Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል ስድስት)

ዛሬ በጧቱ አንድ ጅንስ ሱሪና ነጭ አዲዳስ ሲኒከር ጫማ ያደረገ (እድሜው አምሳ የሚሆን እንቢ አላረጅም ነገር) ማስቲካ የሚያላምጥ ….ደግሞ በሽቶ ተጠምቆ የወጣ የሚመስል ….(ልክ ሲገባ ክፍሉ በሽቶ ተሞላ) ወደተኛሁባት ክፍል ገባና መነፅሩን አውልቆ አንዴ ክፍሏን በትእቢተኛ አይኑ ገርምሟት ሲያበቃ …ወደእኔ በመነፅሩ እጀታ እየጠቆመ እህቴን እንዲህ ሲል ጠየቃት
‹‹ አብርሃም ማለት እሱ ነው? ››
እንግዲህ እኔ አልተኛሁ …አፍጥጨ እያየሁት ነው… ልክ እዛ እንደሌለሁ አክብራው ለቆመችው እህቴ ሰላምታ እንኳን ሳያቀርብ በንቄት ጥያቄውን ፊቷ ላይ ወረወረላት ……
‹‹አወ …ልክነዎት ይቀመጡ አለችው ›› በአክብሮት እየተሸቆጠቆጠች …..ተመልሶ ክፍቱን ትቶት በገባው በር አንገቱን ብቻ ብቅ አደረገና ‹‹ ና›› የምትል ቀጭን ትዛዝ ውጭ ለቆመ ሰው ተናገረ …. በፌስታል ሙሉ የታሸገ ጭማቂና ፍራፍሬ ያንጠለጠለ ወጣት እየተሸቆጠቆጠ ገባ ….. ሰውየው አለቃው ነው የሚመስለው …እንደውሻ ጅራቱን እየቆላ ከሰውየው ስር ቆመ …..ይሄ ትእቢተኛ ሰውየ እህቴ ያስጠጋችለት ወንበር ላይ አረፍ አለና ገና ከመቀመጡ የጫማውን ሶል ለእኔ ሊያሳይ የመጣ ይመስል አንድ እግሩን ሌላኛው ላይ ጭኖ ‹‹እንኳን ተረፍክ ወንድሜ›› አለኝ ….አንቱም አንተም ለማለት የሚቸግር ሰውየ ስለሆነ እኔ ራሱ ተደበላለቀብኝ …
አነጋገሩ መትረፌ የገረመው አይነት ቅላፄ አለው (አለ አይደል ወንድየ በቢላ የወጋቸው ሰዎች የመትረፍ እድላቸው ከመቶ አንድ ነው የሚል አይነት) ቀጠል አድርጎም ‹‹ ነገ ዛሬ እመጣለሁ ስል ስራውም ምኑም ሲያዋክበኝ ሳላይህ ቀረሁ ….አሁን እንዴት ነህ ….ለነገሩ ብዙም እንዳልተጎዳህ ሰምቸ ነበር ›› አለኝ …ኧረ ይሄ ሰውየ ማነው ?…..መነፅሩ መስተዋት ላይ ትንፋሹን እፉ እፉ አለና መሃረሙን አውጥቶ እየወለወለ …
‹‹በዚህ ዘመን ሞልቶ ለተልከሰከሰ ሴት እንዴት በሴት ትጋጫላችሁ …? አትረቡም!! ካፍቴሪያ ብትገባ ሴት ነው …መንገዱን ሴትና ሴት የጫነ መኪና ነው ያጣበበው….የትም ብትሄድ ሴት ነው ….. የዛሬ ልጆች ‹‹ደሃ ልጅ አፈር አበድሩኝ ብሎ ይጣላል ›› እንደሚባለው ናችሁ ጎንበስ ብሎ መዝገን ሲችል ….ሃሃሃሃሃ››አለ …ፌስታል ተሸካሚው ልጅ አለቃው ስለሳቀ ለማጀብ ነው መሰል ሂሂሂሂሂ እያለ አጀበው ….የልጁ ድምፅ የዛገ የብረት በር ሲከፈት የሚያሰማው አይነት ሲጥሲጥታ ይመስላል …ሰውየው ልጁን በፈገግታ ዙሮ አየው …ልክ ሲያየው ‹‹ሳቅ ጨምር›› ያለው ይመስል በዛ ድምፁ ፍርፍር ብሎ ሳቀ ! መሳቅ ብቻ መሰላችሁ የሰውየውን ንግግር አብራራው
‹‹ጋሸ ያለው ነገር ልክ ነው …ዛሬኮ አዲስ አበባ ላይ ዘጠና ፐርሰንቱ ነዋሪ ሴት ነው ….በዚህ ሰዓት በሴት መጣላት ያስቃል ሂሂሂ››እኔም እህቴም ተገርመን እናያቸዋለን …..
‹‹እ ….አብርሃም ….ይቅርታ አላወከኝም መሰል…. የወንድየ አባት ነኝ …. ያው የመጣሁት ሁለታችሁም ያደረጋችሁት ነገር ልክ አለመሆኑን እንደአባት ለመገሰፅና ነገሮችን በቀላሉ ለመፍታት ነው ….ይችኮ ይሄን ያህልም የምትጋነን ነገር አልነበረችም ….እኔ አባትህ ስንቱን ነገር ፈትቸዋለሁ …. እንኳን በጩቤ መጫጫር በሽጉጥ ስንፈሳፈስ በብረት ቦክስ ስንቱን ጥርስ ስናረግፈው ….ነው የኖርነው …ምናላት ይች …?!.›› አለ ሰውየው …..ታዲያ ከመጀመሪያው አይናገርም?….. ልጅየው ከዚህ ሰው ወጥቶ እንኳን ቢላ መድፍ እየጎተተ ቢመጣ ምን ይገርማል …ዘረ እብሪተኛ !! ልጁ ትልቅ ነገር እንደሰራ ሲጀነን ደግሞ አለማፈሩ !
‹‹ጋሸ አሁን ያለው ነገር ልክ ነው … ምናላት ይች በ‹ፒስ› የምታልቅ ነገር ነች …. ጋሸ እንኳን ያኔ አሁንም ስንቱን ነው ካፈር የሚደባልቀው ….›› አለ ፌስታል ተሸካሚው ….
‹‹እንደውም ቀደም ብየ ብደርስ ደህና ሆስፒታል ታክመህ እስካሁን ስራ ላይ ነበርክ …እዚህ ስርቻ ውስጥ ይሄን ያህል ቀን …›› ብሎ በአይኑ ክፍሏን ገረመማት የወንድየ አንበሳው አባት ሌላው ‹‹አንበሳ››…. የሚገርመው እስካሁን እኔም እህቴም አንድ ነገር አልተናገርንም ሰውየውም ግድ ያለው አይመስልም …
‹‹ ጋሸ አሁን ያለው ነገር ልክ ነው …ስንት ስፔሻሊስት ሃኪሞች በእጁ ነበሩ …እንዳዘዛቸው የሚሆኑ የሰው ጭንቅላት ነቅላችሁ ግጠሙ ቢላቸው የሚገጥሙ ….. ›› ኧረ ይሄንን ልጅ ዛሬ አንድ በሉልኝ … እጎኔ በጠቀመጠው ልእልት ባመጣችው የሾርባ ብርጭቆ አናቱን ልለው ትንሽ ነው የቀረኝ ከምር ! የምን አስተርጓሚ መሆን ነው ….ደግሞኮ ልጁ ስለሰውየው እያጋነነ ሲናገር ሰውየው በፈገግታ እየተመለከተው ‹‹ጥሩ ብለሃል›› አይነት ራሱን በመስማማት ይነቀንቅለታል …. ሰውን ምን ነካው ገድሉን አጅቦ የሚጮህ በቀቀን ይዞ ይዞራል እንዴ ?
‹‹እ….እህቱ ነሽ ….?›› አላት እህቴን
‹‹አዎ››
‹‹ኦ የቆንጆ ልጅ ወንድም ደብድቦ ይሄ ባለጌ ልጅ ….እንዲህ ከሚያንከራትተኝ እንዳንች አይነት ቆንጆ ጋር ተዛምዶ ቢያኮራኝ ምን ነበረበት ሃሃሃሃሃ ›› እህቴን በጎረምሳና እና አስቀያሚ አይን ከእግር እስከፀጉሯ ተመለከታት …እግሯን ሰብሰብ ስታደርግ አያታለሁ ! ‹‹ያው መቸም ጉዳየን ትረጅዋለሽ በእናተ የመጣ ፀብ አይበርድም …ወጣትነት አለ በዛ ላይ ወንድየ አስተዳደጉም ባህሪውም ፍርሃት የሚባል ነገር አያውቀውም ….ሰው ላይ አይደርስም ከደረሱበት ደግሞ አይመለስም ይገርምሻል … ያች ሚስት ተብየዋን ከአመድ ላይ አንስተን እዚህ ያደረስናት እኛ ነን ….እንዲህ አፍንጫው ስር ሌላ ወንድ ጋር …..››
‹‹አሁን ጋሸ ያለው ነገር ልክ ነው ….ልእልት ወንዴ ጋር ስትተዋወቅ ፀጉሯ ራሱ እንደጃርት የቆመ ነበር …ምን ፀጉሯ ብቻ ….››
‹‹ይቅርታ የኔ ወንድም እሳቸው እየተናገሩ ነው አይደል እንዴ ….የአንተ ማብራሪያ ምንድነው …..›› አልኩት ደሜ ፈልቶ ….
‹‹አይ ጋሸ ባሉት ላይ ለመጨመር ያህል ነው ….ልእልት ያደረገችው ነገር በጣም ሸም ነው …ወይ ሰው ግን ….ማን ይታመናል በዚህ ዘመን ›› ብሎ ምራቁን ወደመሬት ትፍ አለ …ሲያወራ ልክ እንደ ነገረኛ ሴት ነው …አንገቱን እየሰበቀ ….ቀፈፈኝ !
ሰውየው ቀጠሉ …‹‹እየውልህ አብርሃም በቃ የሆነው ሆነ ….ስህተቱ ያንተም የወንድየም አይደለም …የዛች የውሻ ነው …አሁን መሆን ያለበት …››ከምር ልእልትን ውሻ ሲሏት ሰውነቴ ሰማ እንደነካኝ ሲለበልበኝ ተሰማኝ ….
‹‹ይቅርታ …..ስህተቱ የእርሰዎ ልጅ ነው …ባልተፈጠረ ነገር በራሱ ቅዠት ያውም እንደሚሉት ጀግና ስለሆነ ምናምን ሳይሆን በመጠጥ ጥንቢራው ዙሮና ባላሰብኩት ሰአት የፈሪ ብትር ያሳረፈብኝ …ይሄ የሚያዳንቁት ባለጌ ልጅዎት ነው … ለመሆኑ እንደአባት ትንሽ እንኳን በልጅዎት ድርጊት እንደመፀፀት ጭራሽ እዚህ ድረስ መጥተው የማይረባ እንቶ ፈንቶ ሲያወሩ አያፍሩም ›› ብየ ልቀጥል ስል
‹‹አብርሽ ›› አለችኝ እህቴ …ሲተረጎም ዝም በል ማለት ነው ! ቁጣየ ሲንቀለቀል ሰውየው ያነባበሩትን እግራቸውን አወረዱ ፌስታል ያዡም እግሩን አወረደ …እኔም ስላልወጣልኝ ቀጠልኩ …
‹‹ልጅዎት በመታሰሩ እግዚአብሔርን ያመስግኑ … ከዚህ በኋላ እፊቴ ባገኘው በሂዎት አያገኙትም !! ሁለተኛ ደግሞ እዚህ መጥተው ደህና ልጅ እንዳሳደገ ሰው እንዳይኮፈሱብኝ !!››
‹‹ኖኖ አብርሃም ….ልል የፈለኩት ምን መሰለህ …ድርጊቱ ተገቢ ነው እያልኩ አይደለም ….ግን ወንዴ አንድ ፍሬ ….ልጅ ነው …››
‹‹ምን ልጅ ነው …..እኔን ዘጠኝ አመት በእድሜ የሚበልጥ ሰውየ ልጅ ነው ይላሉ እንዴ ›› አፈጠጥኩባቸው ….ሰውየው በልጃቸው ነው የወጡት ቆጣ ሲሉባቸው ይደነግጣሉ …ማታ ቢላ ይዘው ካልተመለሱ !!
‹‹አይ ጋሸ ሊል የፈለገው …›› አለ ፌስታል ያዡ
‹‹ አንተ ዝም በል በናትህ …ወንድ ልጅ ቆፍጠን ሲል ነው ደስ የሚለው ምን ጋሸ ጋሸ ትላለህ ›› አለችው እህቴ ሽምቅቅ አለ !
ሰውየው ረጋ ብሎ ወደእኔ አጎበደደና ‹‹አብርሃም …እባክህ ብስጭትህንም ቁጣህንም ተቆጣጠረውና የሚሻለውን እንነጋገር ››
‹‹የሚሻለውንማ ህግ ይዞታል …መጥተው ስላዩኝ እግዜር ይስጥልኝ …ካሁን በኋላ እዛው ፍርድ ቤት እንገናኝ ››
‹‹አይ እንዲህማ አይደረግም አብርሃም …..ማንም ሰው ይሳሳታል …እየውልህ …እኔ ለህክምና ያወጣሃውን ወጭ እሸፍናለሁ ….ልጀ ስንት ቀን ሙሉ ከማንም ወሮበላ ጋር ቁንጫ እየበላው መታሰሩ በራሱ ትልቅ ቅጣት ነው ….እኔም ይቀጣ ብየ ነው ‹ይሄን ሁሉ ቀን› ዝም ያልኩት …እንጅ ባለስልጣኑም ፖሊሱም ዳኛውም በእጀ ነው ….››
‹‹ጋሸ አሁን ያለው ልክ ነው …. ጓዳ ጎድጓዳውን እንደእጁ መዳፍ ነው የሚያውቀው ….ለጋሸ ይች ምናላት …›› እህቴ ዞር ብላ አየችን እኔም በግርምት አየኋት (ምን በሽታ ነው ይሄን ልጅ የለከፈው )
‹‹ ጥሩ እንግዲያውስ እርሰዎ ልጅዎትን ከዛች እስር ቤት በብርም ይሁን በዘመድ ያስፈቱት ቀን እኔ ደግሞ ወደማይመለስበት እልክለዎታለሁ ….እኔ ብምረው እንኳን ዘመድና ጓደኞቸ አይለቁትም ›› ስል ከብዙ ጉራ ከትንሽ ውሸት እንዲሁም ከመካከለኛ እልህ የተቀመመ ፉከራ ፎከርኩ ! አባትየው ግን ካሰብኩት በላይ በድንጋጤ ሙሽሽ ብለው አንዴ እህቴን አንዴ እኔን እያዩ ….ቆዩና …‹‹ቆንጆ ወንድምሽን ምከሪው እንጅ›› አሏት …..አሁንም ትእቢታቸው በደንብ አልተነፈሰችም !
‹‹ ኧረ እመክረዋለሁ …. ›› አለችና ወደኔ ዙራ ኮስተር ባለ ንግግር ‹‹ ወንድሜ አንተ አትነካካ …ያንን ጫት የጨረሰው ልጅ ገና ከእስር ቤት እግሩ ሲወጣ እኔ ራሴ አንዱን ጎረምሳ ልኬ ነው የማስደፋው ›› ብላ በእልህ ወደሰውየው ዞረች እና እጇን አነባብራ አፈጠጠችባቸው! ሰውየው ቀልቡ ተገፈፈ … ከምር አንዴ እኔን አንዴ እህቴን ተራ በተራ እየተመለከተ ግራ ተጋባ …የሆነ የአእምሮ ችግር ያለብን ሳይመስለው አልቀረም ….
‹‹ ይቅርታ ጠየኩኮ … በቃ የለት ግጭት ነው …ተሳሳተ ልጅ ነው …. አብርሃም እባክህ እሽ በለኝ ጉዳዩን በሽምግልና እንጨርሰው…. እኔ ላንተ የፈለከውን ያህል ካሳ ልክፈል …እኔ ግርማቸው እንኳን ላንተ ለስንቱ እተርፋለሁ ሰው ነው የማደርግህ›› ብሎኝ እርፍ …
‹‹ኧረ ሰው የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው አንቱ ሰውየ ….በገንዘበዎት ከሚመኩ ቢያንስ ከልብዎ ይቅርታ እንኳን ቢጠይቁ ምናለ ›› አለች እህቴ…. አሁን ከምር እንደተበሳጨች ታስታውቃለች ….
የወንዴ አንበሳው አባት ልባችን ዝቅ እስከሚል ብዙ ብዙ ትእቢት የቀላቀለ ውሽንፍር ወሬ ሲያዘንብብን ቆይቶ እንደሚመለስ ነግሮን ወጣ …. ሲወጣ ‹‹ ይችን እስቲ ያዝ ባዶ እጀን ከምመጣ ብየ ነው›› ..ብሎ ፌስታሉን ወደአልጋየ ጠጋ አድርጎ አስቀመጠ እና እየተጀነነ ያንን ቶስቷሳ ልጅ አስከትሎ ወጣ …..!ልጆ ሲወጣ ዞር ብሎ ልክ እንደቅብጥብጥ ሴት እጆን እየወዘወዘ ‹‹ባ….ይ ›› አለን !
ሰውየው እንደወጡ …ሁለታችንም ከት ብለን ሳቅን …..እህቴ በእጇ አየሩን ወደአፍንጫዋ እያርገበገበች ‹‹ አንተ ሸባው ግን ሽቷቸው እንዴት ይጥማል …ይሄንን ሳምንት ሙሉ የሾርባና መድሃኒት ሽታ ያፈነው ቤት ሙዱን ቀያየሩትኮ …በአፍንጫየ ነበር ትእቢታቸውን ስሰማው የነበረው ሂሂ …ምን ዋጋ አለው ትእቢታቸው ከሽቶው በላይ ገኖ ይቀረናል ›› ብላ ያመጡትን ፌስታል ወደመደርደሪያው ልትወስድ ስታነሳው ቡትርፍ ብሎ ፍራፍሬ መሬቱን ሞላው …
የታሸገ ሶስት ኪሎ የሚሆን አፕል …የታሸገ የሆነ ነገር ጭማቂ …በስሎ የተቆረ የወይን ዘለላ … እና ስሙን የማላውቀው የታሸጉ ባቄላ ባቄላ በሚያካክሉ ፍሬዎች ….ፌስታሉ ሞልቶ ነበር ….እህቴ የተበተነውን እየሰበሰበች ‹‹የሚስታችሁ አባት ይሄን ሁሉ ፍራፍሬ ኬት አመጡት ባክህ …በትእቢት ከገነት ተባረው ነው መሰል የመጡት ሂሂሂ›› ልእልትን ‹‹ሚስታችሁ ›› እያለች ማውራት ጀምራለች …ፍራፍሬውን አስቀምጣ አንዱን አፕል አወጣችና …አጠበች ….ከዛም ወደወንበሯ ላይ ተቀምጣ ኮርሸም አድርጋ አንዴ ገመጠችለትና
‹‹እኔ የምልህ አብርሽ …..ወንዴ አንበሳው በዘጠኝ አመት እንደሚበልጥህ በምን አወክ …. ?›› አለችኝና የነገረኛ ፈገግታዋን ፈገግ አለችው …እንግዲህ ጀመራት …እንዲት ነገር አታመልጣትምኮ ….(አምልጦኝ በዘጠኝ አመት እንደሚበልጠኝ የተናገርኩት ልእልት ነግራኝ ነበር )እንደው ብቻየን አፍኘ ከምይዘው ብየ ለእህቴ የልእልትን ታሪክ ልነግራት ወሰንኩ እና እንዲህ ብየ ጀመርኩት
‹‹ ወንዴ አንበሳው ባለጌ ነበር …ያውም ምንም ሸም የሌለው ባለጌ …››
‹‹ባለጌም ቢሆን ሚስቱን መመኘት የለብህም ….›› ብላ ከነጀሰችኝ በኋላ ታሪኩን ለመስማት ተመቻቸች …..
ልክ ልእልትን ሁኘ የሰማሁትን ነገርኳት …
‹‹ይሄ ብሽቅ እኔ ብሆን የተኛበት ነበር ጋዝ አርከፍክፌ እሳት የምለቅበት ›› ብላ እጇ ላይ የተረፋትን አፕል በብስጭት ወደቆሻሻው ቅርጫት ወረወረችው … ትራፊው አፕል ልክ ጎበዝ የባስኬት ቦል ተጫዋች እንደወረወረው ኳስ ቅርጫቱ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ !

በአልጋው ትክክል (ክፍል ሰባት)

2 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *