(እውነተኛ ታሪክ)
ቀደም ባለው ጽሑፌ እንደገለጽኩት ኦነግና ኢህአዴግ ባደረጉት ስምምነት መነሻነት በኢህአዴግ ስር ያለው የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ-OPDO) በአካባቢያችን በሚኖረው ህዝብ ውስጥ ተሰማርቶ የፖለቲካ ስራ እንዲሰራ ተፈቅዶለት ነበር። በዚህም መሰረት የተወሰኑ የኦህዴድ ወታደሮች በሀብሮ አውራጃ ማረሚያ ቤት (ከርቸሌ) እንዲሰፍሩ የተፈቀደላቸው ሲሆን የቀድሞው የሀብሮ አውራጃ ገበሬዎች ማህበር ጽ/ቤት ደግሞ ድርጅቱ የፖለቲካ ስራ የሚሰራበት ቢሮ እንዲሆን ተሰጥቶታል (ይህ ቤት በአሁኑ ወቅት የሀብሮ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት የሆነው ነው)።
የኦህዴድ ካድሬዎች በህዝቡ ውስጥ የፖለቲካ ስራ ለመስራት ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም። ህዝቡ “የኦነግ ፕሮግራም የኦሮሞ ህዝብ ችግርን ለመፍታት የሚያስችል ብቸኛው ማኒፌስቶ ነው” ብሎ ያምን ስለነበር ሌሎች ድርጅቶችን ለመከተል ዝግጁ አልነበረም። በመሆኑም የኦህዴድ ካድሬዎች በቢሮአቸው ብቻ ተገድበው ቆይተዋል። በዚያ ድንግዝግዝ ጊዜ በነበራቸው ቆይታ አንድ ጊዜ ብቻ በገለምሶ ስታድየም ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ሞክረዋል።
በዚያን ጊዜ በርካታ ወጣቶች ወደ ኦህዴድ ቢሮ እየሄዱ ከካድሬዎቹ ጋር በፖለቲካ ጉዳዮች ይከራከሩ ነበር። ሆኖም ክርክሮቹ አንድም ውጤት አልነበራቸውም። እኔም በወቅቱ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ኦህዴድ ቢሮ እየሄድኩ ከካድሬዎቹ ጋር እከራከር ነበር (ያኔ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ብሆንም በጊዜው የነበረኝ የፖለቲካ ግንዛቤ ከጓደኞቼ አያንስም)። ታዲያ ከካድሬዎቹ ጋር እንደዚያ እየተከራከርን ከቆየን በኋላ በሰላም ነበር የምንለያየው። በማግስቱ ስንመጣም ካድሬዎቹ ክርክሩን ለመቀጠል ፈቃደኛ ነበሩ። ይሁን እንጅ ስሙን ያልያዝኩት አንደኛው ልጅ ፊቱን ኮስተር አድርጎ ነው የሚቀበለን። እኛም ክርክሩን እንዳልፈለገ ስለሚገባን እርሱን እንተውና ከሌሎቹ ጋር ክርክራችንን እንቀጥላለን።
ታዲያ እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ በሉ። እኛ ወደ ኦህዴድ ጽ/ቤት እየሄድን ከካድሬዎቹ ጋር እንከራከር የነበርነው ልጆች የኦነግ አባላት አይደለንም። ከግንባሩ ጋርም በየትኛውም መስመር አንገናኝም። ኦነግ የኦህዴድ ካድሬዎችን የማስደንገጥ ተልዕኮም ስለሰጠንም አይደለም በክርክሩ የተጠመድነው። ነገሩን ያስነሳው በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ወጀብ ነው። በዚያ ዘመን ሁሉም ሰው ሌሎች ወሬዎችን አቁሙ የፖለቲካ ወሬዎችን ማገላበጥን እንደ ሱስ ይዞት ነበር። ታዳጊ ይሁን አዋቂ፣ ወንድ ይሁን ሴት የፖለቲካ ወሬ ሱስ ሆኖበታል።
ሆኖም ያ ስሙን ያልያዝኩት የኦህዴድ ካድሬ እኛን እንደ ኦነግ አባላት አድርጎ የሚያየን ይመስለኛል። ኢህአዴጎች ከተማችንን በተቆጣጠሩበት ዕለት ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ “ማህዲ ከማል” ከሚባል ጓኛዬ ጋር ወደ ከተማዋ አውራ ጎዳና ስሄድ ይህ ካድሬ ሙሉ ትጥቁን እንደታጠቀ ከሀብሮ አውራጃ ግብርና ጽ/ቤት አጠገብ አገኘሁት። ካድሬው በአጠገቤ በማለፍ ላይ ሳለም በኦሮምኛ “ይህቺ ጩጬም እኛን ስትሳደብ ነው የከረመችው፤ አሁን በዚህ ክላሽ ዋጋዋን መስጠት ነው” የሚል ቃል ሲናገር ሰማሁት። አባባሉ በጣም ስላስደነገጠኝ ወደ ኋላ ዞር ሳልል በቀጥታ ወደ ቤት ሄድኩኝ።
ከቤት ቁጭ ብዬ ካድሬው የተናገረውን ነገር በውስጤ መላለስኩት። “በጽ/ቤታቸው በምናደርገው ክርክሩ ተናዶ ሀይለኛ ቂም በልቡ ቋጥሯል” በማለት ደመደምኩ። በመሆኑም በጧት ተነስቼ ከገለምሶ ለመጥፋት ወሰንኩ። መሄጃዬን በትክክል ባላውቅም አባቴ የተወለደበትን “በልበሌቲ የሚባለውን መንደር ጊዜያዊ ምርጫዬ አደረግኩት (መንደሩ ከገለምሶ ከተማ በስተደቡብ በአስር ኪሎ ሜትር ላይ ነው የሚገኘው)።
*****
ሰኞ ሰኔ 15/1984….
ጧት ቁርሴን ከበላሁ በኋላ አንድ አንሶላ በፌስታል ደብቄ ከቤት ወጣሁ። በጊዜው ቆዳ ጫማዬን አልለበስኩም። በዚያ ዘመን ባለ ላስቲኩ ኮንጎ ጫማ እና ከጎማ የሚሰራውን “በረባሶ” የተባለ ክፍት ጫማ መልበስ ፋሽን ሆኖ ስለነበረ እኔም በእግሬ ያጠለቅኩት “በረባሶዬ”ን ነው (ጉዞዬን በእግር የማደርግ በመሆኑም ጭምር ነው “ቆዳው ለእግሬ ይሞቀኛል” በማለት በረባሶውን የመረጥኩት)። ለጉዞ ስነሳ በእጄ ገንዘብ አልነበረኝም። ዓላማዬ ካድሬው እንዳይገድለኝ ከከተማዋ መራቅ ስለሆነ ስለስንቅና ሌሎች ነገሮች የማስብበት አዕምሮ አልነበረኝም።
በሶስት ሰዓት ገደማ ጉዞዬን ጀመርኩ። በውስጥ ለውስጥ መንገዶች እያቆራርጥኩ ከከተማዋ ወጣሁና በከተማችን ግርጌ ከሚፈሰው የ“አው-ሰዒድ” ወንዝ ደረስኩ። አው-ሰዒድን እንደተሻገርኩ እንደኔው ከከተማው በመጥፋት ላይ ከነበሩ ሶስት ሰዎች ጋር ተገናኘሁ። ከነርሱ መካከል አንደኛው “አህመዶ ሙሄ” ይባላል። ሁለተኛው ደግሞ “ዘከሪያ አብዱላሂ” (ዘኮ) ይባላል። እነዚህ ልጆች የከተማችን ተወላጅ ሲሆኑ በወቅቱ በነበራቸው የኪነት ተሰጥኦ ምክንያት ኦነግ ከገለምሶ ወደ ደደር ወስዶአቸው ለዓመት ያህል “ሀዊሶ በከልቻ” በሚባለው የኪነት ቡድን ውስጥ ሲያገለግሉ ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል እዚያ ቆይተው “ ቤተሰብ ናፈቀን” በማለት ወደ ገለምሶ በመጡበት ወቅት ነው ከተማዋ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር የገባችው። በመሆኑም “አደጋ ይደርስብናል” በማለት ሰለፈሩ ከከተማዋ ለመጥፋት ወሰኑ።
ሌላኛው ሰውዬ ሌንጮ ይባላል። በርካታ ሰዎች ግን “አይካ” በሚል የቅጽል ስም ነው የሚጠሩት። “አይካ” የአካባቢያችን ሰው አልነበረም። የተወለደበትን ቦታ ባላውቅም ለረጅም ዓመት በጅቡቲ ኖሯል። ከኦነግ ጋር የተቀላቀላውም እዚያው ጅቡቲ ነው። “አይካ” ቦክስ ጊታር እንደ ጉድ ይጫወታል። ኦነግ እርሱን ወደ ገለምሶ ያስመጣውም በከተማዋ የነበረውንና “ሀዊሶ ኦዳ ቡልቱም” የሚባለውን የኪነት ቡድን እንዲያሰለጥን በሚል ነው። (አይካን ከዚያች ቀን በኋላ በድጋሚ አላየሁትም፤ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለም አላውቅም፤ ዘኮና አህመዶ ሙሄ ግን አሁንም በገለምሶ ከተማ ነው የሚኖሩት)።
*****
በጉዞዬ ላይ ሶስቱ ሰዎች ስለገጠሙኝ በጣም ተደሰትኩ። ከነርሱ ጋር የፖለቲካ ወሬ እያወራሁ መንገዴን ቀጠልኩ። ገርቢ ጎባ ከሚባለው ሰፈር ስደንርስ “ታጁ” ከሚባል ዘመዳችን ጋር ተገናኘን። ታጁ “ደረኩ” ከሚባለው የትውልድ ሰፈሩ ወደ ገለምሶ እየሄደ ነበር። በመንገዱ ስላየው ነገር ስንጠይቀው “የኦነግ ጦር በመንገዱ ግራና በቀኝ ባለው የቡና እርሻ ሁሉ ሰፍሮበታል” የሚል መረጃ ሰጠን።
ከላይ እንደለገለጽኩት ከቤቴ የወጣሁት በልበሌቲ (ጭረቲ) ከሚባለው ሰፈር ለመድረስ ነበር። ሶስቱ ሰዎች ደግሞ የኦነግ አባላት በመሆናቸው በመንገዳቸው ከሚያገኙት የኦነግ ጦር ጋር ለመቀላቀል ነው የሚሄዱት። የታጁን ንግግግር ስሰማ ግን በጣም ነሽጠኝና አቅጣጫዬን ለመቀየር ወሰንኩኝ። ስለዚህ ወደ በልበሌቲ የሚወስደውን መንገድ ትቼ ወደ ደረኩ የሚወስደውን የእግር መንገድ ከሶስቱ ሰዎች ጋር ተያያዝኩት። ጥቂት እንደሄድን ዐሊይ አሕመድ ዓሊ ከሚባል የጓደኛዬ ወንድም ተገጣጠምን። ዐሊይ ሰላምታ ከሰጠን በኋላ የኦነግ ሰራዊት “ገንደ ሀጂ ዑመር” (የሀጂ ዑመር መንደር) ከሚባለው ሰፈር እንደሚገኝ ጠቆመን (ይህኛውም ሰፈር ከገለምሶ አስር ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነው የሚርቀው)።
ከሶስቱ ተጓዦች ጋር ጉዞዬን ቀጠልኩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አይካ “ረሃብ ተነሳብኝ” አለን። “አይካ” እንደዚያ ሲል እኔም ተራብኩኝ። ሁለቱ ልጆችም ተዳክመው መጓዝ አቃታቸው። በጊዜው አንዳችንም በኪሳችን ገንዘብ ስላልነበረን የምናደርገው ጠፋን። ሆኖም ለግብይት “ቢታኒያ” ከሚባለው ከተማ ትሄድ የነበረች በዐይን ብቻ የማውቃት አንዲት የጨውና የበርበሬ ነጋዴ ችግራችንን ሰምታ አምስት ብር ሰጠችን (የቢታኒያ ገበያ የሚቆመው ሰኞ ሰኞ ነው፤ ከላይ የጠቀስኩት እለት ሰኞ መሆኑን እያስታወሳችሁ!!)። ደረቅ እንጀራ ወደ ከተማ ከምትወስድ የገጠር ሴት ላይ ብዙ እንጀራዎችን በመግዛት ረሀባችንን ተወጣንበት።
*****
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ከሀጂ ዑመር ሰፈር ደረስን። የኦነግ ወታደሮች ያሉበትን ስንጠይቅ ከሰፈሩ ዝቅ ብሎ በሚገኝ እርሻ ውስጥ ሆጃ እየጠጡ መሆናቸው ተነገረን። እኛም ሰተት ብለን ከእርሻው ሄድን። ይሁንና እንጂ በእርሻው ውስጥ ያገኘነው ሰራዊት ብዙ የሚባል አልነበረም። በስፍራው የነበሩት ሰዎች በግምት ከሃምሳ የሚበልጡ አይመስለኝም። መሪያቸው የቀይ ዳማ መልክ የነበረው አንድ ወጣት ነው (ያ አዛዥ ሮዝ መልክ ያለው ሸሚዝ ከተመሳሳይ ሱሪ ጋር ለብሶ ነበር)። እኛ በስፍራው ስንደርስ ወታደሮቹ በርግጥም ከዛፍ ጥላ ስር ሆነው “ሆጃ” ሲጠጡ ነው ያገኘናው። አንዳንዶቹም ጫት ይቅማሉ።
ከነዚያ ሰዎች መካከል ማንንም አላውቅም። ከኔ ጋር ከከተማ የመጡት ሶስት ልጆች የድርጅቱ አባላት በመሆናቸው ከሰዎቹ ጋር ለመቀላቀል አልተቸገሩም። በተለይም ጊታሪስቱ “አይካ” በከተማው የሚታወቅ በመሆኑ ከወታደሮቹ ጋር ሞቅ ያለ ሰላምታ ነው የተለዋወጠው። እኔም ለወታደሮቹ ሰላምታ ከሰጠሁ በኋላ ከአንዱ ጥግ ሆኜ ሆጃዬን ጠጣሁ። ወታደሮቹ በከተማ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ለጠየቁን ጥያቄዎች የምናውቀውን ሁሉ መለስን። ታዲያ እኔ ከሌሎቹ ልጆች ተለይቼ “ኢህአዴጎች በኢሠፓ ጽ/ቤት የነበሩትን ካድሬዎችንና የኪነት ቡድን አባላትን አባረዋል” ስል አንድ ቀጠን ያለ ወጣት ሳቅ እያለ “እውነቱን ነው፤ ከኢሠፓ የተባረርነውና እኮ እኛ ነን” በማለት የኔን መረጃ አጠናከረልኝ። እኔም የሀሰት መረጃ እየሰጠሁ አለመሆኔ ስለታወቀልኝ በልቤ ኩራት ተሰማኝ።
ይሁንና የኔ ኩራት ለረጅም ጊዜ አልቆየም። የወታደሮቹ አዛዥ ወደኔ ፍጥጥ ብሎ እያየ ስለነበረ ፍርሃትና ሽብር ሰውነቴን ወረረው። “ምን አይቶብኝ ነው?” ብዬ ራሴን ስጠይቅ ሰውዬው ጫማዬን ማየት ጀመረ። እኔም የባሰ ፈራሁ። ቀስ ብዬ በአካባቢዬ የነበሩት ሰዎች የለበሱትን ጫማ ሳይ ከኔ በስተቀር አንድም ሰው “በረባሶ” እንዳልተጫማ ለማወቅ ቻልኩኝ። በመሆኑም አዛዡ በረባሶ ማጥለቄን በሌላ ነገር የተረዳው መሆኑ ገባኝ። “በረባሶ መልበስ ፋሽን መሆኑን አላወቀውም ማለት ነው?፣ እንዴትስ እኔን የመሰለ ታዳጊ በመጥፎ ነገር ይጠረጥረኛል? ወይ በረባሶ! ለጉዞው ከቆዳ ይልቅ አንተ ምቹ ነህ ብዬ ብመርጥህ እንዲህ ጉድ ታደርገኛለህ?… ደግሞስ ወደ በልበሌቲ መሄዱን ትቼ ወደዚህ ለምን መጣሁ?… ያ አላህ! የዛሬን ብቻ አውጣኝ” እያልኩ ጭንቀቴን በልቤ አገላበጥኩት።
(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 13/2007
ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (ክፍል ሶስት)