በመጀመሪያ ወንደ ላጤ ነበርኩ፡፡ በሰውም በሴጣንም ምክር፣ ትዳር ለመያዝ ቆረጠኩ( ፈጣሪ ምክር አይወድም መሰል ምንም አላለኝ)! …. እናም ነገር በሶስት ይፀናል ብዬ ሶስት ጊዜ አገባሁ፡፡ ፍቺም በሶስት ይፀናል ብዬ፣ ሶስት ጊዜ ፈታሁ፡፡ መቼም ሶስቴ አግብቼ፣ ሶስቴ መፍታቴ ከማመንዘር ፍላጎት የመነጨ እንዳልሆነ አንባቢዬ ከኔ በላይ ያውቅል፤ ከአንባቢዬ በተሻለ ደግሞ ፈጣሪ ያውቃል፡፡ ለትዳር የማልስማማ ዓይነት ሰው ሆኜም አይደለም፤ በሴቶቹ ፀረ-ትዳር የሆነ ባህሪ እንጂ! እንደሚከተለው በቅደም ተከተል አብራራለሁ፡፡
‹‹‹‹
ትዳር-1(ማንኮራፋት)
የዚህችኛዋ ችግሯ ማንኮራፋት ነው፡፡ ወይኔ ስታንኮራፋ!! በተጋባን በመጀመሪያው ሳምንት ምንም ዓይነት ማንኮራፋት አልነበረም፡፡ በሳምንቱ የሆነ የሚያስበረግግ ድምፅ ሰምቼ፣ ደንብሬ ተነሳሁ፡፡ የሆነ ትልቅ ነገር የቤቴ ጣራ ላይ እንደወደቀ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ አዎ ሄሊኮፕተር ጣራዬ ላይ ወድቆ መሆን አለበት፡፡ ወጥቼ ባይ ምንም የለም፡፡ ድምፁም አልቆመም፡፡ ምንድን ነው? የድምፁ ምንጭ ከቤት ውስጥ ነበር፡፡ ወደውስጥ ገባሁ፡፡ እሷ ነበረች፡፡ ቤቴ ላይ ሄሊኮፕተር የወደቀ የመሰለኝ እሷ እያንኮራፋች ነው ለካ፡፡ ኮርርርር …..ኮርርርር! በድንጋጤ እና በግራ መጋባት አያታለሁ፡፡ ያን ቀን ሳልተኛ አደርኩ- ስታናፋ አደረች፡፡
ጠዋት ወደ ስራ ለመሄድ ስወጣ፣ ሶስት የሰፈሩ ህፃናት ሱቅ አጠገብ ቆመዋል፤ “ ማታ ምንድን ነው ስንደዛ ሲጪህ የነበረው?” ሲል ሰማሁ አንዱ፡፡ “አንበሳ ነዋ!” መለሰ ሌላኛው፡፡
“አንበሳ ይላል እንዴ፣ አንበሳ ከየት መቶ ነው የሚጮኸው? እናቴ የሰው ጅብ ነው ብላኛለች ” ብሎ መለሰ ሌላኛው፡፡ ….እሰይ! ለካ በአዲሱ ትዳሬ እኔ ብቻ ሳልሆን ሰፈሬውም ነው እንቅልፉን ሰውቶ ያደረው፡፡ እራሳቸው አግባ አግባ ሲሉኝ አልነበር እሰይ!
››››››
ከዛ ቀን በኋላ የማንኮራፋትን ፕሮግራሟን ሳታስተጓጉል ቀጠለች፡፡ እኔም በትዳር ስም ሌሊቱን ሙሉ የሚሰራ ወፍጮ ቤት ውስጥ ገብቼ ኑሬዬን ቀጠልኩ፡፡
በእሷ ማንኮራፋት ምክንያት….
-ግድግዳዬን እንደ መስክ መውጫቸው ያዩት የነበሩት በረሮዎች ደንብረው ጠፍተዋል(በዚህ አመሰግናታለሁ)
– አይተውኝ የማይበረግጉ የነበሩት አይጦች ከዛች ቀን በኋላ ድራሻቸው ጠፍቷል(በዚህም አመሰግናታለሁ)
– በዛች መጀመሪያ ባንኮራፋችባት ቀን፣ በማንኮራፋቷ ጥናት ግድግዳ ላይ የሰቀልኩት የአያቴ ጋሻ ወደቀ( የዚህ ትርጉሙ ምን ይሆን ብዬ ተብሰልስያለሁ)፤
-አዎ በማንኮራፋቷ ብርታት አሉኝ የምላቸው ብርጭቆዎች ተሰባበሩ፤ ቅስሜም ተሰበረ፡፡
– አዎ በማንኮራፋቷ ኀያልነት፣ የሚታይ እንጂ የማይበላ የሰብል እህል ሲያሳየኝ የነበረው የቴሊቪዥኔ ስርጭት ላይሰራ ተቋረጠ( ሲኦሌን ገነት አድርጎ ከሚያሳየኝ ኢቲቢ ገላልላኛለችና በዚህም አመሰግናታለሁ)
የከፋው ግን….
እንቅልፍ ህልም ሆነ፡፡ በዬት አባቴ በኩል ልተኛ፣ ጩህ ጩህ ይለኛል! ኮርርርርር ኮርርርርርር…..ዶቅ ዶቅ ዶቅ ዶቅ… ቤቴ ዘጠና ሚሊዮን የሚጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠራርቶ፣ ሺሻ የሚስብበት መሰለ፡፡ ዶቅ ዶቅ ዶቅቅ ዶቅ-90 ሚሊየኑም ህዝብ! … ሰውነቴ ከሳ፡፡ ማንኮራፋቷን ድንገት ተረክ ስታደርግ፣ ስንጥቅ የሚያደርገኝ ድንጋጤ አሳቆ ሊገድለኝ ሆነ፡፡
ከቀረው ዓለም ሁሉ ተለይታ፣ የኔ ቤት ብቻ፣ በ 8.9 ሬክተር ስኬል የምትናጥ ሆነች፡፡ ይህንን ማን ዘገበ? ማንም! የቱ ጋዜጣ አተመ? የቱም!
ይሄ ነጋዴው መንግስታችን! ከዚህ ማንኮራፋት ውስጥ፣ ሃይል አመኝጭቶ ለምን ለሙሉ የአፍሪካ አገራት እየነገደ ትርፍ አያገኝበትም? እኔስ መንግስቴን ትርፍ ካስገኘልኝ፣ አንድ ሚስቴን ብሰጠው ምን ኀጢያት አለው?
…. ይህን ሁሉ ችዬ! በተደጋጋሚ ጊዜ እንቅልፍ በማጣት ሳቢያ የስራ ገበታዬ ላይ ስተኛ በመገኘቴ ከስራ ተባረርኩ፡፡ እኔም እሷን ከቤቴ አባረርኩ፡፡ ማን ተባሮ ማን ይቀራል፡፡
‹‹‹‹‹
ትዳር-2(ወሲብ)
የዚህችኛዋ ችግር እንትን ላይ ነው፡፡( “እንትን” ባህላችን “እንትንን” በስሙ እንዳንጠራ የጣለብን ግዴታ ነው) እናላችሁ እቺ ሁለተኛይቱ እንትን በቃኝ አታውቅም፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀቷ፣ “የገባ ያገለለግላል” የሚለውን ምሳሌ ብቻ ነው መሰለኝ የምታውቀው፣ እናድርግ ነው…. እናድርግ ነው! አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመጓጓቷ የተነሳ፣ በመሀል “ቶሎ ጨርስና እንደገና ሌላ እናድርግ …” ትለኛለች፡፡
በመጀመሪያ ሰሞን፣ አዲስ ጉልበት እንደመሆኑ መጠን የሶስት አባወራ ሚና ወስጄ የበኩሌን ማድረግ ቀጠልኩ፡፡ እሷ ግን የአርባ ሁለት ሴት አምሮት ነበር ያለባት፡፡ ሰለቸኝ፡፡ ታከተኝ፡፡ በገዛ “መሳሪያዬ” የጥቃት ሰለባ ሆንኩ፡፡ ጠዋት ከቁርስ በፊት እሱኑ ነው፡፡ ረፋድም፣ ከሰዓትም እሱው፡፡ እሷን ካገባሁ በኋላ በዓለም ላይ በጣም ጠንቅቄ የማውቀው አንድ ቦታ ቢኖር አልጋዬ ነው፡፡ የብርድ ልብሴ ቅንጣት ብኛኝ እንኳን ብትጎድል ሰከንድ ሳትቆይ አውቃለሁ፡፡ ዓይኗ ወደሌላ እንዳያይ ስል ግን፣ አልጋ መስሪያ ቤቴ ሆነ፡፡ ሳትሰማኝ አንድ የአዝማሪ ግጥም ለራሴ በሚስማማ መልኩ ቀይሬ ማዜም ጀመርኩ፤
“ መቀመጥሽ ነው ወይ ትዳሬ ብለሽ
ልቤን እንደ ኬብል ከጭንሽ ቀብረሽ” ….. አክዬም፤
የስልሳ ሴት አምሮት ከጭንሽ ከተሽ
ምን ትጠቀሚያለሽ፣ አንድ የዋህ ገድለሽ?! …እል ጀመር(ለራሴ)….እሷ ግን ሁሌም፣
“ የቤታችን ዶሮ ይሰፍራል በጊዜ፣
ሌሊቱ ገና ነው ድገም አንድ ጊዜ” ማለቷን ቀጠለች፡፡
….. ሱሬዬን የምታጠቅባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ሆኑ፡፡ አሁን ባደርገው አሁን ላወልቀው ለምን እታጠቀዋለሁ? አንዴ እንደውም ከቤት ስወጣ ማድረጉን ሁሉ ረስቼ፣እራቁቴን ወጣሁ፡፡ ሁለት ሴቶች ቆመው፤
“ አንቺ… ይሄ ልጅ አበደ እንዴ? ውይይ… መቼ ነው የጀመረው?…” ሲባባሉ ሰምቻቼው፣ እራሴን ባየው እራቁቴን ኖሪያለሁ፡፡ አቤት ወደ ቤቴ የሮጥኩት እሩጫ፡፡ ስሮጥ ያዩ የሰፈር ህፃናት ደግሞ ከኋላ ጨመሩልኝ፤
አበደ! አበደ! አበደ…እብዱ….እብዱ…” እያሉ ሩጫዬን አጀቡት፡፡
…. ወደቤት ገብቼ፣ ለዚህ ህዝብ አለማበዴን ቶሎ ልብሴን ለብሼ ላሳየው ስጣደፍ፤
“ ቆይ! ቆይ! ከመልበስህ በፊት…” ብላ አስቆመችኝ፤ “ ከመልበስህ በፊት አንዴ እናድርግ!”
:
:
እናማ ፈትቻት ተፈታሁ!
››››
ትዳር 3( አምባገነንነት)
“እስቲ ቢያንስ፣ እቺ የሶስተኛ ትዳሬን የተባረከች አድርግልኝ” ስል ፀሎቴን ገልብጦ ወደሚሰማው አምላኬ ፀለይኩ፡፡ ሰማኝና ትንሽ ሰላም ብዙ ጦርነት ያለበት ትዳር ሰጠኝ፡፡ ምን! “አባወራ ሰጠኝ” ልበል እንጂ! በአንድ ቤት ሁለት አባወራ እንዲኖር የአባወራነት ደንብ ያዛል? መልካም ሚስት ከእግዚኣብሔር ናት ያሉኝ ሰዎች፣ ሚስቶቼ ከሴይጣን እንደሆኑ ሊነግሩኝ ነውን?
… እቺኛዋ ደግሞ አባወራ ካልሆንኩ ብላ ቁጭ! ከጓደኞቼ ጋር አንድ ሁለት እያልን ሳለ ትደውልና፤
“ ትመጣለህ ታድራለህ?!…. ነው እዛ መጠጥ ቤትህ ድረስ መጥቼ አንጠልጥዬ ልውሰድህ?!” …ከሁሉ በላይ አንጠልጥዬ የሚለው ቃሏ ይገርመኛል፡፡ ተናንቀናል እኮ ጓዶች! ምንአባቱዋንስና ምን ታመጣለች ብዬ፤ ከምሽት አራት ሰዓት ላይ ቤቴ ልገባ የነበርኩት ሰውዬ፣ ሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ ዘና ብዬ እመጣለሁ፡፡ታብዳለች! ትጮሃለች! ታጓራለች! ይህ ሁሉ ሲደክማት “ ማንም እንዳንተ የናቀኝ የለም! ትዳሬን ብዬ ተሰብስቤ ስለ ተቀመጥኩ ነው…..!” እያለች ማልቀስ ትጀምራለች፡፡
“አባወራ መሆን የምትፈልግ እማወራ ዱላዋ እምባ ነው” እያልኩ እስቃለሁ በልቤ! ሁላችንም እቺን ምድር እያለቀስን የተቀላቀልን ቢሆንም፤ ሴት ግን ሁሌም ልቧ እየሳቀ፣ ከዓይኗ እንባ የማውረድ አስማትን ታድላለች! -ነቄ ነን!
››››
እያደር አበዛችው! እሷ መንግስቱ ኀይለማርያም ሆና፣ እኔን “ውብአንቺ”ን ልታደርገኝ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ጦርነትም ሆነ! ትዳራችን ኢሕአፓ እና ደርግ በአንድ ቤት ውስጥ ከማኖር መሳ ሆነ! በአንዱ ቀን በሆነ ጉዳይ ላይ ስትጮህ ቆየችና፤ “ምንም እንዳልሰራ ዝም ይላል እንዴ ደግሞ!” ብላ እጇ ላይ ያለውን እቃ ስትወረውር፣ ከኋላዬ ያለው ግድግዳ ላይ አረፈ፡፡ አላመንኩም!
“እኔን ነው? ሊሆን አይችልም! እዚህ ድረስ ተናንቀን?…” ብዬ አስቤ ሳልጨርስ፤ እጇ ላይ ካለው ብርጭቆ ውሃ ከለበሰችብኝ፡፡ እቺን ናትናናና! በፍጥነት ተነስቼ የተሰቀለውን የአያቴን ጋሻ አወረድኩ፡፡ ጋሻውን ወድሬ ለሃያ ደቂቃ ያህል ፎከርኩ! ሸለልኩ! አቅራራሁ!….
እትትት አታታታ….
እኔ ወንዱ! ዘራፍ! ዘራፍ!
በላት በካልቾ፣ በላት በጡጫ
በላት በጥፊ፣ በላት በእርግጫ!
በትዳር ሰበብ የለም ልግጫ!!
እትትት….
ዘራፍ ወንዱ! ዘራፍ!…. እያልኩ በመዓት መንቀጥቀጥ፣ በመዓት እትትት… በመዓት ዘራፍ! የታጀበ ትንሽ ግጥም( ጊዜው ነው እንግዲህ) እየተንጎራደድኩ ካሰማሁ በኋላ፣ በያዝኩት ዱላ አንቆራጥጣት ጀመር፡፡ “Mr & Mrs smith” የተባለው ፊልም ላይ ያለውን የባልና ሚስቱን ድብድብ ዓይታችኋል አይደል? እኔ ቤቴ ካደረኩት አንፃር፣ ያ ተቃቅፎ የመሳሳም ያህል ነው፡፡
ባታውቅ ነው!!……..አያቴ ኮሪያ ዘምቶ ሲመለስ፣ በኮሪያ ቆይታው የተማረውን የቴኳንዶ ትምህርት ላለመርሳት፤ “አብቻጊ”፣ “ቴሌቻጊ” “ጎሬቻይጊ” … እና ሌሎች ብዙ “ቻይጊ”ዎች ያሉባቸው የካራቴ ምቶች፣ ሰበብ አስባብ እየፈለገ ሚስቱን ሲቀጠቅጥ እንደኖረ ባታውቅ ነው፡፡ በዘራችን ሚስትን መምታት፣ መሚወዱት አምላክ ፊት፣ ለምስጋና ከበሮ የመምታት ያህል “የተቀደሰ ተግባር” መሆኑን ባታውቅ ነው፡፡ ሚስቶቻቸውም እንዴት “አሜን” ብለው ዱላቸውን እንደሚቀበሉ ባታውቅ ነው፡፡
…. ደህና አድርጌ ሳቀምሳት ግን፣ “ዋይይ… ዉይይ…” እያለች ስትጮኽ ቆይታ፣ ሮጣ ከቤት ወጣች፡፡ …ወደ “ሴቶች ጉዳይ ቢሮ” ሄዳ ከሰሰችኝ፡፡ ጊዜው እንዴት ተበላሽቷል እናንተው? ሚስት ተመታሁኝ ብላ የምትከስበት ጊዜ? ስምንተኛውን ሺ ሳናልፈውም አልቀረን ግድ የላችሁም፡፡ … የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሄድኩ ከ ………………………………………………………………………………………………………. በኋላ ተፋታን፡፡
››››
ንሰሃ….
መቼም የኛ ወንድ፣ ትዳር ውስጥ ሲገባ “የቦክስ ሪንግ” ውስጥ የገባ ነው የሚመስለው፡፡ እስከዛሬ በትዳር ውስጥ ሚስቶቻችን ላይ ያሳረፍነው ዱላ፣ ዛሬ እንዲመለስብን ቢወሰን፣ እዳው ከእኛ አልፎ፣ ሰባት ዘሮቻችን ድረስ ያሉት ወንድ ልጆቻችን መትረፋቸውን እንጃ፡፡ አዳሜ፣ ስራ ቦታም ተበሳጭቶ ሲመጣ፣ መንግስትም አማሮት ሲገባ፣ ምሬቱን ሚስቱ ላይ ያራግፋል፡፡ የአደባባይ ጥንቸል ሆኖ ውሎ፣ ቤቱ ሲገባ አንበሳ ይሆናል፡፡ እቺ ጓዳ ውስጥ የተቆለፈባት ወንድነት ምነው አደባባይ አትወጣሳ፡፡ የሚገርመው፣ ዘመናይ ነኝ የሚለውም ወንድ፣ ነቄ ነኝ የሚለውም ወጣት- ሚስቱ ላይ ሲሆን ታይሰን አስተኔ ይሆናል፡፡
አሁን ሚስቶቻችን እንደ መኢሶን፣ “አስታጥቁን አታስጨርሱን” ቢሉስ?…… ኸረ ባስታጠቋቸው እዛ!