Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል አምስት)

“ኤደን ምን ይሰማሻል?”
“ምንም”
(ዝም ተባብለን ሰዓቴ አልቆ እመለሳለሁ::)
በሌላኛው ቀንም ……..
“ኤደን ዛሬስ ለማውራት ዝግጁ ነሽ?”
“አይደለሁም!! ማውራት አልፈልግም!”
(ዝምምምምም….. ሰዓቱ ያልቃል)
ደግሞ በሌላኛውም ቀን
“ኤደን ዛሬስ ለመጀመር ዝግጁ ነሽ?”
“ምኑን?”
” ማውራት ትፈልጊያለሽ?”
“እኔ ምንም የማድረግ ፍላጎት የለኝም!!”
(የምፈልገው አንድና አንድ ነገር …. የቀብሯ ቀን ጭልጥ አድርጎ የወሰደኝ ጨለማ ለዘለዓለሙ እንዲወስደኝ ነው)
በሌላኛው ቀን አልጠየቀኝም:: ገብቼ ስቀመጥ ሰላምታ ሰጥቶኝ ዝም አለ::
“ዛሬ አትጠይቀኝም እንዴ?”
“ምኑን?”
“ዝግጁ መሆን አለመሆኔን?”
“ነሽ?”
“አይደለሁም!”
“ጥሩ!! ዝግጁ እስክትሆኚ ድረስ የሚሰማሽ እዚህ መጥቶ መቀመጡ ከሆነ ዝም በይ… ማውራት ሲሰማሽ አውሪ…. ማልቀስ ሲሰማሽ አልቅሺ…. መጮህ ሲሰማሽ ጩሂ ….. ሰዎች ሀዘናቸውን በተለያያየ መንገድ ነው የሚያስተናግዱት…. የተለያየ ጊዜ ይወስድባቸዋል::”
“ሀዘን አይደለም የሚሰማኝ!!”
“እሺ!! ምንድነው የሚሰማሽ?”
“ምንም!!! ዝም … ፀጥ …. ያለ ስሜት!!”
ለብዙ ቀናት ተመላለስኩ …. እሄዳለሁ:: እቀመጣለሁ:: ሰዓቴ ያልቃል:: እመለሳለሁ::
“ዛሬ አሻንጉሊትሽን የት ትተሻት መጣሽ?” አለኝ
“ሰጥቻት መጣሁ:: ….. ‘ያውልሽ’ ብዬ መቃብሯ ላይ ወርውሬላት መጣሁ:: ትውሰደው …. ” እንባዬ ከወራት በኃላ ላስቆመው እንዳልችል ሆኖ ይንጠኝ ገባ …… ማልቀስ ማቆም እፈልጋለሁ:: .. አቃተኝ…. የቀብሯ ቀን እንደሆነው ራሴን የምስት መሰለኝ …. ጨለማው ናፈቀኝ… ግን አልመጣም… አልወሰደኝም…. ደብዳቤዋን ከኪሴ አውጥቼ ሰጠሁት::
“አየህ በዝህች ሁለት መስመር ደብዳቤ እንዳልሞትም እንዳልኖርም አስራኝ ሞተች:: አንብበውማ! ጮክ ብለህ አንብበው!!”
” አንቺ ደግሞ በተራሽ የእኔንም ደርበሽ ኑሪልኝ:: የከፈልኩትን ዋጋ እንዳታከስሪኝ …. ደስ ተሰኝተሽ ኑሪና ዋጋዬን ክፈዪ!! …. ፖኒን ትቼልሻለሁ::” ጮክ ብሎ አነበበው …. ቤተሰቦቻችን እንዳልገባቸው ሁሉ እሱም አልገባውም….. የሆነው ሳይገባቸው ነው ‘ጭንቅላቷ ተቃውሷል’ ብለው ሳይካትሪስት የቀጠሩልኝ….
“ፖኒ ያቺ አሻንጉሊት ናት!” እንደገባው ራሱን ነቀነቀ…. “በጣም ልጅ ሆነን ለሁለት አንድ አሻንጉሊት ተገዛልን:: እሷ ስም አወጣችላት:: አልተቃወምኩም:: …. የሆነ ቀን እኔ ስጫወት ደርሳ ካልወሰድኩ አለች … ተደባደብን … አባታችን መጥቶ አሻንጉሊቷን ከእኔ ቀምቶ ለሷ ሰጣት … ቀን ቀን በአሻንጉሊቷ መጫወት የምትችለው እሷ መሆኗን አወጀ:: ከፈለግኩ ማታ እሷ ስትተኛ መጫወት እንደምትችል… ያውም እሷ ከፈቀደችልኝ….. ነገረኝ:: ምርርርርርር ብዬ አለቀስኩ::…… ያስለቀሰኝ ከአባታችን ለሷ ማገዝ በላይ የሷ መደሰት ነበር:: እንዳለመታደል ሆኖ ሁሌም እሷ ስትተኛ ጠብቄ ለመጫወት እቀመጥና እንቅልፍ ቀድሞ ስለሚጥለኝ ያልፈኛል::…. ምን ማለቷ ነው? ስትሞት ትታልኝ የምትሞተው?”
“ምን ማለቷ ይመስልሻል አንቺ?”
“እኔ ምን አውቅላታለሁ? ህይወትሽን የቀማሁሽ እዛጋ ነው … ከዛ ጀምሪ ማለቷ? ያውልሽ ይስፋሽ ማለቷ? እኔ ምን አውቅላታለሁ ምን አድርጊ እንደምትለኝ? ቆይ እሷ ራሷን እንደክርስቶስ ነው የምታየው? ማነኝ ብላ ነው የምታስበው ህይወቷን ስትሰጠኝ ….. በቃ ሞተችልኝ ብዬ በደስታ የምኖር ነው የመሰላት? ደሞ ቆይ ክርስቶስኮ ለአንድ ሰው አልሞተም …. ለዓለም ህዝብ ነው የሞተው… ክርስቶስ ለአንተ እንደሞተልህ ብታውቅም ስላላመንከው እኔ አሁን የሚሰማኝ አይነት ሸክም አይሰማህም …. ሌላ የሆነ ሰው አምኖ እንደሚያገለግለው ታውቃለህ … እሷ ምን አስባ ነው ለአንድ ለእኔ ህይወት ከፍላ … ከዛ በደስታ እንድኖርላት የምትፈልገው? ቆይ የቱጋ ሀ ብዬ መኖር እንድጀምርላት ነው? ቆይ አንተ ስታስበው ጤነኛ ሆኜ ራሱ መኖር የምችል ይመስልሃል?”
“አዎ ይመስለኛል!!”
“እኮ እንዴት?” ….. እስከዛሬ ያላወራሁበትን ሰዓታት ጨምሬ ለፈለፍኩ::
“ራስሽን ይቅር በማለት ትጀምሪያለሽ!!”
“ሌላ 30 ዓመት መኖር ቢሰጥሽም መኖር አትጀምሪም አትለኝም ታዲያ?”
“ሳይኖሩ ከመሞት መኖር ጀምሮ መሞቱ አይሻልም ታዲያ? …… ”
……
…..
“ለራሴ ስል መኖር አልፈልግም….. ለሷ ስል ደግሞ መሞት አልፈልግም”
…..
“ሁለቱን ለማስታረቅ ነው ከራስሽ መታረቅ ያለብሽ….. “

3 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *