Tidarfelagi.com

‹‹በሃገር ነው››

ጎረቤቴ ካለው ቤተክርስትያን የሚመጣው የቅዳሴ ዜማ እና የወፎች ዝማሬ አነቃኝ።

እንዴት ውብ አነቃቅ ነው! በሰላም አሳድሮ ይሄንን አዲስ ቀን ስላሳየኝ ምንኛ የታደልኩ ነኝ? ዛሬን ከማያዩት ስላልደባለቀኝ ምንኛ አድለኛ ነኝ?

አልጋዬ ውስጥ እንዳለሁ ተንጠራራሁ።

ሌላ ጊዜ ቅዳሜ እንደማደርገው አልጋ ውስጥ ስንደባለል ሳላረፍድ ተነሳሁ።

ተጣጥቤ ከጨረስኩ በኋላ፣ በግማሽ ስንፍና፣ በግማሽ ጓደኞቼን መናፈቅ ምክንያት የቅዳሜ ቁርሴን ከወዳጆቼ ጋር ውጪ ለመብላት ወሰንኩና፤ የእረፍት ቀን እና ዘና የሚያደርገኝን አለባበስ ለብሼ፣ ምቹ ጫማዬን ተጫምቼ፣ በሬን ከፍቼ ወጣሁ። በረንዳ ላይ የተሰደሩት አትክልቶቼን ሳያቸው ግ ውሃ ማጠጣት አለብኝ ብዬ አሰብኩና ወደ ቤት ገብቼ ባልዲ ውሃ ሞልቼ አመጣሁና ማጠጣት ጀመርኩ።

ጤናዳሜ አብባለች፣ ፅጌረዳዬ ፈክታለች፣ የሃረግ ተክሌ ግድግዳዬን ታክካ መዘርጋት ጀምራለች።

ለአትክልቶቼ ቁርስ ሰጥቼ ሳልጨርስ ጎረቤቴ ቲጂ ከማር የተሰራ የሚመስለውን የ11 ወር ልጇን አቅፋ አጠገቤ ቆመች።

‹‹ሂዊዬ ደህና አደርሽ?›› አለችኝ
‹‹እግዚአብሄር ይመስገን ቲጂዬ እንዴት አደራችሁ ?››
‹‹ሰላም ነን ይመስገን››

ሰላምታችን ሲያልቅ ፣ ልጇን ተቀብዬ ‹‹በቃ ዛሬ ቁርስ አልበላም…አንተን ነው የምበላው…›› እያልኩ ያገኘሁት ቦታ ሁሉ ሳምኩት።

ሲያየኝ ይፈነድቃል። ለሃጩ ይዝረበረባል። ከዚያ ደግሞ ሳቅፈው ይቦርቃል።
ለእናቱ መልሼው ወደ ቤት ለመግባት መንገድ ስጀምር በራሱ ቻውም ሰላምም ለማለት ያልሰለጠኑ እጆቹን ያወናጭፋል። እንደገና እመለሳለሁ። እንደገና አቅፈዋለሁ። እንደገና እጆቹን ያወናጭፋል።
በራሱ መንገድ ‹‹ፒስ ነው?›› እያለኝ ነው።

እንዲህ ካጃጃለኝ በኋላ፣ በሉ ደህና ዋሉ ብዬ፣ በሬን ቆልፌ ደረጃ መውረድ ስጀምር ቤት የሚለቁ ሰዎች ጋር ተገጣጠምኩ።
ከእኛ ህንፃ ወጥቼ ሳይ ደግሞ ወደ ሌላ ህንጻ የሚገቡ ሰዎች ከመኪና እቃ ሲያወርዱ አየሁ።

ጥበቃዎች የሚቀመጡበት በር ላይ ስደርስ የሁሌው ተእይነት አገኘኝ።

ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያሉት ትልቅ ሰውዬ ሰራተኛ (በጣም ትልቅ ቂጥ አላት) ከአንዱ ጥበቃ ጋር ትጀናጀናለች። ‹‹እንዴት ነሽ ታዲያ…ሰላም ነሽ?›› እያላት ነው። ሁሌ የሚያደርጉት ነው።

በእጇ ሁለት ዳቦ በፌስታል ይዛለች። ይሄኔ ከአርባ ደቂቃ በፊት ለቁርስ ገዝተሸ ነይ ተብላ ተልካ ነው። ጋሼ እየራባቸው ይሆናል።

‹‹ሰላም ነው?››> አልኩና ፈገግ ብዬ አይቼያቸው አለፍኩ።

ከፍ ስል ቲ ኤም ቪዲዮ ቤት ሙዚቃውን በጠዋት እያስጮኸ የሰፈሬን ወጣቶች ለፊልም አሰልፏል። አዲስ ቤት ነው። ከባጃጅና ከጋሪ ድምፅ በስተቀር ያልለመደውን ሰፈር እየረበሸው፣ ግን ደግሞ ብጉራቸውን ሲያፈርጡና ጠጉራቸውን ሲገምዱ ለሚውሉ ጎረምሶች አዳዲስ እና ተከታታይ ፊልም ያቀርባል።

ይሄው በሌሊት ተሰጥተዋል።

በሩ ላይ የአገልግሎቱ ዝርዝርና ዋጋው ተለጥፏል
Serious Movie – 1 br
HD movie – 5 br
Serious Movie translation Amaric – 2 br
Erotic Movie- 5 br
ይላል። የጎረምሶቹን አቋቋም ሳይ ለፍተው ወይ ሰርቀው ያመጧትን አምስት አምስት ብራቸውን ጨምድደው ይዘው ለኤሮቲክ ሙቪ የተሰለፉ ይመስላሉ። ‹‹እሙዬ ኤሮቲክ ፊልም ልጋብዝሽ›› በማለት የሚያሽኮረምሟቸው ሴቶች ደግሞ የካርዳሺያንስን ውሎ ለማወቅ ጓጉተው የተሰጡ ናቸው።

ሳፈጥባቸው አስተውለው ኖረዋል ለካ መልሰው ሲያፈጡብኝ ‹‹ልጆች! ሰላም ነው› ›› አልኩኝ።
‹‹ሰላም ነው›› አሉኝ።

እንደገና ፈገግ ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ።

ከፍ ስል ጠላ ቤቶቹ ጋር ሴቶች እየተሳሳቁ ትላንት ተጎዝጉዞ የነበረውን ደረቅ ቄጠማ ተባብረው ይጠርጋሉ።
አንድ እናት ልጇን ጭኖቿ መሃል ወትፋ ሹሩባዋን ትፈታላታለች።
ፈቀቅ ብሎ አንድ ጎረምሳ ‹‹ሲስ መጋረጃ›› በሚል ማስታወቂያ ያበደ ባጃጁን ያፀዳል።
የቁርስ ዳቦ ተልከው ገዝተው የሚመለሱ ልጆች እየተጎሻሸሙ ይራመዳሉ።
የክት ልብስ ለብሰው፣ ሹል ጫማ ተጫምተው ኮብልስቶን መንገድ ላይ ለመራመድ የሚሰቃዩ ሴቶች በትግል ይሄዳሉ።
መሮና መዶሻ ይዘው የእለት ስራ የሚጠባበቁ ጎልማሶች ተሰብሰበው ያወጋሉ።
አንድ አዛውነት ሊሸከማቸው ከከበደው ያረጀ የእንጨት ወንበር ተቀምጠው የጠዋት ፀሃይን ይሞቃሉ።

ባልትና ቤቱ ፊት ለፊት ሁለት ሴቶች እያወሩ በርበሬ ያሰጣሉ።
አዲስ የተከፈተው ማሳጅ ቤትን የመስታወት በር የሚወለውሉ ሁሉት ወጣት ሴቶች ያሽካካሉ።

ነግቶ የተገናኙ ሰዎች ‹‹ደህና አደርሽ…ደህና አደርክ..›› ይባባላሉ።

ዋናው አስፋልት ላይ ስወጣ ባጃጅ፣ የቤት መኪና፣ ሲኖትራክ እና ብዙ አይነት መኪና በየአቅጣጫው ይከንፋል።
እግረኛው የእለት ጉዳዩን ለመጨረስ፣ የእለት እንጀራውን ለማግኘት ወዲህ ወዲህ ይራወጣል።
ንግድ ቤቶች ተከፍተዋል።

ሕይወት ጀምሯል።
ኑሮ ቀጥሏል።

ታክሲ ውስጥ ገብቼ ጓደኞቼን ወደቀጠርኩበት ስፍራ ስሄድ ከነቃሁ ጀምሮ ያየሁት ሁሉ የሆነው፣ ነገም የማየው ሁሉ የሚሆነው በሃገር መሆኑን አሰብኩ።

ለአምላክ ምስጋና ሲቂርብ የምንሰማው ሃገር ሰላም ስትሆን ነው።
ወፎች የሚዘምሩት ሃገር ሰላም ብትሆን ነው።
በሰላም አድረን ተመስገን የምንለው ምድራችን ሰላም ውላ ብታድር ነው።

ጥሩ ልብስ ለብሰን የምንታየው፣ አጊጠን የምንወጣው፣ ከጎረቤት የምናወጋው፣ ከህጻናት ጋር የምንቦርቀው፣ በጉርብትና የምንረዳዳው፣ በፍቅረኞች ፍቅር ፈገግ የምንለው፣ በጎረምሶች ባህርይ የምንገረመው፣ ጠዋት ተነስተን ለእንጀራ የምንሮጠው፣ ከወዳጅ ዘመድ የምንገናኘው፣ ያገኘነውን አብረን የምንበላው ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ነው።

ጥላሁን ገሠሠ እንዳለው፤

‹ሳቅ ፈገግታ ደስታ ሁሌ የምናየው-
ሃገር በነፃነት ኮርታ ስትኖር ነው- ሁሉም የሚያምረው
ጥሩ ልብስ ለብሰን አምሮብን ተውበን- የምንታየው
ሰዎች እንረዳው- ቢገባን ትርጉሙ- ሁሉም በሃገር ነው››

…የአሁን አሁን ምኞቴ አንድ ብቻ ነው፤ እሱም የሰላምን ዋጋ ለማወቅ ከባድ ዋጋ የማንከፍል ህዝብ ሆነን ማየት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *