Tidarfelagi.com

ነገር ቶሎ አይገባኝም

ደም መላሽ እባላለሁ… ከደም ውጪ ታሪክ መዘገብ የሚከብደው ዓለም ላይ እኖራለሁ…

አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንቸውን ከስክሰው… ሲባል፣

ክርስቶስ በደሙ አዳነን( በደሙ ሃጢያታችንን አጠበልን) ሲባል፣
ያለምንም ደም፣ ኢትዮጵያ ትቅ”ደም” ሲባል ( ትቅደም የሚለው ቃል፣ አፈፃፀሙም ቃሉም “ደም” እንዳለበት ሳይ)… አይገባኝም።

ዓለም ይህን ያህል ደም በደም ሲሆን የሰው ልጅ የት ነበር። ስንቱ በየሆስፒታሉ ደም አጥቶ ሲሞት፣ ምን ያለ ቀልደኛ እንዲህ በየጎዳናው ደም ያፈሳል?

የ “ደም ገንቦ” የተባለችው ልጅ እውነት ቆንጆ ናት? እኔ የደም ገንቦ ሲባል የሚታየኝ በደም የተሞላ ገንቦ ነው። ወንጀል የተፈፀመ እንጂ፣ ቁንጅና የተገለፀ አይመስለኝም።

ደም መላሽ የሚለው ስሜን አልወደውም። ሲተረጎም፣ ደም አፍሳሽ ማለት ነው። ደም የሰው ማሳ እንደገባ በግ ክስ ተብሎ አይመለስም። ሰው ተገድሎ ነው። ዓለም በደም ፍቅር የወደቀበት ሰበብ አይገባኝም።

ቬጂቴሪያን ነኝ። ስጋ ወ ደሜን የበላ ሲባል ግራ ይገባኛል። ይህ cannibalism አይደለም? ሌላ መንገድ የለም? ለአንድ ቬጅትሪያን ይህንን ትዕዛዝ ከቁም ነገር አለመጣፍ፣ የዘላለም ሕይወት ከማጣት እኩል ነው? …

“Blood and Iron ” በሚል መርህ አገር ያቀናውን ሰው ቢስማርክን ሳስብ፣ የቫምፓየር ፊልሞች ላይ ካሉ አክተሮች አንዱ ይመስለኛል።

ብዙ ነገር አይገለጥልኝም። የደም ታሪክን አወድሶ የሚዘግበው ዓለም አይገባኝም። ትንሽ ስሰነብት ግን የሚገባኝ፣ ላልገባቸውም የማስረዳ ይመስለኛል።

One Comment

  • ያኪኒ commented on August 19, 2017 Reply

    ዋውውውውውውው ምርጥ ሰው ነህ!
    keep it up

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *