በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የካቲት ታሪካዊ ወር ነው። ታላላቅ አብዮቶችም ታላላቅ ድሎችም በየካቲት ወር ተከናውነዋል። ዐድዋን ያህል ከፍታው ሰማየ ሰማያትን የሚነካ ድል የተገኘው በየካቲት 23 ነው። ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችን (የአዲስ አበባ ኗሪዎች ብቻ) በፋሽስት በግፍ የተጨፈጨፉትም በየካቲት 12 ነው። የካቲት ድልም ደምም ነው። የካቲት የብዙ አስደሳችም አናዳጅም ታሪኮች የክዋኔ ወር!!!!
የዘንድሮው የካቲትም የዋዛ ወር ሆኖ የሚያልፍ አይመስልም። ነገሮች ከሚገመተው በላይ በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው። ይህኛው የካቲትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ ለውጦች የምናይበት ሊሆን እንደሚችል ማሳያዎች ብዙ ናቸው። ለውጦች በጎም መጥፎም የመሆን ዕድል አላቸው።
እስካሁን የካቲት ከባተ ጀምሮ… ቄሮ በኦሮሚያ ክልል ታሪካዊ የሚባል የሦስት ቀናት አድማ አድርጓል። አድማውን ተከትሎ እነ ኦቦ በቀለ ገርባ ተፈተዋል። (በቀጥታ ከቄሮ አመጽ ጋር ባይያያዝም) እነ-እስክንድር ነጋንና እነ-አንዷለም አራጌን የመሰለ የፖለቲካ ዘዋሪዎች ከማጎሪያቸው ወጥተዋል። የሙስሊም መብት ተሟጋቾችም ተለቀዋል። በዚህ ተደመን ሳናበቃ… ሳይጠበቅ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትርነት በቃኝ… በጌታ ልቀቁኝ›› ማለታቸውን ሰማን። መልቀቂያቸውንም ፓርቲያቸው ተቀበለ። በዚህ እንደመሳቅም እንደመደንገጥም ብለን ጎናችን ሳያርፍ…. ‹የ3 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ነው› ተባልን። ተወዲያ ማዶ ደግሞ…. አሜሪካን ‹‹በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አደጋ እያንዣበበ ነውና መጠንቀቅ ይበጃል›› እያለች ነው። እነዚህ ከየካቲት አንድ እስከ ዛሬ ከተከሰቱ ክስተቶች መካከል ናቸው።
ነገስ…
በዚሁ በየካቲት ወር የኢህአዴግ ጉባኤ ይካሄደል። ፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣል። ኢህአዴግ ኃይለ-ማርያምን የሚተካ ሊቀመንበሩን ይመርጣል። የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል። ግን ማን…? ከየትኛው ብሔራዊ ድርጅት…? ለመገመት ይከብዳል። ብዙዎቹ… ከኦህዴድ አይወጣም እያሉ ነው። አንዳንዶች ‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጠ/ሚኒስትሩ በድንገት ከለቀቀ ምክትሉ አቶ ደመቀ… እስከሚቀጥለው ምርጫ ይመራል›› ሲሉ… ‹‹የለም… ደመቀንማ አሁን በስብሰባ ላይ ያለው ብአዴን ከሊቀመንበርነት ያወርደዋል… ኦህዴድን ወደ መንበሩ ለማምጣት አስቀድሞ የብአዴኑ ደመቀ መኮንን ከኃላፊነት ይነሳል›› ብለው መላምታዊ ሙግት እያስቀመጡ ነው። ሌላ የማይጠበቅና ያልተገመተ ነገርም ሊከሰት ይችላል። የኢህአዴግ ቀጣዩ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆን? የካቲት መልስ ይኖረዋል።
ሌላም ስጋት የሚያስቀምጡ አሉ። የኢህአዴግ አኃት ድርጅቶች መስማማት ካልቻሉ… መከላከያው መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርግ ይችላል። ይህም የሚሆን ከሆነ ከየካቲት ወር አይዘልም። ምን አልባትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ለዚህ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላልም ይላሉ። ‹‹በተለይ ሰሞኑን ባልተለመደ መልኩ… የመከላከያው ጀግንነት፣ ለሕዳሴው ግድብ ያለው ጠበቃነት፣ ‹ለሕዝቡ ያለው ወገንተኝነት›፣ ልማታዊነቱ…ወዘተ በኢቢሲ ተደጋግሞ መዘገቡ… ከዓመታዊ በዓል በዘለለ ሌላ መልእክት አለው። በእኛ ተማመኑብን… ሀገሪቱን በሰላም እንመራታለን… አይነት መልእክትም አለው›› የሚሉ ፖለቲከኞችም ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ከሆነ ለምን…? ምን አልባት አጠቃላይ የሆነ ሀገራዊ ሽግግር ለመፍጠር ወይስ ሀገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ ለመምራት…?
ለማንኛውም ወሩ የካቲት ነውና ብዙ ታሪካዊ ክስተት ያሳየናል ብለን እንጠብቃለን። ‹‹ኢህአዴግ ብቻውን ይህንን ሀገሪቱ የገባችበትን ችግር መፍታትና በሰላም መምራት ስለማይችል ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና በውጭም በውስጥም ለነፃነት ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር ሥልጣን ይጋራ… ሰላማያዊ ሽግግር ይፈጠር›› የሚሉ ወገኖች ሰሚ ቢያገኙ ግን… ለኢትዮጵያ የተሻለ መፍትሔ ይሰጣል።
ሰላም ለሀገራችን !
ሰላም ለሕዝባችን !