Tidarfelagi.com

ኤልያስ፡- ሀገር ነው እኖርበታለው!

የጌቴ አንለይ፥ የቀይ ጥቁር ጠይም፣ የቤሪ፥ ሕሊና እና የልዑል ኃይሉ፥ አንቺ ነሽ አካሌ ዘፈኖች በቁጥር ሶስት ቢሆኑም፥ በመንፈስ አንድ ናቸው። ከኢትዮጵያዊው ኤልያስ ማህፀን የተማጡ። ወንዱ ኤልያስ ወላድ ነው፥ ያውም ልበ መልካሞችን የሚወልድ።
እያንዳንዳቸው ዘፈኖች ብቻቸው ቁመው መነበብ ቢችሉም፥ ሶስቱም ገምደን ካነበብን ሀገር፥ ሰው ይገለፅልናል። ተጋርዶብናልና። ሀሳቦች በአንድ ሲገመዱ ወንዝ ሁነው መፍሰስ ይችላሉ፥ ብቻቸውን ቢሆኑም ውብ የህይወት ምንጭ ናቸው።
ዘመን መቆጠር ሳይጀምር፡-
ሰው ደግሞ በፍጥረት አለም ውስጥ ዘመን መቆጠር ከመጀመሩ ቀድሞ በአምላኩ (በፈጣሪው) የታሰበ ነው። እድል፥ ፈንታው በጌታው እጅ ነው። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ህግ ነው። ተፈጥሮን ታህል ግዝፍ ህግ ደግሞ የለም። ሰውም የፍጥረት ማዕከላዊ ነጥብ ነው። (የሳይንስም) የሰው ልጅም ጥቁር ነጭነታችን የከባቢ እና የዘረ መል ውጤት ናቸው። የታናሽ እና የታላቅ የመሆን ሀቲት አይደለም። ሰው መሆን ነው የእፁብ ድንቅ መጀመር እና ዘላለማዊነት። አሳቢው ኤልያስም እንዲህ ይላል።

ማን ቀድሞ አይቶ
መልኩን አውቆ በልጦ
መርጦ መጣ
ጠቁሮ ወይ ነጣ
ሁሉ አብሮት እንጂ
ሰው ተማክሮ መች ራሱን ፈጠረ
እንዲህ አብሮት እንጂ

የሰው ልጅም ከዘመን፥ ዘመን ባደረገው ጉዞ ውስጥ በተለየያ አይነት ባህል፣ አስተሳሰብ፣ መልክና ፈርጅ ውስጥ እየኖረ ነው። የብዙ እልፍ ባህል ንብርብር፣ የመልከ ቅይጥነት፣ የኑሮ ሰንሰለታምነት የሚኖርበት ዳና ነው። ኢትዮጵያ የዚህ መልከ ዥንጉርጉርነት መልክ ናት። በቋንቋ፣ በአናናር ይትበሀል የተለያዩ ቀለማት የሰራን ህብረ ቀለም ነን። መልክህ፥ ልብህ ተብዬ ብጠየቅም ኤልያስ እንዳለው የቀይ ጥቁር ጠይም ነኝ እምለው። ድብልቅልቅ ያልኩኝ መልካም ነኝ። እኔ ከጥቁሩ፣ ከነጩ፣ ከቢጫው ብዬ ራሴን አልመድብም። ኢትዮጵያም የዚህ እውነት የበኩር ልጅ ናት። ኤልያስም ይህንን እውነት በዜማ ቋንቋ ሁሉን አቃፊነትነት፣ ሰውኛ ኢትዮጵያዊ እውነትን በአደባባይ ይመሰክራል።
የሚነጣው ሁሉ የሚጠቁረውም ሰው፥ የቀይ ዳማውም ሰው፣
በክፉ አይን አይነሳም ማንም ሰው።

በአለማችንም ሆነ፥ በሀገራችን ታሪክም ሰውን ከፋፍሎ አንዱን ሎሌ፥ ሌላውን የከበረ። አንዳን ደንገጡር፥ ሌላውን ንግስት የጠራች አድርጎ ማሰብ የኖርንበት ጅረት ነው። በዚህ ዘመንም ነገድን መርጦ፥ ደሙን አይቶ የሚከፈሰው የአል-ዘመነ እሳቤ የዘወትር ፀሎት ሆናል። የእኔ የሚለው ሀቲት ቀድሞም፥ ሌላውን አሳንሶ ማየት ከጓዳ እስከ አደባባይ የሚታይ የዘመን ደዌ ነው። ይህ መጉደል የሞላበት ህይወት የቀይ ጥቁር ጠይም በሚላት ምሳሌ በሆነች እናት ሀገር ውስጥ አልሞተችም ይለናል። ልጆቻን በእኩል የምታይ እናት ሀገር ሰርቶልናል። ሁሉንም እጆቻን ዘርግታ፥ ልባን ከፍታ እንደምታኖር እና ኢትዮጵያም የዚህ የማር፥ የወተት ዘመን አድራጊ እንደሆነች ያሳስበናል። የቀይ ጥቁር ጠይም አብነቷ ሀገሬ፥ ኢትዮጵያ ናት።

አለች ቆጣ ቆጣ ፊታን ከፋው እሳ
የሩቅ አርገው ቢያሙት ጠይም ሰው ለራሳ
ጥቁርስ ቢታማ እንዴት አያማትም ጠይም ናት ልጅቷ
ባዕድ ሰው የላትም።
አፉን አስያዘችው ያንተው ይባስ ብላ
ከኔ አይቀርቡሽ ባዩን ሀሜተኛን ሁላ።

በሀገራችንም የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርትቶ፥ በፈጠራ የፓለቲካ ተረክ ምክንያትም አንዱን በዝባዥ፥ ሌላውን ተጠቃሚ አድርገው የሚስሉ ንቅናቄዎች፣ ነፃ አውጪ ነን ባዮች ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛት አድርገው በመሳል ልጆቻን አንዳቸው ከሌላቸው በጠላትነት እንዲተያዩ ያልቆፈሩት ጉድጋድ የለም። ከኖርነው እውነት ይልቅ፥ በውሸት መስመሮች ዥንጉርጉርነታችን ተዘንግቶአቸው ‘የራስ መልክን’ ከግማዱ ውስጥ ሊፈለቅቁ እንቅልፋ ያጡ የሞት መልእክተኞች በዝተዋል። ኣሳቢው ኤልያስ፥ ሰው በሚገባው ቋንቋ ይናገራል። (the constructed myth)

ሕሊና ይህን ካላስተዋለ
ሰውን በዘር ኮናኝ ብዙ አለ
ሕሊና ጥሎ ካታለለ
የጠቢብ ዘር ነኝ ባይ ከንቱ አለ

ዛሬ እና ነገ፡-
ሕሊናን፣ ሰውነትን እና ክፉ ፍሬን የሚፀየፈው ኤልያስም ሀገሩ ምን የመሰለች እንደሆነ በእሳቱ ሰአት አልበም ውስጥ በታላቅ ግርማ ይናገራል። አንቺ ነሽ ሀገሬ የሚላትንም ይዘረዝራቷል። ኢትዮጵያም ከነብሱ ጋር ይገምዳታል። ባለ ቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ እንደሚለው ነብስ ዘር የላትም። ህብረቷም ከዘላለማዊነት እና ከሰውነት ጋር ታላቅ መንግስት መስራት ነው። ለዚህ ነብሳም ሀሳብ ኢትዮጵያን በኩር አድርጋታል። በሰውነት እፁብ ድንቅ ህይወት ውስጥ ያስቀምጣታል። በዚህች ሀገርም የፍቅር ዜማ የሚሰማበት፣ ሰው የማይጠላበት፣ ከምድር ያልተዋደደች አድማሱን የምታስንቅ አድርጎ አክብራታል። ሰው የማይጠላበት፣ ሰው የሚቀድምበትን ምድርንም ሰርቶልናል።

አንቺው ነሽ ሀገሬ
ነፍስ ያለሽ አካሌ ሃያ
አንቺው ነሽ ህይወቴ ሆያ
አንቺው ነሽ ህይወቴ ሃያ

እናም፡-
የኤልያስ ሀገር በሶስቱ ዘፈኖች ውስጥ ድብልቅልቅ ያለ መልክ ያላቸው ሰዎች፣ ሕሊናን የታደሉ እውነቶች፣ ነብስ ያላቸው ስብስቦች፣ በሰው ፍቅር ልባቸው የሞላ የፍጥረት ቀዳሚዎች የሞሉበት ነው። በዚህ የኤልያስ ምድር እኔም ልኖር እመኛለው። ሀገሬ ኢትዮጵያ የታላቁ እውነት የሰውነት መልክ ውስጥ እንድትኖር እሰራለሁ። የኤልያስ የተምኔት ሀገር፥ የእውነተኛ ኢትዮጵያም ነፀብራቅ ነች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *