Tidarfelagi.com

የአድዋ ድል በአል ሲከበር

ልጅ ሆኜ የአድዋ ድል በአል ሲከበር ያለው ሸብ-ረብ ስለምን እንደሆነ አይገባኝም ነበር፡፡

ለምን?

የድሉን ዋጋ የመገመቻ እውቀት ስላልነበረኝ፡፡

የካቲት 23 መጥቶ በሄደ ቁጥር በአንዱ ጆሮዬ ጥልቅ ብለው በሌላው የሚወጡት ቃላትና ግጥሞች ብቻ ትዝ ይሉኛል፡፡ ‹‹አጤ ምኒልክ›› ‹‹የውጫሌ ውል›› ‹‹ እቴጌ ጣይቱ›› ‹‹አንቀፅ 17››
‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤
ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ››

ከፍ ስል አባቴ መቼም በማልረሳው መንገድ የአድዋ ድልን ምንነት እስኪያስረዳኝ ድረስ የድሉን ዋጋ የመገመቻ እውቀት አልነበረኝም፡፡

እርግጥ ነው ፤ የአድዋ ድል የቀኝ ገዢዎችን ቅስም ሰብሯል፡፡
የተገዢዎችን የተደፋ አንገት ቀና አድርጓል፡፡
እርግጥ ነው፤ የአድዋ ድል በአለም ዙሪያ ለተከፉና ለተገፉ የነፃነትና የክብር ፋና ሆኗል፡፡

ለኔ ግን ፤ ከሁሉ በላይ የአድዋን ድል ዋጋ ቀልብጭ አድርጎ የሚያሳየኝ ከዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› መፅሃፍ ላይ ያገኘሁት በሌላ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የተደረገ ውይይት ነው፡፡

‹‹…ሀገሬን እወዳለሁ የምልበት ብዙ ርስት አለኝ….ካንዱ ቦታ ወደ ሌላው አፍንጫዬን አየር ላይ ሰቅዬ፣ እግሬ ሳይፈራ ሙሉ በሙሉ የተራመድኩበት ርስቴ ነው….ሀገርና መንግስት አለኝ የሚያሰኙ ልማድ፣ ወግ፣ ቅርስና ባህሎች በሰው ላይ አድረው በውህደታቸው ደም ግባትና ትከሻ ክብደት ሲመጣ ነው….አለዚያ ሀገረ ቢስ ወይም ውቃቢ ቢስ….እንጂ ባለ ሃገር ባለመንግስት አይደለሽም….››

አፍንጫዬን በአየር እንድሰቅል፣
እግሬ ሳይፈራ እንድራመድ፣
ትከሻዬ እንዲከብድ፣
የባለ ሀገር ደምግባት እንዲኖረኝ፣
ላደረጉ አባቶቼም እናቶቼም ክብር ይገባቸዋል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *