Tidarfelagi.com

ሸምበቆ እና ሸንኮሬ

አመት ከማይሞላው ጊዜ በፊት ለመስክ ስራ ወጣ ስል እግረ መንገዴን ‹‹የአባቴን ሀገር እና ዘመዶች ልይ›› ብዬ ከተወለደበት የገጠር መንደር ጎራ ብዬ ነበር።

በቅጡ ያልወጠንኩት የእግረ መንገድ ጉዞዬ ወሬ አባቴ ዘመዶች ዘንድ ከብርሃን ፈጥኖ ደረሰና እኔን ለማስተናገድ ወጥነው ሲንገላቱብኝ ሰነበቱ። በተለይ የሸንኮሬ ከሁሉ ባሰ።
ቤት ያፈራውን ያልበላሁበት፣ የተጠመቀውን ሁሉ ያልጠጣሁበት ቤት አልነበረም።
የሸንኮሬ ግን ባሰ።
መምጣቴን ስትሰማ ያለቻትን አንዲት በግ ያለርህራሄ፣ ያለማንገራገር ሸክ አድርጋ፣ ጠብ እርግፍ ብላ አስተናገደችኝ።
መደቧን ለቅቃ አስተኛችኝ።
‹‹እንደ ሸምበቆ ተመዝዘህ የለም እንዴ! አይ..አይ.. አይ.. ቁመት!›› ብላ ራሴን በፍቅር ስትዳብስ፣ ጉንጮቼን ስትስም፣ አይን አይኔን ስታይ ውላ እና አድራ ተለያየን።

ከሃያ ቀን በፊት ሸንኮሬ በጠና ታማ አዲስ አበባ እንደመጣች እና ሃኪም ቤት እየተመላለሰች መሆኑን ሰማሁ።
አንዱን ቀን የስብሰባ ሰልፍ ሲበላብኝ፣ ሌላውን ቀን እንቅልፍ ሲያባክንብኝ፣ የተረፈውን ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ ሲወስዱብኝ፤ ሳላያት ሳምንት አለፈ።
‹‹ነገ እሄዳለሁ››
‹‹እሁድ አልቀርም››
‹‹አርብ ከሰአት ከስራም ወጥቼ ቢሆን ሳላያት አላድርም›› እያልኩ ከራሴ ጋር ስነጋገር፣ መደወል እየፈለግኩ፤ ‹‹እንደዛ ያስተናገደችኝን ሴትማ በስልክ ተሸለሽ ወይ ብዬ አላልፋትም›› እያልኩ ራሴን ስሞግት ሌላ ሳምንት አለፈ።
በሚቀጥለው ሰኞ ማታ እራት የበላንበትን እቃ ሳጥብ ስልኬ ጮኸ። አጎቴ ጋሽ አባተ ነው።
እጄን አደራረቅኩ እና አነሳሁት።
‹‹አቤት ጋሽ ከቤ?›› አልኩ።
ሰላምታም ሳይሰጠኝ ፣ ‹‹አንት የማትረባ! ያቺ መከረኛ ሸንኮሬ እኮ ሳትጠይቃት አረፈች››
አንዲት በጓን ሳትሰስት ያረደችልኝ ስጋዬ፣
አንዲት በጓን ሳታንገራግር ያበላችኝ ሸንኮሬ፣
ያላትን ያልነፈገችኝ ዘመዴ ሳልጠይቃት ሞተች።
የረከሰ ጊዜዬን የሰሰትኩባት፣
የተረፈ ሰአቴን የነፈግኳት ደጓ ሴት፤ ‹‹እግዜር ይማርሽ›› እንኳን ሳልላት አረፈች።
ከቀብሯ ስመለስ ከሳግ በተረፈ ድምፄ ማለት የቻልኩት ይሄን ብቻ ነበር።
‹‹እቴ ሸንኮሬ፤ ሸምበቆ ምን ቢመዘዝ ምሶሶ አይሆንምና ይቅር በይኝ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *