እዚህ ኮንዶሞኒየማችን አራተኛ ፎቅ ላይ አንዲት ቆንጆ ልጅ አለች….ቁንጅናን ሳይሰስት የሰጣት እሷም ሳትሰስት ውበቷንና ሽቶዋን ለብሎኩ ነዋሪዎች በቸርነት የምታሳይ ቆንጆ ! እውነቴን ነው …አንዴ ስታልፍ ከአንደኛ ፎቅ እስከአራተኛ ፎቅ ደረጃው ሁሉ የሷን ውድ ሽቶ ይታጠንና ባለአራት ፎቅ ገነት ይመስላል ….በአካል ከተገጣጠማችሁ ደግሞ ከፊቷ ይሆን ከኋላዋ ከታች ይሁን ከላይ አማላይ ውበቷ ከአራቱም መዓዘን እኩል አስደማሚ!
መቸም አከራይ ክፉ ነው እሷንም ግምት ውስጥ በማስገባት ኪራይ ሲጨምሩ ‹‹አይንም ራህመት ነው›› ብለን አርፈን እንጨምራለን፡!! እንደው የፈጣሪ እዝነቱና ትእግስቱ በዝቶ እንጅ ‹‹ያየ የተመኘም አመነዘረ›› በሚለው ህጌ ቅጣት ጀምሪያለሁ ቢል መጀመሪያ መብረቅ የሚወርደው እኛ ብሎክ ላይ ነበር !!
እና ትላንት ማታ ይች ልጅ ታመመች ተብሎ ድፍን የብሎኩ ወንድ ‹‹ኢትዮጲያዊነት በጎነት›› ብሎ ለእርዳታ ታመሰ … መኪና ያለው መኪናውን አስነስቶ የሌለው የኮንትራት ላዳ ጠርቶ ሆስፒታል ካልወሰድንሽ እያለ ታመሰ ወንዱ ! ልጅቱ ሞልቀቅ ባለ ንግግር ‹‹ደህና ነኝኮ ረዥም ሰዓት ተኝቸ ፊልም ሳይ ቆየሁና ስነሳ እግሬን ትንሽ ደንዝዞኝ ነው ›› ብትል ማን ይስማት
‹‹እንዴ ድንዛዜ ቀላል ነገር ነው እንዴ ታይፎይድ ሊሆን ይችላል›› ይላል አንዱ…ሌላው አተት ቢሆንስ …ብቻ ወንዱ ግድ ካልታመምሽ አይነት ችክ አለ! እኔ በበኩሌ የህመሙን መንሰኤከሰማሁ በኋላ ለእርዳታ ተቀላቀልኩ ከዛ በፊትማ ጥጌን ይዠ በንቃት ጉዳዩን እየተከታተልኩ ነበር …ምን ላድርግ ልጅቱን የማይሸኛት አፍሪካዊ ወንድ የለም …ያውም በኮር ዲፕሎማት ታርጋ መኪና ነዋ! ሴኔጋላዊ ታንዛኒያዊ ዛየራዊ ናይጀሪያ ….እንደውም አንድ ቀን ጆርጅ ዊሃን የሚመስል ላይቤሪያዊ መኪና ውስጥ ሲስማት አይቻለሁ ….ታዲያ ‹‹ጉድ ባይ ኪስ›› ብሎ እንደዛ በዛ የአደጋ ጊዜ የውሃ ላይ መንሳፈፊያ በሚያህል ከንፈር ሲያፍሳት አይቸ ታመመች ሲባል ኢቦላ ብጠረጥር እና ለእርዳታ ብዘገይ ይፈረድብኛል?
እውነቴን ነው ልጅቱ ግቢያችንን የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት እንዲመስል የተለያዩ አገር ተወካዮችን ወደግቢያችን በማምጣት ያደረገችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው …. እንደውም አንድ ቀን ቤት ያከራዬዋት ሰውየ ‹‹ቤቴን ልቀቂ ›› ብለዋት ስም ወጣላቸው ‹‹ጋዳፊ›› ተባሉ …የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከዚህ ኮንዶሚኒየም ለቆ ወደሌላ ይሂድ እንዴት ይባላል ተባለ …እንደውም የግቢው ኮሚቴ ሊቀመንበር መላኩ ኮስተር ብሎ ታሪካዊ ንግግር አደረገ . . .
‹‹ ….የማንዴላን ልጆች ለስብሰባ ሲመጡ ማን ተቀብሎ አስተናገዳቸው? ቤቲ ናት …የጋዳፊን አጃቢዎች ድሪአና ጎርጎራ ለብሶ ማን ተንከባከባቸው ?ቤቲ ናት …ጋዳፊ ለአገራችን ጥሩ አመለካከት አይኑራቸው እንጅ ለአገራችን ቆነጃጅቶች ያላቸው ምኞት ከፍተኛ ነበር …የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ይነሳ ቢሉም አጃቢዎቻቸው ከቆነጃጅቶቻችን መቀመጫ አይናቸውን አያነሱም ነበር …ታዲያ ቤቲ ከዚህ ግቢ ትውጣ ማለት የቱሪስት ፍሰቱንመገደብ አይሆንም ?›› አከራዩ ሰውየ ጉዳዩ ፖለቲካ መስሏቸው እንደውም ከዛ በኋላ ኪራይ ካልቀነስኩ አሉ እየተባለ ይታማል!
እና ይች ቤቲ ታመመች ተብሎ ግቢው ሲታመስ ሁላችንም ልንረዳ ስንራወጥ ማን ገረመህ ብትሉኝ ተስፋየ !!…ከምር ገርሞኝ ልሞት …ሁለት አይነት ነጠላ ጫማ አድርጎ ዘሎ ወጣና …ያችን ድክም ያለች ሃችባግ መኪናውን ለማስነሳት ቁጭ ብዲግ ይል ጀመረ …ኮፈኗን ከፍቶ የነዳጅ ፕላስቲኩን አፉ ላይ ደግኖ መሳብ ጀመረ …እንደውም አንድ ሁለት ጉንጭ ነዳጅ አፉን እየሞላ ወደውጭ ተፋ …ኧረ ይሄ ሰው ‹‹ለበጎነት›› ሲል ነዳጅ ጠጥቶ ሊሞት ነው ብየ እስካስብ ….
ለምን ከዚህ ሁሉ ወንድ እርዳታ የተስፋየ ገረመህ ትሉኝ ይሆናል …ጥሩ ጥያቄ ነው ….ተስፋየ የዛሬ ስድስት ወር ሚስቱ ላይ የሰራውን ከዚህ በፊት ነግሪያችሁ ነበርኮ …
አንድ ቀን በረንዳ ላይ ቁሜ እያለ ሁለት እናቶች ቁመው ያወራሉ ….ጎረቤቶች ናቸው
‹‹ማታ አያልነሽ ምጧ መጥቶባት ታክሲ ፍለጋ ስንራወጥ አመሸን አንቡላንሱም ለመጥራት ኒትወርክ እምቢ አለ ›› ይላሉ አንድኛዋ
‹‹አሃ ….ባሏ ተስፋየ መኪና አለው አይደለም እንዴ ››ሌላኛዋ በግርምት ጠየቀች
‹‹ ኧረ ተይኝ …‹‹ሚስትህ ምጧ መጣ ›› ተብሎ ቢደወልበት …ኳስ እያየሁ ነው ረፍት ሲወጡ እመጣለሁ አለን ››
‹‹ ቱ ! ለማስረገዙ ጊዜ እስኪገለበጡ ይከንፋሉ …ምን ይሻላቸዋል እነዚህ ወንዶች ››
እና ዛሬ ተስፍሽ ለዚች ቆንጆ ልጅ እንዲህ ነዳጅ ጠጥቸ ካልሞትኩ ሲል ገርሞኝ ልሞት …ደግነቱ ወዲያው መብራቱ ግቢውን ፀሃይ የወጣ ያስመሰለ የዲፕሎማት ታርጋ ያለው ግዙፍ እና ውድ መኪና ተከሰተ …ስትሞላቀቅ የነበረችው ጎረቤታችን ቤቲም ከምኔው እንዳጠለቀችው ያላየነውን የራት ለብስ ለብሳ በተረከዘ ረዥም ጫማዋ እየተውረገረገች በሽቶዋ የተሰበሰበውን ጎረቤት እያጠነችው …
‹‹ቴንኪው አስጨነኳችሁ እነሱ ሆስፒታል ያደርሱኛል›› ብላን ስትሄድ ሁላችንም ደንዝዘን ቆምን ….እንግዲህ ድንዛዜ የታይፎይድ ምልክት ነው ያለው ጎረቤታችን ይሄን ወረርሽኝ ምን እንደሚለው እንጃ! የሆነ ሁኖ ታች የቆሙትን ባለውድ መኪና የሆነ አፍሪካ አገር ዜጎች እየተመለከትኩ ቤቲም‹‹ወደውዱ መኪና በሰርዓት በር ተከፍቶላት›› ስትገባ እያየሁ ለራሴ እንዲህ አልኩ ‹‹አፍሪካዊነት በጎነት››
‹‹ቱ ›› የሚል ድምፅ ሰምቸ ዞር ብል ተስፍሽ ነው ….ኮፈኗ የተከፈተች መኪናው ፊት ቁሞ እንደማይክ አፉ ላይ በደቀነው የነዳጅ ማስተላለፊያ ጎማ ለመጨረሻ ጊዜ በአፉ የሳበውን ነዳጅ እየተፋ …!! ከተስፍሽ ቤት የህፃን ልጅ ለቅሶ ይሰማል !!
One Comment
I like this!