎቴ። ሚስት። ቀስ በቀስ ግን የአባወራውን ስራ መረከብ ጀመርኩ። ባል ሆንኩ። እሱ መወሰን ያለበትን ነገር መወሰን። የልጆቹን ትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል።
ያን ጊዜ በሌላ አይን እመለከተው ጀመር። በፊት የምመካበት እና የማደንቀው ወንድ መሆኑን አቆመ። አቅጣጫው ጠፍቶበት የሚማስን ሰው ሆኖ አገኘሁት፣ አቅጣጫው የጠፋበት ሰውን ደግሞ መከትል አልችልም።
ከጊዜ በኋላ አንዳችን ለአንዳችን ጭራሹን ባእድ ሰዎች ሆነን አረፍነው።

የባል እና ሚስት ወጋችን እንደ በርሃ ዝናብ በጭንቅ የሚመጣ እና በስንት ጊዜ የሚከሰት ነገር ሆነ።
ከስንት አንዴ ሆኖልን ፍቅር ስንሰራ እንኳን ሃሳቤ ወደማልመው የእንጆሬ እርሻዬ እየሄደ ያስቸግረኛል።
ስናወራ ከሌላ አለም እንደመጣ ሁሉ፣ ሁሉ ነገሩ እንግዳ ይሆንብኝ ጀመር። የማላውቀውን ቋንቋ እንደሚናገር እንግዳ ሰው።
ይሄ ሁሉ የሆነው አሪፍ ሚስት መሆኔን ስላቆምኩ ይሆናል። እንደ በፊቱ አምሽቶ ሲመጣ እና እራት እየበላ የዚያን እለት ቢሮ ስለተፈጠሩ አስደናቂ ነገሮች ሲያወራኝ እያዳመጥኩ፣ ቁጭ ብዬ አላየውም።

ይልቅ ለጥቂት ቀናት ፊልድ ሲሄድ ልቤ ጮቤ ይረግጣል።፡
ያን ጊዜ ቤቱ ይሰፋኛል፣ ክፍሎቹ ወደ ጎን ልጥጥ ይላሉ… ያኔ.መተንፈስ እችላለሁ።

ከፊልድ የሚመለስ ቀን ቀድሜው ገብቼ ደህና የሚበላ ነገር አዘጋጅቼ (ድሮ ቢሆን የምበላው ነገር እኔ ነበርኩ!) ለመጠበቅ አልቸኩልም። በፊት በፊት በየትኛው አውሮፕላን እንደሚመጣ፣ ትራንዚቱ የት እንደሆነ፣ ስንት ሰአት የት እንደሚደርስ አውቅ ነበር። አንዳንዴማ ኤርፖርት ሁሉ ሄጄ እቀበለው ነበር- ያውም ምን እንደሚናፍቀው ስለማውቅ ትኩስ ቡና በፔርሙስ ይዤ!

አሁንስ? አሁንማ ደስ የሚለኝ ሲሄድልኝ ነው። ምክንያቱም ቤት ውስጥ ሆኖ ልክ እንደ ወንዶቹ፣ ልክ እንደ ቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ እንደ ደህና አባወራ ወዲህ ወዲያ ሲል ላየው ስለማልፈልግ ነው። በዚያ ላይ…የሚያገኘውን ገንዘብ የት እንደሚያደርገው ሳላውቅ ወይ ሳይነግረኝ…
ቤተዘመድ ጋር አብረን ስንሄድ ግን እንደ መልካም ሚስት- እናት እና አባቱ እንደሚፈልጓት አይነት- እሆንና ምግብ አቀርበለታለሁ። እናቱ ልጃቸው እንዲህች አይነት ድንቅ ሚስት አግብቶና በትዳሩ ተደላድሎ ስለሚኖር ኩራት ኩራት ይላቸዋል።

የማያደንቀን ሰው የለም። ‹‹ድንቅ ጥንዶች›› ይሉናል አንዳንዶቹ። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው።
አናወራም።
አንጣላም- ለጠብ የሚሆን ጉልበት እንኳን አልነበረንም።
ውድቅት ላይ ቤት ቢመጣ ግድ አይሰጠኝም።
ውጪ ያስቀመጣት ሴት ብትኖር እንኳን ደንታ የለኝም።
ያስቀመጣት ካለችውም የወንድ ቅርፊት እንጅ ደህና ወንድ እንዳላገኘች ስለማውቅ አይቆረቁረኝም። የወንድ ልጣጭ ነው ያገኘችው። የወንድ ጭራ።
የባለቤቷን ጉድለቶች አንድ በአንድ የምትቆጥር፣ ኩንታል ስህተቶቹን ተሸክማ የምትኖር፣ የወንድነት ጥላ የራቀው እርቃን እና ደካማ ባሏን አብጠርጥራ የምታውቅ ሚስት ሆኛለሁ።

እርግጥ ነው- እኔም ደካማ ጎን አለኝ- ምን ጥያቄ አለው? እዚህና እዚያ ምላሴን ያዳልጠኝ ይሆናል። ነገረኛ ብጤም ሳልሆን አልቀርም። እሱም ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ጨቅጫቃ መሆኔን ነግሮኛል።

እንዲህ ስለመሆኑ እና እንዲህ እንዲሆን ምክንያት ስለሆኑት ነገሮች የማወቅ አንዳችም ፍላጎት ግን የለኝም።
አንዴ የሆነ አውሮፓ ያለ ኤርፖርት ውስጥ ሆኜ በጉዞ የተዳከሙ እና ጥውልግ- ትክት ያሉ ሰዎች- አይኖቻቸውን ባዶ አየር ላይ ተክለው– ዝም ብሎ በራሱ የሚሄደው ተንቀሳቃሽ ደረጃ ላይ በደመነፍስ ሲሳፈሩና በድንዛዜ ሲሄዱ ሳይ ‹‹ትዳሬ ልክ እንደዚህ ነው››› ስል ትዝ ይለኛል።
በቅርቡ የሆነ ደረሰኝ ኪሱ ውስጥ አግኝቼ ነበር። ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናና አምሽቶ የከፈለበት ነው። ለአንድ ጠርሙስ ውስኪ እና ለሚበላ ነገር ሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር ከፍሏል። በአንድ ምሽት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር! ያውም በአዘቦት ቀን።
ደረሰኙን ሳይ ልቤ በጩቤ የተወጋ መሰለኝ። የልጆቹን ትምህርት ቤት ክፍያ አልከፍልም የሚል ግን ለመጠጥ ይሄን ያህል ብር የሚያወጣ ወንድ ሆኗል።
ስለ ልጆቹ ጉብዝና ለወላጆቹ፣ ለዘመድ አዝማድ የሚጎርር ግን ተማሩ አልተማሩ ግን የማይሰጠው ሰው ሆኗል። ያውም ከእኔ በስንት እጥፍ የሚበልጥ ደሞዝ እየበላ።
እርግጥ ነው እንዳሻው እንዲሆን ፈቅጄለታለሁ። የውሸት እንዲኖር ተባብሬዋለሁ። ጥሩ አባት እና መልካም ባል ነኝ ብሎ የሚያምንበትን የቁጩ አለም ገንብቶ የውሸት እንዲኖር ይሁንታዬን ሰጥቼዋለሁ።
እዋሽለታለሁ። ከዚህ ሁሉ ነገር የሚስጠላው ነገር ግን የእሱ ውሸታምነት እኔንም የውሸት የምኖር ውሸታም ማድረጉ ነው። ሁለመናዬ ውሸት የሆነ ሰው አድርጎኛል።

ምናልባት ጠርጥራችሁ ከሆነ ከሌላ ሰው ጋር መውጣት አልጀመርኩም። ሰው ጠፍቶ አይይለም። መግቢያ መውጫ ያሳጡ ብዙ ወትዋቾች አሉኝ።
ግን በህግ ባለትዳር ነኝ፣ ትዳር ያለኝ ላጤ ብሆንም። ከባለቤቴ ጋር ‹‹ትዳር›› የሚባል ለትርፍ የተቋቋመ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የምንመራ ሁለት ሰዎች ብንሆንም።
እንደሚስት በምንም ነገር እንዲያግዘኝ መጠየቅ ካቆምኩ ቆየሁ።
እንደ ቤቱ ራስ፣ እንደ አባዋራ እሱን መከተል ከተውኩ ቆየሁ- መምራት አቁሟላ!
ግርማ ሞገሱ ጠፍቶ አይኔ ላይ ከኮሰሰ፣ ለእሱ ያለኝ ክብር ብን ብሎ ከጠፋ ሰነባበተ።
በፊት በፊት ያማልለኝ የነበረ ያ ወንዳወንድነቱ….ለምሳሌ ጠዋት ጠዋት ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ ጥርሱን ሲፍቅ ሳየው የሚሰማኝ ሞቅታ በፀፀት ተተክቷል።

እስከ መቼ ነው እንደዚህ የምኖረው ግን?
እኔስ እስኪያንገሸግሸኝ፣ እስኪያቅተኝ ድረስ እዚህ ያጋደለ፣ ጣራው የሚያፈስ ጎጆ ውስጥ መኖር እችላለሁ።
ከሁሉ የሚያንገበግበኝ ግን ልጆቼ የአባታቸውን ሁኔታ መረዳት መጀመራቸው ነው።
አባታቸው ለቤተሰቡ ጥላ ከለላ የሚሆን ጠንካራ አባወራ አለመሆኑን ማየት መጀመራቸው ነው።በተለይ ለወንድ ልጆቼ አብዝቼ እጨነቃለሁ። የአባወራ ምሳሌ አድርገው ለሚስሉት ምስኪን ልጆቼ።

የወንድነት አርአያ አድርገው የሚቆጥሩት – እሱን በሆንኩ የሚሉት ሰው ይሄ በመሆኑ፣ ልጆቼ አውላላ ሜዳ ላይ ስለቀሩብኝ አዝናለሁ።
ስለ ልጆቼ እጣ ፈንታ የምጨነቀው እኔ ብቻ፣ ለቤተሰቤ የምወጋው እኔ ብቻ መሆኔ ልቤን በሃዘን ያደማዋል። ውስጤን ይሰረስረዋል። ያበግነኛል።
ከዚህ ግራ የገባው ሁኔታ እንዴት ማምለጥ እንዳለብኝ አላውቀም።
ምክንያቱም….የቤቴን ወጪ መሸፈን እችል ይሆናል፣ ከልጆቼ ጋር ማውራት እና መጫወት እችል ይሆናል፣ የቤት ሥራቸውን አብሬያቸው መስራት፣ ሲጎብዙ ማበረታታት፣ እንደ እናት ስለ እነሱ መፀለይ አያቅተኝ ይሆናል። ግን እንዴት መልካም አባወራ መሆን እንዳለባቸው ላሳያቸው፣ አርአያ ሆኜ ልመራቸው አልችልም። ያንን ሊያደርግ የሚችለው አባወራው ብቻ ነው። የእኔ አባ ወራ ተብዬ ደግሞ ሃላፊነቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ ወንድነቱን እንደ አሮጌ ካፖርት አውልቆ ወንበር ላይ ማንጠልጠልን መርጧል።
—–አበቃ——

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *