እመነኝ፣ እምነትና ሐይማኖት የዘር ጭፍጨፋን አያስቆሙም!
ጭፍጭፍ ሲጀመር ፈጣሪ ከሥፍራው ይሰወራል!?
“In Search of Rwanda’s Génocidaires – French Justice and the Lost Decades” (Author: David Whitehouse, 2014)
ሳላስበው በዓመታት ውስጥ አንድ፣ ሁለት፣ እያልኩ የሩዋንዳን የዘር ጭፍጭፍ (ጄኖሳይድ) ታሪክ ከሚከታተሉ መሐል ተደብልቄ ራሴን አገኘሁት። ለምን? እና እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ወደዚያ የዘር ጭፍጨፋ ታሪክ ደጋግመው የሚስቡኝ። እነዚሁ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ናቸው ወደ አይሁዳውያን ጭፍጨፋ፣ እና በተለያዩ አህጉራት ባሉ ቀደምት ህዝቦች ላይ ቀደም ባሉ ክፍለዘመናት ወደ ተካሄዱት የዘር ጭፍጨፋዎች አትኩሮቴን የሚስቡት።
‹‹የዘር ጭፍጨፋ›› የሚል ስም ይሰጣቸውም አይሰጣቸውም፣ ባለፉት ሁለትና ሶስት ክፍለዘመናት ውስጥ የሰው ልጅ ያስተናገዳቸው አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋዎች የተከናወኑት ጠንካራ የፈጣሪ እምነት ባላቸው የሰው ልጆች አማካይነት ነው። ሐይማኖተኞች ናቸው የዘር ጭፍጨፋን የሚፈጽሙት። ሐይማኖታቸው የሰውን ልጅ ክቡርነት የሚሰብካቸው ሰዎች ናቸው የሰውን ልጅ በዘሩ መርጠው ጅምላ ጭፍጨፋ የሚፈጽሙበት።
ይሄ ነገር መጠኑና ዘዴው፣ ዓላማውና ጊዜው ይለያይ እንጂ፣ ከቦሊቪያ እስከ ጆርጂያ፣ ከዩጎዝላቪያ እስከ ጀርመን፣ ከአሜሪካ እስከ ካናዳ፣ ከቱርክ እስከ ሩዋንዳ፣ ከጃፓን እስከ ቻይና፣ ከህንድ እስከ ኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ አልጄሪያ፣ ከኢራቅ እስከ ሞንጎሊያ.. ሁሉም የየራሳቸው ጠንካራ መንፈሳዊ እምነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው በሌሎች ህዝቦች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ፈጽመው የተገኙት።
ትውልደ እስራኤሎችን፣ ጂፕሲዎችን፣ ከጥቁር ጋር የተዳቀሉ አርያኖችን፣ አቅመ-ደካማ አረጋውያንንና ፍናፍንቶችን በጅምላ የጨፈጨፉት የጀርመን ናዚዎች፣ ከ88 በመቶዎቹ የሚበልጡት አባላቱ እልም ያሉ ክርስትያኖች ነበሩ። አርመኖችንና ኩርዶችን ሲጨፈጭፉ የኖሩት ቱርኮች እልም ያሉ እስላሞች ናቸው። የሮሂንጂያ እስላሞችን አቃጥለው ጨፍጭፈው ከመኖሪያቸው ያበረሩት በርማዎች እልም ያሉ ቡድሂስቶች ናቸው።
ቀደምት ፔሩዎችንና ቦሊቪያኖችን የጨፈጨፉት ስፔኖች እልም ያሉ ካቶሊኮች ናቸው። በብራዚል ቀደምት ነዋሪዎቹን የፈጁት ፖርቹጋሎች እልም ያሉ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። በኮንጎ ቀደምት አፍሪካውያንን የጨፈጨፉት ቤልጂያኖች እልም ያሉ ፕሮቴስታንቶች ናቸው። ላለፉት ሶስት ዓመታት አማራ ናቸው የሚሏቸውን እየነጠሉ ሲያርዱ፣ በጅምላ ሲጨፈጭፉና ሲያፈናቅሉ የምናገኛቸው የወለጋ ኦሮሞዎች አብዛኞቹ ክርስትያኖች (ፕሮቴስታንቶች) ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ‹‹የዘር ማጥፋት ወይም መጠፋፋት›› የሚባልበት ደረጃ ላይ ይድረስም አይድረስም፣ ዘር ለይተው ትግሬና አማራ እየተባባሉ እየተጨፋጨፉ የሚገኙት ህዝቦች ከ90 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑት ላለፉት ሁለት ሺኅ ዓመታት ዘሮቻቸው ሁሉ ለፈጣሪ ሲቀድሱ የኖሩ እልም ያሉ የኦርቶዶክስ ክርስትያን እምነት ተከታዮች ናቸው። ይህን ሁሉ እያሰብኩ ነው ይህን የዴቪድ ዋይትሃውስን “In Search of Rwanda’s Génocidaires – French Justice and the Lost Decades” የሚል መጽሐፍ ያነበብኩት።
እና የሩዋንዳ ሁቱዎችና ቱትሲዎች ሁለቱም እልም ያሉ ክርስትያኖች የመሆናቸውን ያፈጠጠ እውነታ እየመረረኝ የዋጥኩት። ሐይማኖተኞች መሆናቸው ብቻ አይደለም፣ በጄኖሳይዱ ወቅት በፊት መሪነት የተሰለፉ ብዛት ያላቸው የሐይማኖት መሪዎች ተስተውለዋል። የሚያሳዝነውም ጉድ የጭፍጨፋው በትር እነርሱንም አልማራቸውም፡- 105 ቄሶችና 120 ሴቶችና ወንዶች የሩዋንዳ መነኩሴዎች የክርስቶስ ምስል ያለበትን መስቀል በአንገታቸው እንደተሸከሙ በማሼቴ የገጀራ ስለቶች በአማኞቻቸው ተጨፍጭፈዋል።
አንዳንዴ ይህን ሁሉ የዓለማችንን (የእኛን የሰው ልጆች) ጉድ ሳስብ፣ ምን ያህል የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀይል እንደራቀው እገነዘባለሁ። የ20ኛው ክፍለዘመን ያሳየን አንድ ትልቅ ኪሣራ ቢኖር፣ በክፋቶች ፊት የመንፈሳዊውን ሀይል ጉልበት መብረክረክ ነው። መንፈሳዊው ኃይላችን፣ እርኩሱን ስጋዊውን ሀይላችንን ማንበርከክ የተሳነበትን ክፍለዘመን አልፈን፣ ወደለየለት መንፈሳዊ ሰብዕና ክፋትን መከልከል ቀርቶ፣ ክፋትን ለማራገቢያነት ወደሚውልበት ክፍለዘመን ነው የገባነው።
ባጠቃላይ ሐይማኖቶች በእኛ በተከታዮቻቸው በሰው ልጆች ላይ ‹‹moral authority›› አጥተዋል። ሰዎችን ወደ መልካም መንገድ መምራት ተስኗቸዋል። የሐይማኖቶች መንፈሳዊ ሀይል ከጊዜ ወደጊዜ እየተሟጠጠ መጥቶ ለስምና ለይስሙላ ብቻ ሆነዋል። ቅድስናን በምዕመኖቻቸው ልብ ውስጥ መዝራት አልቻሉም። ፍቅርንና ይቅርባይነትን በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ማንገስ አልቻሉም። ይህ ብቻ አይደለም። ሐይማኖቶቹ ራሳቸው የመንፈሳዊ ካባ በደረቡና በብዙ ርቀት ከፈጣሪ መንገድ ባፈነገጡ ስሜታውያን ሰዎች ተሞልተዋልም ማለት ነው።
ይህ ደራሲ የቫቲካንና የፈረንሳይ ሲኖዶሶች እንዴት አድርገው በዘር ጭፍጨፋ የተጠረጠሩ የሩዋንዳ ቀሳውስትን ክስ እንዳያገኛቸው፣ ተጠያቂነት እንዳይጎበኛቸው፣ እና ሥራቸው በአደባባይ እንዳይገለጽ እንደሚከላከሉላቸው በተለያዩ ምሳሌዎች እውነቱን አውጥቶ ያሳየናል። በእርግጥ መጽሐፉ መንፈሳዊ ተቋማት በዚያ ዘግናኝ የሰው ልጆች የኅብረት እብደት መካከል ክቡሩን የሰውን ልጅ ለማዳን የተጫወቱትን አስገራሚ የአዳኝነት ሚና፣ እና ለተቀደሰ ምስኪኖችን የማዳን ዓላማ ሲሉ የሐይማኖት አባቶች የከፈሉትን መስዋዕትነትም አይዘነጋውም።
ሌላ ቀርቶ በቤተክርስትያን ያስጠለሏቸውን የቱትሲ ሴቶች ለኢንተርሃምዌ አሳልፈው ለመስጠት እያስፈራሩ ደፍረዋል የተባሉ ቄሶችን እንኳ፣ እንዲያም ሆነው ያዳኗቸውን በርካታ ሰዎች እማኝነቶችም ጨምሮ ይዘክርልናል ደራሲው። ዜጎች ከቤተክርስትያን እየተጎተቱ በየዕለቱ ይረሸናሉ። ይደፈራሉ። ከሰው ልጅ ህይወት ይልቅ የቤተክርስትያናት ግንቦች እንዳይጎዱ በሚል ጥይት መተኮስ ተከልክሎ፣ ሰዎች በገጀራና መጥረቢያ አካላቸው ይበለት ነበር።
በዚህ ሁሉ አሰቃቂ ታሪክ መሐል ግን ደግሞ ደጋግሞ የሚመጣብኝ አንድ ጥያቄ አለ፡- ፈጣሪ ግን የት ነበር? የሚል። የት ነበር ፈጣሪ ይህ ሁሉ ግፍ በደጃፉ ላይ ሲፈጸም? ይህ ሁሉ ስሙ በሚጠራበት መቅደሱ ሲፈጸም የት ነው ፈጣሪ ግን? የእውነት ግን የዘር ጭፍጭፍ ሲካሄድ፣ ፈጣሪ ፈጥኖ ከሥፍራው የሚጠፋበት ምስጢሩ ምን ይሆን? የዘር ጭፍጨፋዎች የሠይጣን ‹‹Exclusive Show Times›› (የብቻ ትዕይንት ክፍለ-ጊዜዎች) ይሆኑ ወይ? እግዜሩ በሰው ልጆች ጭፍጨፋ መሐል የሚሰወርበት ምክንያቱ?
እውነት እግዜር ግን አለ? ወይስ መናፍቆቹ እነ ስፒኖዛና ኤንግልስ እንዳሉት ‹‹የሰው ልጅ መልካምና ሀያል የሚላቸውን ባህርያት ሁሉ ሰብስቦ የሰጣቸው ልብ-ወለዶች›› ናቸው የምናመልካቸው? ወይስ ለትምህርት ነው ይህን ሁሉ ግፍ የሚያሳጭደን እግዜራችን በየሐይማኖታችን? ወይስ የመጨረሻው ዘመን አፋፍ ላይ ነን? ያሰኘኛል አንዳንዴ። እግዜሩ ከሀጥያታችን ብዛት ይቅር እንዲለን ብቻ ነው የምለምነው፣ ዘር ሳልለይ፣ ሀይማኖት ሳልለይ፣ የሰው ልጆችን ባጠቃላይ። ዘር እየቆጠርን እንደ ክፉ አውሬ እርስ-በእርስ በመንጋ ከመበላላት ያውጣን ነው የምለው።
የሆነ ሆኖ ይህ የዴቪድ ዋይትሃውስ መጽሐፍ ከነማጣቀሻዎቹ 327 ገጾች አሉት። ከዚህ ቀደም ካገኘኋቸው መጻሕፍት በተሻለ ጥልቀት ያላቸውን ከፈረሱ አፍ ከራሱ እንደወረደ በሚባል ዓይነት ነው ከሁሉም ወገን (ለማንም ሳያዳላ) መረጃዎችንና የእማኝነት ቃሎችን የሚያቀርብልን። በመጽሐፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሩዋንዳው አሰቃቂ የዘር ጭፍጭፍ ወቅት በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች ቃል አለ። በወታራዊ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች ጭፍጨፋው ካለፈ በኋላ የሰጧቸው ቃሎች ተካተዋል።
ጋዜጠኛው እውነትን ነው የሚፈልገው። እውነት ደግሞ በሞኖፖል በአንድ ወገን እጅ ብቻ የተያዘች እንዳልሆነች ጠንቅቆ ያውቃል። እና በሁሉም ዘንድ እየዞረ ይፈልጋታል። ከሁሉም አፍ እንድንሰማ ዕድሉን ይሰጠናል። እና በሩዋንዳ ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ቃል ብቻ አያበቃም። በውጭ ሀገራት ጣልቃ-ገብ ሀገር ሀይሎች (ሠላም አስከባሪዎች – ለምሳሌ ፈረንሣይና ቤልጂየም) ውስጥ በኃላፊነት ላይ የነበሩ ጄነራሎችንና ሲቪሎችንም እማኝነቶች አስፍሮልናል።
በተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ በኃላፊነት ላይ የነበሩ (እንደ ካናዳዊው ጄ/ል ሮሚዮ ዴሌር ያሉትን) ሰዎች – እና በዘር ጭፍጭፉ ወቅት እነሱን አግኝተው ያናገሩ – እና መፍትሄ ያገኙም፣ ያላገኙም ተራፊዎችን ቃል አካቶልናል። በወቅቱ በያካባቢው በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በኃላፊነት ላይ የነበሩትን ሰዎች ቃል አስፍሮልናል። እና በተለይ (የእኔን አትኩሮት የሳበው) በመንፈሳዊ አገልግሎት (ከጭፍጨፋ የሸሹ ዜጎችን ባስጠለሉ በቤተክርስትያናት) በኃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰቦችን ቃሎችም አካቶ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እውነቱን እንድንረዳው ብዙ ጥረት አድርጓል ደራሲው።
በዓለማቀፉ የሩዋንዳ የወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው የቀረበ፣ ቃላቸውና ምስክሮቻቸው የተሰሙ የዘር ጭፍጨፋ ተዋንያንን፣ ከዘር ጭፍጨፋው ማግስት ሸሽተውና ራሳቸውን ሰውረው በፈረንሳይ፣ ኢጣልያ፣ ቤልጂየም፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና በመሳሰሉት የአውሮፓ ሀገራት በቀረቡባቸው ስሞታዎችና ክሶች ላይ የሰጧቸውን ቃሎች፣ እና በወቅቱ በእነዚያ የዘር ጭፍጭፍ ጭንቅ ውስጥ አልፈው፣ ቤተሰቦቻቸውን አጥተው፣ በህይወት የተረፉ ሰዎችን ቃሎችና ደብዳቤዎች ሁሉ በሚስብና በወጉ በተደራጀ ፍሰት ያስነብበናል ደራሲው።
ሰዎች ክፉ ሥራ ሠርተው ከሠማዩ አምላክ ምድራዊ ፍርድ ቢያመልጡ፣ ዘለዓለም ግን ተሸሽገው እንደማይቀሩ ይህ መጽሐፍ ያስገነዝበናል። ፍትህ ሊዘገይ ይችላል። አንዳንዶች ወንጀላቸውን በመንፈሳዊ ካባ ሸፍነውት ሊቆዩ ይችላሉ። ሌሎችም ስማቸውንና ደብዛቸውን በማጥፋት ከፈጸሙት አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ ለጊዜው ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። አሊያም በተለይ ሀያላን ሀገራት በተለያዩ የራሳቸው ምክንያቶች ተጠያቂዎችን አሳልፎ ለመስጠትም ሆነ ተገቢውን ፍርድ ለመስጠት ዳተኝነት ሊታይባቸው ይችላል።
ነገር ግን ይህ ደራሲ እንደሚያምንበትና እንደሚያሳየን – የትም ዓለም ላይ ቢሄዱ፣ ማንኛውንም ዓይነት ጭምብል ቢለብሱ – የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ – ሁሉም እንደየሥራቸው መጠየቃቸው እንደማይቀር ነው። ምድር ሰፊ ነች። ግን የዘር ጨፍጫፊን የሚሸሽግ በቂ ሥፍራ የላትም!
በሀገረ ፈረንሣይ ለምሳሌ ደራሲው በ28 የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ተጠርጣሪዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ ወይም የተጀመረ ምርመራ ምን ላይ እንደደረሰ የእያንዳንዱን ኬዝ እያነሳ ያሳውቀናል። በእርግጥ የብዙዎቹ ጉዳይ ክትትል የደረሰበት ደረጃ ባይታወቅም፣ ጉዳያቸው ሳይታወቅና ሰዎቹ ሳይለዩ ግን አልቀሩም።
በሌላ በኩል በተለይ በአሜሪካ አቀንቃኝነትና ግፊት አውሮፓውያኑ (በተለይ ቤልጂየምና ፈረንሳይ) ገፋ አድርገው የገቡበት በፍርድ ቤቶቻቸው የሌላን ሀገር የዘር ጭፍጨፋ ተጠርጣሪዎች የመዳኘት ሥልጣን የሚያገኙበት ‹‹Universal Jurisdiction›› (‹‹ዓለማቀፋዊ ወንጀልን በሀገር ውስጥ የመዳኘት ሥልጣን››) የሚያጎናፅፋቸውን የህግ ሥርዓት ማበልጸጋቸውን ያሳየናል።
ብዙዎቹን ወደ አውሮፓ ያመለጡ የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ተሳታፊዎች ለተወሰኑ ዓመታትም ቢሆን ከመጠየቅ ያዳናቸው አንድ ክፍተት፣ ሀገሮች በዓለማቀፍ ደረጃ በሌላ ሀገር ምድር ላይ፣ በሌላ ሀገር ዘር ጭፍጨፋ ላይ ተዋንያን የነበረን፣ የሌላ ሀገር ዜጋ ሰው፣ በፍርድ ቤቶቻቸው ለመገተርና ክሱን ተቀብለው ለማየት፣ በየሀገራቱ ያጋጠሙ ግልጽ የህግ ሥርዓት ያለመኖር ክፍተቶች ነበሩ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት በተለያዩ ሀገራት ከተካሄዱ የናዚ ተጠርጣሪዎች ችሎቶች ወዲህ በዓለማቀፍ ህግጋት ልማድ የአንዱ ሀገር የወንጀል ችሎት ‹‹በማይመለከተው ጉዳይ›› የሌላውን ሀገር ተጠርጣሪ እያመጣ የሚከስበትና የሚፈርድበት ልማድ አልነበረም። በሀገሮች መካከል ብዙ የመዳኘት ሥልጣን ይገባኛልና አያገባህም የሚል የህግ ክርክርም የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ጫን ሲልም አንዱ ሀገር፣ የሌላውን ሀገር ወንጀለኛ ይዞ በራሱ ሀገር ፍርድቤት የመዳኘት ጉዳይ የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት እንደመድፈርም የሚቆጠርበት አግባብ አለ።
አሁን ግን – ከሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ማግስት የታዩ ክስተቶች ያስተዋወቁት አዲስ አሰራር – የማንኛውም የዓለም ሀገር ፍርድቤት – የሌላውን የማንኛውም ሀገር የዘር ጭፍጨፋ ተጠርጣሪን ሰው ጉዳይ ተቀብሎ የማየት ሁለንተናዊ ሥልጣን – ‹‹Universal Jurisdiction›› ይሰጠዋል። የዘር ጨፍጫፊን በተመለከተ ‹‹አያገባህም›› ወይም ‹‹አያገባኝም›› የሚባል ነገር አይሰራም። ምክንያቱም የሚጨፈጨፈው የሰው ልጅ ነው። የሰው ልጅ ከሆንክ፣ የሰው ልጅ ጉዳይ የግድ ያገባሃል።
ስለዚህ የሰው ልጅ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሀገር ሁሉ፣ ‹‹በዘር ጭፍጨፋ ማነሳሳት፣ በዘር ጭፍጨፋ፣ እና በዘር ጭፍጨፋ ወቅት ትብብር ያሳየ›› ግለሰብ እጁ ላይ ሲገባ፣ ሰውየውን መብቶቹን ሁሉ ባከበረ መንገድ – ፍርደ ችሎት ላይ ገትሮ የሚገባውን ቅጣት የማከናነብ ሥልጣን አለው ማለት ነው። ሀገሮች በሰው ዘር ጭፍጨፋ የተሳተፈን ሰው ‹‹አሳልፈው መስጠት›› ሳይጠበቅባቸው (በእርግጥ ይህ እንደየስምምነታቸው ሆኖ) በራሳቸው ችሎት ከሰው መፍረድ ይችላሉ ማለት ነው። ደራሲው ይህን ሲናገር፣ በጣልያን፣ በቤልጂየምና በፈረንሳይ ችሎቶች የቀረቡ ጉዳዮችን በማስረጃ እያሳየ ነው።
በእርግጥ ደራሲው ተፈጻሚነታቸው ላይ (በሰዎቹ ላይ የመፈረዱ ነገር) የራሱ ጥርጣሬ አለው። ከተያዝክ አስር ፐርሰንት በአንተ ላይ የመፈረድ አደጋ አለብህ። (ግን ይህንንስ – 10%ቱን ማን አየበት?! ቢያንስ ዛሬ ላይ ሩዋንዳ ውስጥ የሰው ዘር ጭፍጨፋ ላይ ተሳትፈህ፣ ብራስልስ ላይ ወይ ፓሪስ ላይ ወይ ቬኒሲያ ላይ ከዚህ በፊት እንደለመድከው እጅህን ኪስህ ከትተህ በነጻነት መንፈላሰስ አትችልም! ወይ በጥላህ ራሱ እየበረገግክ ትኖራታለህ! ወይ ጋማህን ተይዘህ ተከሰህ፣ ችሎትህን አወራርደሃት፣ ሥራህ ያወጣሃል!)
መፈጠርን የሚያስጠላው ሚሊየኖች ያለቁበት የሩዋንዳው የዘር ጭፍጭፍ – የዛሬ 28 ዓመት – በፋሲካ በዓል ማግሥት በአፕሪል 7 ቀን 1994 (እ.ኤ.አ.) የሩዋንዳውና የቡሩንዲው ፕሬዚደንቶች – ዡቬናል ሃብያሪማና እና ሲፕሪዬን ንታርያሚራ – በፈረንሳውያን የአውሮፕላን አብራሪ ሠራተኞች እየተዘወረ በኪጋሊ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በሰማይ ላይ ዝቅ ብሎ በሚያንዣብበው – ፋልከን 50 – በተሰኘው ቅንጡ ፕሬዚደንታዊ አውሮፕላን ላይ እንዳሉ – በተተኮሰበት ሚሳኤል ተመትቶ ወደ አመድነት በተቀየረባት እለት ነው በመላዋ ሩዋንዳ የተቀጣጠለው።
የፋልከን-50 አውሮፕላኑን በሚሳይል መመታትና የፕሬዚደንቶቹን ሞት ዜና ተከትሎ፣ ህዝቡ ተደናግጦ ባለበት አዋኪ ሰዓት ላይ፣ የ RTLM ራዲዮ-ቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ተደማጭ ሰው ድምጹን ሞርዶ ወጥቶ ለሁቱዎች የክተት አዋጁን አስተላለፈ፡- ‹‹አውሮፕላኑን የመቱት ‹‹ኢንዬንዚ››ዎች (በረሮዎች – ማለትም ቱትሲዎቹ) በየስርቻው፣ ወይ በአንዱ ቤት አልጋ ሥር፣ ወይ በአንዱ ቡና ቤት፣ ወይ በአንድ መጸዳጃ ቤት ተሸሽገው ነው የሚገኙት፣ አሁኑኑ ሳያመልጡ ወጥታችሁ ብትፈልጉ ታገኟቸወላችሁ፣ አሁኑኑ ፈልጉና አግኟቸው፣ እና ለበረሮ የሚገባውን ዋጋ ስጧቸው!››።
ከሬዲዮ-ቲቪው ክተት መልዕክት በኋላ – ለቀደሙት ሶስት ዓመታት በየተራ ሲጋደሉና ሲቋሰሉ የነበሩትና በሚገባ የተደራጁት የኢንተርሃምዌ ወጣቶች ማቼቴያቸውን እየያዙ በየቱትሲዎቹ ቤት እየገቡ መግደልና ማረድ ጀመሩ። ከሚያዚያ 7 እስከ ሰኔ መጨረሻ ብቻ (በ3 ወራት ውስጥ) 800ሺህ ሁቱዎችና በብዛት ቱትሲዎች አለቁ። ከአንድ ‹‹ቡታሬ›› በሚሰኘው የኪጋሊ ክፍለ-ከተማ ብቻ 350ሺህ ሰው ነው ያለቀው።
ሁሌ የሚገርመኝ ነገር በየራሱ እስካልመጣ ድረስ ዓለም ሁሉ በሌላው ሀገር መጨፋጨፍ ጉዳይ ላይ የሚያሳየው አስገራሚ ቸልታ ነው። ከሩዋንዳው ጭፍጭፍ በፊት – ቢያንስ ለ3 ተከታታይ ዓመታት – በሁለቱ መሀል ተከታታይ ግጭቶችና ዘርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች ሲከናወኑ እንደነበርና እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ፈረንሳዮችና ቤልጂያኖች፣ አሜሪካኖችና ጣልያኖች፣ የመንግሥታቱ ድርጅት አሳምረው ያውቃሉ።
ሌላ ቀርቶ – ለጭፍጭፉ አንድ ወር ሲቀር – መጋቢት ወር ላይ – የአርበኞች ግንባሩና የሁቱው መንግሥት አስቀድመው ጥምር-መንግሥት ለመመስረት የገቡት ሥምምነት ቢኖርም፣ ሀገሪቱ በተግባር የገባችበት ህዝባዊ የጥላቻና የደም መፋሰስ ድርጊቶች በሀይለኛ ጣልቃ ገብነት ካለሆነ በቀር መገታት የማይችልና፣ ሀገሪቱ ታይቶ ወደማይታወቅ እልቂት ልትገባ አፋፍ ላይ እንደደረሰች – የአውሮፓ ሀያላንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቂ ሪፖርትና መረጃው ነበራቸው።
የተመድ የወቅቱ ፕሬዚደንት ጋናዊው ኮፊ አናን ነበሩ። ሰው ይላክልኝ ብሎ ወትውቶ ወትውቶ የዝሆን ጆሮ የተሰጠው የተመድ ጸጥታ አስከባሪ ጄ/ል ሮሚዮ ዴሌር – ኮፊ አናንን ሲወርፋቸው :-
“እኔ ከጭፍጨፋው በኋላ በደረሰብኝ የህሊና
ጫናና ጭንቀት ምክንያት መልቀቂያ አስገብቼ
በሚገባ የሚተካኝን በምዕራቡ ዓለም በታወቀ
የጦር አካዳሚ የሰለጠነ አፍሪካዊ ጄነራል ተክቼ
ልሄድ ምክረ-ሀሳቤን ሳሳውቃቸው – ኮፊ አናን –
የሚተካው ሰው ፈረንጅ (አውሮፓዊ) መሆን
እንዳለበት ይከራከሩኝ ነበር”
በማለት ሀቁን አፍርጦታል። እውነት ከሆነ ያሳፍራል። አፍሪካዊ ለአፍሪካዊ የበለጠ መቆርቆር ሲኖርበት፣ ያሳዝናል። ደሞኮ በጣም የሚገርመው እኚሁ ኮፊ አናን ናቸው የ2001ዱን የኖቤል የሰላም ሽልማት ከድርጅታቸው ከዩኤን ጋር በጋራ የተሸለሙት!! ሙት-ወቃሽ ላለመሆን፣ የኮፊን ነገር እዚህ ላይ ልዝጋው!
አንድ የመጨረሻ ጉዳይ! ቆይ ግን ያን የፕሬዚደንቶቹን አውሮፕላን ማን ነው የመታው?
ያን የሩዋንዳ ጦሰኛ አውሮፕላን (‹‹ፋልከን ሳንካንት››) ማን እንደመታው እስከዛሬም በሁሉም ወገን የታመነበት፣ የተረጋገጠ ማስረጃ የለም። ከዚህ በፊት ለወዳጆቼ ባስነበብኩትና ሊንዳ ሜልቨርን በግሩም ጥናት አስደግፋ በጻፈችው ‹‹A People Betrayed: The Role of the West in Rwanda’s Genocide›› የሚል መጽሀፍ ላይ ግን – የሩዋንዳ ሁቱ ወታደራዊ ባለሥልጣናት – አውሮፕላኑ እንደተመታ – በአውሮፕላን ማረፊያ ያገኟቸው የቤልጂየም ወታደሮችን መሆኑን በመጥቀስ – በዘወርዋራም ቢሆን ቤልጂየሞችን ከጉዳዩ ጋር አያይዛቸው ነበር።
ይህ ደራሲ ደግሞ – በ‹‹ፋልከን-ሳንካንት›› አውሮፕላን በሚሳዬል ተመትተው የሞቱት የፈረንሣይ ዜጎች በመሆናቸው ፈረንሳይ ባደረገችው የአደጋ ምክንያት ምርመራ፣ ሚሳዬሎቹን የተኮሰው ፖል ካጋሜ የሚመሩት የቱትሲዎቹ ‹‹የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር›› መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኖ መገኘቱን – ማስረጃ ጠቅሶ ይነግረናል። እና ለዚህ የፈረንሳዮች የምርመራ ውጤት የፖል ካጋሜ መንግሥት የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?
የፖል ካጋሜ ምላሽ ፈጣንና የማያዳግም ነበር፡- በርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት የፈረንሣይ መንግሥት ከዘር ጨፍጫፊው የሁቱ መንግሥት ጎን ሆኖ በማገዝ፣ በዘር ጭፍጨፋው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረጉን የሚገልጽ መንግሥታዊ የጥናት ሰነድ ለዓለም ይፋ ማድረግ ነበር – ይለናል ደራሲው። አዳፍኔ! ይሄን የፖል ካጋሜ አዳፍኔ እያነበብኩ – ‹‹አዳፍኔ!›› የሚለው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መጽሐፍ ድንገት ትዝ አለኝ።
በቃ እርሳቸውን የሚተካ፣ ሥልጣንን የሚታገል፣ አዳፍኔን የሚያጋልጥ፣ እውቅ ምሁር እንዳጣን መቅረታችን ነው አይደል? የልዩነትና የተቃውሞ ድምጽን ማሰማት ለስቃይና ለሞት በሚዳርግበት ሀገር ሰማይ ስር ተጠልሎ መኖር ያሳዝናል። መንፈስን ያደክማል። ለማንኛውም ነፍሳቸውን ይማር! የእሳቸውንም። የሩዋንዳውያኑንም። የእኛን በአሁኑ ወቅት አስፈሪ የብሔር (የዘር) ቅርጽ እየያዘ በመጣው የእርስ-በእርስ እልቂት እየረገፉ ያሉ ወገኖቻችንንም። የሁሉንም፣ የሁላችንንም ነፍስ ይማር። ደራሲውን አመስግኜ አበቃሁ።
ከአንድ ገጽ ቢያንስ አንድ ቁምነገር ሳይገኝ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ። ወቅታዊ ተደራሽነት ያለው የመሰለኝን ንባብ አጋርቼያለሁ። ላነበባችሁኝ ወዳጆች የከበረ ምስጋና ይድረሳችሁ። ያላነበባችሁ ወደፊት ታነቡታላችሁ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ። እኛም ራሳችንን ከክፋት ፈተና እንጠብቅ። መልካም ጊዜ።
One Comment
ደስ የሚያሰኝ አቀራረብ 👌