Tidarfelagi.com

የባል ገበያ – (ክፍል አራት)

“እመኚኝ እኔን ነው እየጠበቅሽ ያለሽው።…… ” እንዳምነው ያወራናቸውን ሁሉ ነገሮች አንድ በአንድ ያወራንበትን ወር፣ ቀንና ሰዓት ሳይቀር ሲነግረኝ…… አንድ የሆነ የተዛባ ነገር የተፈጠረ መሰለኝ…… አይኔ አልያም ጆሮዬ ካልሆነም ህልም ነው…… መውደድ? አይሆንም!! አይሆንም!! ……

“መውደድ እየቀለድኩ ነው በለኝ?”

“እየቀለድኩ አለመሆኔን ታውቂያለሽ!! ስትፃፃፊው የነበረው ሰው እኔ ነኝ።”

መውደድን ልጠብቀው አልችልም። …… በማትረባ ቅንዝራም አሮጊት የቀየረኝን መውደድ በፅጌሬዳ እንኳን ደህና መጣህልኝ ልለው በፍፁም አልችልም።…

… ለወራት በጠዋት ስነቃ በጉጉት ያነበብኩት “good morning ma sunshine” የሚለው ልቤን እንደጠዋት ፀሃይ የሚያሞቅ መልዕክት የመውደድ መሆኑን ሳስብ ያለፉ ጠዋቶቼ አንገሸገሹኝ። ዘወትር ምሽት ለወራት “darling u r in ma arms, hv a sweet dream” …የሚሉትን ቃላት የመውደድ ጣቶች እንደተየቡት ለማመን ሳሰላስል … አልጋዬ ላይ በምቾት የተገላበጠ ጎኔን ጠላሁት…… መውደድን ብበጫጭቀው እንኳን ንዴቴ የሚበርድ አልመሰለኝም።…… በእጄ የያዝኩትን አበባ መሬት ላይ ወርውሬ በእግሬ ደፈጠጥኩት!! ምንም ብናገረው ሁሉም ቃል ገለባ ነው። …… ዝም ብዬው ልሄድ እግሮቼን አነሳሁና… ብስጭት፣ እልህ፣ እንባ…… መላ አካላቴን ናጠኝ።

“ታውቃለህ? መቀለድህ ከነበር ጅላጅል ቀልድ ነው የቀለድከው። የማትረባ ዥልጥ ነህ!! ምን እንዳደረግክ ታውቃለህ? ለነገሩ ልታውቅ የምትችልበት ማሰቢያ አይኖርህም። አፈር ብላ!! ከንቱ!! ቂላ ቂል ከንቱ ነህ!” …… ምንም ያህል ልሰድበው ብሞክር ከተሰማኝ ብስጭት ጋር ሚዛን ላይ ሲሰፈር ያቆለጳጰስኩት ያህል ምርቃት መስሎ ተሰማኝ። …… ለዛሬ ቀን የሚሆን የክት ስድብ አጣሁ። …… አይኖቹን ከአይኖቼ ሳይሰብር ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ ያየኛል። ………

“‘የምታፈቅሪው ሰው ደጋግሞ ግዙፍ በደል ቢበድልሽ ስንቴ ይቅር ትይዋለሽ?‘ ስልሽ የመለስሽልን መልስ ታስታውሻለሽ?” በረጋ ድምፅ ጠየቀኝ።

‘ድርጊቱን ያደረገበት ምክኒያት እንጂ በደሉ ብቻውን ትልቅም ትንሽም አይሆንም።‘ ብዬው እንደነበር አስታወስኩ።

‘በደሉን የሚያገዝፈው የትኛው ምክንያት ነው?‘ ላለኝ ጥያቄ

‘አንደኛ እኔን ለመጉዳት አስቦ ሲሆን ሁለተኛ ራሱን ለመጥቀም አስቦ ሲጎዳኝ። ባጠቃላይ የበደሉ ዘር የክፋት ጭማቂ ሲሆን ጥፋቱ ኢምንትም ቢሆን ይገዝፍብኛል።…… የማፈቅረው ሰው ያለምንም ክፋት፣ ሳያውቅ ወይም ተሳስቶ ለሚበድለኝ በደል ገና ሳይበድለኝ በፊት ሁላ ይቅር ብዬዋለሁ። …… ‘ ብዬ መልሼለት ነበር። …… እንዳስታወስኩት እርግጠኛ በመሆን ከንፈሩን ለመፍገግ እያሸሸ

“በደሌ ከይቅርታ በላይ ትልቅ መሆኑን ለማወቅ እድል ስጪኝና ምክኒያቱን ልንገርሽ።……ካለዚያ ምክኒያታዊነትሽ ከጥሩ አባባሎችሽ መሃል አንዱ ብቻ እንደሆነ ልመን? ”

“ክህደት በምንም መልኩ ቢሆን ክህደት ነው። ቅን ምክንያት ልትለጥፍለት አትችልም። …… ምክኒያትህን ልሰማ ቢገባ እንኳን ያን ማድረግ የነበረብህ ከአራት ዓመት በፊት ነበር። ……” ለሱ ቆሜ ማብራሪያ መስጠቴ በራሱ አበሸቀኝ።

አባቴ ታሞ ለቀናት ባንገናኝ ፍጥረት የሚቀናበት ንፁህ ፍቅራችንን እንደምንም ሲተወው መች ምክኒያት ሰጠኝ? ከፊቷ ይልቅ ስትራመድ ወደ ታች ተረከዟን ወደ ላይ ማጅራቷን የሚነካ እስኪመስለኝ የምታስደንሰው የሚያሳቅቅ ትልቅ ቂጧ ትዝ የሚለኝን ሴትዮ ማግባቱን እንኳን መች ከሱ ሰማሁ? ለአንድ ቀን ድምፄን ካልሰማ ‘ሳልሞትብሽ ስልክሽን አንሺው‘ ይለኝ የነበረ ሰው ከሃገር መውጣቱን ከሄደ በኋላ ቤተሰቦቹ ሲነግሩኝ ሳሎናቸው መሃል ራሴን ስቼ መውደቄ ለሱ ምኑ ነበር? ከዛሬ ነገ መጥቶ ይቅርታ ይጠይቀኛል ብዬ ስጠብቀው መች ለአፍታ ትውስ አልኩት?

አባቴ ከሞተ በኋላ በየቀኑ ሳይደክመኝ ስለሱ አስብ ነበር። ……ቢያንስ ለማፅፅናናት ይደውልልኛል ፣ መከፋቴን ሲያይ አያስችለውም፣ እንባዬን ከሚያይ ከየትኛውም ዓለም ክፍል ይመጣልኛል፣ ከቂጣሟ አሮጊት ሚስቱ እንደምበልጥበት ይነግረኛል…… ሳኮርፈው ሁሌ ያደርግ እንደነበረው የታችኛው ከንፈሬን ብቻ እየደጋገመ ይስመኛል። …… ሲጣፍጠኝ በደሉ ይሸረፍብኛል። …… እጆቹ ወገቤን አልፈው ሲወርዱ ምን አድርጎኝ እንደነበር ይጠፋብኛል። …… ሰውነቱ ሰውነቴን ተጭኖ ሲዘልቀኝ እንኳን የአሮጊቷ ቂጥ ትዝ ሊለኝ ሰማይ በቂጡ ከምድር ቢጋጭ ጉዳዬ አይሆንም…… ከዛ የኔ ብቻ አደርገዋለሁ።…… እያልኩ አስብ ነበር።
ተስፋ ቆርጬ እስክደነዝዝ እሱ የት ነበር?

“ውዴ? እባክሽ ሁሉንም ነገር ያደረግኩት ላንቺ ስል ነበር።” ብሎ ‘አፌዘ‘

እንድናርፍበት የተከራየሁትን ሆቴል ቁልፍ ወርውሬለት ሊቀበለው የመጣውን የሆቴሉን መኪና ጠቁሜው በእግሬም በሃሳቤም ወደተውኩት ኑሮ ተራመድኩ። …… እንደማገባ የነገርኳት እናቴ ፣ ‘ልጄ ልታገባ ነው ግን ሚስጥር ነው‘ ብላ እናቴ የነገረቻቸው ቁጥር አልባ የማውቃቸው ሰወች፣ ከሀገር በመውጣት ስንድት ሰበብ የገተርኩት ኑሮዬ፣ ማንነቱን ለማያውቀው ሰው ጦሽ ያለው ገልቱ ልቤ፣ አርቄ ከሰቀልኩበት የተፈጠፈጠው ከሀገር የመውጣት ህልሜ፣ አከታትዬ የምወልዳቸው ድቅል ሁለት ወንድ ልጆቼ፣ ለእናቴ የምሰራላት ቪላ ቤት ………… የቧቸርኩባቸው ቅዠቶቼ ናቸው። ስነቃ የበነኑ። …… ለካንስ በቅዠት መፈንጠዙ አይከብድም። …… ቅዠቱን ማቆምም ብዙ አያታግልም። …… ወደ እውነታው መመለሱ ነው እብደት። …… ……
………
መውደድን ከኋላዬ ትቼው ከሚታገለኝ እንባዬ ጋር ግብ ግብ ገጥሜ ወደ ቤቴ መጓዝ ጀመርኩ። ……

የባል ገበያ – (የመጨረሻ ክፍል)

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *