(የታሪክ መነሻ ሃሳብ- የካሊድ ሆሴኒ ‹‹ዘ ካይት ረነር›› አንዲት ዘለላ ታሪክ (The Kite Runner- Khaled Hosseini)
ተንበርክኬ ነበር።
በዚያ የጥቅምት ውርጭ፣ ከምሽቱ አራት ሰአት ተኩል ላይ ከሰማይ በላይ እሪታዬን እያቀለጥኩ፣ ቀዝቃዛው አስፋልት ላይ ተንበርክኬ ነበር። በብርድ በሚንጫገጩ ጥርሶቼ መሃከል እጮሃለሁ። ጉሮሮዬ የተሰነጠቀ፣ ደረቴ የተተረተረ እስኪመስለኝ ድረስ እጮሃለሁ።
በኋላ ሲነግሩኝ አደጋው ቦታ አምቡላንስ ደርሶ ልጄን አፋፍሶ እስኪወስደው ድረስ እንዲሁ ስጮህ ነበር።
ሆሰፒታል ስንደርስ በጥድፊያ ልጄን በባለጎማ አልጋ እየገፉ ሌላ ክፍል ወስደውት አላስገባም አሉኝ።
አትገቢም አሉኝ።
መድሃኒት መድሃኒት የሚለው ኮሪደር ላይ ቆሜ ቀረሁ። ። በነጭ ጋወን ውስጥ ወዲህ ወዲያ የሚሯራጡ ሃኪሞች። ሰማያዊ ለብሰው እዚህም እዚያም የሚሉ ነርሶች። በየወንበሩ ላይ አንገታቸውን ደፍተው፣ ጥርሳቸውን እያኘኩ የተቀመጡ ሰዎች። በአንቅልፍ የናወዙ አስታማሚዎች። አዲስ አደጋ ይዘው እየጮሁና እያለቀሱ ወደ ኢመርጀንሲ ክፍል የሚበርሩ ቤተሰቦች። አትገቡም እያሉ የሚከላከሉ ነርሶች። ሃኪሞች።
በቆምኩበት የሆነውን ለማሰብ ሞከርኩ።
እየሳቀ ነበር። እንቅልፌ መጣ ምናምን ብሎኝ አንተ እኮ ከንግዲህ ትንሽ ልጅ አይደለህም…እስከ አምስት ሰአት መቆየት አትችልም እንዴ…ዳይፐር እንደገና መግዛት ልጀመር እንዴ ስለው እየሳቀ ነበር።ያቺ ከአባቱ የወረሳት ዲምፕሉ። ያቺ ፍቅፍቅ እያለ የሚስቃት ሳቁ። የግራ መጠመዝዣውን ይዤ ብቅ ከማለቴ በልጄ በኩል ጠርምሶን የገባው መኪና። ላንደክሩዘር ነበር። ደማቅና የሚያጥበረብረው መብራቱ። ፂርርርርርርር። ጩኸቴ። ግውውውውውው። ጭለማ። የልጄ የሲቃ ጩኸት። ጨለማ። በስሱ የሚሰማኝ የሰዎች ኡኡታ። ከአጥንቴ የተለየ የመሰለኝ ስጋዬ። ድንጋጤዬ። ጩኸቴ። ጨለማ። ደማቅ የሰዎች ጩኸት። በስመአብዎች። አንገቴ ሲዞር። ከሶኬቱ ወጥቶ እንደ ጨርቅ የተንጠለጠለው የልጄ እጅ። ከጆሮው የሚጎርፈው የደም ጅረት። ጩኸቴ። ተርፈዋል ብለህ ነው? በስመአብ! በስመአብ…አረ ለፖሊስ ደውሉ። አረ አምቡላንስ ጥሩ። በስመአብ….የሚሉ ድርብርብ ጩኸቶች። የሚያለቅሱ ሰዎች።
ከዚያ እንደ ጨርቅ ጎትተው ሲያወጡኝ።
እኔን አወጡኝ። ደህና ናት። ተአምር ነው። ልጁ ግን ተጎድቷል። ምንም ሳትሆን ወጣች ምናምን ሲሉ ይሰማኛል።
ልጄስ…ልጄስ…ልጄን….ብዬ ስጮህ ትዝ ይለኛል።
የተከደኑ አይኖቹ። ደም የለበሰው ግማሽ ፊቱ። ደም የተነገከረው ደረቱ። ለብቻው የተንጠለጠለው ቀኝ እጁ። ልጄ!
አትግቢ ወዳሉኝ ዝግ ክፍል ስሮጥ ከወንድ የሚጠነክሩ ሁለት ነርሶች ጠፍንገው ያዙኝ።
– ልጄን…ልጄን ልየው እያልኩ ሳለቅስ ከለከሉኝ።
– እዚህ መጠበቅ አለብሽ…ሰርጀሪ ገብቷል። እዚህ ጠብቂ….አሉኝ።
በመአት አይነት ሰዎች የተሞላው መስኮት አልባ ሰፊ ኮሪደር ውስጥ ተዉኝ። አብዛኞቹ ሰዎች ከብረት የተሰሩ የማይመቹ ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለዋል። ግማሾቹ አቧራ በአቧራ በሆነው ነጭ ወለል ላይ በግዴለሽነት ተዘርፍጠዋል። የመድሃኒትና የሰዉ ሽታ ተቀላቅሎ፣ የልጄ ምስል ተደምሮ ወደላይ አለኝ።
እንደምንም መለስኩት።
አንዲት ሴት ሁኔታዬን አይታ ይሁን መቀመጥ ሰልችቷል በ ነይ እዚህ ተቀመጪ እጆቿን ስታንቀሳቅስ በድን አካሌን ይዤ ሄጄ ብረት ወንበሩ ላይ ተቀመጥኩ። ከዚህ ቦታ፣ ከዚህ ሁኔታ ራሴን ብገነጥል፣ ይሄን አስቀያሚ ቦታና ሁኔታ ደመና ሆኜ ትንን ብዬ ብለየው፣ ከጥቅምት ውርጭ ጋር ተቀላቅዬ በረዶ ሰርቼ ብተወው ምናለ? ከዚህ ሌላ የትም ቦታ ብሆን፣ ከዚህ ውጪ ምንም ነገር ቢደርስብኝ ምን ነበር?
ልጄ!
እንደገና መጮህ ጀመርኩ።
ወንበሯን የለቀቀችልኝ ሴት ትከሻዬን ያዝ አድርጋ
– አታልቀሺ…ፀልዩ…ፀልዩ…. አለችኝ።
ደመና ሆኖ መትነን የለም፣ በረዶ ሆኖ ከአየር መቀላቀል፣ ሌላ ቦታ፣ ሌላ ሁኔታ ላይ መሆን እንደማልችል አውቃ መሰለኝ።
ፀልዩ….
ለቅሶዬን ወደ ቀስታ እህህታ አውርጄ አካባቢዬን ቃኘሁ። እንደኔ በዝምታ የሚያለቅሱ፣ ንፍጥ የሚናፈጡ፣ እምባ የሚጠርጉ፣ እርስ በእርስ የሚፅናኑ እና የሚፀልዩ ብዙ ሰዎችን አየሁ።
በእምባ የራሱ አይኖቼን ጨፈንኩ።
ወዲያው ደግሞ ገለጥኳቸው።
በሩ ጋር አንዷ ነርስ ከፖሊሶች ጋር ስታወራ ተመለከትኩ።
በረጅሙ ተነፈስኩ። በአየር ፈንታ እሳት ያስገባሁ ያህል ውስጤ ተቃጠለ። ውስጤ ነደደ።
– ፀልዩ…አለችኝ አሁንም አጠገቤ የቆመችው ሴት።
ከወንበሬ ተንሸራትቼ ወለሉ ላይ ተንበረከኩ።
አንገቴን አቀረቀርኩ።
አይኖቼን ጨፈንኩ።
እጆቼን በእምባ የበሰበሰ ፌቴ ላይ አደረግኩ።
ከፀለይኩ አስራ አምስት አመታት አልፈዋል። ለቀብር ካልሆነ ለዝክር ወይ ለበአል ቤተ ክርስትያን ከረገጥኩ ብዙ አመታት ሄደው መጥተዋል። ከእናቴ ሞት በኋላ ቀን የቱ ቀን ሚካኤል፣ የቱ ቀን ተክልዬ እንደሆኑ አስቤ አላውቅም።
እና ምን ተብሎ ነው የሚፀለየው? አባታችን ሆይ ግማሹ ከጠፋብኝ ሰንብቷል። …ምንድነው የምለው…?አባቴ ሆይ…በሰማይ የምትኖር….? አይኖቼን ገልጬ ሴቲቱን አየኋት። እርጂኝ አይነት አየኋት።
– ዝም ብለሸ ፀልዩ…. አለችኝ።
እፀልያለሁ። መጀመሪያ ይሄን ሁሉ ጊዜ ስላልፀለይኩ፣ እግዜርን ስለተውኩ ይቅርታ እላለሁ። ስለሃጥያቴ ሁሉ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ። ከዚያ ግን…ከዚያ ግን ልጄን ተውልኝ…ልጄን አትውሰድብኝ እለዋለሁ…..
እንደሚባለው ምህረቱ የበዛ ሩህሩህ ከሆነ ልጄን እንዲያድንልኝ እማፀነዋለሁ።
እያለቀስኩ መሬቱን መሳም ጀመርኩ።
እየጮህኩ…እያጉረመረምኩ መፀለይ ጀመርኩ።
አምላኬ ሆይ….ልጄን ተውልኝ…ልጄን አድንልኝ….እጾማለሁ። አስቀድሳለሁ። እፀልያለሁ። አንተ ብቻ ልጄን ተውልኝ…አድንልኝ….አርብ እሮብ እጾማለሁ። አብይ ፆምን እጾማለሁ። ደሃ በስምህ አበላለሁ። አስቀድሳለሁ…አንተ ግን ልጄን ተውልኝ..አምላኬ እባክህ ልጄን አድንልኝ….
እግዚአብሄር ሆይ….ልጄን ካዳንክ ባሪያህ እሆናለሁ። እንደፈቃድህ እሆናለሁ። ያልከኝን አደርጋለሁ……
አልኩና ቀና ብዬ በእምባማ አይኖቼ አሁንም ቆማ የምታየኝን ሴት አየኋት።
– ዛሬ ምንድነው? አልኩ በጎርናና ድምፅ
– እ? አለችኝ ደንገጥ ብላ
– ዛሬ…ቀኑ ምንድነው?
– አስራ ዘጠኝ…ገብርኤል ነው….
እንደገና መሬት ላይ ተደፋሁ። ከንፈሮቼ በእምባዬ ታጥበው ጨው ጨው ይሉኛል።
ገብርኤልዬ…የኔ ገብርኤል…ልጄን አድንልኝና በአመት ቁልቢ አልቀርም። በየወሩ ሱቄን ዘግቼ አከበርሃለሁ። እዘክርሃለሁ። መልአኩ ገብርኤል ልጄን አድንልኝ…አድንልኝ….
ሴቲቱ ጎትታ አነሳችኝ። ቆምን።
– ይበቃል…በቃ በቃ…..ከእምባዋ እንደምትታገል በእምባ በተሸፈኑት እና እንደ እሳት በሚያቃጥሉኝ አይኖቼ አየሁ። ልክ እንደ ቅርብ ዘመዴ አቅፌያት አለቀስኩ።
– በቃ…በቃ….አይዞሽ…አለችኝ።
ብዙ ደቂቃዎች አለፉ።
ነርሶቹ ምነው ጠፉ? ዶክተሩስ ለምን ዝም አለኝ?
አዲስ ለቅሶ ጀመርኩ፡፤
ሴቲቲ ታባብለኛለች።
የስለት ቃሌን ለገብርኤል እደግማለሁ። መሬት እምበረክካለሁ። እቆማለሁ። ወደ በሩ እሄዳለሁ። ነርሶቹን ስለልጄ እጠይቃለሁ፡፤ ጥብቂ እባላለሁ። አለቅሳለሁ። እቀመጣለሁ። እነሳለሁ። ተምበርክኬ ለገብርኤል እሳላለሁ።
ነፋስ ያስፈልገኛል። ነፋስ….ነፋስ ያስፈልገኛል። ወጥቼም እንዳልወጣ (ሃኪሞቹ መጥተው ቢያጡኝስ?) እዚያ ኮሪደር ላይ ተቀምጬ ትንፋሽ አጥሮኝ የልጄን መጨረሻ ሳልሰማ እንዳልሞት በመስጋት ትልቁ በር ስር ሄጄ ኩምትር ብዬ ተቀመጥኩ።
የሚያንዘረዝር ብርድ ተቀበለኝ። የድግስ ግልጥልጥ ቀሚሴ አላዳነኝም። ግን ዝርፍጥ ባልኩበት ቀረሁ። አየሩ እና የተቀመጥኩበት ቀዝቃዛ ሴራሚክ ወለል የሰውነቴ አካል እስኪመስለኝ ተቀመጥኩ። ለምን ያህል ሰአት እንደቆየሁ ሳላውቅ ስታፅናናኝ የነበረችው ሴት መጥታ በብርድ የገነተረ ክንዴን ስትነካ ነቃ አልኩ።
– ሃኪሙ እየፈለገሽ ነው…ነይ… አለችኝ።
ብርክ ያዘኝ።
ሃኪሙን ሲጠብቅ እንዳልቆየ ሰው ሃከሙ መጣ ስባል ብርክ ያዘኝ። ለሰአታት የጠጣሁት ብርድ ሰውነቴን ያንዘፈዝፈው ያዘ።
– አይዞሽ ነይ…ብላ ጎትታ ስታስገባኝ ትዝ ይለኛል።
ከዚያ የማስታውሰው የሃኪም ነጭ ጋወን የለበሰ ፂማም ሰውዬ ጉንጮቼን በጥፊ አይነት ሲመታቸው ነው። እጆቼን ሲያነቃንቅ። ትሰሚኛለሽ…የኔ እመቤት ትሰሚኛለሽ ሲለኝ።
በጢም የተከበበ አፉን ፈራሁት። ከአፉ የሚወጡትን ቃላት ክፉኛ ፈራሁ። ልሸሸው..ሊነግረኝ ያሰበውን መርዶ ላመልጥ ፈለግኩ ግን እሱም ነርሶቹም ከበውኛል።
ብረት አልጋ ላይ ተኝቻለሁ።
ራሴን ስቼ ነበር?
ማውራት ጀመረ። አቅመ ቢስ ሆኜ መስማት ጀመርኩ።
– ልጅሽ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ( አምላኬ ሆይ ቁልቢ እስክሞት ድረስ ከነልጄ አልቀርም)
– ብዙ ደም ፈሶታል። ( ተአምሩን ላገኘሁት ሰው ሁሉ መንገር አላቆምም)
– በቀኝ በኩል የደረሰበት ጉዳት አስከፊ ነው ( አምላኬ ሆይ፣ ካለ መፅሃፍ ቅዱስ አላነብም። ላንተ ውዳሴ ከሚሰጡ መዝሙሮች ውጪ ጆሮዬን ሙዚቃ አላሰማም። )
– ግን ተአምር ነው….እግዜር በተአምሩ አትርፎታል። አይዞሽ..ይድናል…ለተወሰኑ ቀናት አይ ሲዩ ይቆያል…ለጥንቃቄ ግን የሚያሰጋ ነገር የለም። .
ልጄ አልሞተም።
ልጄ አልሞተም።
ልጄ አልሞተም።
ዶክተሩ ፈገግ ብሎ ያየኛል። ያለኝን ለመረዳት እየታገልኩ መሆኑ ገብቶታል።
በስምንተኛው ቀን ልጄ ከአይሲ ዩ ወጥቶ መደበኛ ክፍል ተኝቷል። እኔ ትንንሽ እግሮቹን እየነካካሁ አልጋው ላይ ተቀምጫለሁ።
የምታምር የጠዋት ፀሃይ በመዳን ላይ ያለ ፊቱ ላይ ታበራለች።
እምባ ባቀረረ አይኔ ጉንጮቹን አያለሁ።
– እማዬ….አለኝ ቀስ ብሎ
– ወዬ ልጄ….
– ዛሬ ቀኑ ምንድነው?
ፈገግ አልኩ።
– ምነው እማዬ አለ እሱም ፈገግ ብሎ። ያቺ ካባቱ የወረሳት ውብ ዲምፕሉ በትንሹ ፊቱ ላይ….
– መድሃኒያለም ነው ልጄ…ዛሬ የአመቱ መድሃኒያለም ነው…. አልኩ በአልጋው በስተግርጌ ካለው ኮመዲኖ ላይ ከጠዋት ጀምሮ የሚበራውን ሻማ በእምባ በተሞሉት አይኖቼ እያየሁ።