Tidarfelagi.com

እኔም!

ስሜት አልባ ነህ ብለሽኝ፣ «አልነበርኩም» ብዬሻለሁ። እውነቴን ነው። የስሜቴን ጅረት ያደረቀችው ቀድማ የሄደችው ነበረች። ታሳዝኚኛለሽ። ያለፈ ህይወቴ ትመስይኛለሽ።
ላፈቅርሽ ሞክሬያለሁ። ሳይሆንልኝ በራሴ እልፍ ጊዜ ተበሳጭቻለሁ።
ትታኝ የሄደችውም እንዲህ የነበረች ይመስለኛል። «አፈቅርሃለሁ» ብላኛለች። ግን አታፈቅረኝም ነበር። ልታፈቅረኝ እየሞከረች እንደነበር ግን አውቃለሁ። ፍቅር ግን እንደ ጅምናስቲክ ስፖርት በሙከራ አይመጣም። 
ልቤን ብዙ ቦታ ሰብራዋለች (ልብ ለስላሳ ስጋ ነው እንዴት ይሰበራል? ትይ ይሆናል። የኔ ግን ደጋግሞ ተሰባበረ)
ወቅሻት ነበር። አዝኜባት ነበር። እሷን ያወኩበትን ቀን በረጃጅም የእርግማን በትር ደብድቤ ነበር። አሁን ግን አልወቅሳትም። በተራዬ እሷን የሆንኩ፣ አንቺ ደሞ በተራሽ እኔን የሆንሽ ይመስለኛል።

ከዓመታት በፊት ካንቺ ያላነስኩ አፍቃሪ ነበርኩ። ያፈቀርኳት ሄደች። ብርሃን ወጣልኝ ብዬ ስኩራራ ጨለማ ወደቀብኝ። ተደናበርኩ። ብዙ ቦታ አነከስኩ። ልቤ አነከሰ። ነብሴ አነከሰ። አዕምሮዬ አነከሰ። ማመዛዘኔን ተመታሁ። ስሜቴን ተሰበርኩ! ሁሉ ነገሬ ዝም አለ። ዝም አልኩ። በዝምታዬ ውስጥ ያንቺ ሹክሹክታ መጣ። አፈረቅርሃለሁ አልሽኝ። ከልብሽ እንደነበር አወቅኩ፣ የቀድሞ አፍቃሪ ነበርኳ! እውነተኛ ፍቅር ከርቀት ጠረኗ ይታወቀኛል። ደነገጥኩ። የደነገጥኩት ላንቺ እንጂ ለኔ አይደለም። የእኔን ስቃይ ስታዪ ማየት አልፈለኩም። አብሬሽ ልሆን ተስማማሁ። ላፈቅርሽ ጣርኩ። አልቻልኩም። አንካሳ ልብ ማፍቀር ይችላል? ባለፈ ጊዜ ውስጥ አዳልጦት የወደቀ ልብ በዛሬ መንገድ ላይ እንደወደደ መጓዝ ይችላል? አይመስለኝም!

ፍቅር ተነቃቃይ እና ተገጣጣሚ ቢሆን ለሷ የነበረኝን ፍቅር አውልቄ ላንቺ ባውለው ደስተኛ ነበርኩ። አየሽ፣ ዛሬዬን እንዳልኖር ተከልክያለሁ። በትናንት ሰንሰለት ታስሬ ወደዛሬ መምጣት ከብዶኛል። ሰንሰሌቴ እሷ ነች። ዛሬ ላይ ያንቺ ሰንሰለት እኔ እንደሆንኩ ይሰማኛል።
የሄደ ሰው ላይ ተተክለን የምንቀረው ለምንድነው? አይገባኝም። ማፍቀር ለምንድነው «አደን» የሆነው? እኔ እሷን ሳባርር፣ አንቺ እኔን ስታባርሪ ምንም ሳንጨብጥ እድሜያችን የሚመሽብን ለምንድነው? ፍቅር መግቢያ መስመር የሌለው ሩጫ ሲሆን ያታክታል!
ቀድማ የተለየችኝም የእራሷ ሌላ የምታድነው ወይ ጥሏት የሄደ ይኖራል። ልቧ ከኔ ጋር ያልነበረው ለዛ ይመስለኛል። የእኔ ደግሞ እሷ ጋር፣ ያንቺ እኔ ጋር! ካንቺ ኋላ ደግሞ ባንቺ ችላ ማለት የተጎዳ አፍቃሪ ይኖራል።እንለያያለን እንላለን እንጂ ተመሳሳይ ነን።
«እስቲ የምታፈቅሩትን አጥታችሁ የተሰበራችሁ ወዲህ ኑ ብንል» አዳሜ በሰልፍ መጋፋቱ አይቀርም!
ስሜት አልባ አይደለሁም። ስሜቴን ተመትቼ እንጂ።
ግድየለሽ ሆኜ አይደለም፣ ግድማለቴን ተሰብሬ እንጂ!
ታሳዝኚኛለሽ፣ እኔም አሳዝናለሁ። ሁላችንም እናሳዝናለን! ፍቅር ውብ ነው ብለው ለማፍቀር የሚዳክሩት ሁሉ ያሳዝናሉ። ያፈቀሩትን ሲያጡ መሬት ከእግራቸው ስር የምትዋልልባቸው ሁሉ ያሳዝናሉ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *