***
አንቺ ሃሳበ ብዙ፣
አንቺ ጓዘ ብዙ
አቅም የሚፈትን፣ጉልበት የሚያጣምን
ከህይወት ዋጋ ይልቅ በሞት ከሚያሳምን
ከዚህ ትግል ጉዞ የሚገላግሉ-
ልጆችሽ እያሉ
የት እንዲያደርስሽ ነው ሰርክ መባተሉ?
“ሁሉ ነፃ አይደለም፣ ውደቁ ተነሱ
ቆፍሩ አፈር ማሱ”
የሚሉ ቂሎችን ከጆሮሽ አርቂ
ለማይረባ ነገር ደጋግሞ መውደቅም፣ ውጤቱ ነፃ ነው ይህንን እወቂ!
ሕይወት ክብ አዙሪት
አልቦ እሽክርክሪት
መሆኑ ካልጠፋሽ፣
ለባዶው በባዶው ዘውትር ምን አለፋሽ?
መፍጨርጨር በባዶ
መጣጣር ለባዶ
በሆነበት ዓለም፣ በአልቦ ሲሳይ ሀገር
ሶስት ሺ አምስት ሺ ስድስት ሰባት በሚል እድሜ ቢደረደር፣
ከማጠር አይበልጥም የመርዘም ቁም ነገር
ነገሩን አልኩ እንጂ ነገሩስ ግልፅ ነው
ልክ እንደ ረጅሙ አጭሩም ባዶ ነው
ባዶውም ባዶ ነው መሳ ነው ትርጉሙ
ባዶ ’ሚመቱበት ባዶ እየተለሙ።
እናልሽ ዓለሜ፣
በምን ልረፍ በሚል እንዳይጠፋሽ ውሉ
ጭንቀትሽ ገብስ ነው ልጆችሽ እስካሉ
እኛ እንደሁ ነፃ ነን ሁሉ የሚያዞረን
መንገደኛ ነፋስ አዝሎ ’ሚዘውረን
ትንታግ ነን ወላፈን ሞት የሚማርከን
መፅሐፉም አውቆ አቤል እና ቃየል ብሎ ’ሚተርከን።
ልጆቼ ጦር ሜዳ ይሄዱ ይሆን ብለሽ በሃሳብ ስትዳክሪ
እኛ ኳስ ሜዳ ነን፣ እንግሊዝ ሃይቤሪ
እናልሽ ዓለሜ፣
ለማይረባ ኑሮ ጉልበት ከማጧመን
ሰሚ የሌለው ፀሎት ሰርክ ከመለመን
ባፋንኮሎ ብሎ መተዉ ጠቀመን!
ስጋት ምን አባቱ፣ የት አባቱ ሃሳብ
ጠላልፎ ሊጥለን ወደኛ የሚሳብ
ለዚህ ከንቱ ዓለም ለምን ትለፊብን ለምንስ እንልፋ፣
ለምን ከፍ ዝቁ፣ ለምን ቀና ደፋ?
የትም በማያደርስ ምንም ጎዳና ላይ ሲጓዙ ከማደር
ከቁርጥ የተቀዳ ውሳኔ መበደር
ውሳኔ!….
የነብስ ውጪ ግቢ ትግል ሳይጎትተን
ከሞት መምጣት በፊት እንተርፋለን ሞተን።
8 Comments
ግሩም ነው
ግጥሙ አሪፍ ነው በተለይ ደግሞ ስለ ኢትዮ ታሪክን የሚገልፅ ግጥም ቢኖር የተሻለ ነው
ግጥሙን ወድጀዋለሁ
Nice
asegid tnk u…enwodihalen
በጣም አሪፍነው
በጣም ደስይላል
ሀሪፍ ነው በርታልኝ