Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል አራት)

‘ከቤቴ ውጪልኝ’ የሚለውን ዘላ ‘ከህይወቴ ውጪልኝ’ ያልኳትን ሰምታኝ መሰለኝ……. የሞተችው……
“ኤዱዬ የኔ ከህይወትሽም ከቤትሽም መውጣት አንቺን አያስተካክልሽም!! Let us make this right!! ላግዝሽ?” አለችኝ ….
“የቱን? የቱን ነው የምናስተካክለው?” አልኳት “ያንቺ እህት አለመሆኔን? ንገሪኝ ከየት እንጀምር? ገና ሳልወለድ ቤተሰቦችሽ ከከዱኝ? ወይስ ለ13 ዓመት እማ አባ ያልኳቸው ቤተሰቦቼ ሳይሆኑ የወለደችኝ ሌላ ሴት መሆኗን እንዴት ነው የምናርመው? ከየት እንጀምር ንገሪኝ? …. ጥፋት ሳጠፋ ‘ዘር ከግንዱ ይመዘዛል’ እየተባልኩ …. በራሴ መንገድ ስጏዝ ‘እንደእህትሽ ብትሆኚ ምናለ?’ እየተባልኩ ማደጌን ምኑጋ እናቅናው ?” ……
እንዲህ ለማንም አውርቼ አላውቅም…. የተሰማኝን ህመም ሁሉ መዋጥ እንዳለብኝ ተነግሮኝ ነው ያደግኩት…. ጭጭ… እሽሽሽሽሽ ተብዬ … እየታመሙ መሳቅ ለምጄ ነው ያደግኩት ….
“ወንድሜ ስለው ያደግኩት ወንድ ከጏደኞቹ ጋር የደፈረኝን ምኑጋ እናቅናው እህቴ? ንገሪኝ ?…. እኔ …. እኔ መቃናት አልችልም!! …. የእኔ ህይወት የቱምጋ አይቃናም!! .. ”
“ወደኃላ ተመልሶ ቢቃና …. ሀ ብዬ ሌላ ሰው ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው…. ያንቺ እህት ሳልባል… አንቺ በምታገኚው ፍቅር ሳልቀና … ባንቺ ጉብዝና ራሴን ሳልለካ…. እንዳንቺ ቆንጆ ለመሆን ሳልመኝ…. ባጠቃላይ ካንቺ ሳያወዳድሩኝ ‘እኔን’ የሚወዱኝ ቤተሰቦች ልጅ ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው ….. ክፉ … ቀናተኛ … ሳልሆን ….”
ከተቀመጠችበት ሳትነሳ ብዙ ቆየች…. እኔ ህመሜን ብዙ አወራሁ …. ከቤቴ ስትወጣ ….
የኔን ሸክም ሲደመር የጥፋተኝነት ስሜት ሲደመር ባሏ ከእህቷጋ የባለገባት ሚስት የልብ ስብራት … ይሄን ሁሉ ተሸክማ ከአንገቷ አቀርቅራ …. የጎበጠች መሰለኝ …
“ኤድዬ ህመምሽን ስላልታመምኩልሽ ይቅርታ!!” ብላኝ ወጣች …. እኔ 30 ዓመት ቀስ በቀስ የጠጣሁትን ጎምዛዛ ክፋትና በደል … በአንድ ቀን ጋትኳት …. ከበዳት!!
….
…..

የቀብር ቦታው ላይ ሬሳዋን ወደ ጉድጏዱ ሲነዱት እያየሁ …ምናለ አቅፌያት ቢሆን? ‘ያንቺ ጥፋት አይደለም’ ብያት ቢሆን? ምናለ ዝም ብዬስ ቢሆን? …. ምናለ….. ምናለ…. እያልኩ እንሰቀሰቃለሁ:: …..
…..
…..
ከቤቴ ከወጣች በኃላ ለሰዓታት ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ስልኬ ጠራ!!
“እህትሽ አርፋለች!”
ምንም አልጠየቅኩም:: እስከአሁንም ድረስ የደወለልኝ ማን እንደሆነ አላውቅም:: … ስልኩንም ከዘጋሁ በኃላ ለሰዓታት እዛው ተቀመጥኩ:: ድጋሚ ስልኬ ጠራ:: ጏደኛዋ ናት::
“ኤዱ የት ነሽ?” አለችኝ በማልቀስ በሻከረ ድምፅ …. ‘እንዴት እህትሽ ሞታ ለቅሶ ቦታ የለሽም’ የሚል ድምፀት ባለው ቃና
“ምን ሆና ነው?” የሚል ጥያቄ ነው ከአፌ የወጣው….
“ወየው ጉዴ አልሰማሽም? (ለቅሶ አስከትላ) ምን እንዳጋጠማት ምን አውቄ? ራሷን ነው ያጠፋችው::” አለችኝ …… ስልኩን ዘጋሁት …. እስኪነጋ ከተቀመጥኩበት አልተነሳሁም:: ….. ፀሀይዋ ብቅ ስትል ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ለቅሶዋ ላይ ተገኘሁ:: ስገባ ነጠላ ትከሻዬ ላይ አደረጉልኝ…. ምፅ ምፅ እያሉ ደግፈው ወንበር ላይ አስቀመጡኝ …… ግራ ገባኝ ….
ሲያፈጡብኝ አለቅሳለሁ …. እንባዬ ይተባበረኛል ….. እስከቀብሯ ቀን ድረስ ሲያለቅሱ ከማልቀስ …. ሲያፈጡብኝ ‘ጨካኝ’ ላለመባል አይኔን ከማስጨነቅ ያለፈ የሚሰማኝንም ስሜት ለይቼ አላወቅኩትም::
አፈሩን ሲያለብሷት ልቤን ሞት ተጫነው:: ዝም ጭጭ …. ያለ ስሜት ተሰማኝ:: አብሬያት ጉድጏድ ውስጥ የገባሁ ስሜት …. አፈሩ እኔ ላይ የሚጫን ስሜት …. ራሴን ልስት አይነት ስሜት ይሰማኝና ተስተካክዬ ለመቆም እሞክራለሁ .. …. የሚሰማኝ ዝምታ ብቻ ሆነ … ከዛ …. ጨለማ!!!!
እንደሞት ያለ ጨለማ ……..
“ምን ሆኜ ነው?” አልኩኝ አይኖቼን ስገልጥ ሆስፒታል እንዳለሁ ገብቶኝ:: …… አጠገቤ የእህቴ ጏደኛ እና እናቴ (አሳዳጊዬ) ነበሩ:;
“ቀብር ቦታ ራስሽን ስተሽ ነው” አለችኝ ጏደኛዋ …. ፊታቸው ላይ የሆነ የጉጉት ስሜት አየሁ….. ስለነቃሁ የመደሰት ግን ያስደሰታቸው መንቃቴ ብቻ ሳይሆን ሌላ ነገር እንዳለ ገባኝ
“ምንድነው?” አልኩኝ ወደ እናቴ ዞሬ ….. ከአፌ
እስኪወጣ ስትጠብቀው የቆየ ቃል ይመስል ቅብል አድርጋ
“ምን ማለቷ ነው? ምንድነው?” ብላ የሆነ ፖስታ ሰጠችኝ
“ምንድነው?” አልኩ እየተቀበልኩኝ
“እህትሽ ከመሞቷ በፊት ያስቀመጠችልሽ ደብዳቤ ነው! ምን ማለቷ ነው? ከሁላችን መርጣ ለምንድነው ላንቺ የፃፈችው? የፃፈችው ምኑን አልገባኝም!” አለችኝ
“ለእኔ ከሆነ የተፃፈው ለምን አነበባችሁት?” አልኩኝ ፖስታው ላይ ለኤደን ብቻ የሚል ፅሁፍ እያየሁ .,,……

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል አምስት)

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *