Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 12)

እንደዛ በብስጭት ተክኘ ወደአልጋው ስንደረደር ወንዴ ከመገረሙ በስተቀር ትንሽ እንኳን አልደነገጠም …እንደውም …ኮራ ብሎ ‹‹ልእልት እባክሽ ልተኛበት ብርድ ልብሱን አቀብይኝ ›› አለኝ (ይታይህ …ሊ የለ ምን የለ ….ልእልት….ፍቅር ሲራቆት መጀመሪያ አውልቆ የሚጥለው በፍቅር የተቆላመጠ የስምህን ካባ ነው …ልእልት አለኝ እንደጎረቤት ….) … ፊቱ ላይ የነበረው መሰላቸው …ቅዝቃዜ መቸም አይረሳኝም …..እንደው ለራሴ የአገልግሎት ዘመኔ ያበቃ የሆነ እቃ የሆንኩ መሰለኝ …. እቃ!
‹‹ምንድነው የሆንከው … ምንድነው እንዲህ የሚያመናጭቅህ በስርአት አታናግረኝም ›› ብየ በእልህ እየተንቀጠቀጥኩ ፊቱ ቆምኩ !እኔማ ያ ግርማ መጎሴ አለ ብየ ….ያ እንኳን ተቆጥቸ በሰላሙም ቀን አይኔ ሲያርፍበት የሚሽቆተቆጠው ወንዴ አለ ብየ ነበር …. ታምነኛለህ አብርሽ … ልክ ዝንብ እንደሚያባርር እጁን አንዴ አወናጭፎ ….ምን ልበልህ ንቄቱ ጥላቻው ፊቱ ላይ በቃ …
ልእልት እንባ ተናንቋት በእልህ ተንቀጠቀጠች …..
‹‹ ንዝንዝሽ ሰለቸኝ ›› አለኝ! ….. ንግግሩ አይደለም ያሳዘነኝ አነጋገሩ ድምፁ ፊቱ ላይ የነበረው ነገር …እሱ ነው የሆነ ነገር ልቤ ላይ እንዲጫነኝ ትንፋሽ እጥር እንዲለኝ ያደረገኝ …..ከአልጋው ላይ ተነስቶ በቆምኩበት ገፋ አድርጎኝ አለፈና የጣልኩትን ብርድ ልብስ እየጎተተ ወደአልጋው ተመለሰና ጥቅልል ብሎ ተኛ ….እንደዛ የተበሳጨሁት እንደዛ ተንደርድሬ የመጣሁት ልጅ ያ ሁሉ አነርነት ድራሹ ጠፍቶ እንደሃውልት ተገትሬ በብርድ ልብስ ተጀቡኖ ጀርባውን የሰጠኝን ወንዴን ማየት ብቻ ሆነ አቅሜ ! በቃ !! እንባየ ተዘረገፈ ….
ወንዴ ምናለ ቢጮህብኝ ….ምናለ ቢሰድበኝ ምናለ ቢቸካቸከኝ …. አፈርኩ አብርሽ … ሴትን ልጅ አታሳፍር በህይዎት ዘመንህ ሴትን ልጅ አታሳፍር …. እስካሁን በህይዎቴ የዘገነኝ ነገር ያ የወንዴ ጀርባ ነው … የሴት ልጅ እፍረት ከይቅርታም በኋላ ቢሆን ከአእምሮዋ አይወጣም … መናቅን ሴት የመሳቢያ መንገድ አድርገው የሚያስቡ ወንዶች አሉ የለየለት ድድብና ነው ! የተናቀች ሴት ምናልባት ወንድን ከተከተለች ክብር ፍለጋ እንጅ ፍቅር ፍለጋ እንደማይሆን በራሴ አይቸዋለሁ ! ወንድ ልጅ ኮራ ሲል ነው እንጅ እየተባለ ስንቱ ወንድ ስንቷን ቅስም በሃፍረት ሰብሮ ጥሎታል !! ለዚሁም ይፎከራል ! አንዳንዴ ጀግንነታችን በሽተኛ ነው !!
ልእለት በትካዜ ግድግዳውን እያየች ከሩቅ የሚሰማ በሚመስል ድምፅ ቀጠለች….
‹‹…እግሬን እየጎተትኩ ወደሳሎን ሄድኩና ሶፋ ላይ ተኛሁ …. እንቅልፍ ግን እንዲች ብሎ በአይኔ አልዞረም … ሌሊት የሆነ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ወንዴ ይቅርታ ሊጠይቀኝ የመጣ እየመሰለኝ ‹‹እንዳትነካኝ ›› ብየ መጮህ ምናምን እያሰብኩ(ያው መቸም ባንዴ አልታረቀውም አይነት የመለመን ፍላጎት ….ተስፋ አይሞትም አይደል) ተዘጋጅቸ ስጠብቀው ወንዴ ወደሳሎን ዝር ሳይል ነጋ !
በህፃንነቴ አባቴ የፈለገ ቢሆን ለምሳ እቤት ሳይመጣ አይቀርም ነበር …ታዲያ ሁልጊዜ በር ላይ ቁሜ ነበር የምጠብቀው ….አንድ ቀን ግን ምን እንደሆነ እንጃ ቀረ… የሚገርምህ ወንዴ ሳሎን ሳይመጣ ሲነጋ ከስንት አመት በኋላ ያች ቅፅበት ናት ትዝ ያለችኝ ….. በሞተ በስንት አመቱ ደግሞ አባቴ ናፈቀኝ !! ከምር አብርሽ አባቴ ከሞተ ስንት አመቱ እስቲ ….›› ብላ አይኗን ወደላይ ወደጣራው ልካ አባቷ የሞተበትን አመት አሰላችና …‹‹አስራ ምናምን አመት›› አለች ! አፏንና አፍንጫዋን በመዳፏ አፍና የሚታገላት እነባ እንዳይወርድ ስትታገል ቆየችና …ቀጠለች …..
‹‹ ……ወንዴ ተነሳ ….ታምነኛለህ አብርሽ …..የወንዴ ፊት እሩቅ አገር ሂዶ እንደተመለሰ ሰው ናፈቀኝ …የሆነ ፊቱ ወደሌላ ሰው ፊት የተቀየረ መሰለኝ ….ሌላ ሰው መሰለኝ ወንዴ ! አንዴ ወደመታጠቢያ ቤት አንዴ ወደመኝታ ቤት ሲገባና ሲወጣ ሶፋ ላይ ተኝቸ አየዋለሁ …ልክ ብቻውን እንደሚኖር ሰው እቤት ውስጥ ሌላ ሰው እንደሌለ አንድ ጊዜ እንኳን ወደኔ አልዞረም … እንደውም ለባብሶ ሊወጣ ወደሳሎኑ በር ሄደ ….አላስቻለኝም ….ተስፈንጥሬ ከሶፋው ላይ ተነሳሁና ፊቱ መንገዱን ዘግቸ ቁሜ ክንድና ክንዱን ያዝኩት ….. በዚች ምድር ላይ ያሉትን ስድቦች ሁሉ ላራግፍበት ነበር አካሄዴ ….ግን ከአፌ የወጣው ቃል ‹‹ይቅርታ ወንዴ›› የሚል ነበር !
እስከዚች ደይቃ ያ ይቅርታ ለምን እንደሆነ አይገባኝም ! ቁንጅና በለው ሃብት በለው እውቀት በለው ብቻ የትኛውም ትእቢት ያሳደረብን ጉዳይ ስብር የሚልበት የሆነች ቅፅበት አለች ያች ቅፅበት እንደዛ ነበረች ለኔ ….ለአመታት ወንድን ያንበረክካል የምለው ቁንጅናየ ….ማንም አልፎኝ አይሄድም ማንም ይለምነኛል ይለማመጠኛል እንጅ ማንንም አልለማመጥም የሚለው ማንነቴ ስብር አለ !! ደግሞ ለካ ትእቢት ጥሩ ነበር ….ስሙ ትእቢት ይሁን አይሁን እኔጃ እንጅ የሆነ እንደጀርባ አጥንት ማንነታችንን ቀጥ አድርጎ የሚያቆም ስሜት አለ እሱ ነው ስብር ያለው ተልፈሰፈስኩ ….ወንዴን እግሩ ስር ወድቄ መለመን ሁሉ አሰኝቶኝ ነበር ….ምነው ይሄን ሰይጣን ሃሳብ ባልተናገርኩ ብየ ተፀፀትኩ !
ወንዴ ገፋ አድርጎኝ ትቶኝ ወጣ …. ብቻየን ቁጭ ብየ ማልቀስ ጀመርኩ ….እስኪወጣልኝ ተነፋርቄ …..ቀለል አለኝ …..!! እስቲ አሁን ለማን ይነገራል ….በምን ተጣላን ይባላል …. ድንገት አንድ ሰው ታወሰኝ የወንዴ አባት … !! በቃ የሆነውን ሁሉ ለሳቸው መንገር መቸስ የልጃቸው ሚስት ነኝ ….ተቆጥተውም ገስፀውም ያስታርቁናል ብየ አሰብኩ ….እስቲ ይታይህ አብርሽ በሰላም የተቀመጠ ልጅ ያላሉኝን ተናግሬ እንዲህ ሰዶ ማሳደድ … አንዳንዴ ምቾታችን ጠንካራ እየመሰለን ፍቅራችን ወዳጅነታችን ከላይ ውበቱን አይተን መንሰፍሰፉን አይተን ጠንካራ ሸክም ስንጭንበት እንክትክቱ ይወጣል ለካ ….የወንዴ ነገር እንደዛ ሆነ ! ለባብሸ ወደወንዴ አባት ለመሄድ ተነሳሁ ….እስከዚች ቅፅበት በምን እንደምሄድ እንኳን አላሰብኩም ነበር ! ምቾት እንዴት ነው የሚያደነዝዘው …. ወንዴ የለም መኪና የለም …ኩንትራት ታክሲ ለመያዝ ወስኘ ብር መፈለግ ጀመርኩ…. በቤቱ ውስጥ የብር ዘር የለም !! አምስት ሳንቲም የለም ! አሁን ይሄ ይታመናል ?››
ልእልት አይኗ እንባ እንደኳተረ ፈገግ አለች ….ፈገግታዋ ልብ ስንጥቅ ያደርጋል ….በሃዘን በዳመነ ፊቷ ውብ ፈገግታዋ ድንገት ፍንትው ሲል በደመና መሃል የወጣች ፀሃይ ትመስላለች … ምን እንዳስፈገጋት እንጃ !
‹‹ቁም ሳጥኑን ከፍቸ የወንዴን ሱሪዎች መፈተሸ ጀመርኩ …. ›› አለችና አንገቷን ወደመሬት አቀረቀረች …. ብር የለም !! ወንዴ ምናልባት ቁጣው በርዶለት ከሆነ ብየ ደወልኩለት ……ስልኩን ዘጋብኝ ! ልብሴን ቀያይሬ አርፌ ተቀመጥኩ !!
በትዝታ ጭልጥ ብየ …ወንዴ ድንገት ውጭ ሁኖ የሆነ ቦታ ለመሄድ አስቤ ከደወልኩለት ‹‹ወንዴ ቀስ ብለህ ንዳ ብዙ አያስቸኩልም ›› ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር ነበር …ስጠራው እንደእብድ እየበረረ እንደሚደርስ አውቅ ነበር …. ብቅርን ተከትለው የሚመጡ ነገሮች ሁሉ እንደጥላ ናቸው ….የፍቅር ፀሃይ ሲጠፋ ሁሉም ነገር ከስርህ ይጠፋል…መከባበር ….መደናነቅ …ለስሜትህ መጠንቀቅ ….ሁሉም ነገር ከስርህ ይጠፋል !! የታደሉ እንደገና የፍቅር ፀሃይ ወጥቶላቸው ጥላቸውም ከነግርማ ሞገሱ ይመለስላቸዋል ….ካልታደልክ ጥላህ እንደናፈቀህ ጥላ ቢስ እንደሆንክ ይችን ምድር ተሰናብተህ ወደመቃብርህ ትወርዳለህ!! ጥላ ቢስ ሆንኩ አብርሽ !!
***** ***** ******
እህቴ የልእልትን ታሪክ ስነግራት እኔም ራሴ ያላሰብኩትን ጥያቄ ወረወረች (መቸም ነገረኛ አይደለች)
‹‹እኔ የምልህ ወንድም አለም (ነገር ስትፈልግ ወንድማለም ነው የምትለኝ) ልእልት ይሄን ሁሉ ታሪክ ዝርግፍ አድርጋ የምትነግርህ አንተ ንስሃ አባት ነህ ወይስ ምን የሚያስወራ ነገር አስነካሃት …››
‹‹አይይይ …››ስል
‹‹ቆይ ሌላም ጥያቄ አለኝ …ልእልት በዚህ ሁሉ ጊዜ እንዴት ሳታረግዝ ቆየች ›› ልነግሽ አይደል ብየ ቀጠልኩ ልእልት የነገረችኝን እያስታወስኩ ….መቸስ ከነገረችኝ ውጭ ለምን እንዴት እንዳልል የሸበበኝ ነገር አለ …..
ልእልት የዛን ቀን ውሎዋን እንዲህ ስትል ቀጠለች አወራሯ ከንፈሮቿ ከምንም በላይ ደግሞ የምትናገረው ነገር ፍፁም እውነት መሆኑን የሚመሰክሩት ንፁህ አይኖቿና ገራገር አነጋገሯ ሙሉ ለሙሉ ቃል በቃል ነጥብ በነጥብ ትረካዋን በጉጉት እንድከታተለው አድርጎኛል …. ምንም ታውራ ደግሞ ልእልት ናት …..በሃዘኗም በደስታዋም እኩል ልቤን የሚያሞቅ አንዳች ነገር ከመላ ሰውነቷ ላይ የሚነሳ ልጅ …..ልእልትን ወድጃታለሁ በዚያች ቅፅበት ከሷ ውጭ ማንንም አልፈልግም ….. የልእልት ድምፅ በውስጤ የሆነ ተአምር የሚፈጥር ይመስለኛል ….አንዳንዴ ደግሞ ታሪኳ መልኳንም ልእልትነቷንም ያስረሳኝና ጆሮ ብቻ ሁኘ ፊቴ የተቀመጠች ሴት እውነት ታሪክ ሳይሆን በሬዲዮ የሚተላለፍ ትረካ የምሰማ እስኪመስለኝ እመሰጣለሁ
‹‹ ወንዴ ጋር ተጣልተን ያደርን ቀን ….ከጧት ስነፋረቅ ብቻየን ሳለቅስ ዋልኩ ጠብታ እንባ እንኳን ውስጤ አልቀረም ….ማልቀስ እንዴት ፈውስ መሰለህ ….እንደውም እኛ ሴቶች ሲከፋን የምናለቅሰውና ከለቅሷችን በኋላ ለመወሰንም የሆነ ነገር ለማድረግም ቀለል የሚለን ….ከማልቀሳችን በፊት እንባችን ባህር ላይ ሃሳባችን እዋለለ ስለሚያስቸግረን ሳይሆን አይቀርም !!
አባባሏ አስፈገገኝ ሙሉ ቀን …
‹‹ከምር አብርሽ …ልክ አልቅሸ ሲወጣልኝ ወዲያው ማሰብ ጀመርኩ ያውም ጥርት ያለ ሃሳብ ….አሰብኩ በቃ ….በዚች ምድር ማንም የለኝም አልኩ …ቁጭ ብየ መነፋረቅ ጥቅም የለውም አልኩ …. እራሴን ደግሞ መውቀስ የለብኝም ምን አጠፋሁ …ዞሮ ዞሮ ይሄ ቀን በእኔ ንግግር ሰበብ ቀድሞ ተገለጠ እንጅ ዘግይቶም ቢሆን መሰለቻቸቱ አይቀር እንኳንም ዛሬ ላይ ቀድሞ መጣ …. እንደውም የእኔና የወንዴ ፍቅር ትዳር የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነበር እንኳን ዛፉ ሳያድግና ከዛ ርቀት ወድቄ ሳልፈጠፈጥ ዛሬ ላይ ከእንቅልፌ ነቃሁ …..አልኩ ….
ዛሬም ልእልት ነኝ ….ዛሬም ቆንጆ ነኝ …እንደውም ወንዴ ጋር ስንገናኝ ከነበርኩት በላይ አምሮብኛል ቆንጆ ሁኛለሁ (መቸስ ያለኝ ብቸኛ ነገር ቁንጅና ነው ሌላ ምን አለኝ ) ነገ በብስጭት ማዲያት ወርሶኝ …ወይ ወልጀ ልጅ አቅፌ አፍንጫሽን ላሽ ቢለኝ ምን ይውጠኝ ነበር … ብየ አሰብኩ …. ራሴን አፅናናሁት ተንጠፍጥፎ ባዶ ሁኖ የነበረ ውስጤን በራሴ ሞላሁት …. እንደውም ተነስቸ እዛው ሰፈር ወደምሰራበት ፀጉር ቤት ሄድኩ ችግር የለም ልጅቱ ወደማታ መጥታ ብር እንድትወስድ ልነግራት እችላለሁ …. እኔ የወንዴ ፊት ሲጠቁር አለም ሁሉ ፊቱ የጠቆረ መስሎኝ …ወጣ ስል መቶ እርምጃ በማትሞላ ርቀት ሁለት ሶስት ወንድ ‹‹ቆንጆ ›› እንሸኝሽ ሲሉኝ …ፊቴን ኮስተር አድርጌ ‹‹ስላፅናናችሁኝ እግዜር ይስጣችሁ›› እላለሁ በውስጤ ››
ሁለታችንም ከልባችን ሳቅን ! ‹‹እውነቴን ነው አብርሽ ….የወንድ ለከፋ እንደዛች ሰአት ጣፍጦኝ አያውቅም አይዞሽ ልእልታችን ዛሬም ቆንጆ ነሽ ዛሬም እንወድሻለን ዛሬም ተስፋ አለሽ ያሉኝ ነበር የመሰለኝ ….የመጨረሻው ፀያፍ ነገር ሳይቀር አንዳንዴ መፅናኛህ ይሆናል .በፊትማ እንደለከፋ ደሜን የሚያፈላው ነገር አልነበረም ›› አለችኝና ሳቃችን ቀጠለ ….ኦህ ልእልት እንዴት እንደምታሳዝን እንዴት ደስ እንደምትል ! እኔ ራሱ የሴት ወሬ እንደዛን ቀን ጣፍጦኝ አያውቅም !!
‹‹ ከፀጉር ቤት ስወጣ እምር …እንዴት እንዳማርኩ ብታየኝ ›› አለችና አንገቷን መዘዝ አድርጋ ያኔ እንዴት እንዳማረች ለማሳየት ጡቶቿን ወደፊት ገፋ አድርጋ ተውረገረገች
‹‹ከዚህ በላይ አምረሽ ›› አልኩ ! አመለጠኝ …አመለጠኝ አ…..መ……ለ…..ጠ…..ኝ ! ልእልት አይኗን በሃፍረት ጣል አድርጋብኝ ወደግድግዳው ዞር አለችና ልክ እንዳልሰማችኝ ወሬዋን ቀጠለች …ግን ወሬዋን ያቆመችበት ጠፍቷት ትንሽ እንደማሰብ ብላ ነው የቀጠለችው (ወይ ጉድ እስቲ ምን አንቀለቀለኝ )
‹‹ ….ከፀጉር ቤት ስመለስ እቤቴ ገብቸ አሪፍ ምሳ ሰራሁ …ቆንጆ ቡና አፈላሁና ‹‹ልእልትየ የኔ ቆንጆ ብይልኝ ጠጭልኝ›› እያልኩ ራሴን ግብዝ !!…ቤቴን ፅድትድት አድርጌ ሙሉ ሌሊት ቁጭ ብየ አድሬ እንቅልፌ በቁሜ ሊጥለኝ ደርሶ የለ …..ምኝታ ቤቴ ገብቸ ለጥ …የዛን ቀን የወሰደኝ እንቅልፍ መቸም ወስዶኝ አያውቅም …..ስነቃ ስለሚጠብቀኝ ነገር ሳላስብ እንደበፊቱ በፍፁም ሰላም ለጥ …እውነቱን ልንገርህ አይደል በዛው እስከዘላለም ተኝቸ ብቀር ደስታየ ነበር …..ይሄ ሃሳብ አነንድ ገራሚ ሃሳብ ጫረብኝ ..እዚች ምድር ላይ ይሄን ያህል ውጣ ውረድ ለምኑ ነው ….ህይዎት እንደሆነች እስካሁን አቀማጥላኛለች …. አሁን ፊቷን እያጠቆረችብኝ ነው …የባሰውን ሳታመጣው ራሴን ባጠፋስ …ግልግል ነዋ ! ›› አወራሯ ፊቷ ላይ ያለው ፈገግታ የፊቷ እንቅስቃሴ ሁሉ እንዴት ደስ እንደሚል ነበር….. የመጨረሻው ንግግር ግን ዘገነነኝ ልክ እንደባሏ አዘናግታ በሃሳብ ቢለዋ የመውጋት ያህል ነበር የሚያመው ….

በአልጋው ትክክል (ክፍል 13)

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *