በምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች ባሕል የኑግ ክምር አዳቦል ይባላል፡፡ የኑግ ክምር ቀላል በመሆኑ ነገረ ቀላል የሆነውን ሰው አዳቦል ይሉታል፡፡ እነርሱ አዳቦል የሚሉት ነገረ ቀላል ሰው ሦስት ነገሮች የሌሉትን ነው፡፡ ወይ ሲናገር አዲስ መረጃ የማይሰጠውን፣ ወይም ዕውቀት የማያዳብረውን ወይም ደግሞ ለሁኔታው የማይመጥን ነገር የሚናገርውን፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ማዕከል ዓመታዊ በዓል ምሽት ላይ በኛ ጠረጲዛ ዙሪያ የነበሩ ምሁራን ይህንን የገበሬውን ነገር ሲሰሙ አዳቦልነት በሦስት ነገሮች የተነሣ ሊመጣ ይችላል ሲሉ ሐሳብ ሠነዘሩ፡፡ የመጀመሪያው ለንግግርና ለጽሑፍ ካለመጠንቀቅ ነው፡፡ ለማን፣ ምን፣ እንዴት ልናገር ብሎ የማያስብና እንዳመጣለት ብቻ የሚናገር ወይም የሚጽፍ ሰው ንግግሩ ወይም ጽሑፉ አዳቦል ይሆናል፡፡ ቃላት ይደረደራሉ፤ ዐረፍተ ነገሮች ይሰካካሉ፤ ዐናቅጽ ይሰደራሉ እንጂ አእምሮን ያዝ ወይም ልብን ስልብ የሚያደርግ ፍሬ ነገር አይገኝበትም፡፡ በውስጡ ንጥረ ነገር የሌለው ሆድ የሚሞላ ምግብ እንደመብላት ነው፡፡ ሆድን ይሞላል እንጂ ለሰውነት ድጋፍ አይሆንም፡፡ ሰምተው ወይም አንብበው ሲጨርሱ የሚይዙት ነገር አይኖርም፡፡ ወፍጮ ቤት ደርሶ የመጣ ሰው ቢያንስ ጥቂት ዱቄት ሳይነካው እንደማይመጣ ሁሉ አንድን ነገር የሰማ ወይም ያነበበ ሰውም ጥቂት ነገር ሳያገኝ መቅረት የለበትም፡፡
ለሰው የሚገባው፣ ግልጽ የሆነና ፍሬ ያለው ነገር ለመናርና ለመጻፍ የቋንቋ ችሎታም ያስፈልጋል፡፡ ቡናን እንዲጠጣ የሚያደርገው ቡናነቱ ብቻ ሳይሆን አፈላሉና አቀዳዱም ጭምር ነው፡፡ ሳይሰክን የተቀዳ ቡናና መግለጫ ያጣ ሐሳብ አቅራቢ አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም የሚሰጡን ነገር እያላቸው አሰጣጡን አያውቁምና፡፡ የቋንቋ ችሎታ ማለት ጉዳዩን እስከ ጥግ ድረስ በመናገሪያው ቋንቋ አልቆ ለመናገር መቻል ነው፡፡ አልቆ ሲልም ይዘቱ በሚፈልገው ደረጃ ለማለት ነው፡፡ ጉዳዩን በምሳሌ፣ በዘይቤ፣ በከሳች ቃላትና ነገሩ እንዳይረሳ በሚያደርግ አገላለጥ ለማቅረብ መቻል፡፡ ሰሚና አንባቢ ሊገባው በሚችል መጠን እንዲረዳው ሆኖ ያልቀረበ ነገር ቃላትን መስማትና ማንበብ ብቻ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ጠረጲዛ ላይ ምግቡን ሁሉ እንደ ተራራ ከምሮ እንደማቅረብ ያለ፡፡ ምንም እንኳን ምግቡ ጣፋጭና በባለሞያ የተሠራም ቢሆን ከክምር ውስጥ ምግብ እየጎረጎሩ ማውጣት ግን አማራጭ ላጣ ሰው ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ያልረታን ንግግር የሚያዳምጠውና ያልበሰለን ጽሑፍም የሚያነበው አማራጭ ያጣው ሰው ብቻ ይሆናል፡፡
የሀገሬ ሰው ጎመን ብቻ መብላት ዐቅምም ጤናም እንደማይሰጥ ያውቃል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይለግማል›› የሚለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ንግግር የሚያደርጉ ወይም የሚጽፉ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ ጸሐፍትና የእምነት መሪዎች ሰው የሚሰማቸው ወይም የሚያነባቸው አማራጭ ስለሌለው ነው ወይስ ገብቶት ነው? የሚለውን የሚለዩበት መንገድ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ‹‹እኛስ ይህቺን ክረምት ወጣናት በመላ በኩርማን እንጀራ ጎመን ተጠቅልላ› እንዲል ገበሬ፡፡ ሌላ አማራጭ አጥቶ ክረምቱን በጎመን ብቻ እንዳለፈው ሁሉ፣ ሰምቶን እየሄደ ያለው አማራጭ ከማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ባለሞያዎችና ባለ ሥልጣናት ለንግግራቸውና ለጽሑፋቸው ተገቢውን የቅድሚያ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፡፡ እነርሱ ነገሮችን የሚጠሩበት ስያሜ ቃል (terminalogy) በኋላ የሚዲያው ትርክት ሆኖ ስለሚቀጥል እንዳመጣ መሰየምን ልማድ ማድረግ የለባቸውም፡፡ ያለበለዚያ ንግግራቸው ለሕዝቡ አዳቦል ይሆንበታል፡፡ አንገቱን እየነቀነቀ የማያደምጠው፡፡ ቢነቀንቅም ለትዝብት ያህል የሚነቀንቀው፡፡ መናገራቸው እንጂ ንግግራቸው የማያስታውሰው፡፡
ሁለተኛው የአዳቦል መነሻ ደግሞ የማያውቁትን ወይም ያላመኑበትን ነገር ሊጽፉ ወይም ሊናገሩ ሲሞክሩ ነው፡፡ እንዲያውም በሀገራችን አንዳንድ ባለ ሥልጣናት እ- እ- እ- እያሉ አንጀት የሚጎትት ንግግር የሚናገሩበት ምክንያት፣ አንድም ያላመኑበትን ወይም የማያውቁትን አለያም ያልተረዱትን ነገር ሊናገሩ ስለሚፈልጉ ነው የሚል ምሳሌ ቀረበ፡፡ አንድን መረጃ አንብቦ ወይም ሰምቶ፣ ከዚያም ተረድቶ፣ በመጨረሻም ቅርጽ አስይዞ ለማውጣት የሚጠይቀው አእምሯዊ ሂደት አለ፡፡ በጉዳዩ ላይ ማሰብ፣ ለራስ መተንተን፣ በራስ ቋንቋ መረዳትና ለማቅረብ መቻልን ይጠይቃል፡፡ እህል ያገኘ ሁሉ ምግብ አይሠራም፣ ምግብ የሠራ ሁሉ ምግብ አያቀርብም፡፡ እህል ያገኘ ምግብ ለመሥራት፣ ምግብ ሠሪም ምግብ ለማቅረብ ሦስቱ ሞያዎች ያስፈልጉታል፡፡ እህሉን ማወቅ፣ ምግብ አሠራሩን ማወቅና ምግብ አቀራረቡን ማወቅ፡፡ ንግግርና ጽሑፍም እንዲሁ ነው፡፡ ጉዳዩን አስልቶ መስማት ወይም ማንበብ፤ አጥልቆ መረዳትና አሣምሮ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡
አንዳንድ ጋዜጠኞቻችንና አሠልጣኞቻችን ከተለያዩ ምንጮች መረጃዎችን ወስደው ሲያቀርቡ የሚያጋጥማቸው ችግር ከዚህ ይመነጫል አሉ ሊቃውንቱ፡፡ አንዳንዴ በሰላ ሁኔታ አይቃርሙትም፣ ወይም በሚገባ አይረዱትም፣ አለበለዚያ ደግሞ እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው አያስቡበትም፡፡ ምናልባት ያገኙት መረጃ አሳዝኗቸዋል፣ አስደስቷቸዋል፣ አስገርሟቸዋል፣ ወይም ደግሞ ከፕሮግራማቸው ጋር ሄዶላቸዋል፡፡ ነገር ግን በውስጣቸው አላመነዥኩትም፡፡ ጥሬውን እንደሆነ ነው ያስቀመጡት፡፡ እናውጣህ ሲሉት ቃል ያጥራቸዋል፡፡ እነርሱ ያገኙትን መረጃ ያህል ለኛ ማስተላለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ያኔ ነው ‹ቃላት ያጥሩኛል፣ ልዩ ነበር፣ ፐ፣ ጉድ ነው፣ አሪፍ ነው፣ ነፍስ ነው፣ የጸዳ ነው፣ አስደናቂ ነው› የሚሉ ነገሩን ከመግለጥ ይልቅ ስሜትን ብቻ የሚገልጡ ቃላት የሚበዙባቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ‹እንትን፣ ምን መሰለህ፣ ያ ነገር፣ እና፣› የሚሉ ቃላትን በመደጋገም መረጃ ሳይሰጡን ይቀራሉ፡፡ ወይም ደግሞ አንዱን ነገር ሰባት ጊዜ ይደጋግሙትና ያሰለቹናል፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ዕውቀት አጠር ከመሆን የሚመጣ ነው፡፡ ስለምትናገረው ወይም ስለምትጽፈው ነገር በንባብ፣ በትምህርት፣ በልምድ ወይም በሌላ መንገድ የተገኘ የተከማቸ ዕውቀት ከሌለህ ያላስገባህውን ልታስወጣ አትችልምና ነገርህ ሁሉ አዳቦል ይሆናል፡፡ ከነጠፈች ላም ወተት እንደመጠበቅ ያለ፡፡ ስለ አንድ ነገር በልዩ ሁኔታ ያጠኑ፣ በዚያ መስክ የሠሩ ወይም ያነበቡና የሠለጠኑበት ሰዎች ይጻፉ ወይም ይናገሩ የሚባለው ወደ አእምሯቸው ባስገቡት መጠን ውኃ ያዘለ ነገር ሊያወጡ ስለሚችሉ ነው፡፡ ‹የምትናገረው ነገር ከሌለህ ዝም በማለት እርዳኝ› የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው አሉ አንደኛው ሊቅ፡፡ ‹ከራበው በሬ ሥጋ አይጠበቅም› ይላሉ አፍሪካውያን› አሉ ሌላኛው፡፡ ዕውቀት ሲያጥርህ ንግግርህና ጽሑፍህ ትርጉም በሌላቸው ቃላት የታጀቡ ይሆናሉ፡፡ ከልክ በላይ የሆኑ አጎላማሾች ይታጨቁባቸዋል፡፡ ‹‹ከተማዋ በአንጸባራቂ ድል ታጅባ በፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች› ዓይነት ይሆናል፡፡ ‹አንጸባራቂ› ና ‹ፈጣን› ምን ያህል ናቸው? እዚህ ውስጥ መጠኑን መለካት አትችልም፤ ሥራህ እንደ በቀቀን ማስተጋባት ብቻ ይሆናል፡፡ ሐሳቡን በራስህ መንገድ ማቅረብ ስለማትችል በአሰልቺ ቃላት(ጃርገን) ትሞላዋለህ፡፡
አዳቦልነት በትምህርታችን፣ በንግግራችን፣ በዜናዎቻችን፣ በጽሑፎቻችንና በመግለጫዎቻችን ውስጥ እየበዛ በሄደ ቁጥር የመልዕክት ልውውጡ የተሰበረ፣ አንጆ አንጆ የሚል፣ ችክታ የበዛበት፤ ተግባቦት የሚያጥረውና ሐሳቡ የነጠፈ ይሆናል፡፡ ይኼ ደግሞ የዕውቀት ሽግግርን፣ የሐሳብ ምይይጥን፣ የመልእክት ዝውውርን ይጎዳል፡፡ ‹በተለይም ደግሞ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የእምነት መሪዎች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ጸሐፍት፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችና ሥልጠና ሰጭዎች በአዳቦል በሽታ እንዳይጠቁ ለዕውቀት፣ ለአቀራረብና ለምናቀርብበት ማኅበረሰብ ተገቢውን ቦታ መስጠት ይገባናል› ሲሉ ምሁራኑ ውይይቱን ዘግተውታል፡፡
One Comment
ጥሩ ገንቢ ፅሁፍ ነው፡፡ ሁሉም ግን በሁሉ የተዋጣለት መሆን አይችልም፡፡ እንደየሞያውና እንደተሰጥዎ ነው፤ የያዝነውን አውቀን በመተጋገዝ ለውጤት መትጋት ነው፡፡