አዲሳባ ጥግ ነው የምኖረው።
ሰፈሬ የቅንጡ ቪላዎች፣ የሞጃ ሪል ስቴት አፓርትማዎች፣ የድሃ ዛኒጋባ ጎጆዎች እና የኮንዶሚንየም ቤቶች ድምር ናት። የግል መኪና ብንነዳም፣ በባጃጅ ተሳፍረን ብንመጣም፣ በእግራችን ብንጓዝም የምንገባበት ቤት እንጂ መንገዳችን አንድ ነው። ከዚህም ከዚያም መጥተን ተደምረን ነው የምንኖረው።
ባጃጆች የሰፈራችን ዋነኛ የመጓጓዣ መንገዶች ሲሆኑ አልፎ አልፎ የጋሪ ፈረሶችም ይታያሉ።
ዛሬ ከጠዋቱ 12፡30 ሲል ለታላቁ ሰልፍ ለመሰናዳት ከአልጋዬ ተነሳሁ። ከዛሬ በፊት በእድሜዬ ያየሁት ታላቅ የህዝብ ሰልፍ የ1997 ብቻ ነው። ጉጉቴ ጨምሮ የሰራሁትን ቁርስ እንኳን ለመመገብ ስለከለከለኝ ምግቤን ከሌላ ነገሬ ጋር ደምሬ ትንሽዬዋ ቦርሳ ውስጥ ጨመሬ ከቤቴ ወጣሁ።
ከግቢያችን ወጥቼ የኮብልስቶኑን መንገድ ከመያዜ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ባንዲራችንን የተሸለመ ጎስቋላ የጋሪ ፈረስ አየሁና ፈገግ አልኩ። ከፍ እንዳልኩ በስተግራዬ በቡድን ሆነው ሚኒባስ ታክሲ ላይ ብዙ ምስሎች እና መፈክሮችን የያዙ ባነሮችን የሚሰቅሉ የሰፈሬን ጎረምሶች አስተዋልኩ። አብዛኞቹ ሰው ቤት ሲለቅ ወይ ወደእኛ ሰፈር ለመኖር እቃ ይዞ ሲመጣ እቃ በማውረድና ከማውጣት ውጪ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚውን እያዩ ብጉራቸውን ሲያፈርጡ የሚውሉ፣ ፀጉራቸውን ሲፈትሉ የሚመሽላቸው ወጣቶች ናቸው። ተስፋ ስላገኙ ደስ አለኝ።
የዶክተር አብይ፣ አቶ ለማ እና አቶ ገዱ ምስል ያለበትን ባነር በፍፁም ደስታ ፊታቸው እያበራ መኪናው ላይ ሲሰቅሉ እጆቼን አውለብልቤ ሰላም አልኳቸውና አለፍኩ።
አሁን ዋናው አስፋልት ላይ ወጥቻለሁ። ሁለት ሰአት ሳይሞላ ባጃጁ፣ እግረኛው፣ የቤት መኪናው፣ አውቶብሱ ይተራመሳል። አብዛኛው እግረኛ ከሰሞኑ በመአት አይነት ምርጫ ሲቸበቸቡ የነበሩትን የዶክተር አብይ ምስል እና የተለያዩ ፅሁፎች ያሉባቸውን ካናቴራዎች ለብሷል።
ካንተ ጋር ነን/ ከጎንህ ነን/ ተደምረናል/ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን/ብሄር አትጠይቁኝ….የሚሉ ካናቴራዎችን ከአስፋልቱ በቀኝም በግራም ከየጉድባው፣ ከየሰፈሩ፣ ከየጉራንጉሩ የሚወጡ ወጠምሻ ወጣቶች፣ ቆነጃጅት እና ወጣት ሴቶች፣ ሽበት የተጎናፀፉ አባቶች፣ ነጠላ ጣል ያደረጉ እናቶች፣በድጋፍ የሚሄዱ አረጋውያን ለብሰው አየሁ።
ከሰፈሬ ርቄ በሄድኩ ቁጥር የማየው ሰው ሁሉ፣ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የገዛ ገንዘቡን ሆጭ አድርጎ በጋለ የሃገር ፍቅር ስሜት የገዛውን ካናቴራ በኩራት ለብሶ ውር ውር ይላል። ለመስቀል አደባባይ ጉዞ ይጣደፋል። አጠገቡ ያለውን አቅፎ ይጓዛል። ይስቃል፣ ይጫወታል።
ሶስት ተኩል ገደማ ላይ ይመስለኛል መስቀል አደባባይ ደረስኩ። ጥቅጥቅ ባለው የህዝብ ጫካ ውስጥ አልፌ በአደባባዩ እምብርት ላይ ከመቆሜ ህዝቡ በየ10 ሰከንዱ ሲያጨበጭብ እና ሲያፏጭ ንግግር እየተደረገ እንደሆነ ገባኝ። ያለሁበት ቦታ የድምፅ ማጉያው ንግግሩን አጥርቶ ስለማያሰማኝ ከነበርኩበት ወደ ኋላ መለስ ስል ዶክተር አብይ ንግግር ሲያደርጉ ተመለከትኩ። በአይኔ አይደለም። ከጀርባዬ የአዲስ አበባ ሙዚየም አጥር ጋር በተሰቀለው ትልቅ ማሳያ።
ግራ ገባኝ።
ሰልፍ ይጀመራል የተባለው አራት ሰአት…ከምኔው ደርሰው ከምኔው ንግግር ጀመሩ?
በንግግራቸው አሁንም አሁንም በደስታ በሚጮኸው ሰው ስለቀናሁ ድምጻቸውና ቃላቸው እንዲሰማኝ ወደ ሚጮኹት ሰዎች ተጠጋሁ። አጥጋቢ ባይሆንም እዚህ ጋር ይሰማል።
እኔም እንደሌላው ሰው በስሜት የሚንጠኝ ነገር በተናገሩ ቁጥር እየጮህኩ፣ እያፏጨሁና እያጨበጨብኩ ጥቂት እንደቆየሁ ንግግሩ አለቀ።
አብረውኝ ከነበሩት ሰዎች ጋር ፎቶ እየተነሳን ግን ድ…ው….የሚል ጠንካራ ድምጽ ሰማን።
‹‹ምንድነው…ምንድነው….›› አለ አጠገቤ የነበረ ሰው ሁሉ።
ረብሻ አልነበረም። ድንጋጤ አልነበረም። ፍርሃት የሚባል ነገር አልነበረም።
‹‹ምንድነው?›› ብዬ ጠየቅኩት አንዱን።
‹‹ማይክራፎኑ መድረክ ላይ ወድቆ ነው…›› ብሎኝ አለፈ።
‹‹እህ…እሺ…›› ብዬ ከወዳጆቼ ጋር መጨዋወት ስጀምር አንዱ መጥቶ ‹‹መድፍ ነው አትፍሩ…መድፍ ተተኩሶ ነው እንዳትፈሩ…›› እያለ ሲያልፍ ተመለከትኩ።
አሁንም ሁላችንም በፍፁም አለመጠራጠር ‹፣እ…እሺ…›› ብለን ጨዋታችንን ስንቀጥል ከመድረክ የሚመጣ አንድ ድምፅ ‹‹አይዟችሁ ተረጋጉ!›› ሲል ደረጃዎቹ ላይ የተቀመጠው ህዝብ በአንድ ጊዜ ‹‹ አንፈራም! አንፈራም!›› ማለት ጀመረ።
የህዝቡ አንፈራም ድምፅ ሲያበቃ ግን ከመድረክ ድምፅ ጠፋ። ዘፈን የለ። ንግግር የለ። እንዲህ ሁኑ የለ። አልቋል ሂዱ የለ….ዝምታው ግራ ያጋባ፣ ትንሽም ያናድድ ነበር። በጭፈራና በጩኸት ስሜቱን ሊገልፅ፣ ታፍኖ ከርሞ እንዳሻው ሊናገር የመጣው ሰው ግራ ተጋብቶ፣ ጥቂትም ተከፍቶ ቁጭ ብሏል።
ይሄን ጊዜ ወደ ኤግዚቢሽን ማእከል በር ጋር ከተከማቸው ህዝብ ከፍተኛ ጭብጨባ ስሰማ ዞርኩ።
በሕይወቴ አየዋለሁ ብዬ ያላሰብኩት ትእይንት ነበር።
የፌዴራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ በርካታ ፖሊሶች የኤግዚቢሺን ማእከል በር የሚወስደውን ደረጃ ተከታትለው በሰልፍ ይወጣሉ። በቀኝ እና ግራ ያለው ህዝብ በከፍተኛ ስሜት ያጨበጭብላቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ጥቂት እንደቆየን በፌስቡክ ከማውቃቸው ልጆች ጋር ተገናኝቼ ‹‹ከዚህ የሚደምቅ መስሎኝ ነበር። ምንድነው ዝምታው…ለምን ዘፈን እንኳን አይከፍቱም አቦ…››ምናምን እያልኩ ስዘባርቅ ትልቁ መድረክ ላይ ለእኛ በማይሰማን ሙዚቃ እንደጉድ የሚጨፍሩት ወጣቶች ቀልባችንን ሳቡትና እነሱን ማየት ጀመርን።
ጭፈራው በህብረት እንደቀጠለ መድረኩን በሚገርም ፍጥነት ያለ መሰላል ወጥተውና ተፈናጥጠው ተንጠልጥለው የነበሩትን ባለኮከብ ባንዲራዎች የሚወርዱ ልጆች አየን። በምትኩ ኮከብ አልባውን የኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልልን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ሰዉ በከፍተኛ ድጋፍ ሲጮህላቸው ሰማን። ጥቂት ቆይቶ ሌሎች ባንዲራዎችን ይዘው የወጡ ልጆችም በተመሳሳይ ሁኔታ በህዝቡ ድጋፍ ባንዲራቸውን ሲያውለበልቡ አየን።
እኛ በቆምንበት ስፍራ ያለው ድባብ ስለተቀዛቀዘ ‹‹በቃ እንሂድ›› ተባብለን ተሰነባበትን እና እኔ የፍላሚንጎ ቦሌን መንገድ ይዤ ለመሄድ የእግር ጉዞዬን በሚገርም ስርአት ያለምንም ግፍያና ትርምስ ከሚተመው ህዝብ ተቀላቀልኩ።
ፍላሚንጎ ጋር ስደርስ ልክ እንደጥምቀት በአል ክብ ሰርተው ዘፈኑን እያስነኩ አካባቢውን በአንድ እግሩ ያቆሙ ወጣቶችን ሳገኝ ተቀላቀልኳቸው። በኮከብ አልባ ባንዲራ ያጌጠው ቡድን በህብረት እንዲህ እያለ ይዘምራል።
ጉዞ ጀመረ…
ጉዞ ጀመረ
እየደመረ…
ይሄ ነው ሰንደቁ ይሄ ነው ሰንደቁ
ጠባሳው ይነሳ ይሄ ነው ሰንደቁ..
ምን አለ አብይ ምናለ…
አገሬን ለጅብ- አገሬን ለጅብ
አልሰጥም አለ….
ምናለ አብይ ምናለ…
እየተጣራ (ሆ!)
እየተጣራ (ሆ!)
ይገባል አለ….!
ጅቦ….አዉ አዉ አዉ….!
እንሂድ እንዲህ በጫካ
አያ ጅቦ ሳይመጣ
አያ ጅቦ አለህ?
….የለም!
በመስቀል አደባባዩ ፀጥታ የተከፋው ልቤ ምሱን አገኘ።
በኦሮሚኛ ከሚጨፍሩ ልጆች ጋር ተያይዤ በወለጋ ዘዬ ተወዘወዝኩ። ጎንደር ጎንደር ከሚሉ ልጆች ጋር ዘለልኩ። በወላይታ ጭፈራ አስፋልቱን ካደመቁ ወጣቶች ጋር ተደመርኩ።
ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም እያሉ በስሜት ከሚዘምሩ ልጆች ጋር ከእንባዬ እየታገልኩ ዘመርኩ።
ሰንደቁ፣ ስሜቱ፣ ህብረቱ፣ ውበቱ፣ በደስታ ያስለቅስ ነበር።
እግሬ የቻለውን ያህል ተከተልኳቸውና የማላውቃቸውን ሰዎች አቅፌ ስሜ ተሰናበቼያቸው ተለየኋቸው።
አስራ አምስት ከማይሞላ ደቂቃ በኋላ የፌስቡክ ገጼን ስከፍት ስለቦምብ የሚያወሩ ብዙ ፅሁፎችን አይቼ ፍፁም ግራ ተጋባሁ።
ከመስቀል አደባባይ አይደለም የመጣሁት ብዬ ራሴን ጠረጠርኩ።
ሬዲዮኔን ከፈትኩ። ሸገር ላይ ጠቅላይ ሚንስትሬ ያወራሉ።
ስለደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ይገልፃሉ።
ሁሉ ነገር ተማታብኝ።
እኛ ሙዚቃ የለም እያልን ስንነጨነጭ ህዝቤ እየሞተ፣ ወገኔ እየቆሰለ እየደማ ነበረ?
በደሰታ እምባ የደመደምኩት ሰልፍ እመሃሉ ቆሜ በቦምብ መመታቱን፣ ተመትቶም ሰላም-ፍቅር እና ኢትዮጵያን ብለው እንደኔው ከቤታቸው ካናቴራቸውን ለብሰው የወጡ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ እንደወጡ ማስቀረቱን፣ ብዙዎቹን ማቁሰሉን ስሰማ ሁሉ ነገር ተማታብኝ።