Tidarfelagi.com

‹‹እኔን ነው?››

ገና እምቦቃቅላ ሳለሁ፣ አባቴ ..‹‹ጠይም ልጅ ባይኔ ላይ ተሸክሜ እንደኩል›› እያለ ጥቁረቴን የሚያወድስ ዘፈን ይዘፍንልኝ ስለነበር ከኩል የተሰራሁ ይመስለኝ ነበር።

ከኩል ስለተሰራሁ ፣ ገና ልጅ ሳለሁ ኩል መኳል ያጓጓኝ ስለነበር አባቴ በእሱ ሃገር ሴት ልጅ የምትኳለው ልትዳር ስትል እንደሆነ እያጫወተ፣ ከሃገሩ መንዝ የባህል ሙዚቃዎች አንዱን እየዘፈነ የመኳል እና የመዳርን ሚስጥር በእድሜዬ መጠን ያስረዳኝ ነበር ። ዛሬ በሮክ ስልት አብዶ- በጃኖ ባንድ የገነነው ‹‹ኳይኝ- ዳሪኝ ሸንኮሬ›› በልጅነቴ የማውቀው የመንዝ ዘፈን ነው።

የሆነው ሆኖ ልጃገረድነት መጥቶ፣ አጎጠጎጤ ወጥቶ፣ የውበት ነገር በሚያሳስበን እድሜ ስደረስ፤ ኩልን ለትዳር ሳይሆን ለውበት መጠቀም ጀመርኩ። ሰርጌ ደርሶ ፣ ‹‹ አረ ኩሉን ማን ኩሏታል- ባትኳለውም ያምርባታል›› ተብሎ ሳይዘፈንልኝ፣ ራሴን በራሴ ደመቅ አድርጌ መኳል ያዝኩ።

ትዳር እስክይዝ ባለው ጊዜ ውስጥ የሜክአፕ ጥበብ እየዘመነ እና እየገነነ ቢመጣም ለእኔ ግን የሜካፕ ጥግ ኩል፣ የማማር ልኬት ደግሞ መኳል ሆኖ ቆየ።

ዱቄቱ የአረብ ሃገር ኩል።
ወፍራሙ የህንድ እርሳስ ኩል።
ቀጭን ሆኖ የማይቀረፀው ውድ የአሜሪካ ኩል።
ቀጭን ሆኖ ባለመቅረጫ ክዳኑ የኬንያ ኩል።

አይኔን ያላሰመርኩበት፣ ያልተኳልኩት አይነት ኩል የለም።

ተድሬ ከእናት ካባቴ ቤት እስክወጣ፣ ከኩል በስተቀር ሰርክ የምጠቀመው ብቸኛ ሜክአፕ ውሃ ቀለሙ ቻፒስቲክ ብቻ ነበር። የሰርጌ እለት ግን ሚዜዎቼ ‹‹አረ ሙሽራ ምሰይ…አረ ለየት በይ›› ብለው ቁም ስቅሌን ሲያሳዩኝ እንደነገሩ ለመነካካት ሞከርኩ። ምቾት ግን አልሰጠኝም።

ከሰርጌ እለት ወዲህ ‹‹ደንበኛ›› ሜካፕ ተቀቢ የሚል የአቻ ግፊት (ሃሃሃ…) የደረሰብኝ ትላንት፣ አዲሱ መፅሃፌ ፍቅፋቂ በሚመረቅበት ቀን ነበር።
ከብዙ እሺ እና እምቢ በኋላ ‹‹መጠነኛ›› ሜክአፕ ለመቀባት ተስማምቼ ‹‹በእጁ ተአምር ያደርጋል›› የተባለው ባለሙያ ወንበር ላይ ተሰየምኩ።

ስሙ አሸናፊ ነው።

ወሬውን እሱ ጀመረ።

– መፅሃፍ ልታስመርቂ ነው አሉኝ…እንኳን ደስ ያለሽ
– አመሰግናለሁ…በናትህ በጣም ሲምፕል ነገር ነው የምፈልገው…ማለቴ ብዙ እንዳትለዋውጠኝ…
– ገብቶኛል…ለየት ማለት ነው የምትፈልጊው አይደል?
– ለየት…አዎ…ግን ሌላ ሰው መሆን አልፈልግም…ማለቴ መምሰል አልፈልግም…ራሴን ሆኜ ግን ትንሽ ደመቅ…ገባህ?
– ገ…ባ…ኝ…አሁን ተኚ…

የተቀመጥኩበት ወንበር ተለጥጦ ወደ አልጋነት ቀረበ።
የሜካፕ ሳጥኑ ተከፈተ። ውስጡ፣ በርካታ ቀለም ያላቸው ዱቄቶች ተቀምጠዋል። ከአምስት በላይ የቀለም መቀቢያ የሚያህሉ ብሩሾች ተሰድረዋል። ቅባቶች ተደርድረዋል። አሸናፊ ግንባታውን ጀመረ።

– አሸናፊ…እንዳይበዛ በናትህ….
እላለሁ በየመሃሉ ስቅቅ እያልኩ….
አስራ ምናምን ደቂቃ አይኔ እና ቅንድቤ ላይ ማጥፋቱ እያሳሰበኝ…
ምን መስዬ ይሆን በሚል እያስጨነቀኝ….
– አታስቢ…ሙሽራ ነው የማስመስልሽ ዛሬ… አለ ፊቴን በብሩሽ እያካለለ…
– ኖ ኖ…ሙሽራ መምሰል አልፈልግም…በናትህ እንዳታበዛው… አልኩ ። ይሄን ጊዜ፣
– ቆይ ከምታስቢ ልብሽ እንዲያርፍ እይው… አለና ሮጥ ብሎ ያመጣውን መስታወት አቀበለኝ።

ፈራ ተባ እያልኩ በመስታወት ራሴን አየሁ።
ከአፍንጫዬ በላይ የማላውቃት ሴት ሆኛለሁ…
ቅንድቤ ተገልብጧል። አይኔ አንሷል። የአፍንጫዬ መጀመሪያ ስልክክ ብሏል። ግንባሬ የቀይ ሴት ግንባር የተለጠፈበት መስሏል።

ክው አልኩ።
– ወደድሽው? አለኝ በኩራት አይን አይኔን እያየ
– እ…ይቺ ማናት? ….አልኩ ግራ እንደተጋባሁ

እሱም ረዳቶቹም ሳቁ።

– ቀልዴን አይደለም…አልሰማኸኝም…ሌላ ሰው መምሰል አልፈልግም ብዬህ ነበር…ቀይረው…አጥፋው…አልኩ እየተጣደፍኩ…
– እንዴ…ያምራል እኮ…አለ ኮስተር እያለ
– ዳንስ ቤት አይደለም የምሄደው…የማከብራቸው ሰዎች ይመጣሉ…እንደዚህ ሆኜ እንዲያዩኝ አልፈልግም…በናትህ ቀንሰው አልኩኝ እነ ሕይወት ተፈራ፣ እነ አምባሳደር ታደለች….እነ ፕሮፌሰር ማስረሻ በአይኔ ላይ እየሄዱ

– ሂዊ…ሌላ ሰው መምሰል ካልፈለግሽ ይሄን ሁሉ ብር ከፍለሽ ለምንድነው ሜካፕ የምትሰሪው? አለችኝ አንዷ ሁሌ ፀጉሬን የምትሰራኝ ልጅ…

እውነቷን ነው….ራሴን መምሰል ከፈለግኩ ምን ቅብጥ አድርጎኝ ለሜካፕ ተቀመጥኩ?
ሃሳቤን ሳልጨርስ…
– ሂዊ..ይሄ እኮ ገና ቤዙ ነው.. አለኝ አሸናፊ
– ቤዙ?
– አዎ…ከዚህ በኋላ እኮ ሶስት ሌየር አለ…ገና በቤዙ እንዲህ ከሆንሽ….
– በቃ ቀንስልኝ…አልኩት ሰአቴን ስመለከት ለድግሴ 1 ሰአት እንደቀረ ስላየሁ እየተዋከብኩ…
– ከዚህ ላይ ምን እቀንሳለሁ ፊትሽን ካልታጠብሽ በስተቀር? .አለ ስራውን ስላበላሸሁበት፣ እጀ ሰባራ ስላደረግኩት ቅሬታው ከፊቱ እየታየ

ግራ ገባኝ።

ሰአቴ ሄዷል። ገንዘብ ከፍያለሁ። በዚህ ጋር ቀጠሮ የያዙልኝ ጓደኞቼ ልፋት አለ…. ልታጠበው ወይስ መቀነስ ከቻለ አስቀንሼው ልሂድ….?

– መቀነስ ከቻልክ ትንሽ ቀንሰውና ሊፕስቲኬን ተቀብቼ ልሂድ አልኩት ዞር ብዬ እያየሁት….
ቅሬታው እንዳልለቀቀው እያስታወቀ እ…ሺ…አለና እርጥብ ሶፍት አምጥቶ ፌቴን በስሱ ይሞዥቅ ጀመር።
– በነገርሽ ላይ ሜካፕ ያምርብሽ ነበር…ፊትሽ ይቀበላል…. አለኝ የሚሰራውን ሳያቆም
ፊትሽ ሜካፕ ይቀበላል ማለት ምንድነው? ሙገሳ ነው? ሽንቆጣ ነው? አመሰግናለሁ ልበል? ዝም ልበል?
– እሺ…አልኩ ዝም ላለማለት
– ይሄ ቅንድብ ቆረጣው ምናምንን ባታስጠፊኝ…ትንሽ አፍንጫ እና አይንሽን ደመቅ ባደረገው መሰረት መብራቴን ነበር የማስመስልሽ..አለኝ አሁንም ስራውን ሳያቆም።

ቀልዱን እንዳልሆነ ያወቅኩት ፊቱ ላይ ምንም ፈገግታ ስላላየሁ ነው።

– ሃሃ…እኔን ነው ውቧን መሰረትን የምታስመስለኝ…? አሹ…ጎበዝ ሜክአፕ አርቲስት ነህ…ተአምረኛ ግን አይደለህም አልኩት እየሳቅኩ…
– አዬ…እድል ስላልሰጠሸኝ ነው…ዛሬ እኮ እድሜ ለሜካፑ እና ለገንዘብሽ እንጂ በሃያ እና ሰላሳ ደቂቃ የፈለግሻትን ውብ ሴት መሆን ትችያለሽሽ..ፌስቡክ ላይ አታይም ሴቱ ሁሉ አንድ አይነት ሆኖ…?እሱ ምን ይመስልሻል…ሜካፕ እኮ ነው….አለኝ መሞዠቁን ሳያቆም

ይሄስ እውነቱን ነው…
የዘንድሮ ሜካፕ ድርፍጭ ያለ አፍንጫን ወደ ሰልካካነት፣ ባለ ጠባብ አይኗን ወደ አይነ- ቦጎነት፣ ጥቁሯን ወደ መሰረት መብራቴ፣ ፉንጋዋን ወደ አምለሰት ሙጬ በደቂቃዎች ያሸጋግራል።

የዘንድሮ ሜካፕ ያለ ቀዶ ጥገና መቀስ፣ ያለ ስፌት የሚካሄድ ጊዜያዊ ጥገና ነው። ለተአምር የቀረበ የመምሰል ጥበብ ነው።

ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ፣ ሜካፑን በእኔ አባባል አስቀንሼ ግን አሁንም ሌላ ሰው መስዬ፣ በእሱ አባባል ደግሞ ‹‹አበላሽቼ›› ለድግሴ እንዳላረፍድ በጥድፊያ ወጣሁ።

ሸበሌ ደረስኩ።

የሚስሙኝን ወዳጆቼን ሁሉ ‹‹ፊቴን እንዳታፈርሱ እያልኩ›› ስጠጋቸው፣ ‹‹ወይኔ ስታምሪ….›› ይሉኛል።
እኔን አይደለም። ሜካፑን ነው።

‹‹ዛሬ ፏ ብለሻል›› ይሉኛል።

እኔን አይደለም። ፋውንዴሽኑን ነው።

‹‹ዛሬ ለየት ብለሻል›› ይሉኛል፡

እኔን አይደለም።ሻዶውን ነው።

‹‹ሂዊዬ…በጣም ቀላሽ›› ይሉኛል››

እኔን አይደለም። ‹‹ሃይላይቱን›› ነው።

ዝግጅቱ አልቆ፣ ሜካፑ ፌቴ ላይ እንደነገሰ.. ከባለቤቴ ጋር ወደቤቴ በመሄድ ላይ ሳለን ዘወትር ከምንገበይበት የሰፈር ሱፐርማርኬት ለቁርስ የሚሆን ነገር ለመሸመት ገባሁ።

ለወትሮው ‹‹‹ታዲያስ›› ብሎ የምፈልገውን እቃ ሳይጠይቅ የሚሰጠኝ ደምበኛዬ የቤቱ ባለቤት ፊቴ ላይ ከባድ የሂሳብ ስሌት የተጻፈ ይመስል ትክ ብሎ እያየኝ ሲወዛገብ ሳቄ መጣ።
‹‹ ምን ልርዳሽ የኔ እመቤት›› ምናምን ብሎ ሳያሳፍረኝ ብዬ ቆፍጠን አልኩና፤
‹‹ዝግጅት ነበረኝ…ለዚያ ነው…እስቲ .ገብስ ዳቦ ስጠኝ›› አልኩት።
መወዛገቡ ሳይለቀው፣ ‹‹እ…እሺ…›› አለና ዳቦውን ሊያመጣ ሲሄድ የምፈልጋቸውን ሌሎች ነገሮች ለማንሳት አንዱ መደዳ ገብቼ ሰፈልግ ከአንድ ሰውዬ ጋር መንገድ ላይ ተገጣጠምን።

ልወስዳቸው ያሰብኳቸውን የመጨረሻ እንቁላሎች ሲያነሳብኝ አፈር ብዬ ልመለስ ስል…

‹‹ሙሽራ ነሽ መሰለኝ….ቅድሚያ ለሙሽራ…አንቺ ውሰጂው›› አለኝ።

ሙሽራ አይደለሁም..ሜክአፑ ነው ልለው ብዬ ነጥቡ ስላልታየኝ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብዬ ተመለስኩና ሂሳቤን ከፍዬ ቤቴ ገባሁ።

የአሸናፊን ስራ ከፊቴ አጥቤ ከባለቤቴ ጋር ለመተኛት ስንሰናዳ ዘወትር እንደሚያደረገው ግንባሬን ሳም አደረገና፣
‹‹ደህና እደሪልኝ የኔ ቆንጆ›› አለኝ››

አሁን እኔን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *