ላልጀመርከው ስኬት —የማይቆም ጭብጨባ
ማያቋርጥ ፉጨት
እያደር ሚገልህ — ቀን ያጣፈጠውን
መርዝ እንደመጎንጨት
እንደ ሱፍ አበባ
ጭለማን ተኳርፎ
ፀሀይ ከሚመስል መብራት ስር መሰጣት
ለምትወደው ስትል ሚያፈቅሩህን ማጣት
አንዳንዴ
ጥሩ
በጣም ጥሩ
እጅግ በጣም ጥሩ
እንደ ፃ‘ፊው ሳይሆን
እንደ አነባበብ ነው ሚገለጥ ሚስጥሩ
ወደ ላይ ሚሄድ ሰው
ወደታች ማንበቡን አትጠራጠሩ
አልጠራጠርም
ውሸት የሰቀለው በእውነት መሳቡን
ቁልቁል ሚወርድ ሰው ወደ ላይ ማንበቡን
* * *
በአጨብጫቢ አሻራ
በፉጨት ገጀራ — በቆራጮች ስለት
በአቋራጭ መንገድ
ዝና ላይ የወጣህ — ስልጣን የያዝክ እለት
ስድብ ይመስልሀል
“እጅግ” ያልጨመረ — “በጣም ጥሩ” ማለት
* * *
የዝናውን ጣሪያ
የስልጣኑን ጣሪያ — በአንድ ሌት ስትደርሰው
ጠላት ይመስልሀል
“በጣም” የቀነሰ — “ጥሩ” ነህ ሚልህ ሰው
* * *
ሙቀት ቢፈልግም
እድገቱን ሚያፈጥን — በሕይወት ሚያሳድረው
ቀስ በቀስ ነው እንቁላል
በእግሩ ሚሄደው — በስኬት ‘ሚበረው
* * *
ዳዴ ዳዴ ሳትል !
ወፌ ቆመች ሳንል ! !
ባልጠነከረ ሀሳብ
በመዳህ አእምሮ
በጭብጨባ ቆመህ — በምኞት ተራምደህ
ወዴት ልትደርስ ነው
ጡት ሳትጠባ አድገህ — አርጅተህ ተወልደህ
አንተ ህዝቡን ስትለምደው ህዝቡ አንተን ሲያጣጥም
እንዲህ ስታድግ ነው ፍሬህም የሚጥም
* * *
በዝግታ አኝከው አላምጠው ግዴለም
የተዋጠ ሁሉ የሚያጠግብ አይደለም
* * *
የፉጨት ጋጋታ የጭብጨባ እንቅፋት
ስንቶቹን አይተናል እያነሳ ሲጥል
እመነኝ ስክነት ነው ከክስመት የሚያድን
ከክስረት የሚያስጥል
* * *
አላስተዋልክ እንጂ
ሁለት እጅ ተጋጭቶ ጩኸቱን ሲያደምቀው
ጭብጨባ መስሎት ነው የቢንቢ ዘር ሚያልቀው