Tidarfelagi.com

ተቃርኖ

አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጆርጅ ኦርዌል “1984” በተባለ ልብወለዱ ውስጥ የጠቀሰውን፣ double think( ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦችን በተመሳሳይ ሰዐት እውነት ናቸው ብሎ መቀበል) የሚከተል ይመስለኛል።

ተቃርኖ #1 ወጣት በድሉ እጩ ዘፋኝ ነው (እጩ ካድሬ ብቻ ነው ያለው፣ ያለው ማነው? ) በቴሌቭዥን ከሚታዮ፣ በባላገሩ አይድል፣ በኮካ ሾው ወይም በአንዱ በሌላው በዘፈን ይወዳደራል። በአንዱ ዙር ጋዜጠኛው ይጠይቀዋል።

“አሸንፋለሁ ብለህ ታስባለህ? ”
“እሱን እግዜር ያውቃል። ፈጣሪ ከረዳኝ አሸንፋለሁ ብዬ አስባለሁ ” ይላል በድሉ።
“ወደፊት ምን ታስባለህ? ”
” ወደፊት ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ ስራ የመስራት ሃሳብ አለኝ ” (ዘፈን ከእግዚአብሔር ጋር??)

መፅሐፉ፣ “ዘፋኝ መንግስተ ሰማያትን አይወርስም” ይላል። በድሉ ደግሞ እግዜር፣ ለዘፈኑ እንዲረዳው ይጠብቃል።

ተቃርኖ #2 ቄስ ኦላና የሰፈሬ ሰው ናቸው። ከኛ ቤት ሁለት ቤቶች ዘሎ አንድ ጠንቋይ አለ። ቄስ ኦላና፣ ጠዋት ቤተክርስትያን፣ ከሰዐት ጠንቋዩ ቤት ያገለግላሉ። እኚሁ ቄስ እኛ ቤትም ይመጣሉ። አልወዳቸውም።

አንድ ቀን እቤታችን ቁጭ ብለው በንግግራቸው መሃል ይህን አወሩ፣

” … እውነቴን ነው። እግዚሃር የለም ሲባል ነው የሚደርሰው። የዘገየ ይመስለናል እንጂ ሲሰጥ እንዳያልቅ አድርጎ ነው። አሁን ይሄ ተፈሪ (ጠንቋዩ) በፊት እንዴት ያለ ደሃ ነበር። እዛ ቀበሌ አስራ ሶስት እያሉ፣ እህል እንኳን ከጎረቤት የሚበደሩበት ጊዜ ነበር። ይሄው ዛሬ እግዜር ከዛ ሁሉ ችግር ውስጥ አቅጥቶ…”
ተነስቼ ወጣሁ።

ተቃርኖ #3 ፓስተር ዳንኤል በኤልሻዳይጣቢያ ከሚታዩ ጯሂ ሰባኪዎች አንዱ ነው። በአንድ የፈውስ ፕሮግራሙ ሁለት ባልና ሚስት አስነስቶ፣
ወደ አሜሪካ ስትሄድ ይታየኛል ይለዋል። ታዳሚው በልክታ ይጮሃል። ከዚህ በፊት ሞክረህ አልተሳካልህም፣ በቅርቡ ግን ኢንቪቴሽን ይመጣልሃል ይለዋል። እልልታ።

ትንሽ ቆይቶ በዛው መድረክ እንዲህ ይላል፣
“ወንድሞቼና እህቶቼ የኛ ህይወት በሰማይ ያለው ነው። ምድራዊ ብልጭልጭ፣ አለማዊ ደስታ፣ ህንፃው፣ መኪናው ሁሉ ከሰማዩ አይወዳደርም። እየሱስ ነው የኛ ህይወት… ”

አሁን አሜንታ እና እልልታ ከታዳሚው።

“ለአሜሪካም እልል፣
ለሰማዩም እልል
ገነጣጥለው ጣሉት፣ የተቃርኖን ክልል ” ልበል? (ተውኩት እሺ፣ አልልም)

አንድ ነገር፣ በተመሳሳይ ሰዐት ሙሉ ነጭ፣ ሙሉ ጥቁር ነው። ነጭ አይደለም። ጥቁር አይደለም። ነጭና ጥቁርም አይደለም። ቅይጥ አይደለም። ሙሉ ነጭ፣ ሙሉ ጥቁር ነው።

ጳጳሱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗንም፣ አዳም የመጀመሪያው ሰው መሆኑንም በእኩል ሰዓት ያምናሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *