Tidarfelagi.com

ተ ላ ቀ ቅ

ከሕላዌው ጽንፍ አልባ እውነት ራስን የመነጠል ግብግብ። ከሆኑት መሆን ሌላ መሆንታን መሻት። ከአማናዊው እውነት ተናጥሎ በሃሳብ ደሴት መገለል። የኔ/ኛ፣ የእነርሱ፣ የነዚያ ባይነት ፍረጃ።

ነኝነት ከሌላው የተለየ መሆንን ሲሰብክ መሆን /Being/ ቅዠት ውስጥ ይቧችራል። ነኝነት ጥግ ሲያሻትት የመሆን ቀለም ይደበዝዛል። የሆንከውን እስላወቅኸው ድረስ ነኝ በምትለው መገደብህ እውነት ነው። የገባህ ነኝነት ያልገባህን አማን ይከልላልና።

ነኝነት አጥር ነው – ከኔ ወዲያ ላሳር የሚል አጥር። ነኝነት ልኬት ነው – ከኔ/ኛ ደፍ የማይሻገር ምጥን። ነኝነት ንፍገት ነው – ከነኝታው ቀዬ በአፍአ ለሚያስቀምጠው ሌላኝነት እውቅና የማይሰጥ ክፋት። መርጦ ማየት፣ መርጦ መስማት፣ መርጦ መቀላቀል፣ መርጦ ማቅረብ፣ መርጦ ማራቅ፣ መርጦ መውደድ፣ መርጦ መጥላት፣ ነጥሎ ማጥቃት፣ ነጥሎ ማቅናት፣ ነጥሎ ማሻገር፣ ነጥሎ መከተር፣ ለይቶ ማጽደቅ፣ ለይቶ መኮነን፣ ለይቶ ማልማት፣ ለይቶ ማድማት። ወዘተ የነኝነት ግሳንግስ ነው። የፍረጃ ውጤት።

መሆን ጥግ የለውም። ልክና ምጣኔም አልተበጀለትም። ከመሆን ውጭ ሁነት የለም – አለመሆንም አልተፈጠረም። አንድና ያውነት ነው መሆን። በመሆን ውስጥ ተቃርኖ የለም – መሆንን በመረዳት አቅም ውስጥ እንጂ። ነኝነት ግን የሕላዌ ግንዱ ተቃርኖ ነው። ከነኝታው በተቃርኖ የሚቆም እስከሌለ ድረስ ነኝነት ነኝ አይሆንም። ነኝ ከምትለው ነገር ሁሉ በተቃርኖም ይሁን በአንፃር ስፍር ሌላው ነኝነቱ ያደረገው ነኝነት አለ። ያንተን ነኝነት ምርጥነት ያጎላልህ ነኝታ። ነጭ አድርጎ ያደመቀህ ጥቀርሻ። ውብ አድርጎ ያደመቀህ አስጠሊታ። መሆን ግን የመሆንነቱ ባዳ – የመሆን ተገልጦው እንግዳ አይደለም። መሆን ከመሆንነቱ ውጭ አይደለም። ውጭም የለውም።

ነኝ ስትል ያልሆንከው አለ ማለት ነው። ያልሆንከው ደግሞ ከሆንከው የሚተናነስ ነው። ልክ ነዋ። ሁሉም ለየራሱ ነኝነት ዘብ ቋሚ ነው። ሁሉም የየራሱን ነኝነት ያንቆለጳጵሳል። ከእኔ በላይ ላሳር ይላል። እናስ በየት ብሎ የሌላውን ነኝነት በአቻ ሚዛን ያኖራል።

ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
በነኝነት ታዛ ውስጥ ከነኝ ባዩ ውጭ አይጠለልም። ነኝነት ጠባብ መንገድ ነው – ነኞችን ብቻ የሚያስኬድ ጠባብ። ነኝነት ምስኪን ጓዳ ነው – ነኝነት ያልተቀባ የማያርፍበት ምስኪን። ነኝነት መንጋ ነው – ጥሬ ለቃሚውን ከሚያመሰኳው የማይቀላቅል መንጋ።

ነኝነት ለሃሳብ ልዩነት ቦታ የለውም። አልተስማማኝም ለሚል ሚጢጢ ክፍተት አይተውም። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እንጂ ዘግይቶ የገባህን አያደላድልም። ተቀበል ብቻ ነው እንደ አዝማሪ ቤት ግጥም። ነኝነት አይጠየቅም። ነኝነት አይመረመርም። አይፈተሽም። አይመዘንም። የማይበጀውን ጥሎ ጠቃሚውን አንጠልጥሎ ለመጓዝ አይሞክርም።

መሆን ውስጥ አለመሆን ስለሌለ መሆንታዎችን መቁጠር ከንቱ ድካም ነው። በመሆን ውስጥ ያልሆንከው ስለሌለ የሆንከውን ቆጠራ አትገባም። ሁልቆ መሳፍርት የሌለው Infinite possibility አካል ነህና መስፈሪያም አይኖርህም። ሁነትህን ‘ለግል’ ይዘህ የነኝነት አጥር አትሰራም። እኔ እንዲህ ነኝ እያልክ ‘ሌላውን’ ባለመሆን ስፍር አትለካም።

ነኝነት ከአዕምሮ ባርነት ይዶልሃል። አዕምሮ ደግሞ ለነኝነት ረሃቡ ዕድሜ ልኩን እንዳለከለከ ነው። ነኝነቱን ማጣት አይፈልግም። ነኝ የሚለው ከሌለ ታዲያ እርሱ ማነው?። ምን ቀረው?። ምንም። ባዶነቱን የሚያርቀው በነኝነት ተክቶ ነው። ነኝነት ስስቱ ነው። ለቅጽበት ካጣው ቅስሙ ስብር ይላል – ድቅቅ።
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
በአዕምሮው ላይ የሰለጠነ ሰው ነኝነት የለውም። ነኝ የማይለው ያልሆነው ስለሌለ ነው። የኔ የማይለው የእርሱ የማይባል ስለሌለ ነው። ልክ በክብ መስመር ላይ እንደመቆም ነው። ቋሚው በክብነቱ ሁሉ ላይ መቆሙን እንጂ የክበቡን አንድ ጎራ ንብረት ማድረጉን አያስብም። ነጠላ መስመር ላይ የቆመ ግን የኔ/ኛ መንገድ ለማለት የሚቀድመው የለም። እውነቱ ክብ ውስጥ መኖራችን ቢሆንም ኑረት ግን በነጠላ መስመር ሞልታ ተርፋለች።

ነኝነት የልዩነት ምንጭ ነው። የግጭት ምንጭ ነው። የጦርነት ምንጭ ነው። የመናናቅ ምንጭ ነው። የጥላቻ ምንጭ ነው።

ሃብታም ነኝ ስለምትል ድሃ አደጉን ትንቃለህ። ባለወንበር ነኝ ስለምትል ባለጉዳዩን ታጉላላለህ። ምሁር ነኝ ስለምትል ባልተማረው ትሳለቃለህ። ብርቱ ነኝ ስለምትል አቅመቢሱን ትገፋለህ። ኢትዮጵያዊ ነኝ ስለምትል የዓለምን ሕመም ትዘነጋለህ። በየደረስክበት በነኝታህ አንፃር አቁመህ የማታሳንሰው አይኖርህም። ነኝታህ ጽኑ ግንብ ነው። ጸንቶ ያከፋሃል። ጸንቶ ይነጥልሃል።
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
ጉዳይ ኖሮህ አንድ ፈፃሚ ዘንድ ሂድ። የአንተ ቢጤ ነኝ ባይ አለ። ዶ/ር ከሆነ የዶክተርነቱን ጠገግ አክብረህ እንድታወራው ይፈልጋል። የድርጅቱ አንበሳ ሰው ከሆነ በወንበሩ ልኬት ሰቅለህ እንድታናግረው ይሻል። ክቡር፣ ጌታዬ፣ ታላቅ። ወዘተ እያልክ። ዳኛ ዘንድ ቅረብ። ዳኛነቱን መቀበልህን በብዙ መንገድ ይገመግማል። እጅህ እንዴት ነበር?። የቃል አጠቃቀምህስ?። የድምጽህስ ከፍታ?። ‘ክቡር ምናምን’ ብለህ ነበር?። አትሸወድ። ዳኛው ለእውነትህም ሆነ ለፍትህ ግድ የለውም። ለነኝታው እንጂ።

እናም ዶክተርነቱ፣ አለቅነቱ፣ ዳኝነቱ፣ ምሁርነቱ፣ ባለስልጣንነቱ፣ ወዘተርፈነቱ ጋ ቆሞ ከሚያወራህ ሰው ጋር ፈጽሞ አትግባባም። ነኝታው ላይ ካቆረረ ሰው ጋር እንዴት መግባባት ይቻላል?። ‘ወርዶ’ መጫወት ከማይችል ሰው ጋር እንዴት መደራረስ ይቻላል?። እናም እንደ ሰው ተገናኝተህ – እንደ ሰው አውርተህ – እንደ ሰው ተግባብተህ የምትለያይበት ቢሮ ይናፍቅሃል። የነኝነት አጥር አያተያይህምና።
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
የፈለግኸውን ሐይማኖት አስብ። ነኝ ላለው ለዚያ መንገድ ቶኪቻነት የሚሟገት እልፍ ነው። ነኝነቱ አንተን በገነት ሌላውን በሲዖል የሚያኖር ዓይነት ክፋት አለው። ማንም ካንተ መንገድ ውጪ እስከሄደ መድረሻው ገሃነም ነው። የትኛውም የእምነት አስተሳሰብ ለሌላኛው የማሰብ መንገድ እውቅና አይሰጥም። ሁሉም ሐይማኖተኛ አንድ መንገድ ነው የሚያውቀው። በእርሱ እምነት እግዜር በለው አላህ ከዚያ መንገድ ውጭ ላሉት እሳቱ የማይጠፋበትን፣ ትሉ የማያንቀላፋበትን ገሃነመ እሳት አዘጋጅቶላቸዋል። በነኝታው የጠበበ አማኝ ከእኔ ውጭ ለሚላቸው ክፉ ነው። ሐይማኖተኝነት ሲከፋ ለእግዜሩ ጠበቃ የመሆንን ድፍረት ይሰጣል። እናም በእግዜር ስም ሰይፍ የሚመዙ እልፍ ናቸው። ነኝነት እርኩስ ነው።
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
ብሔር ጠቅሰህ – ቀዬ ከልለህ – ጎጥ ጓጉጠህ ስንቴ ነኝነትህን አውጀሃል። ስንቴ ያንተ ነኝነት የጠራ፣ የኮራ፣ የከበረ ነኝነት ነው ብለሃል። ስንቴስ ለነኝነትህ ሌሎች ነኝ ባዮች በጠላትነት ነገር ሰሩ ብለህ አቂመሃል። የብሄር ነኝነት ክፋቱ ለምልዓተ ዓለሙ የማይመጥን ማንነትን በአንዲት መንደር መክተቱ። የዚህ ብሔር ወገን ነኝ ባይነት ትንሽነቱ የፍጥረተ ዓለሙን ወገንተኝነት ማሳጣቱ። የብሔርተኝነት ግፉ የሰው ዘርነትን ማንጠፉ። ስለ ብጣቂ መደብ ቅናት እናት ምድርን ማሳጣቱ።
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
በነኝነት እስር እየማቀቁ ነፃነት የለም። በነኝነት ቅዠት እየዋኙ ሰላም የለም። በነኝነት ታጥሮ ከፍታ የለም። በነኝነት ታፍኖ ፍቅር የለም። ነኝነት ነኝ ከምትለው ባሻገር እንድታይ አይፈቅድልህም። ከነኝነትህ ውጣ – ሁሉን እቀፍ – ሁሉን አካት – ሁሉንም ሁን – ከሁሉነትህ ውስጥ አንድነትህ ይወለዳልና!!
__
ተ – ላ – ቀ – ቅ
__
አንድ ወዳጄ ምን አለኝ። “ከጎጆህ ጣራ ስር ማደርህ ከእኔ ጋር በአንድ ሰማይ ስር መሆንህን አይቀይረውም”። እውነት ነው። እልፍ አዕላፍ ጎጆዎች ቢኖሩንም ዞሮዞሮ ያለነው ከአንድ ሰማይ ስር ነው። ምድሪቱም አንድ ናት። ለየተገኘንበት አውድ ስም መስጠታችን የመለያየት ግንብ እንድንሰራ አይግፋን ነው ነገሩ። የሥጋ ኑረት በጠባብ ደረት ቢወሰንም የመንፈስ ልቀት በደቃቅ አስተሳሰብ መንጠፍ የለበትምና!!

ሲጠቃለል።
~~
“The most common ego identifications have to do with possessions, the work you do, social status and recognition, knowledge and education, physical appearance, special abilities, relationships, person and family history, belief systems, and often nationalistic, racial, religious, and other collective identifications. None of these is you.” ― Eckhart Tolle

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *