Tidarfelagi.com

የመታወቂያው ጉዳይ

“ግራጁዬት ሎየር ነኝ” ድንቄም

በግድ የተፃፈብኝን የመታወቂያዬን ብሔር ስያሜ ወደ ኢትዮጵያዊ ለማስቀየር ዛሬ ሶስተኛ ቀን ሙከራዬን ቀጥዬ ውያለሁ። ባለፈው ሳምንት የክፍለ ከተማውን ኃላፊ ሰኞ ወይ ማክሰኞ መጥቼ እንዳነጋግር ተቀጥሬ ነበር ትረካዬን ያቆምኩት። እነሆ የዛሬ ውሎዬ፡-

የክፍለ ከተማው የወሳኝ ኩነቶች ሀላፊ ጋር ከምሳ ቀደም ብዬ ቢሮዋቸው ተገኘሁ። ሰውዬውን ዛሬ በስራ ገበታቸው ላይ አግኝቻቸዋለሁ። ከአምስት ቀናት በኋላም ቢሆን ያገኘኋቸው በእንግዳ አቀባበል ስርዓታቸው እና የማስረዳት ችሎታቸው ቅሬታዬን ወዲያው መፋቅ ሳይችሉ አልቀሩም።

አስቂኙን ጥያቂዬን (‘ብሄሬን ኢትዮጵያዊ ለማስባል ነው የመጣሁት’ ስል ሁሉም እንደሚስቅብኝ ታስታውሳላችሁ) አቀረብኩላቸው። ከት ብለው ስቀው ከዚህ ቀደም በወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ተደውሎላቸው መስማታቸውን ነገር ግን ይህን ያህል እስከ ቢሯቸው ድረስ ጥያቄው ሊደርስ የሚችል መስሎ አለማየታቸውን ነግረውኝ ዝርዝር ወሬ ውስጥ ገባን።

“ለምንድነው ብሔርህ እንዲፃፍ ያልፈለግከው”
“እፈልጋለሁ እኮ” አልኳቸው
“አሁን አልፈልግም አላልክም እንዴ?”
“አልፈልግም ያልኩት እኮ በግድ የተፃፈብኝ የብሔር ስምን ነው”
“እና ብሔር ምን ተብሎ እንዲፃፍልህ ነው የፈለግከው?”
“ብሔር ኢትዮጵያዊ ተብሎ” አልኳቸው
“ኢትዮጵያዊ የሚባል ብሔር አለ እንዴ?”
“ብሔር ማለት እኮ ሀገር ማለት ነው” ስላቸው
“ህገ መንግስቱ ግን እንደዛ አይልም። አይደል?”
“ሊሆን ይችላል”
“ስለዚህ ጥያቄህን እንድታስተካክለው ብዬ ነው። ‘ዜግነቴ ከተፃፈ በቂ ነው። የብሄር ስታተስ መረጃውን አልፈልገውም ወይንም እኔን አይገልጽም ስለዚህም መረጃው ባዶ ተደርጎ በሰረዝ ብቻ ይታለፍልኝ ‘ብትል ነው የሚያስኬድህ” አሉኝ ተረጋግተው።

“እሺ ይሁን። ይህም ጥሩ ተስፋ ነው። ስለዚህ ብሔር የሚለው ሰረዝ ተደርጎ ዜግነቴ ብቻ የተገለፀበት መታወቂያ ይሰጠኝ” አልኩ ጥያቄዬን አስተካክዬ

“ይህ የነዋሪዎች መታወቂያ የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ብቻ ስለሆነ ዜግነትህ ባይጠቀስም ባይ ዲፎልት ኢትዮጵያዊ መሆንህን ይገልፃል።”

“እሺ እሱም ይሁን ግን ብሔር የሚለው አይሞላብኝ”
“አንተ ግን ለምንድነው ብሔርህን ያልፈለግከው?” አሉኝ መልሱን ለኋላ አቆይተው።
“ምክንያቱም በብሔር ስለማላምን ነው። ቤተሰቦቼም አንተ የዚህ ብሔር አባል ነህ ብለው ስላላሳደጉኝ ስለብሔር ምንም አላውቅም። የማውቀው ኢትዮጵያዊ መሆኔን ብቻ ነው። በህገ መምግስቱም ብሔሬ እንዲጠቀስ የሚያስገድድ አንቀጽ የለም” አልኩ ኮራ ብዬ

ንግግሬን በጥሩ ፈገግታ ካወራረዱት በኋላ
“ዛሬ አባቴ ቢሮዬ ድረስ በአካል ነው የመጣብኝ”
“ማለት?”
“አባቴ ልክ እንዳተ ነው የሚያስበው ብሔር ስትጠይቀው ‘ዞር በል!’ ነው የሚለው። በጣም ደስ ይላል። ጥሩ አቋም ነው። በአሁን ሰዓት ሁሉም በጎጥ በተከፋፈለበት ሰዓት ያንተ አቋም እንደዚህ መሆኑ የሚያኮራ ነው።”

መልሱ አጓጉቶኛል። ነገር ግን መንግስት ቤቶች ውስጥ መልስ ከማግኘት ይልቅ ጥያቄ የማሻሻል ትምህር ማግኘት ትልቁ ጥቅም መሆኑን ተምሬያለሁ።

“እስኪ አለቃዬን ላነጋግር እና ሀሳብህ ተቀባይነት ካለው ልሞክር”

በግል ስልካቸው ወደ አለቃቸው ደወሉ እንግዲህ የክፍለ ከተማው ሀላፊ ሊደውሉ የሚችሉት ለአዲስ አበባ መስተዳድሩ የበላይ አለቃቸው ነው ብዬ ተስፋ አድርጌያለሁ። ጥያቄዬን በተሻሻለው አቀራረብ ለአለቃቸው ሪፖርት ማድረግ ጀመሩ። ከራሳቸውም ጨመር አድርገው።

“እንግዳችን የቤተሰቦቹን የብሔር ማንነት አያውቅም። እና ለማወቅ ጥረት እያደረ ቢሆንም ለጊዜው ግን ባለማወቁ ምክንያት ‘ምንም አይነት ብሔር እንዳይፃፍብኝ’ እያለ ነው… አዎ…ግን ወደፊት አጣርቶ ሲጨርስ የደረሰበትን ብሔር አሳውቆ ሊያጽፍ ይችላል”

‘እኚህ ሰውዬ እኔ ያልጠየቅኩትን ጥያቄ ለምንድነው እንዲህ የሚያዛቡት? እኔን ለመተባበር እና ለማገዝ እንደፈለጉ ገብቶኛል። ነገር ግን እኔ መፍትሄ የምፈልገው በቀጥተኛ መንገድ ብቻ ስለሆነ በዚህ አካሄድ የሚመጣ ውጤት አይዋጥልኝም’ እያለኩ ሳሰላስል እሳቸው አውርተው ጨረሱ።
ስልኩን ከዘጉ በኋላ ወደ እኔ ዞረው፥
“አይቻልም!”
“ማለት?”
“ያው እንዳየኸው አለቃዬን ለማሳመን ሞክሬያለሁ። መመሪያውን መሻር የሚችለው ፍርድ ቤት ብቻ ስለሆነ በአስፈፃሚ አካል መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ወደ ፍርድ ቤት ሔደህ ልክ ሰዎች ስማቸውን በፍርድ ቤት እንደሚያስቀይሩት አንተም የብሔር ስታተሴ አይፃፍብኝ ብለህ አመልክትና ከዚያ በምታመጣው ውሳኔ መሰረት ፈጣን መልስ ይሰጥሀል” አሉኝ።

“ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ምንም ችግር የለብኝም። ግን እንደዚያ ባደርግ የሚሳካ ይመስልዎታል?” አልኳቸው
“አዎ። ይመስለኛል ብዙውን ግዜ የፍርድ ቤት ማዘዣ ለሚያመጡ ሰዎች መመሪያ ባይፈቅድም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለሚፈፀም እናስተናግዳለን”

ሞቅ ያለ የስንብት ሰላምታ ተቀያይረን፥ መልካም ምኞታቸውንም ገልፀውልኝና የትኛው ፍርድ ቤት መሄድ እንዳለብኝ ጠቁመውኝ ከቢሮዋቸው ወጣሁ።

የክፍለ ከተማው አንደኛ ደረጃ ምድብ ችሎት፡-

ፍርድ ቤቱ አካባቢው ካለ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ምሳዬን በልቼ የስራ ሰዓታቸው እስኪደርስ መጠበቅ ጀመርኩ። የምሳ ሰዓቴን ከህገ መንግስት አንቀፆች ንባብ ጋር እያመነዠግኹ አሳለፍኩት።

የፍርድ ቤቱ በር ላይ አንድ ረዘም ብለው ወፈር ያሉ ጥበቃ አገኘሁ።
“ባለ ጉዳይ ነህ?”
“አዎ ነኝ”
“አዲስ ነው?”
“አዎ”
“የታል ማመልከቻህ?”
“ገና አላዘጋጀሁም”
“ወደዚህች ወረድ በልና ኮምፕዩተር ቤት አለልህ። እዚያ ማመልከቻ አጽፈህ ና”

የተባልኩት ኮምፕዩተር ቤት ደርሼ ፀሀፊዎን አገኘኋት
“ማመልከቻ ለማፃፍ ነበር”
“ግባ ቁጭ በል”
ኮምፕዩተሯን አሰነዳዳች እና “ምንድነው ጉዳይህ?”
“መታወቂያዬ ላይ ያለውን ብሔር ስለማስቀየር ነው”
“ውይ እንደዚህ የሚል እስከዛሬ አልፃፍኩም” ኮምፕዩተሯ ላይ ከዚህ ቀደም የተፃፉ ማመልከቻዎችን በጠቋሚ ቀስቷ እያንከባለለች ትፈልጋለች።

“ቆይ እስኪ ከኔ ይልቅ ባለሙያውን አነጋግረው ልደውልለት”

የደወለችለት ቀጠን ረዘም ያለ ሰው ከውጭ መጣ “አንተ ነህ አመልካቹ?”
“አዎ”
“ውርስ ነው?”
“አይደለም”
“ስም ዝውውር?”
“አይደለም። እኔ የመጣሁት መታወቂያዬ ላይ የተፃፈውን ብሔር፥ ኢትዮጵያዊ በሚል እንዲቀየርልኝ ለፍርድ ቤቱ ለማመልከት ነው”
“ምን?! እንደዚህ አይነት ጉዳይ ፍርድ ቤቱ አይመለከትም”
“ለምን?”
“በህገ መንግስቱ አንቀጽ 36 ፍርድ ቤቶች ከሚመለከቷቸው የፍርድ አይነቶች መሀል አንተ የጠየቅከውን አይፈቅድም”
“እርግጠኛ ነህ አንቀጽ 36 እንደዚያ ይላል?”
“እንዴት እንዲህ ትጠይቀኛለህ? እኔ እኮ ግራጁዌት ሎየር ነኝ”
“እሺ አመሰግናለሁ” ብዬው ያለ ማመልከቻ ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ”

ለመሆኑ አንቀጽ 36 ምን ይላል ብዬ ህገ መንግስቱን አየሁት። አንቀፁ ስለ ህፃናት መብት ብቻ ነው የሚናገረው። ድንቄም “ግራጁዌት”

ወደ ፍርድ ቤቱ ተመለስኩ። ጥበቃውን አስረድቼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ሰዎች ሰብሰብ ያሉበት ጋር ስደርስ “የመረጃ ባለሙያ ቢሮ የት ነው?” ብዬ ጠየቅኹ። የሚቀጥለው ክፍል መሆኑን ነገሩኝ። የጠቆሙኝ በር ተዘግቷል። በዚያ ላይ መግባት ክልክል ነው የሚል ጽሁፍ እና ሌሎች ብዙ ማስታወቂያዎች በሩ ላይ ተለጥፈዋል። አንኳኳሁ። ዝም! ደግሜ አንኳኳሁ።
“ይግቡ!” የሚል ድምጽ ተሰማ። በድጋሚ አንኳኳሁ “ይግቡ!!” ድምጹ ተደገመ።
አንገቴን አስቀድሜ አስገብቼ ሙሉ አካሌን አስከተልኩ።

“ጤና ይስጥልኝ! መታወቂያዬ ላይ ያለውን የተሳሳተ መረጃ ስለማስተካከል ለማመልከት ነው የመጣሁት።”
“የክብር መዝገብን የሚመለከቱ ጉዳዬች በኛ ደረጃ አይታይም!”
“የክብር መዝገብ ምንድነው?”
“በቃ ተወው። ጥያቄህ ገብቶኛል! ስምህ እድሜህ ወይንም የትውልድ ቦታህ ስህተት ኖሮት ወይም ለማስተካለል አይደለም የፈለግከው?”
“አዎ! ተቀራራቢ ነው። የኔ ጥያቄ ግን ከዚህ ትንሽ ይለያል”
“ብቻ መታወቂያህ ላይ ያለን መረጃ ነው የሚመለከተው አይደል?”
“አዎ”
“እኮ! ይህንን የሚመለከተው የአውራጃ ፍርድ ቤት ነው። ስለዚህ እዚያ ነው የምታመለክተው። እኛ የተሰጠን ስልጣን ውስን ሰለሆነ ይህንን ማየት የሚችለው የአውራጃ ፍርድ ቤት ነው።”

የአውራጃ ፍርድ ቤት መገኛን አጣርቼ አመስግኜ ወጣሁ።

በሁለት ትራንስፖርት አቆራርጮ አውራጃ ፍርድ ቤት ደረስኩ። ግቢው ትኩስ መርዶ የተሰማበት ለቅሶ ቤት ይመስል በርካታ ሰው እዚህም እዚያም ተደነጋግጦ ቆሟል። የመጣሁበትን ጉዳይ ለሁሉም ሰው ማስረዳት ጉዳዩ እንዲሰለቸኝ የሚያደርግ በመሆኑ ሀሳቤን ለሁሉም ከመግለጽ መቆጠብ እንዳለብኝ እያሰብኩ፥ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡቡት ሰፊ ክፍል በር አመራሁ።

እዚህ በር ላይ ፖሊስ ቆሟል።
“አቤት ወዴት ነህ?”
“መረጃ ፈልጌ ነው”
“የምን መረጃ?”
“የመረጃ ባለሙያውን ቢሮ ፈልጌ ነው”
“ምን አይነት መረጃ ነው የፈለግከው?”
“አይ የፈለግኩት የመረጃ ባለሙያ እራሱን ነው”
“እኮ ንገረኝ ምን እንደፈለግክ”
“የመረጃ ባለሙያው ቢሮ የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?”

ፖሊሱ ግራ ጉንጩን ለጥጦ ትንሽ ካየኝ በኋላ በእጁ የመረጃ ባለሙያዋን ዴስክ ጠቁሞኝ ወደ ውስጥ ገባሁ።

የተተረማመሰው ቢሮ ውስጥ አንድ በጣም በስራ የተወጠረ ሰው ለማነጋገር የተሰጠኝ ወንበር ላይ ተቀምጬ የሱን ውክቢያ እያስተዋልኩ ጥሞና የሚጠይቀውን የኔን ጥያቄ እንዴት ማቅረብ እንዳለብኝ እያሰብኩ ጥድፊያው ጋብ እስኪልለት ታግሼ ጠበቅኩት።

ከሶስት ግዜ በላይ ማውራት እየጀመርን፥ በላይ በላይ የሚመጡትን ሰዎች ለማስተናገድ እኔን ይቅርታ እየጠየቀኝ ለብዙ ሰዎች መልስ ለመስጠት እየሞከረ እኔንም ለማድመጥ ይጥራል።

መጨረሻ ላይ ከኔ ጀርባ የቆሙትን ሰዎች አንድ ግዜ እንዲታገሱት ነግሯቸው የኔን ታሪክ ማድመጥ ጀመረ። ለራሳቸው ጉዳይ ተጣድፈው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ሳወራ አንገታቸውን ሰገግ እያደረጉ መስማት ጀመሩ። ጥያቄዬን አቅርቤ ስጨርስ ሲሰሙኝ የነበሩ ሰዎች ፈገግ ብለው እያዩኝ የሰውየውን መልስ እንደኔው በጉጉት መጠበቅ ጀመሩ።

“ጥያቄህን ተረድቼዋለሁ። የመብት ጥያቄ ነው። ህገ መንግስታዊ መብት ነው የምትጠይቀው። ነገር ግን ይህ ጥያቄ በኛ ደረጃ የሚታይ አይደለም። የኛ ማንዴት የዜግነት እና ተያያዥ ጉድዳዩችን የሚያጠቃልል አይደለም። አንተ መፍትሄ የምታገኘው ፌደራል ፍርድ ቤት በመሄድ ነው።” አለኝ
“እና እናንተ ጋር ምንም መፍትሔ የለውም?”
“መፍትሔው በእርግጠኝነት በፌደራል ደረጃ የምታገኘው ነው የሚሆነው”
“እሺ አመሰግናለሁ” ብዬው ልወጣ ስል ጮክ ብሎ
“ይቅናህ” ብሎኝ በፈገግታ እስክወጣ ድረስ በአይኑ ሸኘኝ።

ይህንን ክፍል ለቅቄ ስወጣ አንዲት እድሜዋ ከኔ በለጥ የምትል ሴት ተከትላኝ መጣች።
“ወንድሜ ይቅርታ ካንተ ባላውቅም፥ ዝም ብለህ ከንቱ ድካም ነው የያዝከው።”
“እንዴት?”
“ይኸው እኛ ወንድማችን ሞቶብን መሞቱን ማረጋገጫ ሰርትፊኬት ለማግኘት ስንት እየተጉላላን ያንተ ጥያቄ ዝምብሎ የቅንጦት ነው። ይቅርታ አዝኜልህ ነው”

“ለምክርሽ አመሰግናለሁ እህቴ”

ለሷ የቅንጦት የመሰለው ጥያቄዬ ቀደም ብሎ ባለመመለሱ የብዙዎችን ህይወት በአሉታዊ መልኩ እንደቀየረ እንዴት ብዬ በአጭሩ ላስረዳት እችላለሁ?

የኢትዮጵያዊነት ፍለጋ ይቀጥላል። ቀጣዩ ተስፋዬ የፌደራል ፍርድ ቤት ነው። ከሶስት ቀናት የስራ ቆይታ በኋላ ልመለስበት አቅጄ ለዛሬ እዚህ ላይ አበቃሁ።

ሠላም ለኢትዮጵያ!

የመታወቂያው ጉዳይ – አራተኛው ሙከራ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *