Tidarfelagi.com

አያና ነጋ (የእስክንድር ነጋ ወንድም አይደለም ☺) 

ሰው ራሱን የተፈጥሮ ማእከል አድርጎ ይመለከታል፤ለተንኮል። ያልተመቸውን እየቀጠፈ፣ የተመቸውን እያገዘፈ ለመኖር።
ለሰው ሲባል፣በሌሎች ፍጡራን የሚደረገው ብዙ ነው።

ይሄን የመሰለው በዓል አንዱ መስኮት ነው።
ዓመት በዓል ብዙ እንስሳት የሚገደሉበት ሰዋዊ ስነስርዓት ነው። ሰው ግን እንስሳትን ዝም ብሎ አይገልም። መጀመሪያ ህይወት እንጂ ነብስ የሌላቸው ፍጡሮች አድርጎ ተረት ያወራባቸዋል። ወይም በሃይማኖት ተረኮች ውስጥ «ቢሞቱም ግድ የለ»፣ «ለመስዋት ነው የተፈጠሩት» ዓይነት ትረካ ይጭንባቸዋል። በሸሆና እየለየ ወደ ቢላ ይነዳቸዋል። ለሰው ልጅ ፍላጎት የተፈጠሩ፣ ዓላማ የለሽ ተቅበዝባዥ ፍጡሮች ይሆናሉ።

በኖርኩት እድሜ የገባኝ አንድ ሰዋዊ ባህሪ፣የሰው ልጅ ወይ በተረት አሊያ በፕሮፖጋንዳ ማነጣጠሪያ ሰበብ ሳይፈጥር እርምጃ የማይወስድ ፍጡር መሆኑ ነው። አምባገነን የሚባለው መንግስት ወይ መሪ ዝም ብሎ አይገድልህም።
አሸባሪ፣ ሀገር ከሃዲ፣ ፀረ ህዝብ፣አብዮት ቀልባሽ፣ አድሃሪ፣አናርኪስት፣ ህገመንግስት ለመናድ የሚንቀሳቀስ ወይ የሚቅለሰለስ፣ የእንትን ቡችላ የሚል ስም መጀመሪያ ይሰጥሃል።ዝም ብሎ እኮ ሊገል ይችላል፣ ጊዜ እና መሳሪያው አለው።
«ሳታማሃኝ ብላ»ለሰው የሚሰራ አይመሰልም። ከእንስሳ እስከ መሰል ፍጡሩ ሲገድል አመሃኝቶ ነው!

የትም ብትሄድ የምትሰማው ይሄንን ነው። ዓለም የተፈጠረው እኛ እንኖርበት ዘንድ ነው። ውሾች ምንድናቸው? አጃቢዎች!
በጎች ምንድናቸው? የሰው ልጅ በዓሉን ያደምቅባቸው፣ መስዋዕቱን ያቀርብባቸው ዘንድ ከአምላኩ የተሰጡ ሥጦታዎች!

እንስሳት ሁሉ የሰውን ኑሮ ድምቀት ለማጀብ የተጎለቱ ምድራዊ ክስተቶች ይሆናሉ።

ፆሙን ይፈታባቸዋል፣ ፀቡን ያርቅባቻዋል፣ ደም አፍሶ ጉማ ይፈፅምባቸዋል (ሰበብ እኮ ነው ምንም አያገናኘውም) … እንዲህ የበዓሉ የመጀመሪያ ተጣይም ያደርጋቸዋልም።

ይሄን ስል ለእንስሳቱ አዝኜ አይደለም። እንዳላዝን ተደርጌያለሁ። አንድ ከብት ሞተ አልሞተ ደሞ፣ ሰው ነኛ!! ከራሱ ውጪ ያለ ዓለም ከንቱ የሚመስለው ፍጡር ዘር። በትረካው፣ ከመላዕክት እንኳን ራሱን የተመረጠ አድርጎ ተረት የሚሰራ ነገድ ቤተሰብ ነኝ!

እርድ ይከናወናል። ቤተሰብ ይሰበሰባል። ደስ ብሎን ማዕድ እንቆርሳለን። እልፍ ቤቶች እንዲያ ይሆናል። ያን መሰባሰብ እንስሳቱ በሞታቸው ይባርኩታል። አላዝንም።ማናችንም አናዝንም። እንዳናዝን ተደርገናል። ሰው ነና። ከቢላው በፊት በተረት ካራው የሚጥል ፍጥረት ቤተሰብ።

ደስታን በአጉል ማራቀቅ አለማራቅ ነው። ፈገግ ያለ በዓል ማሳለፍ። ደስታው በእንስሳት መስዋትነት ቢገኝ እንኳን ደግ አደረገ የሚል መልስ በቂ ሊሆን ይችላል 

ሌላው አጋፋሪ ቢቀር እንኳን በዓሉን ደስ ብሎን እናከብራለን ለማለት ነው፤ ምን ታመጪያለሽ አዳሜ? 

መልካም በዓል!

One Comment

  • ገረመው commented on May 5, 2019 Reply

    በእውነት ፅሁፎችህ ይመቹኛል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *