ብዙዎቻችን አንድን ሰው የተማረ ነው የምንለው ወይም ደግሞ እውቀቱን የምንለካው በቆጠራቸው ክፍሎች አለያም በድግሪ፣በማስትሬት እና ዶክትሬት ደረጃው ነው።ነገር ግን እምብዛም በአለማዊ ትምህርት ሳይገፉ ጥበብን የታደሉ እንዲሁም እውቀትን በማንበብ ብዛት ያዳበሩ በየአገሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ቢልጌትስ እና የፌስቡክ ባለቤት ማርክ የጀመሩትን ኮሌጅ እንኩዋን አልጨረሱትም።
ወደ አገራችን ስንመጣ ብዙ አርቲስቶችን ወይንም ታዋቂ ሰዎችን መጥቀስ ቢቻልም።ዛሬ ስለታላቁ የጥበብ ሰው ጳውሎስ ኞኞ ጥቂት ልል ወደድኩ።በጣልያን ወረራ ምክንያት ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል ማዘለል አልቻለም ነገር ግን አያሌ መጻህፍትን ሳይታክት አነበበ። ‘ንባብ ደግሞ የማይገፋው የመሃይምነት ተራራ የለምና ጳውሎስ የመሀይምነትን ግንብ ደርምሶ ከጥበብ ማማ ላይ ደረሰ’። ከጥበብ አናት ላይ ሆኖ ዘመንን ለማሸነፍ በዘመን ሳይቀደም እውቀቱን ለኛ አካፍሎን አለፈ።
ጋዜጠኝነት ብቻ ሳይሆን የታሪክ ምርምር እና ልቦለድም እጣ ክፍሉ ነበረ።የ5 አመቱን የጣልያን ወረራ እንደሱ የከተበው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ‘ከ20 በላይ ምርጥ መፅሀፍትንም ፅፏል ፤ ከኢትዮጵያ ድምፅ እስከ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ልዩነት ፈጣሪ ጋዜጠኛ ከመሆኑም በላይ ፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውም በኢትዮጵያ የነበረውን የጋዜጠኝነት አካሄድ በመለወጥ ለዘርፉ ተስፋ ሠጪ መዳረሻ ለመፍጠር የደከመ ፣ ራሱን በራሱ ያበቃ፤ ያስተማረ የቀለም ቀንድ ለመሆን በቃ’።
ቆብ የተደፋበት ፎቶ በየግድግዳው አንጠልጥሎ ከንባብ መሰናበት ሳይሆን።ዘላቂ አንባቢነት ከእውቀት ማማ እንደሚያሳፍር ጳውሎስ ምስክር ነው።ከማንበብ የተነጠለ ጭንቅላት የሰውን ወሬ ከማራግብ አልፎ የራስን እቁዋም ለማስታወቅ የማይበቃ መሆኑን የተረዳው ጳውሎስ ማንበቡ ሙሉ ሰው እንዳደረገው ትቶልን የሄዳቸው መጽሀፍት ምስክር ናቸው።
የአራተኛ ክፍል ተማሪው ጋዜጠኛ ፣ ደራሲና የታሪክ ተማራማሪው ጳውሎስ ኞኞ ስራዎች ውስጥ ፦አጫጭር ልብ ወለዶች፣ከሴቶቹ አምባ፣የአራዳው ታደሰ፣አጤ ቴዎድሮስ፣አጤ ምኒልክ፣የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት…ጥቂቶቹ ናቸው።
ጳውሎስ ኞኞ በ1984 ዓ /ም በህይወት ቢለየንም ስራዎቹን እና የማንበብን ጥቅም ለትውልድ አትርፎ ሄድዋል!
“ብሞትም እውነትን እየተናገርኩ ነው እና ነፍሴ አትጨነቅም” ጳውሎስ ኞኞ