እግሬና ሀሳቤ ሳይስማሙ እግሬ ቀድሞ ሬስቶራንቱ ውስጥ ተገኘ። ሲሳይ ቀድሞኝ ተገኝቷል። ልጨብጠው የዘረጋሁትን እጄን ሳብ አድርጎ አቀፈኝ። የምቀመጥበትን ወንበር ሳበልኝ። እራትና ወይን አዘዝን። ከእርሱ ጋር መጨቃጨቁ ትርፉ የሌላ ሰው ትኩረት ከመሳብ ያለፈ ስለማይሆን ዝም ብዬ የሚያደርገውን ከማየት ውጪ ተቃውሞም መስማማትም አልተነፈስኩም። አፉ ከማውራት እጁ ከማጉረስ ሳይቦዝን ነበር እራት ተመግበን የጨረስነው።
“እኔ ከዚህ በላይ አልጠጣም። ስራ መመለስ አለብኝ።” ያልኩትን የሰማ አይመስልም። ቀዳልኝ። በአትኩሮት ሲመለከተኝ ከቆየ በኋላ
“ሴክስ ካደረግሽ ስንት ጊዜሽ ነው? ወራት? አመታት?” አለ ቀለል አድርጎ
“አንተ? ያምሃል እንዴ? ” አልኩት ደንግጬ ይሁን አፍሬ ሳይገባኝ
“ምነው? አንቺ? ጭራሽ… ……ዜሮ ዞሮ ነሽ እንዴ?” በማብሸቅ ለዛ ነው ያወራው ። ደሞ አብሽቆኛልም።
“አንተ እኔን ለማንጓጠጥ የሚያስችለህ ቦታ ላይ እንዳለህ ነው የሚሰማህ?” ሳልጨርስ መንፈቅፈቁን ያዘው
” ማሂ ከእኔ ጋር ስታወሪ ጨዋ ቃል አትፈልጊ…… ሃሃሃሃ ‘ትናንት እጄ ላይ ሸለፈትህን ተገርዘህ፣ ልጅህን በማስገረዣ እድሜህ አንዠርግገኸው…ምናምን ……‘ በይው ”
“እንደሱ ለማለት እንኳን አልነበረም።” መለስኩለት
“በጨዋኛ ስለብድ ምን ታውቅና? እንደማለት አይደል?”
“በየሱስ ስም!» ከመደንገጤ የተነሳ ወንበሬ ላይ ዘልያለሁ። እሱ ምንም እንዳላለ ሁሉ በሁኔታዬ ይንፈቀፈቃል።
“ያልተገረዘ ሴክስ አያደርግም ያለሽ ማነው?” አባባሉ ቀዝቃዛ ስሜት ስለነበረው ስሜቱን የጎዳሁት ስለመሰለኝ ወንዶች ስለማይገረዙባቸው ሀገራት፣ ገጥመውኝ ስለሚያውቁ አጋጣሚዎች ነገርኩት።
“ኮንዶም የለ፣ ምን የለ… … ጫፉን ሸብ አድርጎ መሰማራት ነው። ተፈጥሯዊ ኮንዶም በይው ሃሃሃ” ብልግና ያወራ፣ በራሱ ያላገጠ አይመስልም። ደንግጬ ፈጥጬ አየዋለሁ።
“ኸረ ስቀልድሽ ነው አንቺ!!” አለ መሳቁን ሳያቆም።
በህይወቱ ውስጥ የሚያስከፋው፣ የሚያፍርበት፣ ሊያወራው የማይፈልገው ነገሩ ምን ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ሲያወራ ፍፁም ጨዋ፣ ደግሞ ፍፁም ባለጌ፣ ደግሞ ፍፁም አዋቂ፣ ደግሞ ፍፁም ህፃን………ሁሉንም ይሆናል። ሲሳይን ማወቅ ከበደኝ። ያልተገረዘው ቤተሰባቸው ወንድ ልጅ እየሞተ ሲያስቸግራቸው የሄዱበት ጠንቋይ እንዳይገረዝ ስለነገራቸው መሆኑን እንደለመደው በራሱና በቤተሰቡ እየቀለደ ነገረኝ።
“እያደግኩ ከመጣሁ በኋላ መገረዙ አሳፈረኝ እና አረጀሁ።”
“በፍፁም አፍረህበት የምታውቅ ግን አትመስልም ነበር።”
“አንቺጋ ስመጣማ ከማፈር አልፎ አስጠልቶኝ ነበር።”
ሲያወራ በራስ መተማመኑ ለሰከንድ አይለየውም። ደጋግሞ ከሚያወራቸው ነገሮች በወላጆቹና በ6 እህቶቹ የተለየ ፍቅር ተሰጥቶት እንደኖረ ገባኝ። ከብዙ ሰው ጋር መግባባቱ፣ ብዙ ጓደኞች ማፍራቱ ምናልባትም ከተማረው የሳይኮሎጂ ትምህርቱጋ ግንኙነት ይኖረው ይሆናል ስል አሰብኩ።
“ጓደኞች የሉሽም? የሆነ አብረሻቸው አንዳንዴ ዘና የምትዪበት ምናምን?”
“የሉኝም!!”
“እሺ ሲደብርሽ፣ ሲከፋሽ፣ ደስ ሲልሽ ወይ የተለየ ነገር ሲገጥምሽ ለማን ታወሪያለሽ?” አለኝ አይኖቹ የሚያነቡኝ ስለሚመስሉኝ እሸሻቸዋለሁ
“ለራሴ አወራዋለሁ።” አልኩት አይኑን ሳይሰብር አየኝ። “አንተስ?” አልኩት
“ያ ስሜት በተሰማኝ ሰዓት አጠገቤ ላገኘሁት ሰው። ለምሳሌ በኋላ ሸኝቼሽ ስመለስ ለሆስፒታላችሁ ዘበኛ ደስ እንዳለኝ ልነግረው እችላለሁ።” ቀለል አድርጎ ነው የሚያወራው
“እየቀለድክ ነው?”
“የምሬን ነው። ምነው?”
“የምልህ ከእኩዮችህ፣ ቢያንስ ከቤተሰብህ……… ባንተ ደረጃ ካሉ ሰዎች ጋር……… ” አላስጨረሰኝም።
“ደረጃ ምንድነው? ደረጃ መዳቢውስ ማነው? እኔን ከኒኛ ዘበኛ ወይ ከዚህ አስተናጋጅ በላይ ወይ በታች ደረጃ የሰጠን ማን ነው? የኔ መማር እና ቢሮ መቀመጥ? የሳቸው የእኔን እድል አለማግኘትና ዘበኛ መሆን? ንገሪኝ እስኪ እሳቸው የሚያውቁትን ወይ የሚችሉትን ደረጃ ብለን ባወጣንላቸው ዘበኝነት እንዴት እንመዝነዋለን?” አይቼበት የማላውቅበትን የለበጣ ፈገግታ ፈገግ ብሎ ቀጠለ
“አፈር ምን ደረጃ አለው? ነፍስስ ብትሆን ያው ነፍስ አይደለች? በምትሰራው ስራ ካልዳኘናት በቀር? የሰው ደረጃው ‘ሰውነቱ‘ ነው።” አለኝ። ዝም አልኩት። ምንስ ልለው እችል ነበር?
“ቤተሰቦችሽ? የት ናቸው?” አለኝ ወዲያው ከዛኛው ስሜት ወጥቶ
“ቤተሰቦቼ………?…… ”
“ምነው? ሞተዋል? ተጣልታችኋል? ወይስ…… እንደ እህል ዘርተውሽ ነው የበቀቀልሽው?…” ተናድጄ አቋረጥኩት ቁስሌን እያወራ እንደሆነ አልገባውም።
“ምንም ስነስርዓት አታውቅም። ባለጌ ነህ እሺ!!” አልኩት
“እሺ!” አለኝ ቁጣዬን ከምንም ሳይቆጥረው እጄን እየዳበሰ።
“እሺ ግን ንገሪኝ። ማወቅ እፈልጋለሁ።
ምኑን ልንገረው? አባቴ ከእህቱ ልጅ እንደወለደኝ እና ወንድ አያቴ እንዳሳደጉኝ? አድጌ ራሴን እስከማውቅ አባትና እናቴን እንደማላውቅ? ቤተሰቡ ውስጥ እንደ አንዳች መዓት ሲፀየፉኝ እንደኖርኩ? አያቴ ሲሞት ያየሁትን አስቀያሚ የህይወት ገፅታ? የቱን ልንገረው? ለማንም ለማውራት የሚቀል አልነበረም። እንባዬ መጣ። እያየኝ ማልቀስ አልፈለግኩም። ፈርጣጭ ይበለኝ። ተነስቼ መውጣት እንደጀመርኩ እንባዬን ማስቆም አቃተኝ።
ሬስቶራንቱን መግቢያ እንዳለፍኩ እሮጦ ደረሰብኝ። አቀፈኝ። እንደህፃን ደረቱ ላይ አጥብቆ አቀፈኝ። አለቀስኩ። አላባበለኝም። ፀጉሬን እየደባበሰና እየሳመ ለቅሶዬን እስክተው ጠበቀኝ። ያስለቀሰኝ ምን እንደነበረም አልጠየቀኝም። እንደተለመደው እያሳቀኝ የሆስፒታሉ መግቢያ ድረስ ሸኘኝ። ሲሰናበተኝ መልሶ አቀፈኝ። እቅፉ ውስጥ ብዙ መኖር ፈለግኩ። ከሆነ ነገር የሸሸገኝ መሰለኝ። ሰላም ያለበት ዓይነት። እሱም የገባው ይመስል አቅፎኝ ለደቂቃዎች ቆየ። ግንባሬን ሳመኝ።
“ዶክተር ሰላም አይደለሽም እንዴ?” ሲስተር ቀለም መግባቷንም አላስተዋልኩም።
“ሰላም ነው ሲስተር”
“ዶክተር ታዴ እየፈለገሽ ነው። ኢመርጀንሲ ነው። ስልሽ እኮ አልሰማሽኝም።” እያወራችኝ የሻከረ መዳፏን ታፍተለትላለች።
እስከዛሬ እጇን አይቼው አላውቅም። ከድምፅዋ በቀር ምኗንም አስተውዬ አላውቅም። ለምንድ ነበር አውርቻት የማላውቀው? ለምንድነው ግንባሬን እንደቋጠርኩ ገብቼ የምወጣው? እንዲያከብሩኝ? ሲሳይ እንዳለኝ በራሴ ስለማልተማመን? ወይስ ደረጃዬን ስጠብቅ?
“ሲስተር ቤተሰብ አለሽ እንዴ?” አልኳት ለመሄድ እየተሰናዳሁ
“አዎን ባለትዳር ነኝ። አንድ ልጅም አለኝ። ምነው? ምን አጠፋሁ?”
ጉልበቴ ከዳኝ። ዞሬ አየኋት። በደቂቃ ብዙ ነገር አሰብኩ። ትፈራኛለች ምክኒያቱም ስራዋን ማጣት አትፈልግም። ከስራ ውጪ ስለምንም ነገር አውርቻት አላውቅም። ደሜ ቀዘቀዘ። እንዴት አይነት ጭራቅ አድርገው ነው የሚያስቡኝ?
“እንዲሁ ማወቅ ፈልጌ ነው። ለምን ትፈሪኛለሽ? አንቺ በጣም ታታሪ ሰራተኛ ነሽ እኮ!!” ትከሻዋን ዳበስ አድርጌ ወጣሁ።
★ ★ ★
ፈገግ እያልኩ መሆኔ ለራሴ ይታወቀኛል። ታካሚዎቼን እየፈገግኩ እንደማዋራቸው ገብቶኛል። እያፏጨሁም መሰለኝ። ሰሞኑን በተደጋጋሚ ከሲሳይ ጋር እራቴን መብላቴን ተከትሎ እንደዚያ እየሆንኩ ነው። ዶክተር ሰይፈን ይቅርታ መጠየቄ የሆነ ጭነት ከላዬ ላይ እንደማራገፍ ነበር። ወደ ስራ እንዲመለስ የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደማደርግ ስነግረው ግን
«ይቅርብኝ» ካለው ቃል በላይ ከቃሉ ጋር ከንፈሩን ነክሶ የፈገገው ፈገግታ ራሴን ደጋግሜ እንድረግም አድርጎኛል።
ሲስተር ቀለም በተረኛ ታካሚ ፈንታ ገባች
“ዶክተር ሰው ይፈልግሻል?”
“ሲሳይ ነው? ትንሽ ታገሰኝ በይውና ተረኛ ታካሚ አስገቢልኝ።”
“ዶክተር ……… ባለቤትሽ ነው።”