.(ከተስፋዬ ገብረአብ )
ተስፋዬ ገብረ-አብ “በጋዜጠኛው ማስታወሻ” በርካታ ፖለቲካ-ነክ ወጎችን አውግቶናል። እኔ እዚህ የምጽፍላችሁ ግን ፖለቲካውን ሳይሆን ተደጋግመው ቢነገሩ የማይሰለቹ ሌሎች ጨዋታዎቹን ነው። (እኒህን ጨዋታዎች የቀዳሁት ከዚያው መጽሐፍ ነው)።
===አቶ ፍሬው ለምለም እና የቼክ እደላው===
አቶ ፍሬው ለምለም ደግ አዛውንት ነበሩ። የብሄራዊ ሎተሪ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡ ሰሞን እንደ አንበጣ ወረርናቸው። የመንግሥትና የኢህአዴግ ሚዲያዎች ሁሉ ማስታወቂያ ይሰጡአቸው ዘንድ የሽያጭ ወኪሎቻቸውን ላኩባቸው። ከቴሌቪዥን፣ ከሬድዮ፣ ከአዲስ ዘመንና ከበሪሳ ጋዜጦች ለመጡት ሁሉ ይሉኝታ ይዞአቸው ቼክ ፈረሙ። ቀጥሎም “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ጋዜጣ መጣ። እምቢ ማለት አልቻሉም። የሾማቸው ኢህአዴግ ነውና ቼክ ፈረሙ። ከ“ማህቶት” ጋዜጣ ለመጣው ግን ላለመስጠት አንገራግረው ነበር። “በአማራው ክልል ዋና የሎተሪ ደንበኞች ዘንድ እንደርሳለን” እያለ ሲለፈልፍባቸው ለመገላገል ብለው ቼኩን ፈረሙ። በነጋታው የኦሮሚያ ጋዜጣ ወኪል መጣ። “ለአማራው ፈርመህ ለኦሮሞ ያልፈረምከው ነፍጠኛ ስለሆንክ ነው” እንዳይባሉ ቼክ ፈረሙ። ከደቡብና ከትግራይ መጡባቸው። ከነገር ለመሸሽና ላለመነካካት ሲሉ ፈረሙላቸው። በመጨረሻም እኛ ሄድን-ከእፎይታ መጽሔት። ዐርብ ጠዋት የሽያጭ ሰራተኛውን አስከትዬ ከቢሮአቸው ስገባ ግስላ ሆነው ጠበቁኝ።
“ምን ፈለጋችሁ እናንተ ደ’ሞ?!” ሲሉ ጮኹ። “አታፍሩም እንዴ? ፍሬው ለምለም እንደ ጠበል ጠዲቅ ገንዘብ እየመዠረጠ ይሰጣል ያላችሁ ማን ነው? ምንጣፉንም ጠቅልሉትና ውሰዱታ! ጠረጴዛውንም ጫኑ! እሱ ነው የቀራችሁ:: ነውር አይደለም እንዴ?”
ካረጋጋናቸው በኋላ ሳምንቱን በሙሉ የደረሰባቸውን አጫውተውን ሲያበቁ እንዲህ አሉ።
“እስኪ ይሁን እንግዲህ… ዳግመኛ አትምጡብኝ እንጂ ለዛሬው ባዶ እጃችሁን አልመልሳችሁም”::
===መለስ እና ደበበ እሸቱ===
እውቁ ተዋናይ ደበበ እሸቱ በምርጫ-97 ተወዳድሮ እንደነበር ይታወሳል። እናም ጠ/ሚ/ መለስ እንዲህ ተጠይቀው ነበር አሉ።
ጋዜጠኛ፡ ኢህአዴግ በምርጫው ድራማ ሰርቷል ይባላል። እውነት በምርጫው ድራማ ተሰርቶ ነበር እንዴ?
ጠ/ሚ/ መለስ፡ የተሰራ ድራማ የለም። ምናልባት በምርጫው ደበበ እሸቱ ስለተሳተፈ ድራማ የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል”።
(ሆኖም ይህቺ የድረ-ገጾች ፈጠራ ናት ይለናል- ተስፋዬ ገብረ አብ)
===ስብሐትና ቦነስ===
ለጋሽ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ለስድስት ዓመታት ያህል አለቃው ሆኜ ብንሰራም በአንዳንድ ነገሮች ላይ እርሱ ነበር የሚያዘኝ። አንድ ቀን እንዲህ ሲል ጠይቆኛል።
“ላማክርህ ነበር የመጣሁት”
“እሺ ጋሽ ስብሐት ምን ነበር?”
“ገንዘብ ቸግሮኛል”
ዝም አልኩ። ምክንያቱም የመጪዎቹን ሁለት ወራት ደመወዙን ከወዲሁ ወስዶ ነበርና ምን እንደማደርግ ግራ ሊገባኝ ጀምሮ ነበር። እሱም ይህንን ተገንዝቦ ኖሮ ፈጥኖ ንግግሩን ቀጠለ።
“ደመወዜን ቀድመህ ስጠኝ ልልህ አልችልም። ወስጄዋለሁና። አሁን ሳስብበት ቆየሁና አንድ ሌላ ዘዴ መጣልኝ።
“ምን ዘዴ አገኘህ ጋሽ ስብሐት?”
“ታታሪ ሰራተኛ በሚል ለምን ቦነስ አትሰጠኝም?”
===ፈረሰኛው ባህሩ===
የግንቦት ሀያ አንደኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነው። ብዙ ህዝብ በመስቀል አደባባይ ታድሞአል። ሁሉም እንደ አቅሙ ሸልሏል። ከዚያ ህዝብ መሀል አንድ ፈረሰኛ አባት ትኩረቴን ሳቡት። ፈረሳቸው ተንቆጥቁጧል። እሳቸውም ፈረሳቸውን መስለዋል። እኒህ ሽማግሌ ያቅራራሉ። ጃሎታውን ያስነኩታል። ምናልባት ደርግ ብዙ ጋሻ መሬት የወረሰባቸው ይሆን? ወደርሳቸው ቀርቤ ምክንያቱን ብጠይቅ የተሻለ ነው በማለት ለቃለ መጠይቅ ጋበዝኳቸው።
“አባት ስምዎትን ማን ልበል?”
“ባህሩ ከበደ”
“አቶ ባህሩ ዛሬ እንዲህ አምረው በሰንጋ ፈረስዎ እየጋለቡ ወደዚህ አደባባይ የመጡት ለምንድነው?”
“እኔ ከኃይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ፣ በደርግም ጭምር፣ አሁን ወያኔ ከመጣ ወዲህም ሰልፍ የሚባል አምልጦኝ አያውቅም፤ ሰልፍ አለ ከተባለ የክት ልብሴን ለብሼ ሰንጋ ፈረሴን ጭኜ ከተፍ ነው”
===ወይዘሮ ኢትዮጵያ===
ደርባን በምትባል ከተማ ላይ የተዋወቅኩት ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ያጫወተኝ ነው።
ኤርትራ የነጻነት በዓሏን እያከበረች ነው። ህዝቡ በሳባ ስታድየም ታድሟል። ወታደሮች የሰልፍ ትርኢት ያሳያሉ። እናቶች ሹሩባ ተሰርተው በእልልታና በእስክስታ ክብረ በዓሉን አድምቀውታል። ኤርትራዊው ጋዜጠኛም የአንድ ደማም ኤርትራዊት እናት የእስክስታ አወራረድ ስለማረከው ለቃለ መጠይቅ ጋበዛቸው።
“እናት! እንኳን ደስ አለዎት”
“እንኳን አብሮ ደስ አለን። ኤርትራ ሀገራችን ከኢትዮጵያ አገዛዝ ነጻ በመውጣቷ ደስ ብሎናል። የዛሬዋ ዕለት የልደት ቀናችን ናት”
“ስምዎትን ማን ልበል?”
“ወይዘሮ ኢትዮጵያ እባላለሁ”
——-
(ተስፋዬ ገብረ አብ፣ የጋዜጠኛው ማስታወሻ፣ 2001/2009 G.C.)