‹‹ አብርሃም ››
‹‹አቤት አባባ ›› አልኳቸው አከራየ ሻለቃ በላቸው ነበሩ በር ላይ ቁመው የጠሩኝ
‹‹ እየውልህ . . . ይሄ የሸምሱ ሱቅ ጋር መታጠፊያው ታውቀው የለም ? ›› አሉኝ በከዘራቸው ወደሸምሱ ሱቅ አየጠቆሙ
‹‹አዎ ወደ ኢንተርኔት ቤቱ መታጠፊያ አይደል ? ››
‹‹ምን ቤቱ ? ›› አሉ ትዝ ሲለኝ <ኢንተርኔት ቤት> አያውቁም
‹‹ ማለቴ ኮሚፒውተር ቤቱ ….. ውጭ አገር ስልክ የሚደወልበት ››
‹‹አ………….ዎ ! ….›› አሉ ! ኮምውተር ቤቱ ወደውጭ አገር ስልክ ያስደውላሉ ! ከዛም እንዲህ ሲሉ የመጡበትን ነገሩኝ
‹‹ . . . እና እዛ ጋ ማታ አንዱን የጎረቤታችንን ልጅ ጅብ ነከሰው . . . ባለፈው ለሚካኤል ለት እንዲሁ አቶ አሰፋን አሯሩጦ ሊበላው ሲል የጋራዡ ዘበኛ ደርሶ አስጣለው . . .በዚሀ ወር እንኳ ጅቡ ስድስት የመንደራችንን ሰወች ነው የነከሰው እንግዲህ አንተ እዛ ኮምፒተር ቤት እያመሸህ ስትወጣ ተረኛው አንተ ነህ . . . ተጠንቀቅ ብያለሁ አብርሃም . . . ተጠንቀቅ ! ባልወልድህም ልጀ ነህ ! አይኔ እያየ ስትበላ ዝም አልልም መቸስ ››
‹‹ኧረ ጣጣ የለውም አባባ ››
‹‹እንዴት ነው ጣጣ የሌለው ተው እንጅ አብርሃም . . . አንተስ የተሰራሃው እንደሰው ከአጥንትና ከስጋ አይደለም እንዴ ? . . . አንተን ጅብ አይገምጥህም ? …አይቦረትፍህም ? አሃ ምንስ ብትከሳ ረሃቡን ባትከላለት አመሉን ታስታግስለታለህ ! በጨለማ ክልትው ክልትው ስትል ርዝቅ አገኘሁ ብሎ ይሄን ቄጤማ እግርህን አፈፍ ቢያደርግህ የማን ያለህ ይባላል ?….. እንኳን በጨለማ በቀንም ሃይ የሚለው አጥቷል . . . ይሄው በቀደም ለፋሲካ የእትየ ዘውዴን በግ አንጠልጥሏት የሄደው ገና ጀምበር ሳይገባ አይደለም እንዴ ማን ተው አለው …››
‹‹አይ እጠነቀቃለሁ ማለቴ ነው አባባ›› ፈገግ አልኩ የአባባ ምክር ያስቀኛል . . .ምን ቁም ነገር ቢናገሩ የሚናገሩበት መንገድ ያስቃል
‹‹ አያስቅም ! መጠንቀቅ ደግ ነው ልጀ …እንደውም ለዚህ ጅብ መላ እስኪገኝለት ምናለ እዛ ኮሚፒተር ቤት መሄድህን ብትተው … ማምሻ ካጣህ እግሬን ላፍታታ ካልክ እዚህ ሰው ሁሉ ሲያውካካ ሲያሽካካ ሲጫወት የሚያመሽበት ግሮሰሪ እንደወንዶቹ ብታመሽ ምናለ . . . ጅቡ እንደሆነ ከግሮሰሪ የሚወጣ ሰው ነክቶ አያውቅም ከዛ ኮምፒተር ቤት የሚወጣውን ነው የሚተናኮሰው . . . ምን ምን እንደሚሸቱት እንጃለት ›› እያሉ መከሩኝ ዘከሩኝ
እውነትም መንደሩን ጅብ እያመሰው ነበር . . . እንደው ሰው ከመንገዱ ለሽንት እንኳ ወጣ ካለ ለቀም ነው አያ ጅቦ ! አሁንማ ከመንገዱም ባይወጣ ጅቡ ራሱ ወደመንገዱ እየገባ ሰው መጥለፍ ጀምሯል ! ለምሳሌ ባለፈው ምን ሆነ ? አሜሪካ መንግስት ድረስ የተሰማ ታምር መንደራችን ውስጥ ተከሰተ …..
ግርማ የሚባል ጎረቤታችን ከውጭ አገር ሚስቱ ስልክ ደውላለት ኔትወርክ እየተቆራረጠ ስላስቸገረው ኔት ወርክ ፍለጋ ቦታ ሲመርጥ ሳያስበው ከቤቱ ራቀ . . .ይሄ አልበቃ ብሎት ሚስቱ ጅስም የሚያግል ነገር እያወራችው ተመስጦ ያዳምጣታል ‹‹ ሃኒየ ምን እንዳማረኝ ታውቃለህ ››
‹‹ ምን አማረ………ሽ ››
‹‹ ማታ ማታ አልጋችን ላይ ተኝትን . . . እዛ የሚያምር ሳንቃ ደረትህ ላይ ልጥፍ ብየ እንደሙዚቃ የሚጥም ማንኮራፋትህን ማዳመጥ …..ኦህ ሃኒ አይ ሚስ ዩ እኮ በቃ መላጣ ራስህ ከንፈርህ ….አገጭህ …አንገትህ ….ደረትህ …..ሆድህ ….›› ግርማ እየተራመደ ሳይሆነ በምኞት ባህር ላይ እየተንሳፈፈ ሚስቱ በቃል መቅዘፊያ እየቀዘፈችው እግሩ ያገኘበት እየረገጠ ‹‹ቀዩን መስመር ሳተ›› የአያ ጅቦን ክልል …..ልክ የኢንተርኔት ቤት መታጠፊያዋን ….ድንገት ከየት መጣ ሳይባል አያጅቦ የግርማን አንድ እግር አፈፍ አደረገው ! ደግነቱ ጅቡ የግርማን እግር ያዝኩ ብሎ የነከሰው ሰፊ ፒጃማውን ነበር . . . ፒጃማውን እና ስልኩን ጥሎ ወደቤቱ እግሬ አውጭኝ !
ሚስቱ ‹‹ሔሎ የኔ ፍቅር አለህ ›› ስትለው ምን መልስ አገኘች ‹‹ አውውውውውውው›› ‹‹ የኔ ጌታ እንደጅብ ስትጮህ እኮ ጅብ ታስንቃለህ ›› አለች ግርማ እየቀለደ የጮኸ መስሏት ….ነገሩ ሲደጋገምና ሲገባት ግን በድንጋጤ 911 ደወለችና ፖሊስ ጠራች
‹‹ ባለቤቴ እያወራን ድንገት ወደጅብነት ተቀየረ ›› ስትል አመለከተች
ፖሊሱ እጁን ወደሽጉጡ ልኮ ‹‹ የታለ ›› አላት አካባቢውን እየቃኘ
‹‹ በስልክ ነው ኢትዮጲያ ውስጥ ››
‹‹ትቀልጃለሽ እመቤቴ ›› አለ ፖሊሱ እየሳቀ
‹‹ካላመንክ እንካ አናግረው ብላ ስልኳን አቀበለችው ››
‹‹ሄሎ ›› አለ ፖሊሱ
‹‹ አውውውውውውውውውው ›› አለ ኢትዮጲያ ያለው ጅብ አገር በሚያናጋ ድምፅ . . .ፖሊሱ በሃዘን የግርማን ሚስት እየተመለከተ
‹‹ ምናልባት ባለቤትሽን ጅቡ ይዞት ይሆን . . . ›› አለት ‹‹ በልቶት ቀርጭሞት ይሆን ›› ለማለት ከብዶት
‹‹ እባካችሁ እርዱኝ ባሌን ከጅቡ አድኑልኝ . . . ››
‹‹ እስቲ ከቻልን እንሞክራለን ›› አለና ትከሻው ላይ ያለችውን መነጋገሪያ አውርዶ ጉዳዩን ለሃላፊወቹ አሳወቀ . . . ሃላፊወቹ የሰጡትን መልስ በሃዘን ለግርማ ሚስት ነገራት
‹‹ይቅርታ የኔ እህት የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጲያ ጅቦች የተያዘ ባለቤትሽን ቀርቶ በኢትዮጲያ መንግስት የታሰሩ ፀሃፊወችን ማስለቀቅ አልቻለም . . . አንዲት ሉአላዊት አገር ዜጎቿን ከጅብ የመጠበቅ ግዴታ አለባት እዛው ለኤምባሲሽ ደውይ ›› ብሏት መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ ! የግርማ ሚስት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ስታለቅስ አደረች . . . ጧት ከዛች ኢንተርኔት ቤት ግርማ ደውሎ የሆነውን ሁሉ ነገራት . . .
ሚስቱ በማታው ፖሊስ ምላሽ በሽቃ ስለነበረ ዝንጥ ብላ ሁሌም መኪናው ውስጥ ተቀምጦ ቡና ወደሚያንቃርረው የፈረንጅ ፖሊስ ሂዳ ‹‹ ስማ ባሌ ጅቡን ልክ አግብቶት ተረፈ ›› አለችው
‹‹እንዴት እባክሽ ››
‹‹ በቃ ፒጃማውን ጥሎለት ሮጠ እና አመለጠው ››
‹‹ ኦ ኢትዮጲያዊያን ከድህነት ብቻ ሳይሆን ከጅብም በሩጫ ነው የምታመልጡት ለማንኛውም አንኳን ደስ ያለሽ ›› አላት
ከጎኑ የተቀመጠ ሌላ ፖሊስ ፈገግ ብሎ ‹‹ አፍሪካ ውስጥ ሰባት አመት ኑሪያለሁ ….የአፍሪካ ጅቦች አንድ አይነት ናቸው . . . ቢችሉ ሰውየውን ይበሉታል ያንን ካልቻሉ የሰውየውን ሃብት እንደባልሽ ፒጃማ በቁሙ ይገፉታል ››
*** **** *** **** **** ***
ሻለቃ የማታ የምትማር ልጅ አለቻቸው …የማታ የገባችው በመደበኛው ትምህርት ስምንተኛ ክፍል ሶስት ጊዜ በመውደቋ ነበር ! አባቷ ‹‹ እንኳን ማታ ቀንም በጠሃይ አልሆነላት እስቲ ትሞክረው ›› ብለው የማታ እንድተማር ፈቀዱ ! ታዲያ አንድ ቀን አብረዋት የሚማሩት ልጆች ሰፈር ሲደርሱ እርሷ ስለዘገየች
‹‹አብርሃም ይች ልጅ አመሸች እስቲ ናማ እንቀበላት ›› ብለውኝ ፓውዛ የሚያክል ባትሪያቸውን ይዘው . . . መንገድ ጀመርን ልክ ኢንተርኔት ቤቱ መታጠፊያ የአያ ጅቦ ክልል ስንደርስ ጨለም ያለው ቦታ ላይ አንድ ነገር ቁሞ አየን … ሻለቃ ድምፃቸውን ቀንሰው በሹክሹክታ ‹‹ አብርሃም አጅሬው ነው ተጠንቀቅ ድንጋይ አንሳና እኔ ባትሪውን ‹ቦግ › ሳደርግበት አንተ በድንጋይ ታቀምሰዋለህ . . . አሉኝ …ፍርሃቴ ትዝ አለኝ ! እንደምንም ድንጋይ አነሳሁ
ትልቅ አለሎ የሚያህል ድንጋይ እንደጨበጥኩ እጀን ወደላይ ከራሴ በላይ አንስቸ ልወረውር ተዘጋጀሁ …ሻለቃ እንደሽጉጥ በሁለት እጃቸው ባትሪውን ይዘው አነጣጠሩና ቦ ………………..ግ ! አደረጉት ……..ድንጋየን ባንድ እጀ ከፍ አድርጌ እንደያዝኩ የአሜሪካን የነፃነት ሃውልት መስየ ደርቄ ቀረሁ . . . !! አንድ የገደል ስባሪ የሚያክል ሰውየ የሻለቃን ልጅ እታለማሁን እየሳማት ! ልክ ደግሞ ባትሪው የበራው ለክፋቱ ከንፈራቸው ላይ (ለነገሩ ሻለቃ ወታደር አይደሉ አነጣጥረው ነው ያበሩት )
የታለማሁ ከንፈር ቀርቶ አፍንጫዋ አይታይም ጎርሷታል ! አሁን እንዲህ ይሳማል ? . . . ሰው በከንፈር ብቻ አይኖርም በአየርም እንጅ ! እንዲህ አፍንጫ አልቀረ አፍ አልቀረ አገጭ አልተረፈ በጅምላ የሚስም ጉድ መንገድ ላይ እየጠበቀ የተማረችውን እያስረሳት እንዴት ነው ታዲያ እታለማሁ ስምንተኛ ክፍል ሶስት ጊዜ የማትደግመው ! ገና አስር ጊዜ ትደግማለች !
‹‹ በለው ›› አሉኝ ሻለቃ በሚያስፈራ ድምፅ (እዩት እንግዲህ ወታደርነታቸው ሲነሳባቸው )
‹‹ ጅብ አይደለም እኮ ሻለቃ ›› አልኳቸው
‹‹ ከዚህ ወዲያ ጅብ አለ እንዴ …አንዲት ፍሬ ልጅ እዲህ ጠቅልሎ ጎርሷት እያየህ ጅብ አይደለም ትላለህ … በለው ብያለሁ ትዛዝ ነው ›› አሉ ሻለቃ … እንቢ አልል ነገር ‹‹ቤቴን ነገውኑ ልቀቅ ›› ቢሉኝስ ያ መንከራተት ሊመጣ አይደል ብየ ስለፈራሁ …..የያዝኩትን ድንጋይ ባለ በሌለ ሃይሌ አምዘገዘኩት . . . . ዥ ውውውውውውውውውውውውው ጓ! እታለማሁ ‹‹እእ›› ብላ ወደቀች !! ሰውየው ግን ተፈተለከ !
በቀጣዩ ቀን ከቤት ተባረርኩ . . . ‹‹ ልጀን እንዲህ አርጎ እንደፓፓያ ይሰንጥቃት. . . ቤት ባከራየሁ እንደልጀ ባየሁት ግዴላችሁም ይሄ አብረሃም የሚባል መናጢ ተልኮ አለው . . . አዎ የሻለቃን ልጅ ግደል ብሎ የላከው ሰው አለ ››አሉ ሻለቃ !
ጠያቂዎች መጥተው ‹‹ምን ብታደርጊው ነው እንዲህ ‹ጭካኔ በተሞላበት መንገድ› የፈነከተሸ ልጀ ›› ይሏታል
‹‹ምን አደርገዋለሁ ከመሬት ተነስቶ አስጠኝየ ሲሸኘኝ ….ጨለማን ተገን በማድረግ ፈነከተኝ ››
‹‹ውይ የወንዶች ቅናት …. ድሮም ሴት ያለበት ቤት ወንደላጤ ማከራየት …ኧረ እንኳን በዚህ ማረሽ ሁለት አድርጎሽ ቢሄድ የማን ያለህ ይባላል ›› ይሄ ሁሉ ሲሆን ሻለቃ እራሳቸውን እየነቀነቁ ወንጀሌን በቀይ ያሰምሩበታል … የሆነውን ሁሉ እንዳላየ ጠያቂ አስታማሚ ባመጣው ብርቱከላንና ሙዝ ተከበው ዝም !
የዚች አገር ጦር አዛዦች አዘው የራሳቸውን ህዝብ ያስጨርሱና እዳው ጓዳቸውን ሲያምሰው ፍትህ በበራቸው ሲያንዣብብ ተራው ወታደር ኢላማውን ሲስት ‹‹ ጅቦች ጋር ያደረግነው ጦርነት እልህ አስጨራሽ እና አገራዊ ስሜት ያላቸው መሪወች የተሳተፉበት ነበር …ምን ያደርጋል . . በባንዳወች እና በተራ ሆዳም ወታደሮች ክህደት ምክንያት ባላሰብነው መልኩ ሰላማዊ ሰወችን በመጨፍጨፍ ተፈፀመ ›› ይሉናል የሂወት ታሪካቸውን በሚያትቱበት መፅሃፍ !
እኛም ባስለቀቁን ቤታችን ሳይሆን በተሰደድንበት ቦታ ሁነን ‹‹አቤ……ት ውሸት ›› እንላለን . . . ትውልድም ከነጠባሳው ስምንተኛ ክፍል ስምንት ጊዜ ይደግማል !አስታማሚም ያልታመመን ሲጠይቅ እና ያልሞተን ሲያፅናና ይኖራል ! ሀቅን በጓሮ ቀብረው የደለበ ሃሰት ታሪክ ጎጆ ስር ሲያሳድጉ እኮ ነው !
‹‹ባዩ ቀብሩም ገሰሲ አለቁም ›› አለ አሉ ጉራጌ ‹‹ልጁን ቀብረው እንግዴ ልጁን አሳደጉ ›› እንደማለት !