ሁሉም ችግር ያወራል። ሁሉም ወቃሽ ነው። ሁሉም ተጠቅቻለሁ ባይ – ሁሉም በደል ቆጣሪ ነው። እነከሌ ይራገማሉ። እነከሌም ያሳቅላሉ። ሁሉም ነገድ የተገፊነት ተረክ አለው። ሁሉም ጠላት እና ጨቋኝ አለው፤ ሁሉም በጋራ ይከሳል.. ሁሉም በጅምላ ይከሰሳል፤ ‘ጸረ ሰላም፣ ጨቋኝ፣ ሴረኛ፣ ለውጥ አደናቃፊ፣ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ፣ ጨፍላቂ፣ ጽንፈኛ፣ ምንትስ ጠል፣ የጥፋት ኃይል።’ ወዘተ ይባባላሉ። ስም ጠርቶ ማውገዝ የለም። ቢጠራም አሁን የለም። ‘እከሌ’ ባዮች እንኳ እከሌያቸው ሕልው አይደለም። ‘ጠላታቸው’ ቢጠፋ ሌላ ጠላት ይፈጥራሉ።
___
የነገድ ፖለቲካ ያለ ጠላት የማይቆም ቢዝነስ ነው። ፖትላኪዎቹ ‘መጡብህ’ ብለው የሚያስፈራሩበት ‘ጠላት’ ካልያዙ ታዳጊዬ ብሎ የሚጠራቸው ሕዝብ እንደማይኖር ስለሚያስቡ ታሪክ በማጣመም አልያም ሂደት በማጠልሸት ፈርዖንን ፈጥረው ‘ከዚህ የማወጣህ ሙሴ እኔ ነኝ’ ይሉታል።
___
የዜግነትና የነገድ ፖለቲካ አራማጆች መሃል ያለው መሰረታዊ ልዩነት የመጀመሪያዎቹ ሁሌም የሚቃወሙት “ስርዓት” ሲሆን ሁለተኞቹ ጠላቴ የሚሉት የማይታወቅ ቡድን መሆኑ ነው። የሚታወቅ ቡድን ቢጠሩ እንኳ የሚጠየቅ ላይሆን ይችላል። የሚጠየቅ እንኳ ቢሆን ግለሰብ ሆኖ እንጂ ላይቦድን ይችላል። መረር ሲል በፈጠራ ታሪክ ህልው ሊሆን ይችላል – በሌለበት። ብቻ ጠላት መገኘት አለበት። ‘ንጹህ’ እንኳን ቢሆን ለስልጣን ካሰጋ ጥላሸት አይጠፋለትም።
___
ለምሳሌ “የአንድነት ኃይሉ ‘የብሔረሰብ ማንነትን’ ደፍጥጦ አሃዳዊ ስርዓት ካላሰፈንኩ እያለ ነው” ሊል ይችላል ነገዳዊው። የትኛው ‘የአንድነት ኃይል’ ብንለው ግን አይመልስልንም። ‘አሃዳዊ ስርዓት ይስፈን ያለው መቼ ነው? አንድነትና አሃዳዊነት አንድ ነው ወይ? ቢልስ በእኛ ሃገር ሁኔታ መሆን ይችላል ወይ?’ መልስ የለውም። በቀቀናዊ ተረኩን የሚነግርህ ፖትላኪም ጠላት ፈጠርነቱ እንጂ ልክነቱ ግድ ስለማይሰጠው ባገኘው መድረክ ይዋሻል፤ የመጨረሻ ግቡ በተፎካካሪው መጠላት ላይ የተመሰረተ ‘የበላይነት’ አግኝቶ ከስልጣን ማማ ላይ ፊጥ ማለት ብቻ ስለሆነ የስብዕናው ድቀት አያሳስበውም።
___
ያለችን አንድ ሃገር ችግራችንም ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ በፖለቲከኞች ሴራ መፍትሔው እንደ ሰማይ ርቆናል። አንዱ ወዲህ ሲስበን ሌላው ወዲያ ሲጎትተን በመሃል ቤት እንወዘወዛለን። ዛሬም ዋነኛ ጥያቄው አልተለየም። መላሹም አልታወቀም። እኛ 99.9999 % ብንሆንም እፍፍፍ ብለን የምናጠፋው ቁጥር ያላቸው መንደርተኞች ላልጠየቅነው ጥያቄ ያልተፈለገ ምላሽ እያቀረቡ ያውኩናል።
___
1500 የምስረታ ፊርማና የምርጫ ቦርድን ሰርተፊኬት የያዙ ሰዎች በመንደርተኛ አስተሳሰባቸው ብቻ ስሜት ኮርኩረው ‘ለምን እንዴት’ የማይልን ጎርፍ በፈለጉት ቦይ ውስጥ ስለገፉ ‘ብቸኛ ወኪልህ እኛ ነን’ ዓይነት እብሪት ሲሰማቸው ሳይ ያቅለሸልሸኛል።
___
በራሳቸው እርግጠኛ ከሆኑ ሃገራዊ ህልም አያልሙም?። ሕዝቡን ከወደዱ ትልቅ ትልም አይወልዱም?። ትርጉም በሌለው ‘የነጠላ’ ቀለም ዳስ ውስጥ ከሚሸጎጡ ሕብረ ቀለማዊው አዳራሽ ውስጥ አይከሰቱም?። ህዝቡን የሚያራርቅ ተረክ እየፈለጉ ከሚያባሉት ችግሩን የሚፈታበት ቁልፍ አያቀብሉትም?። ዛሬ ‘ሪስክ’ መውሰድ የማይፈልጉ መንደርተኛ ፓርቲዎች እንዴት ነው ሃገር የሚመሩት?.. አሁን የሚያስፈልገን እኮ ወጀቡን የሚያስቆም ትጉህ እንጂ ወደ ወጀቡ የሚገፋን ተረኛ አይደለም። ‘የመጣንበት መንገድ ልክ አይደለም’ ብሎ አዙሪቱን የሚያስቀር ብርቱ እንጂ ‘እሾህን በእሾህ’ የሚል አመክንዮ ቢስ አይደለም። ሰው ይውጣቸውና “ኢትዮጵያ” ይበሉ እስኪ። እንወዳቸው ዘንድ “ሃ-ገ-ራ-ች-ን” ይበሉ።
___
ዳሩ ትልቅ ህልም ትልቅ ልብ ላላቸው ብቻ ነው!!
___
መ-ፍ-ት-ሔ-ው ቀላል ነው። እኛም እነርሱም እናውቀዋለን። ከባድ ያደረገው ችግሩን ለመፍታት የሚፈቅዱ ሰዎች አለመቀመጥ ነው። ኢጎ አለቻ። ሁሉም የማያደራርስ ግንብ ገንብተዋል። የጥላቻ ግንብ። ህልማቸው ቡድናዊ፣ በደንብ ሲጠና ደግሞ ግላዊ ነው። ሃገራዊ ህልም ቢኖራቸው ኖሮ እኛን የማይበልጥ ችግር ለዘመናት አስጎንብሶን ባልታየን ነበር።
___
ፓርቲዎች ሆይ። ኢጎአችሁን ወዲያ ጣሉና ‘ለሃገራችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሚበጀው ምንድነው?’ ብላችሁ ተመካከሩ። ከወደዳችሁን ተፈላለጉ። ሰብሰብ በሉ። ግንባችሁን አፍርሱ። በእናንተ ሰበብ መሞት፣ መፈናቀል፣ መራብና መሰደድ ሰልችቶናል።
___
እነሆ መውጫ።
ሳይደገፍ የማይቆምን አምነው አይደገፉትም!!
One Comment
ደምስ ምን ልልህ እንደምችል እንኳን አላውቅም አንዳንዴ ይሄ ሰው ሳያቀኝ ውስጤን ያነበዋል እንዴ እልና መለስ ብዬ ደሞ ለሌሎች ደሞ እኮ ላይመቻቸው ይችል ይሆናል እልና ታዲያ ይህ አይደል እንዴ ሀሳብ ማለት ሁላችንም በተረዳነው ልክ እንድናብሰለስል ማስቻሉ እላለው፡፡የምር ነው ምልህ አድናቂህ ነኝ