Tidarfelagi.com

ወጣትነቴን ያያችሁ

አላያችሁም አውቃለሁ!
መጠየቅ፣ ልማድ ሆኖብኝ፣
ቁጭቴ ብሶት ጭኖብኝ
የሄደች ወጣትነቴን፣ ያያችሁ…ያያችሁ እያልኩ፣
ባታዩም እጠይቃለሁ፡፡
* * * *
ያያችሁ ወጣትነቴን?
አፍለኛ፣ ማራኪ ወቅቴን?

በጫት ጉዝጓዝ አፍኜ፣ ከፍኜ የገደልኳትን
በማይገባኝ የፈረንጅ አፍ፣ አደንቁሬ የጣልኳትን
ወጣትነቴን ያያችሁ፣
ሳልጨብጥ ያበረርኳትን፡፡
* * * *
ከመጠጥ ከጭሳጭሱ፣
ከእጅል ከግሳንግሱ
ከ `ፓሪው` ከየድግሱ
ሳትበራ ያጨለምኳትን፣
ሳትፈካ የቀጨኋትን
ወጣትነቴን ያያችሁ፣
ሳልጨብጥ የለቀኳትን፡፡

በኤምሬትስ አንሸራሽሬ፣ በኦልትራፎርድ አንቀባርሬ
ከ `ኑካምፕ` አምባ ሞሽሬ፣
ከብክነት ያጋባኋትን፣
ወጣትነቴን ያያችሁ፤
ሳትነጋ ያጨለምኳትን!
ያያችሁ ወጣትነቴን፣
የዕድሜዬ አደዩዋ ወቅቴን
ያልሞቀች ትንታግ ግለቴን!

በማህበራዊ ገፅ ተጥጄ
በእንስት እቅፍ ነድጄ
በ `ሮክ` `ሂፓ-ሃፕ` አብጄ
ከእፍ፣ ክንፉ አላምጄ፤
ቅፅበት አሁኗን እያበራሁ፣
ነግ ተስፋዋን እያጠፋሁ፣
ያፀለምኳት መብራቴን፣
የማለዳ ፍካት ወቅቴን
ያያችሁ ወጣትነቴን?!
* * *
በሆሊውድ የተቃኘች
በእንግሊዝ ኳስ የተገራች
በአስረሽ ምችው የከነፈች
ከእውቀት ጠበል የነጠፈች
ከሃሳብ ምንጭ፣ የደረቀች
በዝንጋዬ ድቅድቅ ያለች፤
በአባት ንቀት የጠለሸች
ከአያት ታሪክ የተለየች
ወጣትነቴን ያያችሁ፣ አደዬን የጠወለገች!

በማበቢያዋ ረግጬ
ጅምር መንገዷን ቆርጬ
ምጥ ውልደቷን አጨንግፌ፣
ያበረርኩ የሰደድኳትን፤
አካልቤ፣ አክለፍልፌ
ወጣትነቴን ያያችሁ፣
የአዲስ ምራፍ በራፌን!

አወይ ወጣትነቴ፣ አወይ ወጣትነትህ፣
አወይ ወጣ–ትነታችን
ትር–ትር ህልማችን!
* * *
ስንቱ የእኔ አይነት፣ ስንቱ እንዳንተ ወጣት
የወጣች ጀምበሩ፣ ሳያያት ጠልቃበት
እድሜ ይገብራል፣ እድሜ የጠፋበት!
ስንቱ ያንተ አይነት፣ ስንቱ እንደኔ ወጣት
እራሱ ያላያትን፣ ያያችሁ እያለ፣
ያለፈች እድሜውን ባላለፈው እድሜ፣ አፋልጉኝ እያለ፤
ወጥታ ለቀረችው፣ ያልወጣች እድሜውን፣ እየሰዋት አለ፡፡

ወጣትነቴን ያያችሁ፣
ያያችሁ ያገኛችኋት
“ በፀፀትሽ አልንሰፍሰፍ፣
በትዝታሽ አልነቀፍ፣
በስላቅሽ አልገረፍ፣
እንዳለፍሽኝ፣ ተይኝ ልለፍ
ከዚህ በላይ፣ በፀፀትሽ አልገረፍ
`አሁን` ሳያልፍ፣ እሱን ልቀፍ
በአሁኔ ውስጥ አሁን ልለፍ“

ብላችሁ ግን አስረዱልኝ፣
ላልፎ ሂያጇ ንገሩልኝ
ወጣትነቴን ካያችሁ፣
ካያችሁ፣ ካገኛችኋት!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *