አሁንስ እነዚህ ኑሮ እጅ በጆሮ ያስያዘው ምስኪን ሕዝብ ላይ በይፋ የሚያላግጡ የሪል እስቴት ማስታወቂያዎች ቃር ሆኑብኝ።
አነፈሩኝ።
መቼስ፣ በለስ ቀንቶት፣ ወርሶ ወይም ከመንግሥቱ ነዋይ ግርግር ጀምሮ ቆጥቦ እዚህ ለደረሰ የናጠጠ ሃብታም ማስተዋወቃቸውን አልቃወምም።
እነዚህ በሌላ የተንጣለለ እልፍኛቸው እየኖሩ ማስታወቂያውን የሚመለከቱ ሰዎች፣ በገንዘባቸው የሚፈልጉትን ይገዙበት ዘንድ መብታቸው ነውና መረጃውን ማግኘታቸው ክፋት የለውም።
ክፋቱ፤ የማስታወቂያዎቹ አወቃቀር ነው። አሳሳላቸው ነው። አቀራረባቸው ነው።
የማስታወቂያዎቹ ክፋት ፤ በደሳሳ ጎጆው ቁጭ ብሎ የሚፈልገውን ነገር አይደለም የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት አቅቶት ጣር ላይ ሆኖ፣ ፊቱን ክስክስ አድርጎ የሚመለከተውን ሰው አለማገናዘባቸው ነው።
የማስታወቂያዎቹ ክፋት ፣ እንዲህ ያለው ሰው በባለ አራት ቆርቆሮ ቤቱ ቁጭ ብሎ እያያቸው የአርባ ቀን እድሉን እንዲያማርር፣ ጥርሱን እንዲነክስ ማድረጋቸው ነው።
አሳሩን አይቶ፣ ፍዳውን በልቶ ዩኒቨርስቲ ቢያስተምራትም፣ ሥራ አግኝታ ካላሳረፈችው ልጁ ጋር ቁጭ ብሎ አሹቅ እየቆረጠመ ብሶቱን በአማርኛ ፊልም ለመርሳት ቴሌቪዥን ለሚያይ አባት፤ አንዲት ብርጭቆ ጭማቂ የገዛ እንኳን ሳይመስል፣ <<ልጄ፣ አስተምሬሻለሁ። አሁን ደግሞ ለቀሪው ሕይወትሽ ይሄንን የማንትስ አፓርትማ ገዝቼ ሰጥቼሻለሁ›› ብሎ የሚደነፋ ከበርቴን እያሳዩ በቁስሉ ላይ እንጨት መስደድን ምን ይሉታል?
ከወር ወር ልጆቻቸው ሳይራቡ እና ሳይታረዙ ደሞዛቸው ዞሮ አለመድረሱ ከሰውነት ጎዳና ያወጣቸውን ባል እና ሚስት <<በቀን ሶስት መቶ ብር ቆጥበው የቤት ባለቤት ይሁኑ›› በሚል ማላገጫ ማሳቀቁን ምን ይሉታል?
የማስታወቂያ ፀሃፊዎች፣
የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች፣
የረሳችሁት ሕዝብ እኮ ቢላዋ አጣ እንጂ የበሬውን ሽንጥና ዳቢት ለይቶ ያውቀዋል።
የዘነጋችሁት ሰው እኮ ጫማ አጣ እንጂ ቤት ማግኛውን መንገድ አሳምሮ አጥንቶታል።
እናም ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፤
እስቲ ንቁ።
እስቲ ብቁ።
እስቲ ከባለ ተድላ እና ከባለ ድሎቶቹ ብቻ ሳይሆን ከጎስቋላውንም ሕዝባችሁ ተዋወቁ።