Tidarfelagi.com

እምየ ካስትሮ (ካስትሮ ነጭ ሰው!)

ካስትሮ ተወልዶ ባይልክ ወታደር
የአልሸባብ ነበሩ ድሬና ሃረር!!

‹‹ከሚኒሊክ ጥቁር ሰው›› እኩል የምትወደውና የምታከብረው ሰው ጥራ ብትሉኝ የኩባው ፊደል ካስትሮ ማለቴ አይቀርም! ‹‹ካስትሮ ነጭ ሰው›› እኔ ኢትዮጲያ ላይ ያንን የማድረግ ስልጣን ቢኖረኝ ኖሮ … እምየ ሚኒሊክ በፈረስ በክብር በቆሙበት አደባባይ ካስትሮም ታንክ ላይ እንደቆመ የሚያሳይ ሃውልት አስቆምለት ነበር። ቦታ ቢጠብ እንኳን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለምኘ (መቸም የኢትዮጲያ ነገር አይሆንላትምና መፍቀዷ አይቀርም) እዛው ጊዮርጊስ አጥሩ ስር ሃውልቱን አቆምለት ነበር። በእርግጥ ካስትሮ ኮሚኒስት ነበር ! በእግዚአብሔር አያምንም! ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስን ብሩክታዊትን እንዴት እንደታደገ ገድሉን ከሰማ ጊዮርጊስን ሊሳለም ሁሉ ይችላል …ካስትሮ ነፃነታቸው የተነፈገ ደጋፊ ያጡ ሚስኪኖችን ከተፍ ብሎ የሚታደግ ጀግና ይወዳል። ካስትሮ ራሱ እንደዛ ነው!

ሁልጊዜም የሚያስገርመኝ እምየ ምኒሊክስ መቸም ክተት ብለው ያንን ፋሽት አፈር ከድሜ ያስበሉት እትብታቸው ለተቀበረባት፣ ለሚወዷት ለነገሱባት አገራቸው …እምየ ለሚላቸውም ህዝባቸው ነው። ኢትዮጲያን የነካ በአይኔ ዳር መጣ ያሉትም እውነትም ኢትዮጲያ አይናቸው ስለሆነች ነበር። የካስትሮ ነገር ግን አይገርማችሁም?  አንዛመደው አንዋለደው በርስት አንገናኝ በእምነት አንመሳሰል እንደው ኢትዮጲያ ተነካች ሲባልና ዓለም ሁሉ እንዳላየ ጥጉን ሲይዝ ክተት ብሎ ወታደሩን ማዝመቱ ይገርመኛል። ያው ሶሻሊስት ሰለነበር ነዋ እንዳትል። ወራሪው ዚያድ ባሬ በሶሻሊስቷ እናት ሶቪየት ህብረት ጭምር የሚረዳ በእነአሜሪካ የሚታገዝ በጦር መሳሪያም በወታደርም የፈረጠመ ነበር!!

እና አቅማችን ተልፈስፍሶ አንበሳ ሲያረጅ እንዲሉ …እኛም የዝንብ መጨዋቻ በሆንበት ሰዓት አስራሰባት ሺህ ተዋጊ ወታደሮችና ከፍተኛ አሰልጣኞችን አሰልፎ በነብሳችን ከተፍ ብሎ ከጉድ ያወጣን መሪ ነው! ታላቁ የአውሮፓ ጦር ያላንበረከካትን አገር የዝያድ ባሬ ቅዥት ያሰከረው የሱማሊያ ጀሌ ወሮ ሃረር የለ ድሬዳዋ መነጣጥቆ ባዶ እጃችንን ሊያስቀረን ሲልኮ ነው ‹‹ካስትሮ ነጭ ሰው›› እንደቅዱስ ጊዮርጊስ ከተፍ ያለው! በተደረገው አስጨናቂና አሰቃቂ መስዋእትነት የተከፈለበት ውጊያ ላይ የኩባዊያን እና ኢትዮጲያዊያን ወታደሮች ተሰውተዋል! ዘኪ …(ደቡብ የመን እና ምስራቅ ጀርመን በወቅቱ ያደረጉልንን ድጋፍም አልዘነጋንም የሰውየው ነገር ገርሞን እንጅ) እና የወራሪውን ድንፋታ ለዘላለሙ ያስተነፈሰው ይሄ ሃይል ነበር !
በእውነት ካስትሮ ከሚያኮራው የራሱ ታሪክ በላይ እንደአንድ ኢትዮጲያዊ ላገሬ ያደረገው ውለታ ያኮራኛል! መቸም በዚህ ሰዓት መቶ ሰው ይዠ ብሄድ ዘጠና ስምንቱ ጥገኝነት ጠይቆ እዛው ይቀራል ብየ ፈርቸ እንጅ እንደጉዙ አደዋ ጉዞ ኩባ ላዘጋጅ ሁሉ አስቤ ነበር 🙂ቢሆንም ኩባን አንድ ቀን መጎብኘቴ አይቀርም! ከምሬ ነው! ላይቭ ነው የማስጎበኛችሁ! እስከዛው ግን እምየ ካስትሮ እንደምየ ምኒሊክ በልባችን ነግሶ ይኖራልና በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ሃውልት ስር የምታልፉ ጓዶች በልባችሁ ያንን ጀግና ዘክሩልኝ! እንዲህ እያላችሁ …

ካስትሮ ተወልዶ ባይልክ ወታደር
የአልሸባብ ነበሩ ድሬና ሃረር !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *