ምን አባቴ አቀበጠኝ ቀድሞውንስ? ምን ስሆን ያልሆንኩትን አወራሁ? ይሄው ለደቂቃ በተናገርኳት ነገር ለሳምንታት እየተሳቀኩ ነው፡፡ ሰፈር ሰላም ብዬ ከቤቴ ወጣ ብል፣ የሆነ ድምፅ ከኋላዬ “ኢንጂነር” ሲል ያሾፍብኛል- ኢንጂነር! “ሌባ! …ሌባው” ከመባል በላይ ያሳቅቀኛል፡፡
ህፃናት፣አዋቂዎች፣ የሰፈር ውስጥ ተራቢዎች፣ተመርቀው ስራ ያጡ ሰፈር ዋዮች “ኢንጂነር¡ ኢንጁ¡…” ይሉኛል በመሳለቅ- ስቅቅ!!! ምን አሳቃቀኝ? ከአስረኛ ክፍል ያላለፍኩን ሰው፣ ኢንጀነር እያሉ ሲሳለቁብኝ እንደምን አልሳቀቅ? ጥያቄው ኢንጂነር ሳልሆን ለምን ይሉኛል ነው….
ከወር በፊት በአንድ መከረኛ ቀን ነው፡፡ የሆኑ ጋዜጤኞች የምንሰራበት ቦታ መጡና ሊያነጋግሩን እንደሚፈልጉ ነገሩን፡፡ ብዙው ሰራተኛ ባይስማማም እኔና ትንሽ ቢጠየዎቼ ተስማማን፡፡ ኮብልስቶን መጥረብ ነው ስራዬ፡፡ ታዲያ ትልልቅ ባለስልጣናት በሚቀርቡበት የቴሌቪዥን ጣቢያ “ታይ እናሳይህ” ስባል እንቢ ማለት ነበረብኝ? እኔ እኮ በሺ በሚቆጠሩ ሰዎች ቀርቶ፣ ከቁጥር በማይገቡም ሰዎች ቢሆን መታየት የሚናፍቀኝ ሰው ነኝ፡፡ እና ታየሁ፡፡ ችግሩ መታዬቴ አልነበረም፡፡ በታየሁ ሰዓት እኔን ያልሆነ፣ ኑሬዬን ያልመሰለ፣ የቴሌቪዢን ጣቢያውን ያስደሰተ፣ የሰፈሬን ሰው ያበሳጨ ንግግር ተናገርኩ… አዎ ቃል በቃል እንዲህ ነበር ያልኩት፤
“… የሚገርምህ እኔ በኢንጂነሪንግ ትምህርት በጥሩ ውጤት ባለፈው ዓመት ነው የተመረኩት፡፡ ነገር ግን ተመርቄ ስራ እስኪመጣ ቁጭ ብዬ መጠበቅ እንደሌለብኝ ተረዳሁ፡፡ እናም መንግስት ስራ ለሌላቸው ዜጎች ባመቻቸው እድል መሰረት የኮብል ስቶን በመጥረብ በቐን ከፍተኛ የሚባል ገቢ እያገኘሁ እገኛለሁ፡፡ …. እውነቴን ነው የምልህ አሁን በተማርኩበት ሙያ እንኳ ስራ ባገኝ ይሄን ስራ የምተወው አይመስለኝም፡፡
…. ሁል ግዜ በጣም የሚያሳዝነኝና የሚያበሳጨኝ ነገር አለ፡፡ ለምንድን ነው ወጣቶች ተመርቀው ቁጭ የሚሉት? መንግስት ውጤታማ የሚሆኑበትን ስራ አመቻችቶላቸዋል፡፡ ሰርተው እንደመለወጥ ለምን ሁሉን ነገር ከመንግስት ይጠብቃሉ? መንግስት ለስንቱ ስራ ሰጥቶ ይችላል? ይሄ ስንፍናችንን ሌላው ላይ ለማላከክ ካልሆነ፣ምንም ሊሆን አይችልም፡፡…”
ይሄን ስናገር ጋዜጠኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጌ ሾሜሃለው ያልኩት ይመስል፣ ለደርዘን ሰዎች የሚበቃ ፈገግታ ከንፈሩ ላይ ሲራወጥ ነበር፡፡ ከቀረፃው በኋላ እራሱ ማሳ ጋብዞኝ ነው የሄደው፡፡
ፕሮግራሙ ተላለፈ፡፡ ንግግሬ ተኳኩሎ ቀረበ፡፡ ጋዜጠኛው ፕሮግራሙን ስለ እኔ ብቻ የሰራ ይመስል ስሜን ደጋግሞ እያነሳ ለማስታወስም ደግሞ ለማውራትም የሚከብድ ብዙ ነገር አወራ፡፡ ፕሮግራሙ በተላለፈ ምሽት ደስ ብሎኝ ወደቤቴ ገባሁ፡፡ ወደተከራየሁበት ግቢ ስገባ፣ አከራዬ እትዬ ስንቄ የማይሰማ ነገር ስላጉተመቶሙብኝ ትንሽ ቅር አለኝ፡፡ ፕሮግራሙን አላዩት ይሆን እንዴ? ቢያዩት እማ በአክብሮት ሰጥ ለጥ ብለው ነበር እጅ የሚነሱት፡፡ አይ ባያዩት ነው፡፡ ምን አገባኝ፣ ሌላ ስንት ሺ ህዝብ ያየው የለ- ደሞ ያዩ ይነግሯቸዋል ባያዩትም፡፡ እያፏጨሁ ገብቼ ተኛሁ፡፡
ከዚህ ቀን በኋላ ነው ሁሉ ነገር የተበላሸው፡፡ ጠዋት ለስራ ስወጣ ያምርልኛል ብዬ የተናገርኩት የሹፈት ስም ሆኖ ጠበቀኝ፡፡ የተናገርኩትን የሰሙም ያልሰሙም እየተቀባበሉ ይሳለቁብኝ ያዙ፡፡ መውጫ መግቢያ አጣሁ፡፡ በተለይ ተመርቀው ዉሏቸውን ሰፈር ያደረጉ፣ ሰፈር ዋዮች እኔን መስደብና ማንጓጠጥ ስራቸው አደሩጉት፡፡ ከአስረኛ ክፍል ንቅንቅ አለማለቴን ሙሉ ሰፈሩ ያውቃል፤ አምስት ዓመቴ እዚህ ሰፈር …..ልጆች ከትልልቆቹ አፍ የነጠቁትን የጋለ ተረብ ሳይቀዘቅዝ ይወረውሩበረኝ ያዙ፡፡ ምነው ባለፈው ለቡሄ ጭፈራ የመጡ ጊዜስ ቢሆን፤
እዛ ማዶ ሆ!
ጭስ ይጨሳል፣ሆ!
የኔማ ኢንጂነር፣ ሆ!
ቤት ይቀልሳል፣ ሆ!
በዛች ቤት ውስጥ፣ ሆ!
ኖሬ ኖሬ፣ ሆ!
እሞታለሁ፣ ሆ!
ተከብሬ፣ ሆ!
…በል ፍጠን ፍጠን፣ ሆ!
ጨርስልኝ፣ ሆ!
እንዳንተ ስዋሽ፣ ሆ!
ጅብ አይብላኝ! ሆ! …
አዘንኩ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ ባይኖረኝም በዚህ እንኳን ይቅር ቢሉኝ ብዬ ባይኖረኝም ሰባት ብር ከኪሴ አውጥቼ ሰጠኋቸው፡፡ ቢሆንም የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡
ባለፈው ደግሞ እትዬ ስንቄ፣ ስለማድቤታቸው በአንድ ጎን መፍረስ ለጎረቤታቸው በአጥር ያውራሉ፡፡ ጎረቤቷ ሆዬ፤
“ታዲያ ምንሽ ይጎዳል አንቺ፣ ቤትሽ እንደሁ የኢንጂኒየር መዓት ነው ያለው… እንወልስልሽ ማድረግ ነው እንጂ” -እኔው መሆኔ ነው እንግዲህ “መዓቱ”
“ አይ! ምን ባክሽ የዛሬ ኢንጂነሮች አስረኛ ክፍል ሳይጨርሱ ዲግሪውን እየጫኑ፣ ማድቤት መቀለሱን እንኳን መች ይችሉታል ብለሽ? አሄሄሄሄ ኢንጂኒየር እቴ…” ሆን ብለው፣ እኔ እንድሰማ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ነው የሚያወሩት፡፡ ይሄኔ ነው አንድ ውሳኔ የወሰንኩት፤ አዎ ከዚህ ሰፈር መልቀቅ አለብኝ፡፡ እስከመቼ እኚያ የዋህ አከራዬ እንኳን ሰላምታ ነፍገውኝ፣ እስከመቼ የሰፈሩን ወጣቶች ተረብ እየጠጣሁ ልዘልቅ( እኔ ስራ የነሳዋቸው ይመስል ጥርሳቸውን ነክሰውብኝ-ሊያውም ጫት ሲነክስ በኖረ ጥርሳቸው )…. አፍ ያልፈቱ ህፃናት አፍ መፍቻ ልሁን እዚህ ቆይቼ? አምስት አመት የቆየሑበትን፣ የምወደውን ሰፈር ሳልወድ ለመልቀቅ ወሰንኩ፡፡ እቃዬን ሸካክፌ እትዬ ስንቄን ልሰናበታቸው በራቸውን አንኳኳሁ፡፡ ልሄድ እንደሆነ ነግሬ ስሰናበታቸው፤
“ምነው በተማርክበት ሙያ ስራ አገኘህ?” አሉኝ ሹፈት በተቀባ ድምፅ፡፡ ሳልመልስላቸው አንገቴን ደፍቼወጣሁ፡፡ እቃዮን አስጭኜ ሰፈሩን ስለቅም፣
“ኢንጂነሩ፣ ተባረሩ…. ኢንጂነሩ ተባረሩ” በሚል የማትዎች በዜማ የታጀበ ተረብ ታጅቤ ነበር፡፡
የኛ ህብረተሰብ ሲቀጣ በትር አይቆርጥም፡፡ ያገልሃል፣ያንጓጥሃል አሊያም ከየቱጋር እንደተወረወረ በማታውቀው አጥንት ሰባሪ ተረብ እያደማ መድረሻ ያሳጣሃል፡፡ ብርርር ብለህ እንድትጠፋ ያደርግሀል፡፡ በነጠላ ለሰነዘርክበት ስድብ፣ በጅምላ ሆኖ ጥቃቱን ይመልሳል፡፡ አንድ ለብዙ ይሆናል ፀቡ…. ማሸነፍ ሁሌም የብዙሀኑ አይደለች