Tidarfelagi.com

ከጊቤ ባሻገር ያለችው ጅማ!

በለምለሚቷ ምድራችን ላይ እየተሽከረከረ ዚያራ ማድረግ ወጉ የሆነው የኢትኖግራፊ ፈረሳችን ታሪካዊቷን ጅማንና ህዝቧን መጎብኘት አሰኘው። እኛም “አበጀህ! ጥሩ ሀገር መርጠሃል” በማለት መረቅነው። ፈረሳችንም የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫን ይዞ ገሰገሰ። ከጊቤ ዉሃ ከተጎነጨ በኋላም ወደ ታሪካዊቷ ቀበሌ ሰተት ብሎ ገባ።

ጅማ! የአባጅፋር ሀገር! የአባ ፎጊ ሀገር! የአባ ቦጊቦ ሀገር! የአባ ጎመል ሀገር! ዝንተ-ዓለም አይረሴ የሆኑ ነገሥታት ታሪክ ሰርተውባት ለታሪክ ያኖሯት ውብ መንደር!!
ጂማ! የሰቃ ጨቆርሳ ሀገር! የጌራ ሀገር! የጉማ ሀገር! የጎማ ሀገር! የሊሙ ሂናሪያ ሀገር! አምስቱ የጊቤ መንግሥታት የለመለሙባት ምድር!!
ጅማ! የአባ ሚዛን ሀገር! የአባ ቆሮ ሀገር! የአባ ገንዳ ሀገር! የአባ ዱላ ሀገር! በኦሮሞ ምድር የዘመናዊ ቢሮክራሲ ጥንስስ የተጀመረባት ሰፈር!
ጅማ! የአቦል ሀገር! የበረካ ሀገር! የቃህዋ ጀባ ሀገር! ለስምንት መቶ ዓመታት ተወዳጅነቱ ሳይቀንስ የዘለቀውን “ቡና”ን ለዓለም ያበረከተች የሙሐባ መንበር!!
ጅማ! የተሚማ ሀገር! የገሜቲ ሀገር! የአያንቱ ሀገር! የአስሊያ ሀገር! የበድሪያ ሀገር! የፈይሩዝ ሀገር! ውብ ልዕልታትና ወይዛዝርት የወጡባት ምድር!!
*****
ተሚማ ነው ያልኩት? ይገርማል!! ገና የፈረሳችን ኮቴ መሬቱን ከመርገጡ ተሚማ በፈገግታ ታጅባ ልትቀበለን መጣች። ተወዳጅዋ የጅማ ጉብል!
ወይ አፈጣጠር!! “ቁርጥ ባለቤቴን” አለ ሰውዬው። በእውነት ይህቺ የጅማ ጉብል ናት ወይስ በሀረርጌ የምናውቃት ቀሽቲ? እንዲያው ሁለመናዋ ከኛዋ ቀሽቲ ጋር አንድ ነው እኮ!!

ይህቺን “ኑረል ዐይን” የምትመስል ጉብል በተራ ሰላምታ ማነጋገር ተገቢ መስሎ አልታየንም። በመሆኑም ድሮ የ“ሐፈዝናቸውን” ሙገሳዎችና በቅርብ ጊዜያት የሰማናቸውን “ወለሎ”ዎች ተራ በተራ እየደረደርን ዐጃኢብ እስክትል ድረስ እንዘምርላታለን።
*****
እውነቴን ነው!! ለጂማዋ ጉብል ማን ያልዘመረ አለ?… ብዙ ተዘፍኖላታል። ብዙ ተብሎላታል። እንዲያም ሆኖ ግን ለርሷ የተደረደረው ሙገሳ በጣም ያንሳታል። እልፍ አዕላፍ “ቀሲዳ”፣ “ሩባኢያት”፣ “ወለሎ”፣ “ቅኔ”፣ “ገዛል”፣ ወዘተ… ይገባታል። የኛም ዚያራ ያማረ ይሆንልን ዘንድ ወደ ሌሎች ወጎች ከማለፋችን በፊት ለርሷ ክብር የተዜሙትን ዜማዎች አንዴ በጀመዓ ብንከልሳቸው መልካም ይመስለኛል (በአጸፌታው የጂማዋ ጉብል ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ አድርጋልን ዚያራችንን ልታደምቀው ተሰናድታለች)።

ለጅማዋ ጉብል የተዜመው የመጀመሪያው ዜማ የትኛው እንደሆነ በትክክል አናውቅም (አንቺ ተሚማ! ያ ገሜቲ ጂማ!! ያ በሬዱ ነማ!! እኛ “እኛ” መሆናችንን ታውቂዋለሽ አይደል?…. አዎን! “እኛ” እያልን የምንጽፈው ከሀረርጌ በመሆናችን ነው)። እስካሁን ድረስ ባለን መረጃ መሰረት ግን የጥላሁን ገሠሠ “ሰላመካ ያ ገንኔ ሰላመካ” ለጅማዋ ጉብል የተዘፈነ የመጀመሪያው ዜማ ይመስለኛል። የግጥሙ ደራሲ ተገኑ ባልከው ይባላል (“አሸም ያ ማተቤ”ንም የጻፈው እርሱ ነው)። ጥላሁን ለጅማዋ ጉብል ሲዘፍን እንዲህ ነበር ያለው።

Salaama kaa yaa gannee salaama kaa
Harka fuune yaa immeetee salaamka.
Dubbiin Tamiima dubbiin mucayyoo magaala
Ija koo qabee gurra koo qabee na raasa
Gandan dhagayee dhiisi naan jenaani
Ittin dhiise yaadden na qabnaani.

ጥላሁን በዘፈኑ ውስጥ የጅማን ስም አልጠቀሰም። ነገር ግን በግጥሙ ውስጥ የተጠቀማቸውን ቃላት እና የሙዚቃውን ምት (rhythm) በአንክሮ ስናያቸው ዘፈኑ “ለጅማዋ ተሚማ” እንደተዘፈነ በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ከበርካታ የኦሮምኛ ዘዬዎች መካከል “ሰላመ-ካ” እያሉ ሰላምታ መስጠት የሚቻለው በጅማው ዘዬ ነው። “ሰላመት” ከዐረብኛ ወደ ኦሮምኛ የገባ ቃል መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ቃሉ በኦሮምኛ ውስጥ የሚያገለግልበት ስልት እንደየአካባቢው ይለያያል። በሀረር ኦሮምኛ አንድን ሰው ስንገናኝ “ሰላም ጄኔ” (ሰላም ብለናል) ለማለት እንችላለን። በጅማው ዘዬ ደግሞ “ሰላመ-ካ” እንላለን (ሌሎች ስልቶችን ከወደታች እንመጣባቸዋለን)።

በሌላ በኩል ደግሞ ጥላሁን ልጅቷን “ተሚማ” እያለ ነበር የጠራት። ይህም ዘፈኑ ለጅማ ጉብል የተዜመ መሆኑን ያሳብቃል። የጅማ ሴቶች ከሚጠሩባቸው ስሞች መካከል በጣም ዝነኛ የሆነው እርሱ ነው። ሌሎች አርቲስቶችም የጅማን ኮረዳ ለመጥራት ሲፈልጉ በዚህ ስም ነው የሚጠቀሙት (ጥላሁን “ፋጡማ” ወይንም “አዒሻ” ቢል ኖሮ ለሀረር ቆንጆ ነው ያዜመው ብለን እንጠረጥር ነበር)።
*****
ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው። “ሃጫሉ ሁንዴሳ” (Haacaaluu Hundeessaa) የሚባል የኦሮምኛ ዘፋኝ ባሳተመው የመጀመሪያ ካሴቱ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር። በካሴቱ ውስጥ ከተካተቱት ዜማዎች መካከል በጣም ተወዳጅ ሆኖ የወጣው ደግሞ ለጅማዋ ጉብል የተገጠመው ነው። ሃጫሉ ከጅማ ጉብል የያዘውን ፍቅር ሲገልጽ እንዲህ ነበር ያለው።

Galaanni Gibee guutus daaktuuf bidiruutu nama ceesisaa
Garaan jaalatte hin rafuu halkuu jilbibbii nama deemsisaa
Ani sossodaadhe barana qalbii kootii
Gibee gaman jaaladhe sanyii mootii.

ሃጫሉ የዘፈነውን ወደ አማርኛ ስንተረጎመው እንደሚከተለው ይሆናል።
“የጊቤ ወንዝ የሞላበት ሰው በዋናተኛና በታንኳ ይሻገራል
ያፈቀረ ሆድ ግን አያስተኛም፤ ሌሊቱን በሙሉ በዳዴ ያስኬዳል።
አረ ዘንድሮስ ፈራሁኝ እንዳይታመም ይሄ ቀልቤ
ከጊቤ ወዲያ ያለችውን የንጉሥ ዘር አፍቅሬ ከልቤ።

ሃጫሉ የወደዳት ልጅ “ጉብል” ብቻ ሳትሆን “የንጉሥ ዘር” እንደሆነች ነግሮናል። የዚህን አባባል “ተፍሲር” ወደፊት ስለምንመጣበት በአዕምሮአችሁ ውስጥ መዝግባችሁት ቆዩ።
*****
ከላይ እንደገለጽኩት ለ“ጅማ ጉብል” የተዜመው የመጀመሪያ ዜማ የጥላሁን ገሠሠ “ሰላመካ” ነው። ነገር ግን ጥላሁን “ጉብሊቷ”ን በስም አልጠቀሳትም። ታዲያ “የጅማ ጉብል” የሚለውን ሐረግ በግጥሙ ውስጥ በግልፅ (explicitly) በማሳየት ማዜሙን የጀመረው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁን?

ነፍሱን ይማረውና አሁን በህይወት የለም። አብደላ መሐመድ ይባላል። አብደላ የፖሊስ ኦርኬስትራ አባል ነበረ። በኦርኬስትራው ውስጥ በነበረው ቆይታ “አሪፍ” ጣዕመ ዜማዎችን አስመዝግቦ አልፏል። ከነርሱ ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ “መጋለ ቀሎ ያ በሬዱ ጅማ” የተሰኘው ዘፈን ነው። አስታወሳችሁት አይደል?… አዎን!! አብደላ ያዜመው ዜማ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ በአንድ ሰሞን የህዝብ ዘፈን እስከመሆን ደርሷል። በተለይም በቀድሞው ጊዜ የኢትዮጵያ ሬድዮ የኦሮምኛ ፕሮግራም የአብደላን ዘፈን እየደጋገመ ያጫውተው የነበረ መሆኑ ኦሮምኛ የማይሰሙ ሰዎችም ጭምር የዘፈኑን ግጥሞች እንዲሸመድዱ አስችሎአቸው ነበር። እነሆ አዝማቹን ላስታውሳችሁ ነው።

Jenneen ashamaan ashamaa jenneen ashamaa
Magaala qalloo yaa bareedduu Jimmaa

የአብደላ ዘፈን መልዕክቱ እንዲህ ሊሆን ይችላል።
“እንዴት ነሽ… ሰላም ነሽ ወይ” አልናት።
ያቺን ጠይም ጉብል የጅማ ወጣት።

አብደላ በዚህ ዘፈኑ የጅማዋን ጉብል በማወደሱ ብቻ አይደለም የሚለየው። በዘፈኑ ውስጥ የጅማ ሰዎች መታወቂያ የሆነውን የኦሮምኛ ቃል በመጠቀም ግጥሙን ያቀናበረ በመሆኑም ጭምር ነው የሚታወሰው። ነገሩ እንዲህ ነው።

በርግጥም የጅማ ሰዎች ሰላምታ ሲሰጣጡ ከላይ በጠቀስኩት “ሰላመ-ካ” የተሰኘ ቃል ይገለገላሉ። ሆኖም ጅማዎች ሰላምታውን በመጠይቃዊ ዘዴ ሲያቀርቡልን ብዙሃኑ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች በሚናገሩበት ስልት “አከም” (Akkam) አይሉም። ከዚህ በተለየ ስልት “አሸም” (Asham) ወይንም “አሸማ” (Ashamaa) ነው የሚሉት። አንድ ኦሮሞ የትም ሆኖ “አሸም” ብሎ ሰላምታ ካቀረበላችሁ ትውልዱ ከወደ ጅማ እንደሆነ ልብ በሉ።(በነገራችን ላይ ለየት ያለ መጠይቃዊ የሰላምታ ማቅረቢያ ቃል የምናገኝበት ሌላው የኦሮምኛ ዘዬ በኢሉባቦር የሚነገረው ነው፤ የኢሉባቦር ሰዎች “አከም” ለማለት ሲሹ “አተም” ነው የሚሉት። የወለጋና የምዕራብ ሸዋ ኦሮሞዎችም “አተም”ን ያውቁታል። ነገር ግን ወለጋዎችና ሸዋዎች በአብዛኛው “አከም”ን ነው የሚጠቀሙት)።

የጅማ ሰዎች በሚያዜሟቸው ዘፈኖች ላይ በብዛት የሚጠቀሙት ሌላ ቃል አለ። እንዲያውም ያ ቃል ከቋንቋነትም አልፎ የጅማን ዘፈን የምንለይበት ምልክት (mark) እስከመሆንም ደርሷል። ለምሳሌ አንድ አርቲስት በዘፈኑ ውስጥ “አራዳ… አራዳ ሆዬ” የሚል ሐረግ ከደጋገመ ዘፋኙ ስለአዲስ አበባ እየዜመ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። “እሪኩም” እና “መጋሎ” የተሰኙ ቃላትን የሚያበዛ ዘፋኝም ስለወሎ የሚያዜም ነው። ስለጅማ የሚያዜም ሰው ደግሞ ብዙ ጊዜ “አህላን አህላ” እያለ ነው ዘፈኑን የሚጀምረው።

አዎን! በኦሮምኛ ጨዋታዎች ውስጥ “አህለን አህላ” ከተባለ ዘፈኑ የጅማ መሆኑ ምንም አያከራክርም። “አህለን” በመሰረቱ የዐረብኛ ቃል ነው። በዐረብኛ “አህለን ወሳህለን” ከተባለ “ጤና ይስጥልኝ” እንደማለት ነው (አገባቡ ሰፋ ሲል ደግሞ “እንኳን ደህና መጡ” እንደማለትም ይሆናል)። በሃይማኖታቸው ሙስሊሞች የሆኑት የጅማ ሰዎች “አህለን”ን ከዐረብኛ ወርሰው ነው ቤተኛ ያደረጉት።
*****
ጅማዎች “አህለ”ን የሚሉት ከልብ የመነጨ ስሜታቸውን ለመግለጽ ነው። እኛ ጅማ ስንገባ የፈረሳችንን ልጓም ይዛ የጅማን መሬት እንድንረግጥ የረዳችን “ተሚማ”ም ከፈገግታ ጋር “አህለን” በማለት ተቀብላናለች።
አህለን አህላ… ሸጌ አህለን አህላ
አህለን.. አህላ.. ጊፍቲ አህለን አህላ

አፈንዲ ሙተቂ

ህዳር 22/2007
በሀረር ከተማ ተጻፈ።

ከጊቤ ባሻገር ያለችው ጅማ (ክፍል ሁለት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *