Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል 13)

ሙሉ ለሙሉ ድኘ ስራ ከጀመርኩ ሁለት ሳምንት አለፈኝ …. ከመትረፌ የተረዳሁት ሞት የትም እንዳለ ሲሆን … የትም ከሚገኝ ሞት የተረዳሁት….እንዴትም ሊወስደን አልያም እንዴትም ሊስተን እንደሚችል ነው…..እንዴትም መሳት ደግሞ እንዴትም ከመኖር ይልቅ ለሆነ ነገር መኖር እንዳለብን ያነቃናል … ከሞት መትረፍ ልክ ሩጫ ላይ የመጨረሻው ዙር ሲደርስ እንደሚደወለው ደውል የህይዎትን አዙሪት ፈጠን ብልን እንድንዞር የሚያነቃ ነገር አለው …. አለበለዚያ ሞት ይቀድምሃል የሚል ዓይነት !!
ከዛን ቀን ጀምሮ …ሞት የሆነ ግዙፍ ጥንባሳ አሞራ ነገር መስሎ በሰዎች ሁሉ አናት ላይ ሲያንዛብብ ይታየኛል … እኛም እንደጫጩት አቀርቅረን ከድካማችን አፈር ውስጥ ጠብ የሚል ጥሬ ስንለቅም ….የስም ጥሬ …የገንዘብ ጥሬ …. ታዲያ አንድ ቀን ጥንባሳው ተምዘግዝጎ ይወርዳል ……ከእኛ ከጫጩቶቹ አንዱን በተንጨፈረሩ ጥፍሮቹ አንቆ ሽቅብ ሊመጥቅ ….ከተሳካለት ይዞን እብስ …ቀሪዎቹ ጫጩቶች ቀና ብለው ትንሽ ይንጫጩና ወደጥሪያቸው ይመለሳሉ !
ጥንባሳው እንደገና እስኪወርድና አንዱን እስኪያነሳው ! አንዳንዴ ታዲያ ….ከጥንባሳው ጥፍሮች አምልጠን መሬት ላይ ምንደፋደፍበትና እንደገና እንኖር ዘንድ አንድ እድል የምናገኝበት ጊዜ ይኖራል ….እንደኔ!! ይሄው አለሁ ….ቢላ ተመስሎ ከመጣው ጥንብ አሳ ሞት አምልጨ …ሳመልጥ ታዲያ እኖር ዘንድ የተሰጠኝ አንድ እድል ለልእልት መኖር እየመሰለኝ ….ከጥቃቱ በፊት ምን እሰራ ምን አስብ እንደነበር ሁሉ ጠፍቶብኝ እሷን ብቻ እያሰብኩ ግራ ተጋብቻለሁ !
ልእልት ጋር በየቀኑ እንደዋወላለን … ብዙ ጊዜ የምትደውለው እሷ ናት ንግግራችን ‹‹እንዴት ነህና እንዴት ነሽ ›› ይበዛዋል! ለምን እንደሆነ እንጃ ውጭ ልቀጥራት አስብና እፈራለሁ … በጣም እፈራለሁ ….ትናፍቀኛለች በጣም ትናፍቀኛለች ….ግን እፈራታለሁ …. ፍርሃቴ ደግሞ ብስጭትና ጭንቀት የተቀላቀለበት ነው ! ስለ,ሷ ሙሉ ቀን አስባለሁ …. ሳቋ ትዝ እያለኝ አንዳንዴ ካለምክንያት ብቻየን ፈገግ እልና …ዞር ዞር በማለት ….‹‹ ሰው አይቶኝ ይሆን›› ብየ መታየት አለመታየቴን አረጋግጣለሁ …. ! ትካዜዋ ሁሉም ነገሯ ፊቴ ተቀምጣ የማያት ያህል ይታወሰኛል …
ከምንም በላይ ያንን ሁሉ ታሪክ አውርታልኝ ከንፈር ከመምጠጥ ውጭ ምንም ልረዳት አለመቻሌ ግራ ይገባኛል ….የሰው ታሪክ ያውም ለብቻችን ሲነገረን ‹‹ይገርማል›› ብለን የምናልፈው ዜና አይደለም …. ወይም ከህዝብ ጋር በሬዲዮ እንደምንሰማው ‹‹እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ ›› አይነት የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ በጅምላ ደውለን ምክር የምናዋጣበት መድረክ አይደለም ….በተነገረን ልክ የተነገረንን ችግር ከነጋሪው ጋር አብረን እንጋፈጥ ዘንድ ሰበዓዊነቱ ቢቀር ያለን ቅርበት …ያለን ቅርበት ቢቀር ለዛ ሰው በውስጣችን ያደረብን ስሜት ግድ ይለናል ….እህቴ እውነቷን ነው ‹‹ምንም ካላደረክላት ለምን ያንን ሁሉ ታሪኳን ሰማህ›› አለችኝ …..እንጃ!! መጀመሪያ ምንም ታውራ የልእልት ድምፅ የልእልት ከንፈሮች ሲንቀሳቀሱ ማየት ለእኔ ሃሴት ነበር …..ሲቆይ ግን የታሪኳ ጥቀርሻ መልኳን ሸፍኖ ልእልት ከጥቁር ግድግዳ ኋላ የቆመች ልጅ ሆነች ለኔ !
ከእርሷ ምንም ልፈልግ ምን …መጀመሪያ ይህን የጋረዳትን ጥቁር ግድግዳ ማፍረስ ይጠበቅብኛል … የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ ሰምቶ ዝምማ ሳይሰሙ ከመጮህ እኩል ኪሳራ ነው !! ‹‹ወንዴ አንበሳው›› እውነቱን ሳይሰማ ጮኸ…ምን ተረፈው ዘብጥያ !! እኔ እውነቱን ሰምቸ ዝም አልኩ ምን ተረፈኝ …የህሊና ዘብጥያ ! ልዩነቱ የእኔ እስር እኔው እፈታው ዘንድ ቁልፉ በእጀ ነው … የወንዴ ግን እጣ ፋንታው በህግና በዳኛው እጅ ነው ! የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ …ምን ነገር ….እኔጃ!!

ልእልት ግን ‹‹ላንተ ብሶቴን በመናገሬ ቢያንስ ዝም ብለህ ስለሰመሃኝ ሃዘኔ ቀለል ብሎልኛል ደግሞ ባላደረጉት ነገር መወንጀል የጋራ ህመማችን ነው አብርሽ ›› አለችኝ ‹‹እኔም የማይታይ ስለት እድሜ ልኬን ማይድን ጠባሳ ጥሎብኛል ያውም ባስታወስኩት ቁጥር የሚጠዘጥዝ ›› አለችኝ …ምንድነው ‹‹ቀለል ማለት›› ችግሩን አሁንም ተሸክመዋለች አይደል እንዴ ….ልእልት በስስ ነፍሷ ያንን ችግር እንደመርግ ተሸክመዋለች ….
የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ … ቆንጆ ስለሆነች አይደለም ….ስለወደድኳት አይደለም (በነገራችን ላይ እንደወደድኳት ማሰብ አልፈልግም) ግን ልእልት እርዳታ ያስፈልጋታል ….የማንም ሳይሆን የእኔ እርዳታ ያስፈልጋታል ….ሰው ከገንዘብም ከሌላ ነገርም በፊት በትክክል ሊረዳ የሚችለው ሃሳቡን በተረዳለት ሰው ነው …. እኔ ልእልትን በሚገባ ተረድቻታለሁ ! ማንም ሰው ቢሆን ልእልትን ሊረዳት የሚችለው በጥርጣሬ ነው … በተለይም ከእኔና ከዛ ድንዙዝ ባሏ ፀብ በኋላ ማንም ልእልትን የሚረዳት ባሏ በነዛው ቆሻሻ የፈጠራ ታሪክ አጅቦ ነው … !‹‹ ጥጋብ ፍንቅል አድርጓት በትዳሯ ላይ የማገጠች ››በሚል ተቀፅላ !!

የጎረቤቱን ነገርማ ዝም ነው …. ሲጀመርም ከድፍን የብሎኩ ሰው አንድ እንኳን ልእልትን የሚወዳት ሰው አለመኖሩ ምናይነት ስነልቦና ቀውስ ውስጥ መሆናችንን ያየሁበት ነው ! … ከአደጋው በኋላ ከቤተሰቦቸ ቤት ወደቤቴ ከተመለስኩ በኋላ …ድፍን የብሎኩ ሰው ወደማታ ላይ ከላይ እስከታች እቤቴ መጡ ‹‹እንኳን ተረፍክ ›› ሊሉኝ (እስቲ ያችን የመሰለች ልጅ… የሞላው የተረፈው ባሏን ትታ እቤቱ ድረስ የሄደችለት ቤቱ ምን ቢኖረው ነው ብለው ለመሰለልም ይሆናል) ….እና የግዜር ወንበር እንኳን የሌለበት ቤቴ መጥተው በቁማቸው እኔን ‹‹እንኳን አተረፈህ ›› እያሉ እግረ መንገዳቸውን ግን የልእልትን ስም እያነሱ ….እንዳትሸጥ እንዳትለወጥ አድርገው አብጠለጠሏት ‹‹ኧረ ተው እንዲህ አይደለችም ›› አልል ነገር ‹‹የተወራችው እውነት ናታ›› ይሉኛል ብየ እፊቴ ካለሃፂያቷ ልእልትን ሲዘለዝሏት እንደኮሶ እየመረረኝ ዋጥ አድርጌ ዝም አልኩ !!(ያአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም አሉ)
የጎረቤቶቹ አሰላለፍ ልክ የኳስ ጨዋታ አይነት ነገር ይመስል ነበር ….(ለካስ ሃሜትም ጥበብ አለው ) እማማ ቁንጥሬ ናቸው የሃሜቱን ኳስ የሚያከፋፍሉት በጎረቤቶቻቸው አቅም እና ስሜት ልክ እየመጠኑ….‹‹እሱማ ምን ያድርግ ›› አሉ ወደኔ በአገጫቸው እየጠቆሙ ‹‹ እሱማ ምን ያድርግ …. ካለሃሳብ እቤት ተወዝፋ እየበላች ያበጠ ዳሌዋን እያገማሸረች እቤቱ ድረስ ያውም በጨለማ ስትመጣበት ›› ይላሉ …ልክ እቤቴ በምሽት ልእልት ስትገባ ባይናቸው በብረቱ ያዩ ይመስል ….

‹‹ እሷ አታደርግም አትባልም …ያንን ጫቷን አቅፋ ከጅሪወቿ ጋር ስትወጣና ስትወርድ ከጥፍሯ ቁራጭ አትቆጥረንምኮ እየተገላፈጠች ስትገባ ስትወጣ ሰው ሰላም አትል …. ›› ትላለች ሌላኛዋ ተቀብላ …(የዚች ሴትዮ ዳሌ ከልእልት ይገዝፋል…ደግሞ ሰላም አለማለትና ከትዳር ውጭ መማገጥ ምን አገናኘው …ወይስ በግላጭ ጫት አቅፋ ለመግባት ያልፈራች ሴት ከትዳሯ ውጭም ለመሄድ አትፈራም ነው ?? )
‹‹ምን ታድርግ አቀማጥሎ ይዟት …ቢነኳት የምትፈርጥ …የተወለወለ መስተዋትኮ ነው የምትመስለው …ጠገበቻ …›› አለ አንዱ ጥቁር መላጣው የሚያብረቀርቅ ሰውየ (ደግሞ ይሄ ማነው …ቆይ ግን ይሄን ሁሉ ጎረቤት እንዴት እስከዛሬ በመልክ እንኳን አላውቅም) ወንድ እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ገብቶ ሲፈተፍት ይደብራል ….ከምር ! ደግሞ አወራሩ በልእልት መጎምጀቱን ያሳብቅበታል ….‹‹ቢነኳት የምትፈርጥ ነው የምትመስለው›› ሲል ሳያፈርጣት መሄዷ ያበሳጨው አይነት ! …እማማ ቆንጥሬ ነገሩ በረድ ሲል ጋዝ ያርከፈክፉበታል
‹‹ ይች ቢመቻት የሰው ባልም ከመቀማት አትመለስም …ሙች ››አሉ ወደአንዷ ደልደል ያለች ሴት ዙረው ….ይች ሴት እንኳን በመልክ አውቃታለሁ ሁልጊዜ ጧት ወደስራ ስሄድ ስተውጣ አያት ነበር …እማማ ቁንጥሬ ታዲያ ወደሷ እየተመለከቱ እሳቱን ጫሩት ….ቀጠ ‹‹አሁን አንች አዜብየ የምትውይው ስራ ነው …ባልሽ ያ የተረገመ መስሪያ ቤት ቀንሶት እቤት ከዋለ መንፈቅ ሆነው ….ያን የመሰለ ጎምላላ ከረባቱ ብቻ የሚበቃ ……እንግዲህ ጎረቤት ናችሁ …ይች ባለጌ እግርሽን ጠብቃ ወጣ ስትይ ቤትሽ ዘው ብትል ምን ታውቂያለሽ…መቸስ ወንድ አይቶ ልቡ አይጨክንባት …..ለቁም ነገር አታጋድድም እንጅ ዛላውንማ ሰጥቷል ›› አሉ ….
አዜብ የተባለችው አቀርቅራ ዝም አለች ….‹‹ይሆን እንዴ›› የምትል ነው የምትመስለው !ልክ እባብ ለህይዋን ፍሬዋን እንዳስታወሳት እማማ ቁንጥሬም ለአዜብ ባሏ ሌላ ቆንጆ የጎረቤት ሴት ጎን ስራ ፈቶ እየዋለ ተሳስቶ ቢሆንስ ….የሚል ጥርጣሬ አስታወሷት (ይች እማማ ቁንጥሬ የሚባሉ ሴትዮ መቸም …. እንኳን በሁለት ሰዎች መሃል በአገሮች መካከል ጦርነት መቀስቀስ የሚችል ቀንዳም ጋኔል ውስጣቸው ሳይኖር አይቀርም ….ፖለቲከኛ ማለትኮ ይች ሴትዮ ያላቸው ፀባይ ላይ ድግሪ ተጨምሮበት ማለት ነው )
‹‹ ታዲያ … ሲጀመር ይሄን የመሰለ መልአክ ባል ትታ ወንድ የምታሳድድ ….ሴት እንኳን ጎረቤት አግኝታው ….መንገድስ ሂዳ ጎትታ ከማምጣት ትመለሳለች ይድፋት እቴ …. ›› ትቀጥላለች ሌላዋ …..(ሁኔታቸውን ሳየው እንደምሳሌ ያነሱትን እቤት የሚውል ባል በልእልት ሳያሙት አልቀሩም …እንግዲህ ጥግጥጉን ለሚስቲቱ ለመንገር ይሆናል ክፉዎች….)
‹‹ ሚስኪንኮነው ወንዴ …የኔ ጌታ ! እሷ እንዲች ብላ ፀሃይ አይነካት …በገባ ቁጥር ሊ…. ሊ እያለ አንዴ ከሰል አሸክሞ አንዴ እጁ እስኪገነጠል አስቤዛ አንጠልጥሎ …አሁን እስቲ በማማ ሞት እንዲህ አይነት ባል በስለትስ ይገኛል …..ቱ እኛ ሴቶች መቸም ገና ለገና ቆንጆ ነን ብለን ጡራችን ….›› ትላለች ….አንዲት ድሮ ቆንጆ እንደነበረች የምታስታውቅ ነገረኛ ነገር !
‹‹ኤዲያ መልክ ታጥቦ አይጠጣ …. ትዳራችን ቤታችን ብለን ጓዳ ለጓዳ ቀበርነው እንጅ ለባብሰን እንሞላፈጥ ብንል መልኩ መች አነሰን ….መልካችን እንደሆነ ረጋፊ ነው›› አለች ሌላኛዋ …ልእልትን ስሟን አጥበው አለቅልቀው ሲጨልጡ እየዋሉ ….መልክ ታጥቦ አይጠጣ .. እና መልኳ ነው አንዲህ ያበሳጫቸው ! መልከ ጥፉ ሁሉ …መንግስት የዚህን ብሎክ እጣ ሆነ ብሎ ለመልከ ጥፉዎች ያወጣው እኮ ነው የሚመስለው …ወይስ ባለቤቶቹ ለመልከጥፉ አከራዩት ….እንጃለታቸው አበሳጭተውኛል !! (ዞር ብየ ተናጋሪዋን አየኋት…ከበሩ ኋላ ደማቅ ቀይ የእራት ቀሚስ ለብሳ ቁማለች …(የራት ልብስ ለብሳ ለሃሜት መምጣት)አስሩም ጣቶቿ ላይ ረዣዥም ሰው ሰራሽ ጥፍር ሰክታ ቦግ ያለ ቀለም ተቀብታቸዋለች …!! የተነኮረ የጤፍ ቂጣ የመሰለች መልከ ጥፉ ናት ….ደግሞ አለች ‹መልኩ መች አነሰን› እውነት ይወራ ከተባለማ ቀላል አንሷታል ! እንደውም እንዲህ ነብሷን እስክትስት ዘንጣ መጥታ እንኳን አንሷታል … አሁን የዚች ሴት መልክ ምኑ ነው የሚረግፈው ….እንደተሰጣ ልብስ መልክ የሚባለውን ሁሉ ከላይዋ ላይ አራግፎ ወደህይዎት ያስገባት ነገር …ወይኔ ልእልትየ የማንም ያፈር ገንፎ ስሟን ይፈትፍተው ! )
ተፀፀትኩ ! ሁሉም እኔንና ወንዴ አንበሳውን ጨዋ…. ልእልትን ባለጌ ስድ የማትታመን ‹ወንድ አውል› አድርገው እፊቴ ሲያበሻቅጧት…(ልክ እቤቴ መጥታ አልፈልግም ብየ የመለስኳት ይመስል) ሲያሞካሹኝ (ሜዳሊያ አንገቴ ላይ ማጥለቅ ነው የቀራቸው) ዝም በማለቴ ተፀፀትኩ ‹‹ልእልት እንደምትሏት አይደለችም ›› ማለት ቢያቅተኝ እንኳ ‹‹ልእልት የዛን ቀን እዚህ አልመጣችም እኔ እዚህ እንደምትኖርም ወኩት …. ›› ማለት እንዴት አቃተኝ ብየ ተፀፀትኩ ….ሌላው ቢቀር ወደኪችን ገብቸ ቢላ መዝዠ እነዚህን ጎረቤቶቸን ማሳደድ ሁሉ ተመኝቸ ነበር …. (እንኳን እኔ የማንም ቦዘኔ ለመዘዘው ቢላ ደግሞ)

አንዳንዴ ግን ለምን ውሸት ሲወራ አፋችን እንደሚያያዝ ይገርመኛል …እውነት ተናግሬ ከስራየ ብባረርስ …..ብታሰርስ ….እያልን ለምዶብን ምንም በማይፈጠርበት ሁኔታም አፋችንን በእውነት ላይ መሸበብ ብሔራዊ ዓመል ሁኖብን ቀረ !!ልእልት ምንም እንዳላደረገች አውቃለሁ አይደል እንዴ ??… እነዚህ ቱልቱላ ጎረቤቶች የቤት ኪራይ አይከፍሉልኝ ደመዎዝ አይከፍሉኝ …..እንዳሻቸው ሲቀደዱ ምን አፌን ለጎመው … ውሸት ሲወራ ሰው ካለነገሩ ሲወነጀል ዝም ከማለት በላይ ውሸታምነት ህሊና ቢስነት የለም ! አሁን ነገ መስሪያ ቤት ጓደኞቸ ጋር አጉል ሃቀኛ ልሁን እያልኩ ስደሰኩር እገኛለሁ የሞትኩ !! ትልቁ ውሸታም ውሸት መሆኑን እያወቀ ውሸትን እራሱን እየነቀነቀ የሚያዳምጠው ሰው ነው !! ውሸታሙማ ያው ከውሸቱ የሚያገኘውን እርካታ እያጣጠመ ነው !!
በእርግጥ ግማሻቸው ድፎ ግማሻቸው ብርቱካን ይዘው ቤቴ መጥተዋል …ግን እውነት በድፎ ይቀየራል ?(ይድፋቸውና) እውነት በብርቱካን ይቀየራል …. ?ጉርብትናስ ከሃቅ የበለጠ ዋጋ አለው ?…አንዲት መድረሻ ያጣች ልጅ ላይ ይሄ ሁሉ ጎረቤት ያውም ካለስረዋ ሲረባረብ ዝምታ ነበር ከእኔ የሚጠበቀው ?….አቤት ፊታቸው ላይ የነበረው ጥላቻ ….ዋና ችግራቸው ቅናት መሆኑን በሽ ማስረጃ አስደግፌ መናገር እችላለሁ …..ልእልትን ስለወደድኳት ለሷ ለማገዝ ነው? ….አይደለም !!
የሚገርመኝ ልእልት ይሄን ሁሉ ጊዜ ከቻለችው ችግርና መከራ ይልቅ ((((የመባለጓ ወሬ)))) እግር አውጥቶ አገሩን አዳርሶታል …ለምን እንደሆነ እንጃ ህዝቡ ቆንጆ ሴትን እንደጥላት የመመልከት አባዜ ተጠናውቶታል ….((ቆንጆዋ የእኔ ካልሆነች በቃ ባለጌ ናት አይነት እውር ድምዳሜ)) ስራ ብትይዝ በቁንጅናዋ ባልጋ … በትምህርት የተሸለ ውጤት ብታመጣ አስተማሪዋ አልጋ ላይ እንጅ ትምህርት ቤት ወንበርና ጠረጴዛ ላይ ተፈትና ነው አይባል ….መኪና ብትይዝ በቁንጅናዋ አንዱ ሃብታም መፅውቷት …. ቢሞት ቆንጆ ሴትን የማያምን ማህበረሰብ የት አለ ቢባል እዚህ አዲስ አበባ!! …
የሴቶች መብት እኩልነት ምናምን እያለ በአደባባይ የሚጮኸው ሁሉ ቆንጆ ሴት መኪና ይዛ ባጠገቡ ካለፈች አይኑ ደም ይለብሳል !!እንኳን መኪና ደህና ጫማ አድርጋ ስታልፍም ሳይቸግረው የሚበሳጭ ህዝብ ! የቆንጆ ሴት ትዳር ሳይቀር በፍቅር የተመሰረተ ነው ማለት የሚተናነቀው ህዝብ እንደኛ የት አለ ….የቆንጆ ሴት ትዳር ከፈረሰ ሆዱ ቢያውቅ እንኳን … ባል ‹‹ሚስቴ ወስልታ ነው›› ካለ ይሄንኑ ወሬ ይዞ የሚሮጠው ይበዛል ….ቁንጅና በራሱ ብልግና እስኪመስል የሁሉም ፀያፍ ባህሪ ባለቤቶች ቆንጆ ሴቶች ተደርገው የመታየት አባዜ እንደወረርሽኝ ከቦናል …. ለነገሩ ድራማው ፊልሙ ሁሉም ቆንጆ ሴትን ብልግና በመተረክ በየቀኑ ይሞላናል …የተሞላነው ፀባይ ሁኖ ወደውጭ ይረጫል !! ይሄም ሁኖ እያማን እያናናቅን እየሰደብን እና እየረገምን ቆንጆ ሴቶችን ስናሳድድ ውለን ስናሳድድ የምናድረው የትየለሌ ነን ! በውበቷ አሳሳተችኝ ለማለትኮ ነው ! ስራችንና ድርጊታችን የየቅል !!
ታዲያ ሃሜት አስመስለን ጥላቻ አስመስለን ግሳፄ አስመስለን በሾርኔ (ርግማናችን ራሱ ሰምና ወርቅ አለው) ‹‹ቁንጅና የማያመጣው ሃብት የማየከፍተው በር የለም›› የሚል መልእክት እንዘራለን ….የዛሬ ህፃን ሴቶች እያጠጣናቸው ባሳደግናቸው የርግማን ዝናብ ….እርግማን ለበስ አድናቆቷን አይስቷትም ( አበሻ አይደሉ እንዴ ቅኔ ለመፍታት ማን ብሏቸው !!) …. እና ከሁሉም ቆንጆ ሴቶች ከሚወገዙበት ቃል ጀርባ ቁንጅና የሚያስገኘው ጥቅም የመርገምት ‹ሰሙን› ተጀቡኖ የስኬት ‹ወርቅ› ሁኖ ተቀምጧል ! በእጃቸው ሰርተው በአእምሯቸው አስበው ከማደር ይልቅ ተጎልተው ጥፍራቸውን እየሞረዱ በተመልካች አይን እና በወንድ አድናቆት ሚዛን ልክ ሰውነታቸውን እየመዘኑ የምናገኛቸው ቆነጃጅት ይችን መሃበረሰቡ የሚዘርፍላቸውን ቅኔ በሴትነት ቁልፍ የፈቱ ናቸው … ለዚህ ነው በየመስሪያ ቤቱ…. በየመዝናኛው በየመንገዱ አንጥፈው ቁንጅናቸውን እንደለማኝ ድሪቶ አንጥፈው የስኬት ሳንቲም እስኪጣልላቸው አይናቸውን የሚያቁለጨልጩ ቆነጃጅት እንደአሸን የፈሉት !

እዚህ የኑሮ ህበረ ቃል ውስጥ …… እዚህ ለቅሶው ሳቅ… ሳቁም ለቅሶ የሆነበት አዙሪት ውስጥ ስንቀለቀል ተዘፍቄ ፍዳየን አያለሁ !! …..አንዲት ቆንጆ (እጅግ በጣም ቆንጆ) ባለትዳር ሴት ….ያውም እኔ ጋር ግንኙነት እንዳላት በመጠርጠር ባሏ በቢለዋ ወግቶኝ እስር ቤት የሚገኝ ….ጎረቤቱም ግንኙነት ይኑረን አይኑረን ግራ ገብቶት በብዥታ ላይ ባለበት ሰዓት እንዴት ነው የምረዳት ?? መርዳቱ ይቅር እንዴት ነው የናፈቀኝ አይኗን የምመለከተው ….አውቃለሁ ልእልት ባለትዳር ናት …. ትዳር ክቡር ነገር ነው … ፈጣሪም በማያወላውል ቋንቋ አስቀምጦታል ….ባለትዳር ሴት የቱንም ያህል ውብ ቆንጆ ትሁን ….የቱንም ያህል ትቅረብህ የቱንም ያህል ትዳሯ ጥሩ አይሁን …. ስታምርህ ትቅር ነው ትዛዙ !!
እኔ ግን አልቻልኩም !!…. ከእናቴ ቤት ተመልሸ እቤቴ ከገባሁ በኋላ ደረጃዎቹ ላይ የልእልት ዳና ይታየኛል …..አልጋየ ላይ በጀርባየ ተንጋልየ ከበላየ ከተዘረጋው ጣራ በላይ ልእልት ስንት ሌሊቶች ተደፍታ ስታለቅስበት የነበረው አልጋ መኖሩን እያሰብኩ እተክዛለሁ ….አንሶላው ላይ አሸዋ የተዘራበት ይመስል ምኝታው ይኮሰኩሰኛል …. የቢሮ ወንበሬ ላይ ጠጠር በገልባጭ መኪና አምጥተው የደፉበት ይመስል መቀመጥ ስቃይ ሁኖብኛል …..ኡኡኡኡ ከምር ልእልት ናፍቃኛለች !!
*** **** *****
ትላንት እህቴ ደወለችና
‹‹ስማ …በቃ አንተ እንደዚህ ቋጣሪ ሁነህ ቀረህ …. ትላንት የደሞዝ ቀንህ ነበር አይደል ….እስቲ ዛሬ ሞቅ ያለ ግብዣ ጋብዘን ›› አለችኝ …
‹‹ምንን ምክንያት በማድረግ›› አልኩ … እህቴ ጋብዘን ካለችኝ የሆነ ወሬ አላት ማለት ነው
‹‹ ምክንያት ትላለህ እንዴ ….. ብትሞት ኖሮ ዛሬ ሁለት ሰባትህ ነበርኮ ….ስለዚህ ለምን የቁም ተስካርህን ምክንያት በማድረግ አትጋብዘንም ?››
‹‹እንዴ ስንት ናችሁ ?››
‹‹አራት ነና …ጓደኞቸ ጋር …. ሆስፒታል ሁነህ አብረውኝ ሲጨነቁ ነበር…. ዛሬ ላንተ በጭንቀት ያወጡትን ላብ ተካላቸው ሂሂሂ›› እህቴና ሶስት ጓደኞቿ የማይለያዩ ናቸው ሁልጊዜም አራት … ከሃይስኩል ጀምሮ አሉ አሉ እኔን እያከሰሩ !
‹‹ተይ እንጅ ‹እህት አለም› አራት ሴት በምን አቅሜ …አንድ ሰው ጣል ብታደርጉበት እኮ አምስት ሁናችሁ የትጥቅ ትግል መጀመር ትችላላችሁ ››
‹‹አያስቅም!! በቃ ፓሮት ሬስቶራንት ፎቁ ላይ 9፡00 ሰዓት ›› ብላ ስልኳን ዘጋች …እኔኮ ነገረ ስራዋ ያስቀኛል ….!!
*** **** *****
በጭራሽ አልጠበኩትም ነበር…በጭራሽ … በቀጠሯችን ሰዓት ሬስቶራንቱ ፎቅ አንድ ጥግ ….እህቴ ከልእልት ጋር ተቀምጣ አገኘኋት ….ልቤ ስንጥቅ ነው ያለው …. እህቴ አንድ ከጥይት የፈጠነ ጥቅሻ ጠቅሳኝ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም አለች ….ልእልት ፈገግ ብላ ከወንበሯ ተነሳች ….ፀጉሯ አሁንታጥባ የለቀቀችው አይነት ፍርፍር ብሏል….. ከላይ የለበሰችው ቢጫ ቦዲ ሰውነቷ ላይ ጥብቅ ብሎ ጡቶቿን አሳምሯቸዋል …..የዚች ልጅ ሆድ ግን ዝም ብየ ሳው ወደውስጥ አየር ስባ የያዘችው ነው የሚመስለው ….እሷን ሳይ ስለሚጨንቀኝ እኔ ወደውጭ እተነፍሳለሁ ! ፈገግ ብላ ‹‹አብርሽ›› አለችኝ … ልክ አፋችን በትልቅ በሚጣፍጥና ወጥ በረሰረሰ የሚያስጨንቅ ጉርሻ እንደሚሞላው …. የልእልትን የፈገግታ ጉርሻ ጎርሶ አይኔ በእይታ ብቻ ጥግብ ሲል ይታወቀኛል ጉንጯ ጉንጨን ሲነካኝ ለስላሳ ቆዳዋ ሰመመን ሆነብኝ …. !(እግዜር ያሳድግሽ አንች ቀልቃላ እህቴ )
ቀድመውኝ አዘው ስለነበር ያዘዙት ፒዛ ሲቀርብ ልእልት ልትታጠብ ተነሳች ….ይችን አጋጣሚ ተጠቅሜ (ያልፈለኩ ለመምሰል) እህቴን አፈጠጥኩባትና ….‹‹ስሚ›› …አልኳት
ኮስተር ብላ
‹‹እ ›› ብላ እሷም ኮስተር ብላ ስታፈጥብኝ …ምንም ማድረግ አልቻልኩም ሳቄ አመለጠኝ ….ሁለታችንም ተሳሳቅን …
‹‹አራት ጓደኛ ምናምን አላልሽም … ››
‹‹ …እሱን ተወው ….እኔማ በቁንጅናቸው አገር ያወቃቸው ጓደኞቸ ጋር ባስተዋውቅህ አንተ የሰው ሚስት ጋር ሙጭጭ አልክ ….››
‹‹ እነማናቸው ደግሞ አገር ያወቃቸው ቆንጆዎች ….››
‹‹ ባክህ ታውቃቸዋለህ ሄርሚ አሁን ፎቶዋ መፅሄት ላይ ቢወጣ አንድ ሚሊየን ኮፒ ነገውኑ አይሸጥም ….? ›› ብላ ጀመረች ….….እውነቷን ነው ሄረሜላ በጣም ቆንጆ ትሁት የእህቴ ጓደኛ ነች …ለምን እንደሆነ እንጃ የእህቴ ጓደኞች እህቴን ራሷን ነው የሚመስሉኝ …እንኳን በሌላ ነገር ማሰብ …. እና ስለጓደኞቿ ካነሳች መቀለድ ነው የሚቀናኝ አሁነም ስለእህቴ ጓደኞች ከእህቴ አፍ ነጥቄ ቀጠልኩ
‹‹እሱንኳን ተይው የሄርሜላን ኮስታራ ፊት መንግስት ራሱ መፅሄት ላይ ቢያየው የትጥቅ ትግል የጀመረች ታጋይ መስላው መፅሄቱን ወዲያው ነው የሚዘጋው …..…ቬቨን …ትንሽ አገጯ ረዘም ቢልም ውብ ነች …..ትእግስት ቁመቷ ከማጠሩ ውጭ ምን ይወጣላታል …ያም ቢሆን ለማቀፍ ትመቻለች …. ሳምሪ በቀን አንድ ጊዜ ማልቀስ ሆቢዋ ከመሆኑና ውጭ የጠየም እንቁኮነች …. ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን የእኔ ምርጥ እህት አርባ ክንድ ምላሷ ጋር ሽጉጥ የታጠቀ የብረት አማች የምታመጣ ምርጥ ….
‹‹ ሂድ እዛ ቀልደህ ሙተሃል ሞዛዛ …..እየው ደግሞ ….የሰው ሚስት እንዲች ብለህ ትነካና ባሏ እንደሸንኮራ ለአራት ነው የሚሰነጣጥቅህ እንደውም ጀምሮሃል …››
‹‹ታዲያ ለምን አገናኘሽን ….››
‹‹ የጀመረችልህን ታሪክ እንድትቀጥልልህ ነዋ …አየህ በዛው እኔም ከልእልት ትዳር በመማር ትዳሬ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ …››
‹‹እንዴ ….እኔ ሳልሰማ ባለሽጉጡ ሽማገሌ ላከ እንዴ …››
‹‹ሂድ ወደዛ…..›› ብላ በእፍረት ተነስታ ልትታጠብ ሄደች ….እህቴና ልእልት መንገድ ላይ ተላለፉ ….ልእልት መጥታ እህቴ ወንበር ላይ ተቀመጠች (በለው…. የተነሳንበትን እስክንረሳ ከተምታታብንማ ጥሩ ጅማሬ ነው፡) እህቴ ስትመለስ በወንበሮቹ ለውጥ ትንሽ የተንኮል ፈገግታ ፊቷ ላይ በለጭ ብሎ ጠፋና …ፒዛውን ጀመርነው ….
ፒዛውን ስቆርጥ እህቴ በነገረኛ አይኗ አየት አደረገችኝና ….
‹‹ ወንድም አለም እሱን ቢላ እንዳይቆርጥህ ተጠንቀቅ ›› አለችኝ
ልእልት ቡፍ ብላ ሳቀች ….ወይ ሴቶች ! እኔ የእህቴ አሽሙር ዘግይቶ ነበር የገባኝ !! የተረገመች !! ቀና ስል ልእልት ጋር አይን ለአይን ተጋጨን …አይኖቿን ወደፒዛው መለሰቻቸው ‹‹እሰይ ልእልትየ እስቲ እንዲህ የማይናገረውን አርፈሽ ብይ ››

በአልጋው ትክክል (ክፍል 14)

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *