ማምሻውን ነው።
ዝናብ ያረሰረሰውን የሰፈራችንን ኮብልስቶን መንገድ በጥንቃቄ እየረገጥኩ ወደ ቤቴ አዘግማለሁ። በድንጋዮቹ መሃከል የፈሰሰው ውሃ በረገጥኩት ቁጥር ፊጭ ፊጭ ይላል። ዘንቦ ማባራቱ ስለሆነ ይበርዳል።
ፊጭ ፊጭ እያደረግኩ መራመዴን ስቀጥል፣ ከዚህ በፊት አይቼ በማላውቀው ሁኔታ በመንገዴ ላይ ከሰል አቀጣጥለው፣ በቆሎ ጠብሰው በተርታ ተሰድረው ገበያ የሚጠብቁ ሶስት ሴቶችን አየሁ።
የመጀመሪያዋ ወጣት ቢጤ ናት። አጠገቧ ከባድ ዝናብ ያዘመመው ወልጋዳ ጃንጥላና እና ኩምትር ብሎ የተቀመጠ ህፃን ይታየኛል። ከእሷ ቀጥሎ ያሉት ሴቶች ሌጣቸውን ናቸው። ከእርሷ ለመግዛት መረጥኩና ስደርስ፤
– እናት…በቆሎ ጥብስ ስጪኝ አልኩ አንዴ እሳቱ የሚንቀለቀለው ከሰል ምድጃ ዙሪያ አልቆላቸው የተቀመጡ ሶስት በቆሎዎችን፣ ከዚያ ደግሞ ህፃኑን ልጅ አፈራርቄ እያየሁ። ከብርድ የማያስጥል ቡቱቶ ቢጤ ለብሷል። ክሳቱ የሚያሳቀቅ፣ የፊቱ መገርጣት አንጀት የሚያንሰፈስፍ ልጅ ነው። ሲርበው የከረመ ይመስላል።
‹‹የቱን ላድርግልሽ?›› አለችኝ
-የቱ ይሻላል?
– ይህችኛዋ ቆንጆ ናት…በደንብ በስላለች ግን አላረረችም …አይሽ? አለችኝ አንዷን በቆሎ መሬት ላይ ከነሽፋናቸው ከተቀመጡ ጥሬ በቆሎዎች ገንጥላ ባመጣችው ሽፋን ጥቅልል አድርጋ ልታሳየኝ እየሞከረች።
ተቀበልኳት።
– ስንት ነው አልኩ ልጁን፣በተለይ አይኖቹን ሰርቄ እያየሁ። ከርታታ አይኖቹ ልገዛው የተቀበልኩት በቆሎ ላይ ናቸው።
ማሙሽ በጣም ርቦታል።
– ስድስት ብር አለችኝ
-እሺ ሁለት ስጪኝ አልኩና አስራ ሁለት ብር አውጥቼ ሰጠኋት።
ሌላ ቆንጆ ነው ያለችውን መረጠችና ልትሰጠኝ ስትጠቀልል ወደ ልጁ ዞርኩ። አንደኛውን በቆሎ ልሰጠው ጎንበስ ስል ከደረስኩ ጀምሮ አይኑን ከእኔ ላይ ያልነቀለው ልጅ ተስፈንጥሮ ተነሳ።
– እንካ ማሙሽ አልኩት ስፍስፍ እያልኩ…ለመንጠቅ በሚቀርብ ሁኔታ ሲቀበለኝ አንጀቴ እየተላወሰብኝ።
– እግዜር ይስጥልኝ የኔ እመቤት…ሙሉ ይስጥሽ የኔ እመቤት…ሙሉ ሙሉውን ይስጥሽ…. (የምርቃት ዝናብ አዘነበችብኝ)
ምንም ሳልናገር፣ የማይገባኝ ምርቃት ሽሽት ፊጭ ፊጬን አፍጥኜ ወደ ፊት መራመድ ጀመርኩ።
አስር ከማይሞላ እርምጃ በኋላ ግን ልገልፀው በማልችለው ምክንያት ዞር አልኩ። ልጁን ተመለከትኩ። ሳገኘው እንደነበረው ኩምትር ብሎ ተቀምጧል። እጆቹ ላይ በቆሎው የለም። ወደ ምድጃው ተመለከትኩ። ሁለት የበሰሉ በቆሎዎች ዳር ይዘው ተቀምጠዋል።
ሚዛኔን እንደመሳት አደረገኝ። አንገቴን ወደ ቤቴ አቅጣጫ አዙሬ ለመሄድ ብሞክር እግሮቼ ከረጠበው መንገድ የተመረጉ ይመስል ለገሙብኝ።
ከራበው ልጇ ሰው የገዛለትን በቆሎ ለምን ነጠቀች ብዬ ፈርጄባት አይደለም ማዘኔ።
ይህንን ብያኔ ለመስጠት እኔ ማነኝ….?
ኑሮዋን የማልኖር እኔ፣ ተራራዋን የማልወጣ እኔ፣ ቁልቁለቷን የማልወርድ እኔ በምን ስልጣኔ ልፈርድባት እችላለሁ…?
የስድስት ብር በቆሎ ከሚበላ ሶስት ትልልቅ ባለሁለት ብር ዳቦዎች ልትገዛ አስባ ይሆናል..
ቤት የሚጠብቃት ሌላ ትንሽ አፍ ከዚህ ስድስት ብር መካፈል እንዳለበት ስለምታውቅ ይሆናል…
አስር ወይ አስራ አምስት ብር እየከፈለች የምትኖርበት የቀበሌ ቤትን ግማሽ የቤት ኪራይ ልትከፍልበት ወስና ይሆናል..
ማዘኔ ይህንን እንድታደርግ ያደረጋትን፣ የእናትነት እንስፍስፍ አንጀቷን ያደነደነውን የኑሮዋን ትግል አስቤ ነው።
ማዘኔ የልጇን መቁለጭለጭ እያየች፣ የልጇን ረሃብ እየተመለከተች እንዲህ ያለውን ውሳኔ እንድትወስን የዳረጋትን እጅ በጆሮ ሕይወቷን አስቤ ነው….
ሐይል አሰባስቤ እርምጃዬን ስቀጥል፣ በቀኝ እጄ የያዝኩት ለብ ያለ በቆሎ እየቀዘቀዘ፣ በአይኖቼ ውስጥ ያቀረረው ትኩስ እንባ እየወረደ ነበር።
3 Comments
በጣምታምሪያለሽ
አዛኝ ለወገኑ
wow ተባረኪልኝ