Tidarfelagi.com

ክርስቲያኗ ፍቅረኛዬ ናፈቀችኝ!

ረመዳን ሲመጣ ከማስታውሳቸው ሰዎች አንዷ ናት። በእድሜዋ ከኔ በሁለት ዓመት ታንሳለች። ከ1996-2004 በነበረው ዘመን የኔ ምርጥ ጓደኛ እርሷ ነበረች። ሌላ ሴት የመጋበዝ ባህል አልነበረኝም። እርሷን ግን ከፒያሳው ኡመር ኻያም ጀምሮ እስከ ውድ ሬስቶራንቶች ድረስ እየወሰድኳት እጋብዛት ነበር። እርሷም አጸፋዋን በመክፈሉ ረገድ አንደኛ ነበረች። በተለይ የረመዳን ወር ሲመጣ ቴምር የምትገዛልኝ እርሷ ናት።

ይህቺ ልጅ ፍቅረኛዬ ናት። ፍቅራችን ግን ምንም ጾታዊ ፍላጎት ያልነበረበት ንጹሕ ፍቅር ነው። እናንተ “sisterly- brotherly” ትሉታላችሁ መሰለኝ። ፈረንጆች እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር Platonic love ይሉታል። እኛ ግን በጊዜው ስም አላወጣንለትም ነበር።

ሆነም ቀረ ግን በጣም እወዳታለሁና “ፍቅረኛዬ” ናት። በመረበ- ወሲብ ያልተተበተበ፣ አልኮልና ፈርሾ ያልፈሰሰበት፤ ቅናት፤ መቅናት፤ ማስቀናት ጂንኒ ጀቡቲ… ያልታየበት የንጹሕ ፍቅር ጓደኛዬ!!
——
የህይወት ጥሪ ነገር ሆነና ያቺ “ፍቅረኛዬ” ወደ አሜሪካ በረረች። እኔም እርሷ ከዚህ ሀገር ከጠፋች ጀምሮ አዲስ አበባ ስመጣ በጣም ይጨንቀኛል። እንግዲህ በልጅነቴ የማውቃቸው መምሬ ሙላቱን እና ያቺን ልጅ ሳስብ በእውነትም ፍቅር ለኢትዮጵያ ህዝብ መለያ ባህሪው ነው እንጂ ለስትራቴጂ ተብሎ የሚለማመደው ጊዜያዊ ስልት አይደለም እላለሁ። ሙስሊምና ክርስቲያኑን ኢትዮጵያዊ እለያያቸዋለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ በርግጥም እርሱ ህልመኛ ነው። ህልመኛ!! (የሀረርጌው የአቶረራ ባህል ለዚህ ቋሚ ምስክራችን ነው)።
—-
ከዚህ በፊት ስለፍቅረኛዬ ሳቂታነት ብዙ አውግቼአችሁ ነበር። ሆኖም በጣም የሚገርመኝ ባሕሪዋ ቅንነቷ ነው። በሁሉም ረገድ “አዎንታዊው”ን ነገር ብቻ ነበር የምታስበው። ለምሳሌ እርሷ አትዋሽም። በመሆኑም “ሌላውም ሰው አይዋሽም” ብላ ነበር የምታስበው።

ሀረር ሆኜ እደውልላትና “አዲስ አበባ መጥቻለሁ: ፒያሳ እንገናኝ” እላታለሁ። እርሷም በእሺታ ፒያሳ ትጠብቀኛለች። በየአፍታው እየደወለች “የት ደርሰሃል” ትለኛለች። “ስቴድየም ደርሻለሁ፣ እየመጣሁ ነው” እያልኩ አዘናጋታለሁ። “እዚህ ደርሻለሁ፣ እዚያ ገብቻለሁ” እያልኳት በመጨረሻ “ሀረር ነው ያለሁት” ብዬ በሳቅ እንተከተካለሁ። ታዲያ የርሷ ምላሽ “አፈር ብላ” የሚል ብቻ ነው።

አንድና ሁለት ቀን አይደለም እንዲህ ያደረግኳት። በተደጋጋሚ ጊዜ ተጫውቼባታለሁ። በኋላ ግን እየፈራኋት መጣሁ። “ለምንድነው ይዋሻል ብላ የማትጠረጥረው? አውቃ ነው የምትሸወደው እንዴ?” ብዬ ራሴን ጠይቄ እገረም ነበር። እንግዲህ ሁለታችንም “የውሸታሙ እረኛ ተረት”ን እየሰማን ያደግን ሰዎች ነን። ሆኖም እንደ እረኛው “ይሄ ልጅ ዛሬም በኔ ሊጫወት ነው” ብላ አለመጠርጠሯ ያስደንቀኝ ነበር።

አንድ ቀን ደፍሬ እርሷኑ ጠየቅኳት። እርሷም “እንዲያ ዓይነቱን ጨዋታ በሂደት እንደምትተወው ስለማውቅ ነው የተሸወድኩልህ” አለችኝና ኩም አደረገችኝ።
—-
በነገራችን ላይ ለረጅም ጊዜ የምጽፍበት ኮምፒውተር ከርሷ ያገኘሁት መሆኑን ነግሬአችሁ ነበር አይደል?… አዎን!! በርሷ በረከት ነው ከናንተ ጋር ለመነጋገር የቻልኩት። በወቅቱ በእጄ ላይ ገንዘብ አልነበረም። አንድ የምቀርበውን የስጋ ዘመዴን ኮምፒውተሩን እንዲያውሰኝ ብጠይቀው “እምቢ” ብሎ ዘጋኝ። ክርስቲያኗ የሸገር ልጅ ግን “ይኸውልህ” ብላ ሰጠችኝ። ያ ኮምፒውተር ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግሎኛል።

አላህ በሄደችበት ሁሉ ሰላሙን ያብዛላት!!

One Comment

  • value commented on August 13, 2019 Reply

    ተመችቶኛል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *