ከተመረቅኩኝ አንድ ወር አለፈኝ።(በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ዉሸት) ……የሆነ ልጅ እንደጻፈዉ
እስካሁን ስራ ለምን አልያዝኩም ብዬ አላማርርም። እንኳንስ እኔ መካከለኛ ግሬድ ካላቸዉ ተማሪዎች ተርታ የምመደበዉ ይቅርና ሰቃያችንም ስራ አልያዘም! ይልቁንስ የሚያስጨንቀኝ ሰፈራችን ከእኔ ጋር በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀዉ የአንድ አመት ሲኒየሬ ሙሉቀን እራሱ እስከዛሬ ስራ አለመያዙ ነዉ። በጥዋት ተነስቼ ስራ ፍለጋ ሲቪየን ይዤ ከቤቴ እወጣለሁ። ጆሊ ባር አጠገብ ካለዉ የሥራ ማስታወቂያ ከመሰሎቼ ጋር አልጠፋም።
ድሮ እነ አንዷለም ሲያወሩ እንደሰማሁት ተመርቀዉ ትንሽ አረፍ ካሉ በኋላ በሳምንቱ በስጦታ ከተሳጣቸዉ ሸሚዞች(በአብዛኛዉ “ሰንፉ” የሚባል ነበር) በአንዱ ሽክ ብለዉ ከስር የመመረቂያ ሱፋቸዉን ሱሪ በአዲስ “ዱርሰን ጫማ” አድርገዉ በእናታቸዉ ወይም በአባታቸዉ መስሪያ ቤት ሰዎች የሰራተኛ መረዳጃና ምናምን በሚባል በየቢሮዉ” የእከሊት ልጅ ተመራቂ ነዉ! የምታዋጡትን አዚህ ጋር ጻፉ” እየተባለ በሚዞር ወረቀት ላይ “ኤጭ ማህበራዊ ህይወት አሁንስ ገደለን እኮ!“ እየተባለ ከትንሽ ማማረር ጋር በሚሰጡ ሀያ ብሮች ስብስብ ተዋጥቶ የተገዛዉን የወርቅ ሃብል በአንገታቸዉ ላይ አድርገዉ(ሀብሉን ለማሳየት የሸሚዣቸዉን ሁለት ተከታታይ የደረት ቁልፎች ከፈት አድርገዉ (በዚሁ አጋጣሚ በሚገባ ብርድ ተመተዉ በስሱ እያሳሉ) ዘመድ የሸለማቸዉን እንደ ወርቅ የሚያብረቀረቅዉን” ሲቲዝን” ሰአት ለማሳየት እጅጌያቸዉን ሰብሰብ አድርገዉ ከጓደኞቻቸዉ ጋር በቤት እና በሱቅ ግፋም ሲል በህዝብ ስልክ ተጠራርተዉ አራት ኪሎ ለስራ ፍለጋ ብቅ ሲሉ አቤት የነበረዉ ማእረግ!!
የዛሬን አያድርገዉና የአቶ አቤሰሎም ይህደጎ ንብረት የሆነዉ ጆሊ ባር ምን የመሰለ ቡና(ዛሬ ተጠትቶ ሳምንት ስራ ለመፈለግ የሚያበረታ ወፍራም ቡና በሁለት ብር ) ይታዘዝና “ጋዜጣ! እሰቲ ስራ ያለበትን ፔጅ ወዲህ በል“ ይባላል ።ከዛማ ከጓደኞቻቸዉ ጋር በጋዜጣ ተከልለዉ
“ጆ እዚህ ጋር የወጣዉን ስራ አይተኸዋል?“
“አላየሁትም ነብሴ” ያኛው ይመልሳል….(“ጆ “እና “ነብሴ” በወቅቱ የነበሩ የአራዳ ቃላት ናቸዉ)“
” ጆ” ም በጋዜጣዉ ተከልሎ “ አረ እዚህ ጋርም አሪፍ ስራ ወጥቷል ግን እሩቅ ሀገር በዛ ላይ ገጠር ስለሆነ አልሄድም!“ ይላል።
ነብሴ፡….“ የት ነዉ ባክህ?“
ጆ……“ናዝሬት“
ነብሴ…….“አዉዉዉ! ናዝሬት በጣም ሩቅ ነዉ ጆ!“
ጆ……“ባክህ ነብሴ ይሄኛዉ ግን ደሞዙ አሪፍ ነዉ! የሶስተኛ አመት የኮሌጅ ተማሪ ነዉ የሚለዉ(ት/ት ያልጨረሰ የሚቀጠርበት ደግ ዘመን!)…… ግን ደ/ዘይት ድረስ ለስራ መሄድ አይከብድም?!“ ይላል ሌላኛዉ
“አረ ጆ ጨከን በል ሀገራችንን ተዘዋዉረን በዱር በገደሉ እየገባን እናገልግላት እንጂ! ደ/ዘይትማ ጨከን ብለን መሄድ አለብን!“ ይመልሳል ሌላኛዉ ጓደኛዉን ወደ “አስፈሪዉ“ የደ/ዘይት ጉዞ ለማበረታት ትከሻዉን እየጠበጠበ።
“እሺ ነብሴ ጨክናለሁ ለሀገሬ ስል የማልሆነው የለም!“
ይባል ነበር።
ወይ የእነ አንዱአለም ግፍ!
“ እዚች ቀብሪ ድሃር ስራ ወጥታ ነበር ፡ግን የሚጠይቁት የስራ ልምድ ብዙ ሆነብኝ ባይሆን ከቤተሰብ እንዳልርቅ (የደ/ብርሃን ልጅ ነዉ ተናጋሪዉ) ሽሬ እንዳስላሤ ያለዉን ልሞክረዉ መሰለኝ!? ምንላድርግ እንግዲህ የታች አርማጭሆ ስራ እንኳን ሲቪዬን ሳለስገባ አልፎኛል!ሀሙስ ለት ማስገባት ስችል ….ወይኔ ለዛ ለማይገኝ የጋምቤላ ስረ ስጓጓ እኮ ነዉ ሺት! ….“ ይሄ አንግዲህ ትላንት ከጓደኛዬ ጋር በስልክ ያወራነዉ ነዉ።እነ አንዱአለም ደ/ዘይት ሄደዉ አንድ አመት ሰርተዉ ነዉ “በዱር በገደሉ ተንከራተን የአገለገልናት ሀገራችንን ኢሃዲግ ቁልቁል ወሰዳት እያሉ ” ዛሬ በየፌስቡኩ የሚለፋደዱት፡(መንግስት ድሮ ቀረ !ለእንደዚህ አይነቱ ጨምላቃ ወይኔ!)
በየቀኑ እየመጣሁ ስራ አፈላልጋለሁ። ከመሰሎቼ ጋር እየተጋፋሁ እመለከታለሁ(ደግነቱ እ/ር ግሬዴን ቢያሳጥረዉም ቁመቴን ስላረዘመዉ በቀላሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዉን እቃኛለሁ)። ብቻ በኛ ፊልድ ወፍ የለም!።ሁሉም ስራ አካዉንቲንግ ነዉ። በኛ ፊልድ ቀርቶ የኛን ፊልድ በሚመስል ሌላ ፊልድ የዜሮ አመት የስራ ልምድ የሚል አንድ ማስታወቂያ የለም ።
“ትመጫለሽ ብየ ……..መንገዱን ባየዉ
የሚመላለሰዉ…….. ሌላ ሌላ ሰዉ ነው (አካዉንቲንግ ነው) አሉ ጋሽ ይርጋ ዱባለ። ለዲፓርትመንቴ የመረጥኩላት ዘፈን ነው።
መንግስት የምርቃታችን ቀን የላካቸዉ ያልተማሩ የክብር እንግዳ(በእርግጥ የፒኤችዲ የሚመስል ቢጫ ገዋን ገርግደዋል ባደረጉት ንግግር
“ተመራቂዉ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ እንዳይሆን!“ በማለት ስራ እንደሌለ አርድተዉናል። በመሃላችን የተሰገሰጉ የተማሪ ካድሬዎች ሲያጨበጭቡ እኔም ሳላዉቅ ለዚሁ መርዶ አጨብጭቤአለሁ። አስመራቂዉም ጭብጨባዉን ሲያዩ በተፈጠረባቸዉ መነቃቃት መርዶዉን በላይ በላዩ ያዘንቡት ጀመር ። …ስናጨበጭባለቸዉ እኚህማ ብዙ መከራ መቀበል የሚችሉ ናቸዉ ብለዉ ነው መሰል
“ ከመንግስት ማናቸዉም አይነት ድጋፍ እንዳትጠብቁ“ አሉን።አጨበጨብን
“አንዲት ነገር!“ አሉ አሁንም አጨበጨብን
“ትምህርት የስራ ማግኛ ሳይሆን ስራ ለመፍጠር የሚሆን እርሾ ነዉ!“ አሉ(ማዘር ልጄ በት/ት እንጀራ አገኘ ስትል ገና እዚህ ት/ት እርሾ ነዉ መባሉን ብትሰማ ትገለኝ ነበረ) እኛም አጨበጭብን።
ሰዉየዉ ስናጨበጭብ ይናደዳሉ መሰለኝ የበለጠ የሚያስከፋን ነገር ይናገራሉ። “ለምን ስራ የለም ሲባል አልከፋቸዉም!?” ብለዉ እልህ የተጋቡም ይመስላል። መጀመሪያዉኑ ወኔያችንን ሰልበዉ ሲያበቁ በየት በኩል በየትኛዉ ወኔያችን ተቃዉሞ እንድናሰማ ይጠብቃሉ!?
“እናም በአጠቃላይ ምንም ምንም ነገር የለም !ወላ ሃንቲ ነገር!እራሳችሁ እዛዉ እራሳችሁን ቻሉ!“ አሉ እጃቸዉን “ምንም የለም” የሚለዉን ለማሳየት ዱቄት እንደነካ ሰዉ እያራገፉ ።ቀውጢ ጭብጨባ አጨበጨብን።
“እሺ ያለባችሁን ኮስት ሼር ቶሎ ክፈሉ!“አሉ በቁጣ… አጨበጨብን
“ደደቦች!“ አሉ………(አላሉም ግን ሳስበዉ በዚህኛዉ ዙር ጭብጨባ ማለት ነበረባቸዉ)
እና እሺ ስራ ከየት ላምጣ?!
እኔ የተማርኩት “ፖለቲካ ሳይንስ” ነዉ። አሁን በተማርኩት የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት በግሌ ምን አይነት ስራ ነዉ መፍጠር የምችለዉ? መንግስት በግላችሁ ስራ ፍጠሩ የሚለን ከተማርነዉ ት/ት ጋር በተያያዘ ካልሆነ ለምን ታዲያ አራት አመት አባከነብን?
በእርሻ ት/ት የተመረቁ ጓደኞቼ ተደራጅተዉ ባለፈዉ የበሬ ማደለቢያ ለመክፈት ቀበሌ ሄደዉ ብድር ሲጠይቁ ያዉ ኢሃዲግን እንደሚመርጡ ምለዉ ተገዝተዉ ብድር ተሰጣቸዉ።(አሁን የሚቅሙት ጫት ጫት እንዳይመስላችሁ!)
ይሄንን አይቼ እኔም አራት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራቂ የክላሶቼን ልጆች ይዤ ቀበሌ ሄድኩኝና “በተማርነዉ ት/ት ከመንግስት ስራ ሳንጠብቅ በግላችን ስራ ፈጥረናል ፡በዚህም መሰረት የተቃዋሚ ፓርቲ ለማቋቋም የሚረዳን አነስተኛ ብድር…. ያዉ ለማይክራፎን መግዣ፡ለቢሮ መከራያ ፡ኮከብ የሌለበት ባንዲራ መግዣ ፡ለኮምፒውተር መግዣ እና ሰላማዊ ሰልፍ ስንጠራ ጭንቅላታችን ላይ ለምናደርገዉ ሄልሜት እና ዘወትር ከሰልፍ በኋላ ለምንጠቀማቸዉ ፋሻ፡ አልኮል እና ሙሉ የኦፕራሲዮን እቃዎች መግዣ እና አንዳንዴ ዞር ዞር እያልን የምንነቀሰቀስበት አይሱዙ መግዣ ብር “እንዲሰጡን ጠየቅናቸዉ። የሰጡንን መልስ ለዛ ወሬኛ አንዱአለም ነግሬዋለሁ አሁን እንግዳ ስላለ(ኦባማ) እንግዳ ሲሄድ እነግራችኋለዉ ብሏል። ጠብቁት።
ባለፈዉ አንድ ስራ ወጥቶ ነበር በሲቪል ኢንጂነሪንግ ወይም በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ ይላል። ሲቪዬን አስገባሁ።
በድፍረቴ ተናደዉ ነዉ መሰለኝ አራት ሰዉ “ሾርት ሊስት” ዉሥጥ አስገቡኝና ለኢንተርቪው ጠሩኝ።
በኢንተርቪዉ ቀን ሽክ ብዬ ሄድኩኝ።
“ለመሆኑ ማንበብ ትችላለህ?“ የመጀመሪያዉ ጥያቄ ነበር
“እንዴት አልችልም?! ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ የለም እንዴ?!“ አልኩኝ በጥያቄዉ ተገርሜ
ጠያቂዎቹ እርስበርስ እየተያዩ ተሳሳቁ(የተመረቀ ማንበብ እንደሚችል “ፎርግራንትድ” መወሰድ የሚቻልበት ዘመን አልፏል! እዉነታቸዉን ነዉ!)
“”በኢንጂነሪንግ የት/ት መስክ” እየተባለ ለምንድነዉ የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪ ይዘህ የምታመለክተዉ?!“ አሉኝ
“ያዉ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ይል የለ“ አልኩኝ አንገቴን ደፍቼና እና እጄን እያፍተለተልኩኝ(ሳሳዝን!“)
“ኢንጀነሪንግና ፖለቲካ ምንአባክ አገናኛቸዉ!?“ አሉኝ ስድብ አዘል በሆነ ቁጣ። ከፈለጉ ስራዉ ይቀራል እንጂ በዛ አሁንስ!
“እንዴት አይገናኙም?!እኛ ሀገር ያልተገናኙ የት ይገናኙ? ኢንጂነር ይልቃል ፡ኢንጂነር ሃይሉ ሻዉል ፡ኢንጂነር ግዛቸዉ ፡ኢንጂነር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ወዘተ አይደሉ እንዴ ፖለቲካዉን የሚዘዉሩት!? ፖለቲካ እና ኢንጂነሪንግ ያልተዛመዱ ማን ይዛመ….“
“ዉጣ!“ አምባረቁብኝ ።አላስጨረሱኝም!
ቸግሮኝ ነዉ እንጂ እነሱን ለማናደድ ነዉ እንዴ ሲቪ ያስገባሁት!? ለምን ይቆጡኛል!? እኒህ ሙሰኛ ሼባዎች!
እሺ በግሌ ምን ልስራ? አራጣ ተበድሬ የተቃዋሚ ፓርቲ እንዳላቋቁም እኛ ሀገር የተቃዋሚ ፓርቲ ሽቀላዉ በምርጫ ሰሞን ብቻ ነዉ። ምርጫ ደግሞ ገና አምስት አመት ይቀረዋል። አራጣ አበዳሪዉ አያኖረኝም።
የትጥቅ ትግል እንዳልጀምር ድሮ በፍሬሽማን ድሮፕአዉቶች ይመራ የነበረዉ የትጥቅ ትግል በአቅሙ ዛሬ በፕሮፈሰር ሆነ የሚመራዉ ምን ይሻላል ወገን?!
በል አታልቅስባቸዉ። ዞር በል!። አንዱአለም እራሴዉ መጥቻለሁ።ጀለሶቼ ይሄ ስራ ፈላጊ በቅዳሜ ምድር ጨቀጨቃችሁ አይደል።እኔ ድራፍት ልጠጣ ሄጄ እስከዛዉ አንዴ ላፕቶፕህን ልጠቀምበት ብሎኝ እኮ ነዉ።በሉ አርፋችሁ ትላንት የጻፍኩትን አንብቡ።
መልካም ቅዳሜ
ይመቻችሁ