ይሄ ሁሉ ለሶስት ጥይት ነው ??
የዛን ሰሞን አሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጲያ ኤምባሲ በተነሳ ተቃውሞ የኤምባሲው ጠባቂ ሽጉጥ ወደሰማይ ተኩሶ በ48 ሰዓት ከአሜሪካ እንዲባረር በተወሰነበት ሰሞን ጋሽ አዳሙ የሰፈራችን ታዋቂ ሰካራም ….ማታ አራት ሰዓት ላይ እየዘፈነ ብቻውን እያወራ እየተሳደበና እያመሰገነ ሲመጣ ሁሉም ጎረቤት ‹‹መጣ መጣ ›› ብሎ ቴሌቪዥኑን ሬዲዮውን ቀንሶ በየቤቱ ጆሮውን ያቆማል …..ጋሽ አዳሙን ለመስማት ……
‹‹ እያንዳንድሽ ለሽሽሽ ብለሽ ተኝተሻል …. እ?………..ሃሃሃሃሃሃ ጀግና ህዝብ ጀግና ጎረቤት …..ድፍን ዋሽንግቶን ሶስት ጥይት ወደሰማይ ተተኮሰ ብሎ እንቅልፍ አጥቷል እናተ ተኩስ ላይ ለሽሽሽሽ ….. ለነገሩ ደደብ ፖለቲካ ተኩስ ማስቆም ሳይሆን ህዝቡ ተኩሱ እንዳይሰማው ማደንቆርን ነው የሚመርጠው ….ጥይቱ ጎረቤቱ ላይ ሲያርፍ አይሰማም ደንቁሯላ ተራው ደርሶ ሲቀምሰው ነው እየተተኮሰ መሆኑ የሚገባው ……ለሽሽሽ !
ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ …. መንግስት ጥበብ ይወዳል ….ኪነጥበብ ለኪነ መጥበብ ….አርቲስቱን ይሰበስብና ከበሮ ደልቅ ይለዋል ፀጉሩን አጎፍሮ ማሲንቆውን እያንጠለጠ አፉን ይከፍታል ….ሴቶቹን አሰልፎ ወባ እንደያዘው በሽተኛ እያንቀጠቀጠ ….ህዝቡ ከተኩሱ በላይ የከበሮው ድለቃና የሴቱ መቀመጫ ስለሚያደነቁረውና ስለሚጋርደው አያይም አይሰማም ….አርቲስት ማለት ህዝቡ ተኩሱን እንዳይሰማ የሚያደናቁር ቁራ ማለት ሆነ እንግዲህ ይሁና …. ››
ጋሽ አዳሙ ሁሉም የሰፈሩ ሰው የሚያውቀውን የድሮ ፍቅረኛውን ስም ያነሳል ሊሻን ነው ስሟ አሜሪካ ሂዳ በዛው ቀልጣ ቀረች ….ሁሌም ሞቅ ሲለው ስሟን ያነሳታል …አሜሪካ ከሄደች በኋላ ሊሊ ተብላለች ….
ሊሻንየ …..ዜናውን የሰማሁ ጊዜ ምነው ምላሴን በቆረጠው አልኩ ! ያኔ አግብተሸ ካልወሰድሽኝ በረኪና ጠጥቸ ድፍት እልልሻለሁ ማለቴ ታወሰኝና ‹‹አይ አለማወቄ ›› አልኩ ! አላደረኩትም እንጅ እኔ አዳሙ እንደፎከርኩት ያኔ ጨክኘ ለፍቅር በረኪና በመጠጣት ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ነበርኩ …..ከበረኪና እስከዘፈን እኛ እንፈጥራለን የህዝብ ዘፈን ብለው ይከብሩበታል የህዝብ በረኪና ብለው ፊልም ይሰሩበታል ሃሃ ! ግዴለም ውሰዱ እንኳን የቆነጠረ የፈጠረስ የት ሊደርስ?
እና ሊሻንየ …. እግርሽን እየሳምኩ አፈር ላይ እየተንፈራፈርኩ ‹‹ እባክሽ የኔ እናት ውሰጅኝ እግሬን አውጭኝ ከሰው እኩል ልሁን ካልወሰድሽኝ ወደሰማይ ሳይሆን እንደአጤ ቴውድሮስ ሽጉጤን ጠጥቸ እሞትልሻለሁ ›› ያልኩሽን እያሰብኩ ‹‹ሰይጣን እንዴት ነበር ሊያሳስተኝ የነበረው ›› ብየ ተገረምኩ ! ቢሆንም እግዚሃር ጣልቃ ገብቶ ስላዳነኝ ትላንት ጧፌን ይዠ እንጦጦ ማሪያም ሄጀ ‹‹ያኔ ሊሻን ከወሰደችኝ አገባለሁ›› ያልኩትን ስእለት ስላልወሰድሽኝ አገባሁ ! በተረፈው ጠጣሁበት !! በየውስጣችን የብሶት ታቦት አለ ….እንዲህ የስካር ስእለት የምናገባለት ሃሃሃ !
የጥንቷ ሊሻን የዛሬዋ ሊሊ …..እኔኮ አሜሪካ ውሰጅኝ ብየ እንደዛ አገር ይያዝ ያልኩት የዴሞክራሲ አገር ናት ብለው ሰብከውኝ ነበር ….አይ ዴሞክራሲ እቴ ….ሂሂ ሰው ያውም ሽጉጥ ወደሰማይ ተኮሰ ብላ ከአገር የምታባርር አገር እስቲ አሁን ማን ይሙት ዲሞክራሲን ከነመፈጠሩ ታውቀዋለች? ….እሽ ወደሰማይ ካልተኮስን ወዴት እንኩስ ….እንዲህ የሰለጠነ እና የመጠቀ አገር ቢያንስ ለሲጋራ አጫሾች ‹‹የማጨሻ ክልል›› ብሎ በየስራ ቦታው በየሆቴሉ እንሚከልለው …..ለተኳሾች ‹‹የመተኮሻ ክልል ›› ብሎ ከለል ቢያደርግና አብሿችን ሲነሳ እዛች ገባ ብለን ብንተኩስ ምናለበት … ኤዲያ ወሬ ብቻ ናት ለካ አሜሪካ ! እስካሁን ቻይና ብትሆን ጥይቱን ከሷ እንግዛው እንጅ ለኢላማ የሚሆን አንድ ዜጋ ፊታችን አቁማ ‹‹አይዟችሁ ወዳጆቸ ተኩሱ ኤምባሲያችሁ ለተኩስ ከጠበበ እኛ ቤተ መንግስት ኑና ተኩሱ ›› ትለን ነበር … ቻይና እርዳታዋ ሁሉ ‹‹ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ ›› የለበትማ !ሃሃሃ
በእውነት ይሄን ስሰማ እዚህ መሃል አራት ኪሎ ሰው እያየኝ ተንበርክኬ ‹‹ አገሬ ማሪኝ ›› ብየ ጮህኩ ….‹‹አገሬ እንኳን ሽጉጥ ወደሰማይ መድፍና ታንክ ወደፈለኩበት በነፃነት የምተኩስብሽ ማሪኝ ›› ብየ ጮህኩ …አገሬ እንኳን ወደሰማይ ወደተሰለፈ ህዝብ እንዳሻን የምንተኩስብሽ ማሪን አልኩ …መተኮስ ብርቅ ነው እንዴ…? ችጋራም አሜሪካ…. እና ሽጉጥ ለመሞከር እንደሷ ኢራቅ እንዝመት አፍጋኒስታን ?
‹‹ ቅድስት አገሬ …. የሰላም የልማት የዲሞክራሲ አገሬ እንደውም ተኳሽ አንቱ ክቡር እየተባለ የተተኮሰበት ከሞተም እሰየው ከተረፈም መድረሻህን ፈልግ የሚባልብሽ አገሬ ማሪኝ ›› አልኩ ….ሊሻንየ የኔ ፍቅር ዲሞክራሲ በብረት ካውያ ካልተተኮሰ እኮ ይጨማደዳል ….አሜሪካ አሁን ዲሞክራሲዋ የተጨማደደው ለዛ ነው ሃሃሃሃሃሃ ….. ሊሻንየ ልሙትልሽ ተኩስ ስንት ጉድ ጥቅም አለው መሰለሽ ?….
ከእያንዳንዱ ብሄራዊ በዓል ጀርባ እኮ ተኩስ አለ … እንደውም ብሔራዊ የተኩስ በዓል ነው የምናከብረው …. ከአድዋ ጀርባ ምን አለ …. ተኩስ !! …..ከግንቦት ሃያ ኋላስ ተኩስ ! ተኩሰን ስላባረርነው እና ተኩሰን ስለጣልነው እኮ ነው የምናወራው …..እንግዲህ እንኳን ሰበብ ተገኝቶ አንዳንዴ ሆድ ሲብሰን ወደሰማይ ብንተኩስ ይሄ ነውር ሁኖ ከአገር ያስባርራል …….ሃሃሃሃሃ
እኔ የምልሽ ሊሻንየ ‹‹ ኤምባሲ የእናተ የራሳችሁ ግዛት ነው›› አላሉንም እንዴ ….. ታዲያ ኤምባሲያችን ግቢ ውስጥ ለበዓላት አርባ ጊዜ መድፍ ብንተኩስ አንችልም ማለት ነው? …..እሽ ለመስቀል ሽጉጥ ወደሰማይ ብንተኩስስ? …..አይ አሜሪካማ ዲሞክራሲን አፍና ገድለዋለች … አሜሪካ ዝም ብላ የሰው ስም ብቻ ታቆላምጥ ….አሁን ሊሻን አንችን ሊሊ ከማለት ምናለ ከነሊሻንነትሽ ወደሰማይ መተኮስ ብትፈቅድልሽ? ሃሃ …..ወይስ የኦባማ ዙፋን ያለው በአገራችን ኤምባሲ ትክክል ሰማይ ላይ ተንጠልጥሎ ነው? ….
በጣም ነው የተበሳጨሁት….እኛ ኢትዮጲያዊያን ሽጉጥ አያያዛችን ማማሩ …ማነው ያ …..ሬንቦ ሽዋን ዚንገር ምናምን እንኳን እንዲህ እንደኛ ሰውየ ሽጉጥ አያያዛቸው አያምርም !! …..ልሙትልሽ ሊሻንየ … አተኳኮሳቸውስ ብትይ ….ትንሽ የሚያሳዝነው ኢላማቸውን መሳታቸው ነው …..ሃሃሃሃሃሃ እኛስ ለምደነዋል ለዜናው ድምቀት አንድ ሁለት ዲያስፖራ ቢቀነጭሉ …..ሃሃሃሃሃሃ
ቢሆንም ግድ የለም …. አሜሪካ ሶስት ጥይት ተኮሱ ብላ በ48 ሰዓት ከዓገራቸው ብታባርራቸውም እና ብሔራዊ ክብራችንን ብትዳፈርም ዋና ጠላታችን ድህነት ነው ብለን ዝም ብለናል ….. ደሃ ባንሆን እስካሁን እኛም አንተኩስ ብንተኩስም ኦባማ በሚያምር ድምፃቸው ‹‹ ወዳጆቻችን ባርቆባቸው ነው ›› ይሉ ነበር ….ሃሃሃሃሃ
እና ኣራት ኪሎ ተንበርክኬ እንዲህ እያልኩ ጮሁኩ …ጥጋበኛ አሜሪካ ለሶስቲት ጥይት ያውም ወደሰማይ ለተተኮሰ …በአርባ ስምት ሰአት ከአገሯ ሰው ታባርራለች ….እኛ ምን እንበል አርባ ስምንት ጥይት በቀን እየተተኮሰብን ሃያ ስንት አመት የቻልነው እኛ ምን እንበል ….የኑሮው ጥይት ….የእስሩ ጥይት …የዛቻው ጥይት ….የፍትሁ ጥይት ….የህጉ ጥይት …..የሙስናው ጥይት የስራ አጥነት ጥይት የመብራት ጥይት የውሃ ጥይት ….ያውም ፊት ለፊታችን ….››
‹‹ አንተ ምናባክ ነው ተኩስ ተኩስ የምትለው ›› የሚል ድምፅ ሰምቸ አይኖቸን ብገልጥ ጥቁር ዱላ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ …..በወገቡ ደሞ ገመድ ሳንጃ የታጠቀ ፌዴራል ፖሊስ ፊቴ በቁጣ ቁሟል …..ገረመኝ …ሊሻንየ ሙች ገረመኝ ….ከተማ ውስጥ ያውም መሃል አራት ኪሎ ይሄ ሁሉ ትጥቅ ምን ያደርግለታል ብየ ገረመኝ …. እንደውም ጠረጠርኩ ‹‹ያች ኋላ ቀር አሜሪካ ጥይት ወደሰማይ ተኮስክ ብላ ያባረረችው ይሄን ሰውየ ይሆን እንዴ ›› ብየ ጠረጠርኩ ሂሂሂሂሂሂ
ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ ይሄ ሁሉ ጩኸት ለሶስቲት ጥይት …. ደሞ ነገ የተባረረውን ተኳሽ መስቀል አደባባይ በሰልፍ ወጥታችሁ በእልልታ ተቀበሉ እንዳትይን አረጋሽ …. ብሎ ጮኸ አረጋሽ እኛ ሰፈር የምትኖር የቀበሊያችን ምክትል ሊቀመንበር ናት !
‹‹ ምናላት ሶስት ጥይት ….. ብቻ ይጣራልን አሜሪካ በዶላር ከሆነ የተኮሰው እዚህ መንዝሮ እንዳይተኩስብን …ሶስት ሲባዛ በሃያ …..ሃሃሃሃሃሃሃሃ ››
ጋሽ አዳሙ እየሳቀ ድምፁም እየቀነሰ እየቀነሰ ……ወደቤቱ !