Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል አንድ)

ሞታ የለቅሶ ድንኳኗ ውስጥ የተነጠፈው ፍራሽ ላይ ተቀምጬ ሊቀብሯት በሳጥን አሽገው ጥጉ ላይ አስቀምጠዋት ሲላቀሱ የማስበው
‘አልወዳትም እንጂ አልጠላትም’ …. የሚለውን ነው… በሃሳቤ መሃል ከቤተሰብ ወይ ከወዳጅ አንዱ ሲያፈጥብኝ
“ወይኔ እህቴን .. ወይኔ እህቴን … ትተሺኝ አትሂጂ ..” እሪታዬን አቀልጠዋለሁ … እንባዬ ይተባበረኛል።

እህቴ ናት … አዎ የሞተችው እህቴ ናት … ብዙ መለስተኛ ክፉ ነገሮች አድርጌባት አውቃለሁ …
ለምሳሌ ለሰርጏ ሰዓታት ሲቀሯት የሙሽራ ልብሷን በእስኪሪብቶ ቀለም ቡራቡሬ እንዳደረግኩባት አይነት ትንንሽዬ ክፋቶች …… ግን አልጠላትም!!!
ባሏን ከማባለግና ሰርጏን ከማበላሸት የትኛው ትልቅ ክፋት ነው?
“ካላንቺ እንዴት ልኑረው?” እያለ ወገቡን ተደግፎ ድንኳን ውስጥ ይዝረከረካል ባሏ … እኔ ሰልችቶኝ እስካቆምኩበት ቀን ድረስ እኮ ከሚስቱጋ ከተኛበት ቀስቅሼ የማባልገው ሰውዬ ነበር!! .. እሺ ከኔና ከሱ ማናችን የባሰ ክፉ ነበርን ለሷ?
አያችሁ አልወዳትም እንጂ አልጠላትምኮ …
ኦው የምርቃቷ ቀን የጫማ ሂሏን የሰበርኩባትን መቼም እንደክፋት አትቆጥሩብኝም … ምርቃት የምታክል ክፋት !
ያስቃምኳት… ያሰከርኳት … ያስጨስኳት …. ያጣበስኳት … ይሄ መቼም ከውለታ እንጂ ከተንኮል ከተቆጠረ … ደግ ነገር የለም ማለት እኮ ነው…ሆ!!
“እህቴ መካሪዬ … ” … እናቴ አየችኛ … ለቀስተኛውን ተቀላቅዬ የፈረደበት ዓይኔን ላስጨንቀው …
እህቴ ክፉ ሴት ሆና አይደለም!! በተቃራኒው ከማውቃቸው ሰዎች ለፍፅምና የቀረበች መልካም ሴት ናት …. የማልጠላት ለዛ ነው …
የማልወዳት በዚህ ፍፅምናዋ እሷ በፍሬም የተቀመጠች ሞዴል ሆና ቤተሰቦቼ እኔን በሷ አምሳል ጠፍጥፈው ሊሰሩኝ እያቦኩ የሚጠፈጥፉኝ ሁሌም በጅምር ያለሁ ቡኮ የሸክላ ጭቃ መሆኔ ነው ….
እሷ በትምህርቷ አንደኛ ስትወጣ ‘እህትሽን አየሻት?’ ያቦኩኛል .. ጎበዝ ተማሪ አድርገው ሊቀርፁኝ ሲጀምሩ እሷ በሆነኛው እስፖርት አሸንፋ ዋንጫ ይዛ ትመጣለች …..
ደሞ የጀመሩትን አፍርሰው ያቦኩኛል … እስፖርተኛ እንድሆን ሊቀርፁኝ ይጀምራሉ … ገና ቅርፅ ሳልይዝ እሷ በሆነኛው በጎ አድራጎት ተሳትፋ ስሟ ይወደሳል … ደሞ ያፈርሱኛል … ይጠፈጥፉኛል ..
‘እህትሽን አየሻት?’
በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ 🤷🏽 ክፉ መስራት ፈልጌ አይደለም …. እኔ እሷን መሆን ብዙ ሞክሬ ያልተሳካልኝ ነገር ስለነበር … የክፋት ሙከራዬ እሷን ወደ እኔ ማውረድ ነበር።…. ትዳር ባይኖራት ….. ባትመረቅ … የክፋት ክፋቱ እሷ ማምለጫ አታጣም ነበር!! ….
ከሞት ማምለጫ የለውም እንጂ ህምምም… አሁንም በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ በመሞቷ አልተደሰትኩም። በመሞቷ ከማንም በላይ የምጎዳው እኔ ነኝ…
ግማሹን ዘመኔን እኔ እሷን ለመምሰል ስጋጋጥ … የቀረውን እሷ እኔን እንድትሆን ስጋጋጥ ነው በመሃል አየር ላይ በትናኝ የሞተችው …. እና አሁን ምን ልስራ? ማንን ልምሰል?

በሞቷም ልከተላት? ራሷን ብቻ ሳይሆን ያቺ በፍሬም የተቀመጠችልኝን ሞዴሌን ይዛት ነው የተቀበረችውኮ ….. ከኔ በላይ ማን ሊያለቅስላት ይችላል?
“እህቴ … ምሳሌዬ ….. ወዮዮዮዮዮዮ ኡኡኡኡኡኡኡኡ” …. አብርዶ የነበረው ለቀስተኛ ማርሹን ጨምሮ እርርርርሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪ…..
“አይዞሽ! አይዞሽ ኤድዬ” … ጀርባዬን ቸብ ቸብ ያደርጉኛል …
እሷ ራሷን ሆና .. የምትፈልገውን አድርጋ … የራሷን የህይወት መንገድ ሮጣ በ30 ዓመቷ ሞተች … ቢያንስ ኖራለችኣ?
እኔ እሷን ስመስል … እሷ እኔን እንድትመስል ተንኮል ስፅፍ 30 ዓመት …. ኖርኩ ነው የሚባለው?
ማነው የሞተው? እኔ ወይስ እሷ?
“ኤድዬ እህትሽን ትሰናበቻታለሽ?” ወደ ቀብር ሊንቀሳቀሱ ነው … እናቴን አየኃት በተከፈተው ሳጥን ጠርዝ ላይ ድግፍ ብላ እህህህህ ትላለች …
እሷን ነው የምሰናበተው ራሴን?
“ቆይ ትንሽ ደቂቃ” አልኩኝ …… ፊቷን የማይበት ጉልበት እያሰባሰብኩ … (ነፍስም ባይኖረውም… ባታየኝም) ጥፋተኝነት ሲሰማኝ ፊቷን እፈራዋለሁ
…..
“ጫማዬን የሰበርሽው አንቺ ነሽኣ?”
“አዎ… በምን አወቅሽ?” አላያትም…. በግድ አጠገቤ መጥታ እንዳያት ታስገድደኛለች
“ለምን? ”
“እኔ እንጃ I guess ቀንቼ ነው” (ትስቅብኛለች)
“We talked about this አይደል እንዴ? Remember? አንቺ ዶክተር መሆን አትፈልጊም.. እኔ ነኝ የምፈልገው… እኔ ዘፋኝ መሆን አልፈልግም አንቺ ነሽ የምትፈልጊው… መሆን በማትፈልጊው ነገር ለምን ትቀኚብኛለሽ? እነ ማሚ እንዲበጠብጡሽ ለምን ትፈቅጅላቸዋለሽ?”
“አላውቅም!” (ታቅፈኛለች … ጭንቅላቴን ያጣበበውን ብስጭት … ቅናት … ተንኳል .. ሀዘን … ስብራት … ታሪክ … ባወራላት ደስ ይለኛል…. እየመጣ ያንቀኛል …. ለምን እንደሆነ በማይገባኝ ምክንያት ሽንፈቴን አምኖ መቀበል ይመስለኛል)
“በደም እህትሽ እንዳልሆንኩ ታውቂያለሽ? አንቺም እንደነሱ እያወቅሽ ነው ወይስ አታውቂም?” ይሄን ያልኳት እሷን መጉዳት ፈልጌ ይሁን መልሱን ፈልጌው አላውቅም።

ፊቷ ላይ መልሱን አገኘሁት። አታውቅም!! በደቂቃዎች ቀድማኝ የተወለደች መንታ እህቷ መሆኔን ነው የምታውቀው።
“ኤድዬ እህትሽን መሰናበት ከፈለግሽ እየጠበቅንሽ ነው።”
“እሺ”

 

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል ሁለት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *