Tidarfelagi.com

አባይ እና ጣና- በጀምስ ብሩስ ካርታ ላይ

ጀምስ ብሩስ ይህንን ካርታ ያነሳው በ1770ዎቹ ነው። ፈረንጆች እርሱ የጻፈውን መጽሐፍ አንብበው “ጀምስ ብሩስ የጥቁር አባይን ምንጭ አገኘ” ይላሉ። ጳውሎስ ኞኞ በዚህ ዙሪያ ሲጽፍ “አረ ለመሆኑ ዕድሜ ልኩን ከአባይ ጋር ሲኖር የነበረው የጎንደርና የጎጃም ገበሬ የት ሄዶ ነው ፈረንጆች እንዲህ የሚሉት?” በማለት ሞግቶ ነበር።

በርግጥም “ምንጩን ጀምስ ብሩስ አገኘው” ማለት ትልቅ ምጸት ነው። ባይሆን “ጀምስ ብሩስ የጥቁር አባይን መነሻ በዐይኑ አይቶ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጻፍ የመጀመሪያው አውሮጳዊ ነው” ቢባል ይሻላል። እዚህ ላይ በእንግሊዝኛ ያልኩት ሊሰመበርት ይገባል። ከጀምስ ብሩስም ሆነ ከሌሎች የውጪ ተወላጆች በፊት ስለአባይ በግዕዝ ቋንቋ የጻፉት የኛው ሀገር ተወላጆች ናቸው። በማስከተልም በዐረብኛ ቋንቋ ስለአባይ መነሻ ተጽፏል።

ከአውሮጳዊያን መካከል የአባይን መነሻ በዐይኑ አይቶ ትክክለኛ ዘገባ ያቀረበው የመጀመሪያው ሰው ደግሞ ፖርቱጋላዊው ቄስ ጄሮኒሞ ሎቦ ናቸው። እኝህ ሰው በአጼ ሱስንዮስ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት “እየሱሳዊያን” (Jesuits) የሚባሉት ሚሲዮኖች አባል ነበሩ። ቄስ ሎቦ በኢትዮጵያ ለዘጠኝ ዓመታት ኖረዋል። “እየሱሳዊያን” ከኢትዮጵያ ከተባረሩ በኋላ ደግሞ ወደ ሀገራቸው በመሄድ በኢትዮጵያ ስላሳለፉት ዓመታት የሚተርክ Itinerário የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ጽፈዋል። በመጽሐፉ ከተጻፈው ነገር ከፊሉ ስህተት ቢሆንም ስለአባይ መነሻ የተጻፈው ግን መቶ በመቶ ትክክል እንደሆነ ተረጋግጧል።

—–
ያኔ ፈረንጆችን ሲያጓጓና ሲያባባ የነበረው ጣና እነሆ በእኛ ዘመን በአረም ተውጦ ሊጠፋ ተቃርቧል። እርሱም እንደ ሀረማያ ሐይቅ ታሪክ ሆኖ ሊሰወር ነው አሉ እንግዲህ!! የሚገርመው ሁለቱም ሐይቆች እጅ ያጠራቸው ከድርቅ ጋር በማይገናኝ ምክንያት መሆኑ ነው። ሀረማያ የጠፋው ደለል ስለሞላው ነው። ጣና ለመጥፋት የተቃረበው “ምንትስ” የተባለ አረም ስለዋጠው ነው። በተለይም ጣናን ለአንድም ቀን ሳላየው ለመጥፋት መቃረቡ አንጀቴን በልቶታል። አላህ እውነት አያድርገው አቦ!!
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 7/2009
አዳማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *