Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ዘጠኝ)

ክፍል ዘጠኝ፡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ

ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው የPFLP መሪዎች የአውሮፕላን ጠለፋዎችን ለማካሄድ የወሰኑት “ለፍልስጥኤማዊያን ትግል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማስገኘትና ለጥያቄአችን የተሻለ መደመጥን ለመፍጠር ያስችላሉ” በማለት ነበር። በእርግጥም አመራሩ እንደጠበቀው በተከታታይ የተካሄዱት የአውሮፕላን ጠለፋዎች ግንባሩን በዓለም ህዝብ ዘንድ ታዋቂ አድርገውታል። የፍልስጥኤም ጥያቄም በብዙዎች ጭንቅላት ማቃጨል ጀምሯል። ከጠለፋዎቹ በፊት ብዙሃኑ የዓለም ማኅበረሰብ ፍልስጥኤም ያለችበትን የጂኦግራፊ ክልል እንኳ በቅጡ አያውቅም ነበር። እነዚያ ጠለፋዎች ከተካሄዱ በኋላ ግን በሁሉም አህጉር የሚኖሩት ህዝቦች ስለፍስጥኤምም ሆነ ታጋዮቿ ስለሚያነሱት ጥያቄ መወያየት ጀምሯል።

ግንባሩ ዛሬም ድረስ “እነዚያ ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸው ትክክል ነው” የሚል አቋም ነው ያለው። የኦፕሬሽኖቹን ቅቡልነት ሲያስረዳ ደግሞ በቅድሚያ ዓለም አቀፍ ህጎችን አይጠቅስም። በግንባሩ እይታ መሠረት አሁን ያሉት ህጎች በሙሉ ኢምፔሪያሊስቶች የዓለም ህዝቦችን ለመቆጣጠር የነደፏቸው የጭቆና መሣሪያዎች ናቸው። የPLFP መሪዎች የአውሮፕላን ጠለፋዎቹ ህጋዊ ተቀባይነት እንዳላቸው የሚከራከሩት የርዕዮተ ዓለም መመሪያቸው የሆነውን ማርክሲዝምን በማጣቀስ ነው። በካርል ማርክስ ፍልስፍና መሠረት በቅኝ ግዛት ስር ያለ ህዝብ ነፃነቴን ለመጎናፀፍ ይበጀኛል ያላቸውን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ ይችላል።

ከዚያ በመለስ ግን የPLFP መሪዎች የአውሮፕላን ጠለፋዎቹ አሁን ባሉት ህጎችም ተቀባይነት እንዳላቸው ያስረዳል። ለዚህም እንደ ማስረጃ በቅድሚያ የሚጠቅሱት እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በተለያዩ ጊዜያት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ባለማክበር ፍልስጥኤምን ይዛ መቆየቷን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወረራ የተያዘ ህዝብ ሀገሩን ነፃ ለማውጣት በሲቪል ህዝብ ላይ ያላነጣጠረ የትኛውንም የትግል ዘዴ መጠቀም እንደሚችል መደንገጉን ይጠቅሳሉ።

በወቅቱ በትግሉ ውስጥ የነበሩ የግንባሩ ታጋዮችና ደጋፊዎች “በአመራሩ የተተገበረው የትግል ስልት ትክክለኛ ነው” በማለት ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተዋል። PFLP እነዚያን ስልቶች ተጠቅሞ የፍልስጥኤም ጥያቄን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተጋባት መቻሉን እንደ ስኬት የቆጠሩ በርካታ ፍልስጥኤማዊያንም ግንባሩን ተቀላቅለውታል። በዚህም የተነሳ በ1968 ሶስት ሺህ ብቻ የነበረው የግንባሩ የሰው ኃይል በ1970 ወደ ሀያ ሺህ አድጓል።
——–
PLFP ባካሄዳቸው የአውሮፕላን ጠለፋዎች ሳቢያ የፍልስጥኤማዊያን ጥያቄ በምስራቁ ካምፕም ሆነ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ባሉት የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኗል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ፍልስጥኤም የዓለም ኃያላን ዓይን ጆሮአቸውን የሚጥሉባት የትኩረት ማዕከል ለመሆን በቅታለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ከ1970ዎቹ አንስቶ የፍልስጥኤማዊያንን ጥያቄ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ዓይነተኛ የውይይት አጀንዳው ከነበረው “የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም” ጎን ለማሰለፍ ተገዷል።

ታዲያ ጥያቄው ጎልቶ የመሰማቱን ያህል መፍትሄው ከየትኛውም አቅጣጫ ሊፈልቅ አልቻለም። በተለይም የወራሪዎቹ ተገን የሆኑት ምዕራባዊያን መንግሥታት ለጥያቄው መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የፍልስጥኤም ችግር ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲዳፈን የሚያደርጉ ዘዴዎችን በመቀየሱ ላይ ነበር የተጠመዱት። በዚህም መሠረት “የPFLP ፋኖዎች ያካሄዷቸው ጠለፋዎች የሽብር ድርጊቶች ናቸው” በማለት ግንባሩንና ታጋዮቹን በማሳጣት ተግባር ላይ በሰፊው ተሰማርተዋል። ከዚህም አልፎ “ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት” የተሰኘ አዲስ ፖሊሲ በስራ ላይ በማዋል የፍልስጥኤም ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የሚያሽመደምዱበትን ዘመቻ ጀምረዋል።

የPFLP አመራር በዚህ ዘመቻ አልበረገገም። ከምዕራባዊያን መንግሥታት ለተሰነዘረበት ክስ ምላሽ ሲሰጥ “እነዚህ ሃይሎች ከጠለፋዎቹ በላይ የህዝባችን ችግር አሳሳቢ ሊሆንባችሁ በተገባ ነበር፤ ምዕራባዊያንና በየቀጣናው ያሉት አድኃሪ መንግሥታት እነርሱ ባስታጠቋት እስራኤል ተወርሮ ሀገሩን ያጣውን ህዝባችንን ሊሰሙት አልፈቀዱም። ወራሪው ኃይል ህዝባችንን በየዕለቱ እየገደለውና ከሀገሩ እያፈናቀለው ነው። ስለዚህ የዓለም ማኅበረሰብ የህዝባችንን ጥያቄ እንዲያውቀውና መንግሥታት በወራሪዎች ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ለማድረግ ስንል አውሮፕላኖቹን ለመጥለፍ ተደገናል” በማለት መልስ ሰጥቷል።

በሶቪየት ህብረት በሚመራው የምሥራቁ ካምፕ የነበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ ያራመዱት አቋም አንድ ወጥ አይደለም። ምሥራቅ ጀርመን እና ኩባ “የPFLP አመራር የሰጠው መግለጫ ትክክል ነው፣ ፍልስጥኤማዊያን ሀገራቸውን የወሰደባቸውን ወራሪ ኃይል በየትኛውም ስፍራ መዋጋት ይችላሉ” በማለት የግንባሩን አቋም ደግፈዋል። ግንባሩ ወደፊት ለሚወስዳቸው ተመሳሳይ እርምጃዎች ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም አስታውቀዋል። ቻይና እና ሶቪየት ህብረት ግን PFLP በእስራኤልና በፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ መዋጋት እንደሚችል ገልጸው ከሁለቱ ግዛቶች ውጪ የሚካሄዱ ኦፕሬሽኖችን ግን እንደማይደግፏቸው ተናግረዋል።

የPFLP አመራር ሶቪየት ህብረት እና ቻይና በወሰዱት አቋም በከፊል በመስማማት የግንባሩ አባላት መስከረም 1970 ካካሄዷቸው የአውሮፕላን ጠለፋዎች በኋላ ለተመሳሳይ ኦፕሬሽኖች እንደማይሰማሩ በይፋ አስታውቋል። ሆኖም እስራኤልንና ደጋፊዎቿን በየትኛውም የዓለም ክፍል መዋጋቱን እንደማያቆም ገልጾአል። ግንባሩ ለዚህ የሰጠው ምክንያት “እስራኤል እና ሲ.አይ.ኤ. ፍልስጥኤማዊያንና የሌሎች ሀገራት ታጋዮችን በጠራራ ጸሐይ ሲገድሉ እጃችንን አጣጥፈን ማየት አንችልም” የሚል ነበር።

ከዐረብ ሀገራት መካከል ኢራቅ፣ ሊብያ እና ሶሪያ “ፍልስጥኤም በወረራ በተያዘችበት ሁኔታ ግንባሩ ሀገሩን እና ህዝቡን ነፃ ለማውጣት የሚያካሄዳቸው እርምጃዎች ሁሉ ትክክል ናቸው” በማለት ድጋፋቸውን በይፋ ገልጸዋል (ደቡብ የመንም ከ1976 በኋላ ይህንን አቋም ይዛለች)። አብዛኞቹ የዐረብ ሀገራት ጉዳዩን በዝምታ ማለፍን ሲመርጡ ከእስራኤል ጋር በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጋጨችው ሊባኖስ ደግሞ “የግንባሩ አባላት አውሮፕላኖችን ሲጠልፉ የኔን ግዛት እንደ መንደርደሪያ መጠቀም አይችሉም፤ ሆኖም ከሌላ ሀገር ተነስተው የሚፈጽሙት ነገር ሁሉ አይመለከተኝም” የሚል አቋም አሳይታለች።

በዚህ ሁሉ መሀል ስር-ነቀል የሆነ የፖሊሲ ለውጥ ያደረገችው ሀገር ዮርዳኖስ ናት። ይህ የዮርዳኖስ የፖሊሲ ለውጥ የግንባሩን ትግል ሙሉ በሙሉ አመሰቃቅሎታል። የፍልስጥኤማዊያንን ስቃይና ስደት ካባባሱት እርሾዎች አንዱ ሆኖም ተመዝግቧል። ዮርዳኖስ ያደረገችው የፖሊሲ ለውጥ ምን ይመስላል? በሚቀጥለው ክፍል እናየዋለን።
——-
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 10/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል አስር)

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *