1. ‹‹ ክፋቱ አዶልፍ ሒትለርን የዋህ የሚያስብል ነው ፣ ጭካኔው እና ግፉ ከግራዚያኒ የበለጠ ነው፣ ተንኮሉ ከሳጥናኤል የረቀቀ ነው፣ ሴራው ከቀኝ ገዢ የተወሳሰበ ነው…ይሄ ዘር ታሪካዊ ጠላትህ ነው….ያኛው ዘር መቼም የማይተኛልህ ነው፣ ካላጠፋኸው ሊያጠፋህ ነው…ካልቀደምከው ሊቀድምህ ነው›› እያለ የሚነግርህ…እዚያ…ከጋራው ማዶ… ከወንዙ ባሻገር የሚኖረው ወገንህ፤ ከአያትና ቅድመ አያትህ፣ ከአባት እና ከእናትህ ተጋብቶ እንደወለደ፣ ወልዶ እንደከበደ፣ አንተንም ከዚያኛው ወገን በማይበጠስ የደም ሃረግ እንዳዛመደ…አይነግርህም
2. ‹‹ጠላትህ ነው ጥላው…አጥፊህ ነው አትጠጋው›› ብሎ ሳያሳልስ የሚሰብክህ ወንድምህ አባት እና አያቶች ዛሬ በነፃነት ለቆምክባት መሬት ከአገር ነጣቂ ጠላት ካንተው አባትና አያቶች ጎን ለጎን ሆኖ ሲፋለም፣ ጎን ለጎን ወድቆ ከአንድ ጉድጓድ እንደገባ… አይነግርህም
3. በራሱ ልሙጥ ወረቀት፣ በራሱ ብእር ያመቸውን ታሪክ ፈጥሮ ከወንድምህ ደም ሊያቃባህ ሲያጓራ፣ ከወገንህ ሊያፋጅህ የጥላቻ ድር ሲያደራ፣ ያ…‹‹እሱ እኮ ባንተ ላብ በለፀገ፣ ባንተ መቆርቆዝ እሱ አደገ፣ ባንተ መስዋእትነት ነፃነትን ተጎናፀፈ!›› እያለ የሚነግርህ ያ… ሰርክ የማታየው ወገንህ፤ ልክ እንዳንተው….ያጣ የነጣ አፋሽ አጎንባሽ መሆኑን፣ ምድር ስትደርቅበት ዝናብ ልመና እንዳንተው ቀና ብሎ ፈጣሪውን የሚማፀን ምስኪን መሆኑን፣ ልክ እንዳንተው ዘመን ባነገሰው፣ ጊዜ ባገነነው ጨቋኝ መሪ ነኝ ባይ ወደጠርዝ የሚገፋ ፣ ስለ ቤተሰቡ የእለት ጉርስ፣ ስለ ልጆቹ የአመት ልብስ የሚጨነቅ የሚጠበብ፣ ሲሆንለት በጎደለው የሚሞላ፣ ሳይሆንለት ተስፋ ሳይቆርጥ እድሜውን ሙሉ ያቺን ጎዶሎ ለመሙላት የሚውተረተር ደሃ መሆኑን…አይነግርህም
4. ዛሬ በእሱ አርትኦት ያቀረበልህ ታሪክ፣ ዛሬ በእሱ ፍላጎት የቀመመልህ ጥላቻ ያመረረው ታሪክ እንደምኞቱ መንፈስህን ካልመረዘው፣ እንደምኞቱ ልብህን በወገንህ ላይ ካላደነደነው፣ እንዳቀደው ተዋድዶ የመኖር ስሜትህን ብትንትኑን ካላወጣው፤ አማራጭ ታሪክ አሰናድቶ፣ በአጤሪራ ለስርጭት አዘጋጅቶ ከሚስጥር ኪሱ ያስቀመጣት ‹‹አማራጭ የማፋጃ ታሪክ›› እንዳለችው …አይነግርህም
5. ያለመው ባይሳካ፣ የወጠነው ባይሰምር….የሄደበት መንገድ በአሜኬላ ቢታጠር፣ ደህንቱን ለደቂቃ እንኳን ቢጠራጠር፣ አንተና ሺህ ‹‹ተከታዮቹን›› አውላላ ሜዳ ላይ በትኖ፣ ለጅብ እራትነት ጥሎ፤ እሱ በጊዜ ባዘጋጃት ቀዳዳው ሹልክ ብሎ እንደሚሄድ…መሄድ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ጠላትህ ናቸው ካላቸው ሰዎች ተሻርኮ፣ አንደ ጴጥሮስ እንደሚያውቅህ እንኳን ሽምጥጥ አድርጎ ክዶ አሳድዳቸው ካለህ ሰዎች ጉያ እንደሚወሸቅ…አይነግርህም
6. ላንተ የሚቆረቆረቆር ሆኖ የሚታየው፣ ባንተ ችግር የሚንገበገበው መስሎ የሚቀርበው፣ ባንተ ብሶት ሆድ ባሰኝ ብሎ የአዞ እንባውነ በየመድረኩ የሚረጨው ፣ በታማኝነትህ የገነባህለት የዝና እና የሃብት ማማ ከተወዳዳሪው አክቲቪስት መብለጡን እስካረጋገጠ ብቻ እንደሆነ….አይነግርህም
7. በአንተና ጠላትህ ነው ብሎ ባቃቃረህ ወንድምህ መሃከል ባቢሎንን የሚያስንቅ ግንብ የገነባው፣ ቋንቋችሁን የደበላለቀው….ተነጋግራችሁ እንዳትግባቡ፣ ተግባብታችሁ እንዳትዋደዱ፣ ተዋድዳችሁ በጥላቻ መንግስቱ ላይ እንዳታምፁ…ብሎም በታማኝነታችሁ ትኩስ ምጣድ ላይ የሚጋገረውን ወፍራም እንጀራውን እንዳታስቀሩበት መሆኑን…አይነግርህም
8. ዛሬ አንተን ክብሪት አድርጎ የሚለኩሳት እሳት ነገ ሰደድ ሆና አንተን፣ ወገኖችህ እና ጠላት ነው ብሎ ያሳመነህን ወንድምህን ባንድነት ሲበላ፤ እሱና መሰሎቹ ግን ለዚህች ቀን ባበጇት ጎሬ፣ ለመከራ ቀን በቀደዷት ማምለጫ ሹልክ ብለው እንደሚያመልጡ፣ ሽል ብለው እንደሚሰወሩ፣ ብን ብለወው እንደሚጠፉ…አይነግርህም
ከሁሉ በላይ ግን….ዛሬ በየአደባባዩ እየማለና እየተገዘተ ‹‹እሞትልሃለሁ›› ሲልህ ‹‹ አንተ ግን ቀድመህ ትሞትልኛለህ›› ማለቱ እንደሆነ ፈጽሞ አይነግርህም….
One Comment
ያልነገሩንን ቀድመን በማወቅ ከሚነግሩን ሃሰተኛ፣ ሤረኛና መርዛማ ነገራቸው ራሳችንን ለመጠበቅ እንትጋ።