ትናንት በለጠፍኩት አንድ ጽሑፍ ግንቦት 19/1983 በለንደን ስለተከፈተው ኮንፈረንስ ተናግሬ ነበር። እስቲ አሁን ደግሞ የለንደን ኮንፈረንስ ቀጥተኛ ውጤት ስለነበረው የያኔው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት እናውጋ።
ከግንቦት 19-20/1983 በተካሄደው የለንደን ኮንፈረንስ ላይ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል የተቆጣጠረው ኢህአዴግ፣ በሀገሪቱ ምስራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎችን የያዘው ኦነግ እና ኤርትራን ሙሉ በሙሉ የያዘው ህግሓኤ ናቸው።
*****
በለንደን ኮንፈረንስ በተደረሰበት ውጤት መሰረት ኢህአዴግ በሽግግር መንግሥቱ የመሪነት ሚና እንዲኖረው የተወሰነ ሲሆን ኦነግ ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ዋነኛው የስልጣን ተጋሪ ነበር። የሽግግሩ መንግሥት በይፋ የተመሠረተው ከሰኔ 23-27/1983 በተካሄደ ኮንፈረንስ ሲሆን ኮንፈረንሱ ሁለት ነገሮችን በማጽደቅ ነበር የተጠናቀቀው። እነርሱም የሽግግር ጊዜ መተዳደሪያ ቻርተር እና ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ሽግግር መንግሥት ናቸው። አህአዴግ የሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ከነበሩት 87 መቀመጫዎች መካከል ሠላሣ ሁለቱን ሲያገኝ ኦነግ ደግሞ አስራ ሁለት መቀመጫዎች ነበሩት።
በዚህ የወንበር ክፍፍል የኢህአዴግ መቀመጫ የበዛው በስሩ የነበሩት ህወሐት፣ ኢህዴን እና ኦህዴድ እያንዳንዳቸው አስር መቀመጫዎች ስለተሰጣቸው ነው። ሁለቱ መቀመጫዎች ደግሞ በኢህአዴግ ስር ለነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአን) የተባለ ድርጅት ነው የተሰጡት። (በነገራችን ላይ ይህ ኢዴመአን የተባለ ድርጅት በ1985 ህልውናው አብቅቷል፤ ታጋዮቹም በየብሄራቸው ለህወሐት፣ ኢህዴንና ኦህዴድ ተሰጥተዋል፣ በኢዴመአን ፈንታ በዚያው ዓመት የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኗል። በኋላ ላይ ከግንባር ወደ “ንቅናቄ” ተቀይሯል)።
ከኢህአዴግ እና ኦነግ የተረፉት 43 መቀመጫዎች 30 ለሚሆኑ ድርጅቶች ተከፋፍለዋል። ከነዚያ ድርጅቶች መካከል ጎላ ብለው የሚጠቀሱት ሶስት መቀመጫዎች የነበሩትና በዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የደቡብ ህብረት፣ በተመሳሳይ መልኩ ሶስት መቀመጫዎችን ያገኘውና በጃራ አባገዳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ግንባር፣ ሁለት መቀመጫዎች የነበሩትና በአቶ አሰፋ ጫቦ የሚመራው የኦሞቲክ ነጻነት ግንባር፣ እንዲሁም ሁለት መቀመጫዎች የነበሩት የቤኒሻንጉል ነጻነት ግንባር ይጠቀሳሉ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የፋብሪካ ላብ አደሮች እና ሴቶችም አንዳንድ መቀመጫ ተሰጥቷቸው ነበር)።
በዚያ ወቅት አስመራን የያዘው ህግሓኤ በኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት መስርቶ የነበረ ሲሆን በሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ኮንፈረንስ ላይ በታዛቢነት ብቻ ነበር የተገኘው።
*****
አቶ መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ም/ቤት ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የጉራጌ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የወከላቸው ዶ/ር ፈቃደ ገዳሙ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል። የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በመሆን የተሰየሙት ደግሞ የሀዲያ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የወከላቸው አቶ ተስፋዬ ሐቢሶ ነበሩ (ዶ/ር ፈቃደ ገዳሙ የሽግግር ዘመኑ ካበቃ በኋላ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። አሁን የት እንዳሉ ግን መረጃው የለኝም፤ አቶ ተስፋዬ ሐቢሶ በደቡብ አፍሪቃና በኡጋንዳ በአምባሳደርነት ካገለገሉ በኋላ የመንግሥት ስራ በመልቀቅ በግላቸው እየሰሩ ይገኛሉ)። አቶ መለስ ዜናዊ ከሽግግሩ ም/ቤት ሰብሳቢነታቸው በተጨማሪ የመንግሥቱ ፕሬዚዳንት ናቸው። የሽግግር መንግሥቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በይፋ ባይሰይምም እንደ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የነበሩት የኦነግ ም/ዋና ጸሐፊ አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው።
የሽግግር መንግሥቱ ካቢኔ ሲቋቋም ኢህአዴግ የጤና (ዶ/ር አዳነች ኪዳነ ማሪያም)፤ የውጭ ጉዳይ (አቶ ስዩም መስፍን)፤ የመከላከያ (አቶ ስየ አብረሃ)፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ)፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ (አቶ ኩማ ደመቅሳ) ጨምሮ ሰባት የካቢኔ ሹመቶችን አግኝቷል። ኦነግ በበኩሉ አራት የሚኒስትርነት ሹመቶችን ያገኘ ሲሆን እነርሱም የግብርናና ተፈጥሮ ጥበቃ (አቶ ዘገዬ አስፋው)፤ የማስታወቂያ (አቶ ዲማ ኖጎ)፣ የንግድና ቱሪዝም (አቶ አሕመድ ሑሴን) እና የትምህርት (አቶ ኢብሳ ጉተማ) ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አቶ ታምራት ላይኔ (ኢህአዴግ) ነበሩ። የደቡብ ህብረቱ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሲሆኑ የኦሞቲክ ነጻነት ግንባሩ ፊታውራሪ መኮንን ዶሪ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ።
የሱማሌ ህዝብ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አብዱልመጅድ ሑሴን የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር፣ የአፋሩ አቶ ሐሰን አብደላ የቡናና ሻይ ልማት ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ሚኒስትሮች ግን በሙያቸው እንጂ በድርጅት ተወክለው የተመረጡ አልነበሩም። ከነርሱም መካከል የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ኢዘዲን ዓሊ (በደርግ ዘመንም ሚኒስትር የነበሩ) እንዲሁም የስራና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሃይሌ አሰግዴ ይጠቀሳሉ።
ኦነግ ሰኔ 16/84 የሽግግር መንግሥቱን ለቆ የወጣ ሲሆን የደቡብ ህብረትና ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ በመጋቢት ወር 1985 በነ ኢህአፓና መኢሶን አዘጋጅነት በተካሄደው የፓሪስ ኮንፈረንስ ላይ በመሳተፋቸው ከሽግግር መንግሥቱ እንዲወጡ ተደርገዋል። እነርሱ ሲወጡ ሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በኢህአዴግ እና በደጋፊዎቹ እጅ ገብተዋል። የሽግግር መንግሥቱ በኦፊሴል ያበቃው ግን በነሐሴ ወር 1987 ነው።
——
መጀመሪያ መስከረም 12/2007 ተጻፈ።
እንደገና ተሻሽሎ ግንቦት 21/2014 ተጻፈ።