Tidarfelagi.com

ጥቂት ቁንጣሪ ሃሳብ ከ “Born a Crime” መፅሐፍ!

የዚህ መፅሐፍ ፀሐፊ ትሬቨር ኖህ (Trevor Noah) በሙያው አዘጋጅ፣ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ተዋንያን እና ኮሜዲ ነው። ይሄ ፀሐፊ የኮሜዲ ስራውን ማቅረብ የጀመረው በሐገሩ በደቡብ አፍሪካ ነበር። ይሄንንም ስራውን በመቀጠል አሁን በሚገኝባት አሜሪካም በተፅዕኖ ፈጣሪነት በሚታወቀው ፕሮግራም ላይ ምፀታዊ ዜናዎችን የሚያቀርብ (The Daily Show, an American satirical news program on Comedy Central) የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ እየሠራ ይገኛል።

“Born a Crime” መፅሐፍ በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም. ለአንባቢያን የቀረበ ሲሆን ከፍተኛ ሽያጭን አስገኝቷል። ፀሐፊው በትውልድ ሐገሩ በደቡብ አፍሪካ ያሳለፈውን የልጅነት ሕይወቱን በመፅሐፉ በሚጥም ቋንቋ ይተርክልናል።

መፅሐፉ የቅኝ አገዛዝ አስከፊነትን የበለጠ የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ዘረኝነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል የሚያስተምር ብዙ ቁምነገሮችን አጭቋል። በተለይ መፅሐፉ ሲጀምር በቅኝ ገዢዎቹ እንግሊዛውያን እ.ኤ.አ. በ1927 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካውያን ላይ የተጣለውን ፅኑ ሕግ (Immortality Act) ያስቀምጣል። ህጉ በጊዜው በነበረው የእንግሊዝ ንጉስ ረቅቆ የወጣ ሲሆን በውስጡም ሁለት አንቀፆችን ብቻ ያካተተ ነበር።

1. ‹‹ማንኛውም ነጭ ወይም አውሮፓዊ ወንድ ከደቡብ አፍሪካዊ ጥቁር ሴት ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ የለበትም። ማንኛውም ደቡብ አፍሪካዊ ጥቁር ወንድ ከማንኛዋም ነጭ ወይም አውሮፓዊ ሴት ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ አይፈቀድለትም። ይሄንን ህግ የጣሰ ወንድ ወንጀለኛ ነው፤ ከአምስት ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ይታሰራል።››

2. ‹‹ማንኛዋም ጥቁር ወይም ደቡብ አፍሪካዊ ሴት ከማንኛውም ነጭ ወይም አውሮፓዊ ወንድ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ አይፈቀድላትም። ማንኛዋም ነጭ ወይም አውሮፓዊ ሴት ከማንኛውም ጥቁር ወይም ደቡብ አፍሪካዊ ወንድ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ ክልክል ነው። ይሄንን ህግ የጣሰች ሴት ወንጀለኛ ነች። ቅጣቱም ከአራት ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ወህኒ ያስወርዳል።››… ይላል።

ቅኝ ገዢዎች የሚያመሳስላቸው ባህሪ ቢኖር ቅኝ የሚገዙትን ሐገርና ሕዝብ በብሔርና በጎሳ በመለያየት እርስበርሱ እንዲጠላላ ማድረግ ነው። እነሱ ገላጋይ በመሆን የስልጣን እድሜአቸውን ያራዝማሉ። ዛሬም በእኛ ሐገር የጎሳ ፖለቲካ ችግር የሚስተዋለው ቅኝ ገዢዎች አጥምደውት የነበረው የዘረኝነት ቦንብ እየፈነዳ በመሆኑ ነው።

በዚህ መፅሐፍም በዋናነት የምናየው ይሄንኑ ነው። በደቡብ አፍሪካ ከመቶ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቢኖሩም በዋናነት ግን በህዝብ ብዛታቸውና በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ሁለት ታላላቅ ብሔሮች ብቻ ናቸው። እነዚህም ዙሉ (Zulu) እና ኮክሳ (Xhosa) በመባል ይታወቃሉ። ዙሉዎች (Zulu) ከነጮቹ ገዢዎች ጋር ሁልጊዜም ውጊያ ላይ ናቸው። ኮክሳዎች (Xhosa) ግን ከዙሉዎች በተቃራኒ አሳቢዎች ነን ብለው ያስባሉ። በዚህም ምክንያት ከነጮቹ ቅኝ ገዢዎች ጋር አብረው ቁጭ ብለው ቼዝ እስከመጫወት ደርሰዋል።

ኮክሳዎች ‹‹ወደድንም ጠላንም ነጮቹ እዚሁ ከእኛ ጋር ናቸው። ምናልባት ሊጠቅመን ስለሚችል እስቲ የያዙትን ዕውቀትም ይሁን መሳሪያ እንይ። ከእነሱ ጋር ሁልጊዜ ከመዋጋት እንግሊዘኛ ቋንቋቸውን ለምደን የሚሉትን ነገር በመረዳት ስምምነት ልናደርግ እንችላለን›› ይላሉ።

የሁለቱ ታላላቅ ጎሳዎች አለመስማማት ቀኝ ገዢዎቹን ዕድሜ ሠጥቷቸዋል። በስተመጨረሻ ግን ሁለቱ ጎሳዎች መስማማት ሲጀምሩና የጋራ ጠላታቸው ማን እንደሆነ ሲረዱ ቅኝ ገዢዎች ሊሸነፉ ችለዋል። ቅኝ ገዢዎቹ ወድቀው ደቡብ አፍሪካ ነፃነቷን ብትጎናፀፍም እስካሁን ድረስ እርስበርስ የብሔር ግጭቱ ሊቆም አልቻለም። ይሄም ቅኝ ገዢዎቹ የዘሩት የዘረኝነት ዘር ነው።

ደቡብ አፍሪካውያን እምነታቸው እንኳን ወደውና ፈቅደው የተቀበሉት ሳይሆን ተጭኖባቸው ስለመሆኑ ፀሐፊው ይናገራል። ፈረንጁ ይመጣና፡- ‹‹ለኢየሱስ መፀለይ አለብህ›› ይለናል። ቀጥሎም ‹‹ኢየሱስ ያድንሃል!›› ይለናል። ደቡብ አፍሪካዊው ሲመልስ ግን፡- ‹‹አዎ መዳን እንፈልጋለን። ነገር ግን መዳን የምንፈልገው ከእናንተ ነው እንለዋለን›› በማለት የቅኝ አገዛዝን የነፃ አዕምሮ እስረኝነት ጭምር በሚያሳዝን አገላለጽ ያስረዳናል።

ፀሐፊው የነጭ የበላይነትን ሲተች እንዲህ ይለናል፡-

‹‹ጥቁር አሜሪካዊ ሆነህና በተኩላ ብታምን አንተ አውሬ ነህ። አፍሪካዊ ሆነህ የጥንታዊውን የአባቶችህን አምላክ ብትለማመን አንተ ኋላቀር ነህ። ነገር ግን ውሃን ወደወይን የቀየረውን ሰው ብታመልክ ያኔ ማንም ይቀበልሃል›› (If you are native American and pray to the wolves, you are a savage. If you are African and you pray to your ancestor, you are primitive. But when white people pray to a guy who turns water to wine, well, that’s just common sense.) በማለት ቁጭቱን ይናገራል።

ወዳጆች የቅኝ አገዛዝ አስከፊነት እጅግ ሰቅጣጭ ነው። በነፃነት መኖር ምን ያህል ከአዕምሮ እስረኝነት ነፃ እንደሚያወጣና ሙሉ ሰው እንደሚያደርግ ይሄን መፅሐፍ ያነበበ ይረዳዋል። ዛሬ ደቡብ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ቢሆኑም የቅኝ አገዛዝ ጠባሳው ግን ከአዕምሯቸው አልጠፋም። መንፈሳዊ እስራታቸው በበቂ ሁኔታ አልተፈታም። መፅሐፉም የሚያስረዳን ይሄንኑ ነው።

ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን የነፃነት አየር እንድንተነፍስና መንፈሳዊ ፀጋችን እንዳይጓደል ስላደረጉልን የደምና የአጥንት መስዋዕትነት ምስጋና ይገባቸዋል። የነፃነትን ጥቅም የሚያውቀው ነፃነቱን የተቀማ ነውና በነፃነት መኖር ታላቅ ቁምነገር ነው። እዚህ ቁምነገር ላይ ያደረሱን ይክበሩ ይመስገኑ!

ለማንኛውም ከመጽሐፉ ከተጠቀሱት የትየለሌ ሃሳቦች ኢምንቷን ነውና ያቀረብኩት መፅሐፉን በሙላት ታነቡት ዘንድ ግብዣዬ ነው።

መልካም ንባብ!

ቸር ሃሳብ!

________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሐሙስ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *